መንፈሳዊ ሰው መሆን—ምን ማለት ነው?
“አምላክ፣ ሁላችሁም ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራችሁ ያድርግ።”—ሮም 15:5
1, 2. (ሀ) ብዙዎች መንፈሳዊ አስተሳሰብ ማዳበር ስለሚያስገኛቸው ጥቅሞች ምን ይሰማቸዋል? (ለ) ከመንፈሳዊነት ጋር በተያያዘ የትኞቹን መሠረታዊ ጥያቄዎች እንመረምራለን?
“መንፈሳዊ ሰው መሆኔ፣ ይበልