በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 21

‘በዚህ ዓለም ጥበብ’ እንዳትታለሉ ተጠንቀቁ

‘በዚህ ዓለም ጥበብ’ እንዳትታለሉ ተጠንቀቁ

“የዚህ ዓለም ጥበብ በአምላክ ፊት ሞኝነት ነው።”—1 ቆሮ. 3:19

መዝሙር 98 ቅዱሳን መጻሕፍት በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው

የትምህርቱ ዓላማ a

1. የአምላክ ቃል የሚረዳን እንዴት ነው?

 ታላቁ አስተማሪያችን ይሖዋ ስለሚመራን፣ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሁሉ መወጣት እንችላለን። (ኢሳ. 30:20, 21) ቃሉ ‘ለማንኛውም መልካም ሥራ በሚገባ የታጠቅን እንድንሆን’ እንዲሁም ‘ሙሉ በሙሉ ብቁ ሆነን እንድንገኝ’ ይረዳናል። (2 ጢሞ. 3:17) በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ሕይወታችንን የምንመራ ከሆነ ‘የዚህን ዓለም ጥበብ’ ከሚያራምዱ ሰዎች ይበልጥ ጥበበኛ እንሆናለን።—1 ቆሮ. 3:19፤ መዝ. 119:97-100

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

2 ቀጥለን እንደምንመለከተው የዚህ ዓለም ጥበብ ሥጋዊ ፍላጎታችንን የሚማርክ ነው። በመሆኑም የዓለም ክፍል የሆኑ ሰዎች አስተሳሰብና የአኗኗር ዘይቤ እንዳይጋባብን መከላከል ከባድ ሊሆንብን ይችላል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ “በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ ማንም ማርኮ እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ” የሚል ምክር መስጠቱ ተገቢ ነው። (ቆላ. 2:8) በዚህ ርዕስ ውስጥ ሰዎች ሰይጣን የሚያስተምራቸውን ሁለት ውሸቶች መቀበል የጀመሩት እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ከእነዚህ ውሸቶች ጋር በተያያዘ፣ የዚህ ዓለም ጥበብ ሞኝነት የሆነበትን ምክንያት እንመረምራለን። በተጨማሪም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ጥበብ ይህ ዓለም ከሚያቀርበው ከማንኛውም ነገር የላቀ ነው የምንለው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

ሰዎች ስለ ሥነ ምግባር ያላቸው አመለካከት መለወጡ

3-4. በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ አንስቶ፣ ሰዎች ስለ ሥነ ምግባር ባላቸው አመለካከት ላይ ምን ለውጥ ታይቷል?

3 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ አንስቶ፣ ሰዎች ስለ ሥነ ምግባር ያላቸው አመለካከት በእጅጉ ተለውጧል። ቀደም ሲል፣ ከጋብቻ ውጭ የፆታ ግንኙነት መፈጸም እንዲሁም ስለ ፆታ ግንኙነት በይፋ ማውራት እንደ ነውር ይታይ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ሰዎች የነበራቸው ይህ አመለካከት ተለውጦ ብዙዎች ልል የሆነ አቋም መያዝ ጀመሩ።

4 ከ1920 እስከ 1929 ያሉት ዓመታት በማኅበራዊ እሴቶች ረገድ ከፍተኛ ለውጥ የታየባቸው ዓመታት ናቸው። አንድ ተመራማሪ እንደተናገሩት በእነዚያ ዓመታት “ተንቀሳቃሽ ምስሎች፣ ቲያትሮች፣ ዘፈኖች፣ ልብ ወለድ መጻሕፍትና ማስታወቂያዎች በሙሉ ፆታዊ ይዘት ያላቸው መሆን ጀመሩ።” በተጨማሪም ሰዎች የፆታ ስሜትን የሚያነሳሱ ጭፈራዎችን መጨፈርና ልከኝነት የጎደለው አለባበስ መልበስ ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ የሚኖሩትን ሰዎች አስመልክቶ እንደተነበየው ብዙዎች “ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ” ሆኑ።—2 ጢሞ. 3:4

የይሖዋ ሕዝቦች ዓለም ባለው ልቅ የሥነ ምግባር አቋም ተማርከው አይወሰዱም (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት) c

5. ከ1960ዎቹ ዓመታት ጀምሮ ሰዎች ስለ ሥነ ምግባር ያላቸው አመለካከት የተለወጠው እንዴት ነው?

5 ከ1960ዎቹ ዓመታት ወዲህ ግብረ ሰዶማዊነት፣ ሳይጋቡ አብሮ መኖርና በረባ ባልረባው መፋታት የተለመዱ ነገሮች ሆኑ። በርካታ መዝናኛዎች የፆታ ግንኙነትን በይፋ ያቀርቡ ነበር። እንዲህ ያለው ልቅ የሆነ የሥነ ምግባር አቋም ያስከተለው መዘዝ፣ ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ በግልጽ ታይቷል። አንድ ደራሲ እንደተናገሩት ለቤተሰብ መፈራረስ፣ በነጠላ ወላጅ ለሚያድጉ ልጆች መበራከት፣ ለስሜታዊ ቁስል፣ ለብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ሱሰኝነት እንዲሁም ለሌሎች መሰል ችግሮች እንደ መንስኤ የሚጠቀሰው “ማኅበረሰቡ ከፆታ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ የሚመራባቸው ደንቦች ማሽቆልቆላቸው” ነው። እንደ ኤድስ ያሉ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች መስፋፋታቸው በዚህ ዓለም ጥበብ መመራት ሞኝነት እንደሆነ ከሚያሳዩ በርካታ ማስረጃዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው።—2 ጴጥ. 2:19

6. ዓለም ስለ ፆታ ያለው አመለካከት የሰይጣንን ዓላማ የሚያራምደው እንዴት ነው?

6 ዓለም ስለ ፆታ ያለው አመለካከት የሰይጣንን ዓላማ የሚያራምድ ነው። ሰዎች የአምላክ ስጦታ የሆነውን የፆታ ግንኙነትን አላግባብ ሲጠቀሙበትና የጋብቻ ስጦታን ሲያቃልሉት ማየት ሰይጣንን በጣም እንደሚያስደስተው ምንም ጥርጥር የለውም። (ኤፌ. 2:2) የፆታ ብልግና መፈጸም፣ አምላክ የሰው ልጆች ዘራቸውን እንዲተኩ ሲል የሰጣቸውን ልዩ ስጦታ የሚያቃልል ድርጊት ነው፤ ደግሞም በዚህ ድርጊት የሚካፈሉ ሁሉ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚያቸውን ያጣሉ።—1 ቆሮ. 6:9, 10

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ሥነ ምግባር ምን ይላል?

7-8. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት የትኛውን ሚዛናዊና ጤናማ ትምህርት ያስተምራል?

7 የዚህን ዓለም ጥበብ የሚከተሉ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምክንያታዊነት የጎደላቸው እንደሆኑ በመናገር እነዚህን መሥፈርቶች ያቃልላሉ። ምናልባትም ‘አምላክ የፆታ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ከፈጠረን በኋላ ይህን ፍላጎታችንን እንዳናረካ የሚከለክለን ለምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። እንዲህ ያለ ጥያቄ የሚያነሱት፣ ‘ሰዎች ውስጣቸው የገፋፋቸውን ነገር ሁሉ ሊያደርጉ ይገባል’ የሚል የተሳሳተ አመለካከት ስላላቸው ነው። የአምላክ ቃል ግን ከዚህ የተለየ ትምህርት ያስተምራል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ለሰው ልጆች ተገቢ ያልሆኑ ውስጣዊ ግፊቶችን የመቆጣጠር ችሎታ በመስጠት እንዳከበራቸው ይገልጻል። (ቆላ. 3:5) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ሰዎች የፆታ ስሜታቸውን ተገቢ በሆነ መንገድ ማርካት የሚችሉበትን የጋብቻ ዝግጅት አድርጎላቸዋል። (1 ቆሮ. 7:8, 9) በመሆኑም አንድ ባልና ሚስት፣ የፆታ ብልግና መፈጸም ከሚያስከትለው ጸጸትና ጭንቀት ነፃ ሆነው የፆታ ፍላጎታቸውን ማርካት ይችላሉ።

