በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ታማኞች ሲባረኩ አይቻለሁ

ታማኞች ሲባረኩ አይቻለሁ

ከሌሎች ጋር ያደረጋችኋቸውን ሕይወታችሁን የቀየሩ ውይይቶች ታስታውሱ ይሆናል። እኔ በበኩሌ ከ50 ዓመት ገደማ በፊት ኬንያ ውስጥ ከጓደኛዬ ጋር እሳት አጠገብ ተቀምጠን ያወራነውን ወሬ መቼም አልረሳውም። በወቅቱ ለወራት ያህል ካደረግነው ጉዞ የተነሳ ቆዳችን በፀሐይ ጠቁሮና ሻክሮ ነበር። እዚያ እሳት አጠገብ ቁጭ ብለን ሃይማኖታዊ ይዘት ስላለው አንድ ፊልም ስናወራ ጓደኛዬ “ፊልሙ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መረጃ የተዛባ ነው” አለኝ።

ጓደኛዬ ሃይማኖተኛ ሰው እንደሆነ ስላላሰብኩ የተናገረው ነገር አሳቀኝ። “ለመሆኑ አንተ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ታውቅና ነው?” ብዬ ጠየቅኩት። ለጥያቄዬ መልስ ለመስጠት አመንትቶ ነበር። በመጨረሻ ግን እናቱ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነችና ከእሷ አንዳንድ ነገሮችን እንደተማረ ነገረኝ። ለማወቅ ስለጓጓሁ ተጨማሪ ጥያቄዎች ጠየቅኩት።

ስለዚህ ጉዳይ እያወራን በጣም አመሸን። ጓደኛዬ መጽሐፍ ቅዱስ የዚህ ዓለም ገዢ ሰይጣን መሆኑን እንደሚያስተምር ነገረኝ። (ዮሐ. 14:30) ምናልባት አንዳንዶቻችሁ ይህን ነገር ከልጅነታችሁ አንስቶ ታውቁ ይሆናል፤ ለእኔ ግን ይህ ሐሳብ አዲስና ትኩረት የሚስብ ነበር። ዓለምን የሚቆጣጠረው ደግና ፍትሐዊ የሆነ አምላክ ነው ሲባል እሰማለሁ። ግን በሕይወት ውስጥ ያየኋቸው ነገሮች ከዚህ አባባል ጋር የሚስማሙ አልነበሩም። ገና የ26 ዓመት ወጣት የነበርኩ ቢሆንም ብዙ አሳዛኝ ነገሮች አይቻለሁ።

አባቴ በዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል ውስጥ ጄት አብራሪ ነበር። ስለዚህ የጦር ሠራዊቱ በማንኛውም ጊዜ የኑክሌር ጦርነት ሊጀምር እንደሚችል ገና ከልጅነቴ እጠብቅ ነበር። በካሊፎርኒያ የኮሌጅ ትምህርቴን ስከታተል ደግሞ የቬትናም ጦርነት ተነሳ። ተማሪዎች በሚያደርጓቸው የተቃውሞ ሰልፎች እካፈል ጀመር። ፖሊሶች ዱላ ይዘው ሲያባርሩን በአስለቃሽ ጭሱ የተነሳ መተንፈስና ዓይናችንን መግለጥ አቅቶን እንሸሻለን። በዓመፅና በትርምስ የተሞላ ጊዜ ነበር። በወቅቱ በፖለቲካ ምክንያት የተገደሉ ሰዎችን፣ የተቃውሞ ሰልፎችንና ረብሻዎችን ማየት የተለመደ ነው። ሁሉም ሰው ሊደረግ ከሚገባው ነገር ጋር በተያያዘ የተለያየ አመለካከት ነበረው። ሁኔታው በጣም ግራ የሚያጋባ ነበር።

ከለንደን ወደ ማዕከላዊ አፍሪካ

በ1970 በአላስካ ሰሜናዊ ጠረፍ ሥራ ይዤ ብዙ ገንዘብ አገኘሁ። ከዚያም ወደ ለንደን ሄጄ ሞተር ሳይክል ገዛሁና ምንም መድረሻ በአእምሮዬ ሳልይዝ ወደ ደቡብ ጉዞ ጀመርኩ። ከወራት በኋላ አፍሪካ ደረስኩ። በጉዞዬ ላይ ያገኘኋቸው ሰዎችም ተብትበው ከያዟቸው ችግሮች ማምለጥ የሚፈልጉ ነበሩ።

