በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኑሮን ማቅለል የሚያስገኘው ደስታ

ኑሮን ማቅለል የሚያስገኘው ደስታ

ዳንኤል እና ሚርያም የተጋቡት መስከረም 2000 ሲሆን በስፔን በምትገኘው በባርሴሎና ከተማ ይኖሩ ነበር። ዳንኤል እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “የተደላደለ የሚባለው ዓይነት ሕይወት እንመራ ነበር። ሥራችን፣ በጥሩ ምግብ ቤቶች ውስጥ ለመመገብ፣ ወደ ሌሎች አገሮች ለመጓዝ እንዲሁም ጥራት ያለው ልብስ ለመልበስ የሚያስችለን ነበር። በአገልግሎትም ቢሆን አዘውትረን እንካፈል ነበር።” ይሁንና ሕይወታቸውን የሚቀይር ነገር አጋጠማቸው።

በ2006 በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ የቀረበ አንድ ንግግር የዳንኤልን ልብ ነካው፤ በንግግሩ ላይ “‘እየተጐተቱ ለዕርድ የሚሄዱትን’ ሰዎች ወደ ሕይወት ጎዳና ለመመለስ የቻልነውን ሁሉ እያደረግን ነው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር። (ምሳሌ 24:11) ንግግሩ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ሕይወት አድን መልእክት ለሌሎች የማሳወቅ ኃላፊነት እንዳለብን የሚያጎላ ነበር። (ሥራ 20:26, 27) ዳንኤል “ይሖዋ እኔን እያነጋገረኝ እንዳለ ተሰምቶኝ ነበር” ብሏል። በተጨማሪም አገልግሎትን ማስፋት የበለጠ ደስተኛ እንደሚያደርግ በንግግሩ ላይ ተገልጾ ነበር። ዳንኤል ይህ ሐሳብ እውነት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ባለቤቱ ሚርያም፣ አቅኚ ሆና ማገልገል ጀምራ የነበረ ሲሆን የተለያዩ በረከቶችን በማግኘቷ ደስተኛ ሆናለች።

ዳንኤል ከንግግሩ በኋላ “በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ለማድረግ ወሰንኩ” ሲል ተናግሯል። ደግሞም ያደረገው ይህንኑ ነው። በሥራ የሚያሳልፈውን ሰዓት ቀንሶ የዘወትር አቅኚ ሆነ፤ በተጨማሪም እሱና ባለቤቱ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረው ቢያገለግሉ ምን ያህል ደስተኛ እንደሚሆኑ ማሰብ ጀመረ።

ተፈታታኝ ሁኔታዎች ከዚያም አስደሳች ዜና

ግንቦት 2007 ዳንኤልና ሚርያም ሥራቸውን በማቆም ከዚያ በፊት ጎብኝተዋት ወደነበረችው ፓናማ ተዛወሩ። አዲሱ የአገልግሎት ክልላቸው፣ በካሪቢያን ባሕር ላይ የሚገኙትን ቦካስ ዴል ቶሮ የሚባሉ ደሴቶችን ያቀፈ ነው፤ አብዛኞቹ የደሴቶቹ ነዋሪዎች የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት የንጋቤ ሕዝቦች ናቸው። ዳንኤልና ሚርያም ያጠራቀሙትን ገንዘብ በመጠቀም ፓናማ ውስጥ ለስምንት ወራት ለመቆየት አስበው ነበር።

በደሴቶቹ ላይ የሚጠቀሙበት መጓጓዣ ጀልባ እና ብስክሌት ነበር፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በብስክሌት ያደረጉትን ጉዞ መቼም አይረሱትም። ወደ 32 ኪሎ ሜትር በሚሆን ቀጥ ያለ አቀበት ላይ በጠራራ ፀሐይ መጓዝ ነበረባቸው። ዳንኤል በጣም በመዛሉ ራሱን ሊስት ተቃርቦ ነበር። ይሁንና በጉዞው ወቅት ያገኟቸው የንጋቤ ሰዎች ቤታቸው ተቀብለው አስተናገዷቸው፤ በተለይም ዳንኤልና ሚርያም በአካባቢው ቋንቋ አንዳንድ ቃላትን ሲናገሩ ሰዎቹ በደስታ ተቀበሏቸው። ብዙም ሳይቆይ 23 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ይመሩ ጀመር።

ይሁን እንጂ ያጠራቀሙት ገንዘብ ሲያልቅ የባልና ሚስቱ ደስታ ወደ ሐዘን ተቀየረ። ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ስፔን ስለ መመለስ ስናስብ እንባችን ይመጣ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ትተን መሄድ በጣም ከብዶን ነበር።” ከአንድ ወር በኋላ ግን አስደሳች ዜና ሰሙ። ሚርያም እንዲህ ብላለች፦ “ልዩ አቅኚዎች ሆነን እንድናገለግል ተጋበዝን። በዚሁ የአገልግሎት ምድባችን ላይ መቆየት መቻላችን በጣም አስደሰተን!”

ከሁሉ የላቀ ደስታ ያስገኘላቸው ነገር

በ2015 በድርጅቱ ውስጥ በተካሄዱ ለውጦች የተነሳ ዳንኤል እና ሚርያም በዘወትር አቅኚነት እንዲያገለግሉ ተመደቡ። ታዲያ ምን ያደርጉ ይሆን? በመዝሙር 37:5 ላይ በሚገኘው ማረጋገጫ እንደሚተማመኑ አሳይተዋል፤ ጥቅሱ “መንገድህን ለይሖዋ አደራ ስጥ፤ በእሱ ታመን፤ እሱም ለአንተ ሲል እርምጃ ይወስዳል” ይላል። አቅኚ ሆነው ለማገልገል የሚያስችላቸውን ሰብዓዊ ሥራ ያገኙ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በቤራግዋስ፣ ፓናማ በሚገኝ ጉባኤ ውስጥ እያገለገሉ ነው።

ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “ስፔንን ለቀን ከመሄዳችን በፊት አኗኗራችንን ቀላል በማድረግ ረገድ ምን ያህል እንደሚሳካልን እርግጠኞች አልነበርንም። አሁን ግን ይህን ማድረግ ችለናል፤ ደግሞም መሠረታዊ የሆኑ ነገሮችን አጥተን አናውቅም።” ታዲያ ከሁሉ የላቀ ደስታ ያስገኘላቸው ምን ይሆን? እነዚህ ባልና ሚስት “ትሑት የሆኑ ሰዎችን ስለ ይሖዋ ማስተማር ተወዳዳሪ የሌለው ደስታ ያስገኛል!” በማለት ተናግረዋል።