8 ከዚህ ዓለም ጥበብ በተቃራኒ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፆታ ግንኙነት ጤናማ አመለካከት እንድናዳብር ይረዳናል። የፆታ ግንኙነት ደስታ የሚያስገኝ ነገር እንደሆነ በግልጽ ይናገራል። (ምሳሌ 5:18, 19) በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን አካል በመቆጣጠር እንዴት በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት ሊያውቅ ይገባል። ይህም አምላክን እንደማያውቁት አሕዛብ ስግብግብነት በሚንጸባረቅበት ልቅ የፍትወት ስሜት አይሁን።”—1 ተሰ. 4:4, 5

9. (ሀ) በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ አካባቢ፣ የይሖዋ ሕዝቦች በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው የላቀ ጥበብ እንዲመሩ ማበረታቻ የተሰጣቸው እንዴት ነው? (ለ) በ1 ዮሐንስ 2:15, 16 ላይ ምን ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር ይገኛል? (ሐ) በሮም 1:24-27 መሠረት፣ ከየትኞቹ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ልማዶች መራቅ ይኖርብናል?

9 በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ የነበሩት የይሖዋ ሕዝቦች፣ “የሥነ ምግባር ስሜታቸው [የደነዘዘ]” ሰዎች በሚያራምዱት ከንቱ ማታለያ ተማርከው አልተወሰዱም። (ኤፌ. 4:19) በተቻላቸው መጠን የይሖዋን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በጥብቅ ለመከተል ጥረት አድርገዋል። የግንቦት 15, 1926 መጠበቂያ ግንብ “አንድ ወንድ ወይም አንዲት ሴት፣ በተለይ ከተቃራኒ ፆታ ጋር በተያያዘ በአስተሳሰብም ሆነ በድርጊት ንጹሕ መሆን አለባቸው” የሚል ሐሳብ ይዞ ወጥቶ ነበር። የይሖዋ ሕዝቦች በዙሪያቸው ያለው ዓለም የሚከተለው መሥፈርት ምንም ሆነ ምን፣ በአምላክ ቃል ውስጥ ባለው የላቀ ጥበብ ለመመራት መርጠዋል። (1 ዮሐንስ 2:15, 16ን አንብብ።) የአምላክ ቃል ለሚሰጠን አመራር ምንኛ አመስጋኞች ነን! በተጨማሪም ይሖዋ በተገቢው ጊዜ ለሚያቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ ልባዊ አድናቆት አለን፤ ይህ መንፈሳዊ ምግብ በዚህ ዓለም ጥበብ ተታለን የሥነ ምግባር አቋማችንን እንዳናላላ ይረዳናል። bሮም 1:24-27ን አንብብ።

ሰዎች ለራሳቸው ያላቸው አመለካከት መለወጡ

10-11. መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ስለሚኖሩ ሰዎች ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር?

10 መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ” እንደሚሆኑ አስጠንቅቋል። (2 ጢሞ. 3:1, 2) ከዚህ አንጻር፣ ይህ ዓለም ለራሳችን የተጋነነ አመለካከት እንዲኖረን የሚያበረታታ መሆኑ አያስገርምም። አንድ የማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደተናገረው፣ በ1970ዎቹ ዓመታት “ራስ አገዝ መጻሕፍት በብዛት መታተም” የጀመሩ ሲሆን አንዳንዶቹ መጻሕፍት ሰዎች “ማንነታቸውን እንዲቀበሉና ራሳቸውን ለመለወጥ ምንም ዓይነት ጥረት እንዳያደርጉ የሚያበረታቱ ነበሩ።” ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ራስ አገዝ መጽሐፍ ላይ የሚከተለው ሐሳብ ወጥቶ ነበር፦ “እስከዛሬ በዓለም ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ውብና ማራኪ ከሆነው እንዲሁም ከፍ ያለ ቦታ ከሚሰጠው ሰው ጋር ፍቅር ይያዝህ፤ ይህ ሰው አንተ ራስህ ነህ።” ይኸው መጽሐፍ፣ ሰዎች “ራሳቸውን እንደ ሃይማኖት አድርገው እንዲከተሉ ማለትም ምን ዓይነት ምግባር ማሳየት እንዳለባቸው ለመወሰን በራሳቸው ሕሊና እንዲመሩ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ከሚመራባቸው ሕጎች መካከል ለራሳቸው የሚስማማቸውን ብቻ መርጠው እንዲከተሉ” ያበረታታል።