ካየሁትና ከሰማሁት ነገር አንጻር መጽሐፍ ቅዱስ ምድርን የሚቆጣጠረው አንድ ክፉ መንፈሳዊ ፍጡር እንደሆነ የሚያስተምረውን ትምህርት አሳማኝ ሆኖ አገኘሁት። ግን ‘ታዲያ አምላክ ምን እያደረገ ነው ያለው?’ የሚል ጥያቄ ተፈጠረብኝ።

በቀጣዮቹ ወራት ለጥያቄዬ መልስ አገኘሁ። ከዚያም በጊዜ ሂደት፣ ለእውነተኛው አንድ አምላክ ታማኝነታቸውን ካሳዩ በርካታ ወንዶችና ሴቶች ጋር መተዋወቅ እንዲሁም ከእነሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ቻልኩ።

ሰሜን አየርላንድ—“የቦምብና የጥይት አገር”

ወደ ለንደን ስመለስ ከጓደኛዬ እናት ጋር ተገናኘሁ፤ እሷም መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠችኝ። በኋላም ወደ አምስተርዳም፣ ኔዘርላንድስ ሄድኩ። እዚያ ሳለሁ አንድ የይሖዋ ምሥክር የመንገድ መብራት ሥር ቁጭ ብዬ መጽሐፍ ቅዱስ ሳነብ አይቶኝ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ እንዳውቅ ረዳኝ። ቀጥሎ ደግሞ ወደ ደብሊን፣ አየርላንድ ሄድኩ፤ በዚያም የይሖዋ ምሥክሮችን ቅርንጫፍ ቢሮ አግኝቼ ዋናውን በር አንኳኳሁ። አርተር ማቲውስ ከተባለ አስተዋይና ተሞክሮ ያለው ወንድም ጋር የተዋወቅኩት ያኔ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንደምፈልግ ለአርተር ነገርኩት፤ እሱም ሊያስጠናኝ ተስማማ።

የማጠናው በከፍተኛ ጉጉት ነበር፤ የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጇቸውን መጻሕፍትና የመጽሔት ጥራዞች በትጋት አነብብ ጀመር። መጽሐፍ ቅዱስንም አነብ ነበር። ደስታዬ ወደር አልነበረውም! በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ትናንሽ ልጆች እንኳ የተማሩ ሰዎችን ለዘመናት ሲያሳስቡ የቆዩ ጥያቄዎችን መልስ እንደሚያውቁ ተመለከትኩ። ‘ክፋት የኖረው ለምንድን ነው? አምላክ ማን ነው? ስንሞት ምን እንሆናለን?’ ለሚሉት ጥያቄዎች በቀላሉ መልስ መስጠት ይችላሉ። ጓደኞቼ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ይህ መሆኑ ምንም አያስገርምም፤ ምክንያቱም በአገሪቱ ውስጥ ሌላ የማውቀው ሰው አልነበረም። እነዚህ ወዳጆቼ ይሖዋን እንድወደውና የእሱን ፈቃድ ለማድረግ እንድነሳሳ ረድተውኛል።

ናይጀል፣ ዴኒስ እና እኔ

በ1972 ተጠመቅኩ። ከአንድ ዓመት በኋላ አቅኚ ሆኜ በኒውሪ፣ ሰሜን አየርላንድ ውስጥ ባለ አነስተኛ ጉባኤ ማገልገል ጀመርኩ። እዚያ ሳለሁ ተራራ ላይ ለብቻዋ ነጠል ብላ ያለች የድንጋይ ጎጆ ቤት ተከራይቼ ነበር። ከቤቴ አጠገብ ባለው መስክ ላይ ከብቶች ይሰማሩ ስለነበር ንግግሬን እነሱ ፊት እለማመዳለሁ። ከብቶቹ እያመነዠጉ ሲያዩኝ በትኩረት የሚያዳምጡ ነበር የሚመስሉት። ምክር ሊሰጡኝ ባይችሉም አድማጮችን እያየሁ እንዴት ንግግር ማቅረብ እንደምችል ለመለማመድ ረድተውኛል። በ1974 ልዩ አቅኚ ሆኜ የተሾምኩ ሲሆን ናይጀል ፒት የተባለ ወንድምም አብሮኝ እንዲያገለግል ተመደበ፤ እኔና ናይጀል ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የቅርብ ወዳጆች ነን።

በወቅቱ ሰሜን አየርላንድ በግጭት ትታመስ ነበር። በዚህ የተነሳ አንዳንዶች የሰሜኑን ክፍል “የቦምብና የጥይት አገር” በማለት ይጠሩት ነበር። የመሣሪያ ጥቃቶችን፣ ተኩሶችንና የቦምብ ፍንዳታዎችን ማየት የተለመደ ነበር። ግጭቱ ፖለቲካዊም ሃይማኖታዊም ገጽታ ነበረው። ሆኖም ፕሮቴስታንቶቹም ሆኑ ካቶሊኮቹ የይሖዋ ምሥክሮች ፖለቲካ ውስጥ እንደማይገቡ ስላወቁ በነፃነትና ያለስጋት መስበክ ቻልን። ነዋሪዎቹ ግጭት የሚነሳው መቼና የት እንደሆነ ያውቃሉ፤ ስለዚህ እዚያ አካባቢ እንዳንሄድ አስቀድመው ያስጠነቅቁናል።

ያም ሆኖ አደገኛ ሁኔታዎች መፈጠራቸው አልቀረም። አንድ ቀን እኔና ዴኒስ ካሪጋን የተባለ አቅኚ በአቅራቢያችን ባለ የይሖዋ ምሥክሮች የሌሉበት መንደር ውስጥ እያገለገልን ነበር፤ ወደዚህ መንደር ሄጄ የማውቀው አንዴ ብቻ ነው። አንዲት ሴት ‘ልትሰልሉ የመጣችሁ የብሪታንያ ወታደሮች ናችሁ’ ብላ ወነጀለችን፤ ምናልባት እንዲህ ያለችው የሁለታችንም የአነጋገር ዘዬ ከአይሪሽ የአነጋገር ዘዬ የተለየ ስለሆነ ሳይሆን አይቀርም። ሴትየዋ እንዲህ ስትል በጣም ፈራን። ምክንያቱም በወቅቱ ወታደሮችን ሰላም ሲሉ የታዩ ሰዎች እንኳ ሊገደሉ ወይም ጉልበታቸው ላይ በጥይት ሊመቱ ይችላሉ። ውጭ ላይ ብቻችንን በብርድ ተቆራምደን አውቶቡስ እየጠበቅን ሳለ አንድ መኪና መጥቶ የወነጀለችን ሴት ያለችበት ካፌ በራፍ ላይ ቆመ። ሴትየዋ ከካፌው ወጥታ መኪናው ውስጥ ላሉት ሁለት ሰዎች ወደ እኛ እየጠቆመች በስሜት የሆነ ነገር ትነግራቸው ጀመር። ከዚያም ሰዎቹ ቀስ ብለው በመኪናቸው ወደ እኛ መጡና አውቶቡሱ ስለሚመጣበት ሰዓት አንዳንድ ጥያቄዎችን ጠየቁን። አውቶቡሱ ሲመጣ ሹፌሩን አነጋገሩት። ምን እንደሚሉ መስማት አልቻልንም። ግን አውቶቡሱ ውስጥ ሌሎች ተሳፋሪዎች ስላልነበሩ እኛን ከከተማው ወጣ አድርጎ የሆነ እርምጃ እንዲወስድብን ለሹፌሩ እየነገሩት እንደሆነ እርግጠኞች ሆንን። ሆኖም የፈራነው ነገር አልደረሰም። ከአውቶቡሱ ስወርድ ሹፌሩን “የቅድሞቹ ሰዎች ስለ እኛ እየጠየቁህ ነበር?” አልኩት። እሱም እንዲህ አለኝ፦ “ማን እንደሆናችሁ አውቃለሁ፤ ለእነሱም ነግሬያቸዋለሁ። ስለዚህ ስጋት አይግባችሁ። ምንም ነገር አይደርስባችሁም።”

መጋቢት 1977፣ በሠርጋችን ቀን

በ1976 በደብሊን በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ a ላይ ፖሊን ሎማክስ ከተባለች ከእንግሊዝ የመጣች ልዩ አቅኚ ጋር ተዋወቅኩ። ፖሊን መንፈሳዊ፣ ትሑትና ደስ የምትል እህት ነች። እሷና ወንድሟ ሬይ እውነትን የሰሙት ከወላጆቻቸው ነው። ከአንድ ዓመት በኋላ ከፖሊን ጋር ትዳር መሠረትን፤ ከዚያም በባሊሚና፣ ሰሜን አየርላንድ በልዩ አቅኚነት ማገልገላችንን ቀጠልን።