11 ይህ ሐሳብ ምን ያስታውስሃል? ሰይጣን ሔዋንን ተመሳሳይ ነገር እንድታደርግ አበረታቷት ነበር። “መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ [እንደምትሆን]” ነግሯት ነበር። (ዘፍ. 3:5) በዛሬው ጊዜ በርካታ ሰዎች ለራሳቸው ያላቸው አመለካከት በጣም የተጋነነ ከመሆኑ የተነሳ ማንም ሌላው ቀርቶ አምላክም እንኳ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ሊነግራቸው እንደማይችል ይሰማቸዋል። ይህ ዝንባሌ በተለይም ሰዎች ለጋብቻ ባላቸው አመለካከት ላይ በግልጽ ይታያል።

ክርስቲያኖች ከራሳቸው ፍላጎት ይልቅ ለሌሎች ፍላጎት፣ በተለይም ለትዳር ጓደኛቸው ፍላጎት ቅድሚያ ይሰጣሉ (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት) d

12. ዓለም ለጋብቻ ምን አመለካከት አለው?

12 መጽሐፍ ቅዱስ ባለትዳሮች እርስ በርስ እንዲከባበሩና የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ያዛል። ባልና ሚስት ጥምረታቸው ምን ያህል የጠበቀና ዘላቂ መሆን እንዳለበት ሲናገር “ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል። ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” ይላል። (ዘፍ. 2:24) በዚህ ዓለም ጥበብ የሚመሩ ሰዎች ግን ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አመለካከት ያራምዳሉ፤ ባልም ሆነ ሚስት ለራሳቸው ፍላጎት ብቻ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ይናገራሉ። ፍቺን በተመለከተ የተጻፈ አንድ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “በአንዳንድ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶች ላይ፣ ‘በሕይወት አብረን እስከኖርን ድረስ’ የሚለው የተለመደ ቃለ መሐላ ‘እርስ በርስ እስከተዋደድን ድረስ’ በሚለው ቃለ መሐላ ተተክቷል።” የጋብቻ ቃለ መሐላን የሚያቃልለው እንዲህ ያለው አመለካከት፣ በርካታ ቤተሰቦች እንዲፈራርሱና ብዙዎች ለከባድ ስሜታዊ ሥቃይ እንዲዳረጉ ምክንያት ሆኗል። በእርግጥም ዓለም ለጋብቻ ያለው አመለካከት ሞኝነት የሚንጸባረቅበት ነው።

13. ይሖዋ ኩሩ ሰዎችን የሚጸየፍበት አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?

13 መጽሐፍ ቅዱስ “ይሖዋ ኩሩ ልብ ያለውን ሁሉ ይጸየፋል” ይላል። (ምሳሌ 16:5) ይሖዋ ኩሩ ሰዎችን የሚጸየፈው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ራሳቸውን የሚወዱና ለራሳቸው የተጋነነ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የሰይጣንን የትዕቢት ዝንባሌ ስለሚያንጸባርቁ ነው። እስቲ አስቡት፦ ሰይጣን፣ አምላክ ሁሉንም ነገሮች ለመፍጠር የተጠቀመበት ኢየሱስ ተደፍቶ ሊሰግድለትና ሊያመልከው እንደሚገባ ተሰምቶት ነበር! (ማቴ. 4:8, 9፤ ቆላ. 1:15, 16) ለራሳቸው እንዲህ ያለ የተጋነነ አመለካከት ያላቸው ሁሉ የዚህ ዓለም ጥበብ በአምላክ ፊት ሞኝነት እንደሆነ የሚያሳዩ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው።

መጽሐፍ ቅዱስ ለራሳችን ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት ምን ይላል?

14. ሮም 12:3 ለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት እንድናዳብር የሚረዳን እንዴት ነው?

14 መጽሐፍ ቅዱስ ለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት እንድናዳብር ይረዳናል። በተወሰነ መጠን ራሳችንን መውደድ እንዳለብን ይናገራል። ኢየሱስ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” በማለት የተናገረው ሐሳብ ለራሳችን ፍላጎት መጠነኛ ትኩረት መስጠት እንዳለብን ይጠቁማል። (ማቴ. 19:19) ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን ከሌሎች አስበልጠን መመልከት እንዳለብን አይናገርም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ይላል፦ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ።”—ፊልጵ. 2:3፤ ሮም 12:3ን አንብብ።

15. መጽሐፍ ቅዱስ ለራሳችን ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት የሚሰጠው ምክር የተሻለ እንደሆነ የሚሰማህ ለምንድን ነው?