ለተወሰነ ጊዜ በወረዳ ሥራ በተካፈልንበት ወቅት በቤልፋስት፣ በለንደንዴሪ እና በሌሎች አደገኛ አካባቢዎች ያሉ ወንድሞችን የማገልገል መብት አግኝተናል። ይሖዋን ለማገልገል ሲሉ ሥር የሰደዱ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ያስወገዱ እንዲሁም ጭፍን ጥላቻን የተቋቋሙ ወንድሞችንና እህቶችን እምነት በማየታችን በጣም ተበረታተናል። ይሖዋ ለእነዚህ ወንድሞችና እህቶች ጥበቃ አድርጎላቸዋል፤ እንዲሁም አብዝቶ ባርኳቸዋል!

በአየርላንድ ለአሥር ዓመት ያህል ኖርኩ። ከዚያም በ1981 በ72ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት እንድንካፈል ተጋበዝን። ከተመረቅን በኋላ በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው በሴራ ሊዮን እንድናገለግል ተመደብን።

ሴራ ሊዮን—በድህነት የተፈተነ እምነት

በሚስዮናውያን ቤት ውስጥ በጣም ደስ ከሚሉ 11 ወንድሞችና እህቶች ጋር አብረን እንኖር ነበር። ቤቱ አንድ ኩሽና፣ ሦስት መጸዳጃ ቤት፣ ሁለት መታጠቢያ ቤት፣ አንድ ስልክ፣ አንድ የልብስ ማጠቢያ ማሽንና አንድ ማድረቂያ ነበረው፤ እነዚህን ነገሮች በጋራ እንጠቀም ነበር። በተደጋጋሚ መብራት ይጠፋል፤ መቼ ጠፍቶ መቼ እንደሚመጣም አይታወቅም። ኮርኒሱን አይጦች ይፈነጩበት ነበር፤ ምድር ቤቱ ውስጥ ደግሞ ኮብራዎች ሾልከው ይገባሉ።

አጎራባች አገር በሆነችው በጊኒ በሚደረግ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወንዝ ስናቋርጥ

የኑሮ ሁኔታው አመቺ ባይሆንም አገልግሎቱ በጣም አስደሳች ነበር። ሰዎቹ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ስላላቸው በትኩረት ያዳምጣሉ። ብዙዎች መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው እውነትን ተቀብለዋል። የአካባቢው ሰዎች የሚጠሩኝ “አቶ ሮበርት” ብለው ነበር። ፖሊንን ደግሞ “ወይዘሮ ሮበርት” ብለው ነበር የሚጠሯት። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የምሠራው ሥራ ብዙ ጊዜዬን ስለሚወስድብኝ በመስክ አገልግሎት የማሳልፈው ጊዜ ቀነሰ፤ ስለዚህ ሰዎች ፖሊንን “ወይዘሮ ፖሊን” እኔን ደግሞ “አቶ ፖሊን” ብለው ይጠሩኝ ጀመር። ይህ ፖሊንን አስደስቷታል!

በሴራ ሊዮን በስብከት ዘመቻ ለመካፈል ስንሄድ

አብዛኞቹ ወንድሞች ድሆች ናቸው፤ ይሖዋ ግን ሁሌም ይንከባከባቸዋል፤ አንዳንዴ እንዲህ የሚያደርግበት መንገድ በጣም ያስገርማል። (ማቴ. 6:33) አንዲት እህት ያጋጠማትን አስታውሳለሁ፤ እህት በእጇ የነበራት ለእሷና ለልጆቿ የዕለት ምግብ የምትገዛበት ገንዘብ ብቻ ነበር። ሆኖም አንድ ወንድም የወባ መድኃኒት ለመግዛት ገንዘብ ስላነሰው ያላትን ሁሉ ለእሱ ሰጠችው። በዚያኑ ቀን አንዲት ሴት እህት ጋ ሄዳ ፀጉሯን እንድትሠራት ጠየቀቻት፤ ከዚያም ገንዘብ ከፈለቻት። እንዲህ ያሉ ብዙ አጋጣሚዎችን አስታውሳለሁ።