15 በሌሎች ዘንድ እንደ ጥበበኛ የሚቆጠሩ በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ለራሳችን ሊኖረን ስለሚገባው አመለካከት የሚሰጠውን ምክር ያጣጥላሉ። ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ አድርገን የምናስብ ከሆነ ራሳችንን ለጥቃት እንደምናጋልጥና የሌሎች መጠቀሚያ እንደምንሆን ይናገራሉ። ይሁንና የሰይጣን ዓለም የሚያራምደው ለራስ ትልቅ ቦታ የመስጠት ዝንባሌ ምን ውጤት አስከትሏል? እናንተ በዚህ ረገድ ምን አስተውላችኋል? ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች ደስተኛ ናቸው? አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት እየመሩ ነው? እውነተኛ ወዳጆች አሏቸው? ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት ችለዋል? ካያችሁት ነገር በመነሳት ምን አስተያየት ትሰጣላችሁ? የተሻለ ውጤት የሚያስገኘው በዚህ ዓለም ጥበብ መመራት ነው ወይስ በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው ጥበብ መመራት?

16-17. አመስጋኝ እንድንሆን የሚያነሳሳን ምን ምክንያት አለ? ለምንስ?

16 ዓለም እንደ ጥበበኛ አድርጎ የሚመለከታቸውን ሰዎች ምክር መከተል፣ እሱ ራሱ መንገድ ጠፍቶበት እየተደናበረ ወዳለ ሰው ሄዶ አቅጣጫ ከመጠየቅ ተለይቶ አይታይም። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ጥበበኛ አድርገው የሚቆጥሯቸውን ሰዎች አስመልክቶ ሲናገር “እነሱ ዕውር መሪዎች ናቸው። ስለዚህ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ” ብሏል። (ማቴ. 15:14) በእርግጥም የዚህ ዓለም ጥበብ በአምላክ ፊት ሞኝነት ነው።

የአምላክ አገልጋዮች በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፉትን ሕይወት መለስ ብለው ሲያስቡ ልባቸው በደስታ ይሞላል (አንቀጽ 17⁠ን ተመልከት) e

17 በታሪክ ዘመናት ሁሉ እንደታየው መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክር “ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ለማረምና በጽድቅ ለመገሠጽ” ይጠቅማል። (2 ጢሞ. 3:16 ግርጌ) ይሖዋ በዚህ ዓለም ጥበብ እንዳንታለል በድርጅቱ አማካኝነት ጥበቃ ስለሚያደርግልን ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ኤፌ. 4:14) እሱ የሚያቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ፣ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን መሥፈርቶች በጥብቅ ለመከተል የሚያስችል ጥንካሬ ይሰጠናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው መሬት ጠብ የማይል ምክር መመራት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!

መዝሙር 54 “መንገዱ ይህ ነው”

a ይህ ርዕስ አስተማማኝ መመሪያ የሚገኘው ከይሖዋ ብቻ እንደሆነ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። በተጨማሪም በዚህ ዓለም ጥበብ መመራት አሳዛኝ ውጤት እንዳለው፣ በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኘው ጥበብ መመራት ግን ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝ ያብራራል።

c የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ባልና ሚስት በተለያዩ የዕድሜያቸው ክፍሎች ያሳለፏቸውን ነገሮች የሚያሳዩ ፎቶግራፎች። ባልና ሚስቱ በ1960ዎቹ መገባደጃ አካባቢ በስብከቱ ሥራ ሲካፈሉ።

d የሥዕሉ መግለጫ፦ በ1980ዎቹ ባልየው ሚስቱን ሲያስታምም፤ ትንሿ ልጃቸው ከእናቷ አጠገብ ቆማለች።

e የሥዕሉ መግለጫ፦ አሁን ላይ ሆነው፣ በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፏቸውን አስደሳች ጊዜያት መለስ ብለው ሲመለከቱ። ልጃቸው ከባለቤቷና ከልጇ ጋር ሆና ፎቶግራፎቹን እያየች ነው።