ናይጄርያ—ከአዲስ ባሕል ጋር መላመድ

በሴራ ሊዮን ለዘጠኝ ዓመት ያህል ከቆየን በኋላ ወደ ናይጄርያ ቤቴል ተዛወርን። የናይጄርያ ቅርንጫፍ ቢሮ ትልቅ ነው። እኔ ሴራ ሊዮን ሳለሁ የምሠራውን ያንኑ የቢሮ ሥራ ነበር የምሠራው፤ ለፖሊን ግን ለውጡ ትልቅና ከባድ ነበር። ፖሊን በየወሩ 130 ሰዓት በአገልግሎት ታሳልፍና ውጤታማ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ትመራ ነበር። አሁን ግን የተመደበችው በስፌት ክፍል ውስጥ እንድትሠራ ነው፤ በዚያ ቀኑን ሙሉ የምታሳልፈው የተቀደዱ ልብሶችን በመጠገን ነው። ሁኔታውን ለመልመድ ጊዜ ቢፈጅባትም ሌሎች የምታከናውነውን ሥራ በጣም እንደሚያደንቁ አስተዋለች፤ ደግሞም ሌሎች ቤቴላውያንን በማበረታታት ላይ ትኩረት አደረገች።

የናይጄርያ ባሕል ለእኛ አዲስ ስለነበር ብዙ ነገር መማር አስፈልጎናል። በአንድ ወቅት አንድ ወንድም አንዲትን አዲስ ቤቴላዊ ሊያስተዋውቀኝ ቢሮዬ ይዟት መጣ። ልጨብጣት እጄን ስዘረጋ እግሬ ሥር ተደፋች። በዚህ ጊዜ በጣም ደነገጥኩ። ወዲያውኑ ሁለት ጥቅሶች ወደ አእምሮዬ መጡ፦ የሐዋርያት ሥራ 10:25, 26 እንዲሁም ራእይ 19:10። ‘ይህችን እህት ላስቁማት ወይስ ምን ባደርግ ይሻላል?’ ብዬ አሰብኩ። ‘ግን ደግሞ እህት ቤቴል እንድታገለግል ስለተጠራች መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚያስተምር ታውቃለች’ አልኩ።

እህት ያደረገችው ነገር በጣም ስላስደነገጠኝ ከዚያ በኋላ ምን እንዳወራሁ ራሱ አላውቀውም፤ በኋላ ግን በጉዳዩ ላይ ምርምር አደረግኩ። እህት ያደረገችው ነገር በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የተለመደ ባሕል እንደሆነ ተረዳሁ። ወንዶችም ተመሳሳይ ነገር ያደርጋሉ። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት የአክብሮት መግለጫ እንጂ አምልኮ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ይህን የሚያሳዩ ምሳሌዎች አሉ። (1 ሳሙ. 24:8) በወቅቱ ባለማወቅ እህቴን የሚያሸማቅቅ ነገር ባለመናገሬ ተደሰትኩ።

በናይጄርያ በቆየንባቸው ዓመታት አስደናቂ ታማኝነት ካሳዩ ብዙ ናይጄርያዊ ወንድሞችና እህቶች ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ አግኝተናል። ለምሳሌ የአይዛያ አዳግቦናን ተሞክሮ ልንገራችሁ። b አይዛያ እውነትን የሰማው በወጣትነቱ ነው፤ ከዚያ ግን የሥጋ ደዌ በሽታ እንዳለበት በምርመራ ታወቀ። ስለዚህ የሥጋ ደዌ ሕመምተኞች በሚኖሩበት መንደር እንዲኖር ተደረገ፤ በዚያ ያለው የይሖዋ ምሥክር እሱ ብቻ ነበር። ተቃውሞ ቢደርስበትም ከ30 የሚበልጡ የሥጋ ደዌ ሕመምተኞች ወደ እውነት እንዲመጡና በዚያ መንደር ውስጥ ጉባኤ እንዲቋቋም ረድቷል።

ኬንያ—ወንድሞች በትዕግሥት ይዘውኛል

በኬንያ ወላጆቹ ከሞቱበት አውራሪስ ጋር የተነሳነው ፎቶግራፍ

በ1996 ወደ ኬንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ተዛወርን። መግቢያዬ ላይ ከነገርኳችሁ ወዲህ ወደ ኬንያ ተመልሼ ስሄድ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው። የምንኖረው ቤቴል ውስጥ ነበር። ወደ ግቢያችን ከሚመጡት ጎብኚዎች መካከል ጦጣዎች ይገኙበታል። ጦጣዎቹ እህቶች ፍራፍሬ ተሸክመው ሲሄዱ ይቀሟቸው ነበር። አንድ ቀን ቤቴል ያለች አንዲት እህት መስኮቷን ሳትዘጋ ሄደች። ወደ ክፍሏ ስትመለስ በርከት ያሉ ጦጣዎች ክፍሏ ውስጥ ያለውን ምግብ ሲመገቡ አገኘቻቸው። እህት እየጮኸች ከክፍሉ ወጣች። ጦጣዎቹም እየጮሁ በመስኮት ዘለው ወጡ።

እኔና ፖሊን በስዋሂሊ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ተመደብን። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት እንድመራ ተመደብኩ (አሁን የጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተብሎ ይጠራል)። ሆኖም የስዋሂሊ ቋንቋ ችሎታዬ ከአንድ ሕፃን ያልተሻለ ነበር። ጥያቄዎቹን ማንበብ እንድችል ጽሑፉን አስቀድሜ አጠናዋለሁ። ግን ተሰብሳቢዎቹ የሚሰጡት ሐሳብ በጽሑፉ ላይ ካለው ትንሽ እንኳ ከተለየ ምንም አይገባኝም። ሁኔታው በጣም ጭንቅ የሚል ነበር! ወንድሞችና እህቶች በጣም ነበር የሚያሳዝኑኝ። ዝግጅቱን ምንም ሳያጉረመርሙ በትዕግሥትና በትሕትና መቀበላቸው በጣም አስገረመኝ።

ዩናይትድ ስቴትስ—በብልጽግና የተፈተነ እምነት

ኬንያ የቆየነው አንድ ዓመት ለማይሞላ ጊዜ ነበር። በ1997 በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ ባለው ቤቴል እንድናገለግል ተጠራን። በዚህ ምድባችን ደግሞ ሰዎች ቁሳዊ ሀብት አላቸው፤ ግን ይህ ራሱ የሚያስከትለው ችግር አለ። (ምሳሌ 30:8, 9) ሆኖም እንዲህ ባለ አገርም እንኳ ወንድሞችና እህቶች ያላቸውን አስደናቂ እምነት ማየት ችለናል። ወንድሞቻችን ጊዜያቸውንና ጥሪታቸውን የሚጠቀሙት ራሳቸውን ለማበልጸግ ሳይሆን የይሖዋ ድርጅት የሚያከናውነውን ሥራ ለመደገፍ ነው።

ባሳለፍናቸው ዓመታት ውስጥ የእምነት ባልንጀሮቻችን በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ያሳዩትን እምነት መመልከት ችለናል። በአየርላንድ የእርስ በርስ ጦርነት፣ በአፍሪካ ድህነትና የቦታ ርቀት፣ በዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ብልጽግና የሚያስከትለውን ፈተና ተቋቁመው እምነት አሳይተዋል። ይሖዋ በሁሉም ዓይነት ሁኔታዎች ሥር ለእሱ ያላቸውን ፍቅር የሚያሳዩ ሕዝቦቹን ከላይ ሆኖ ሲመለከት ምንኛ ይደሰት ይሆን!

ከፖሊን ጋር በዎርዊክ ቤቴል

ዓመታቱ “ከሸማኔ መወርወሪያ ይበልጥ በፍጥነት [አልፈዋል]።” (ኢዮብ 7:6) አሁን በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት እያገለገልን ነው፤ በዚህ ጊዜም ቢሆን እርስ በርሳቸው ከልብ ከሚዋደዱ ሰዎች ጋር የማገልገል መብት በማግኘታችን ደስተኞች ነን። ንጉሣችንን ክርስቶስ ኢየሱስን ለመደገፍ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ በመቻላችን ደስታና እርካታ ይሰማናል፤ ክርስቶስ እጅግ ብዙ ለሆኑ ታማኞቹ በቅርቡ ወሮታቸውን ይከፍላቸዋል።—ማቴ. 25:34

a በወቅቱ ክልል ስብሰባዎች የሚጠሩት አውራጃ ስብሰባ ተብለው ነበር።

b የአይዛያ አዳግቦና የሕይወት ታሪክ በሚያዝያ 1, 1998 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 22-27 ላይ ወጥቷል። ወንድም አይዛያ በ2010 ሕይወቱ አልፏል።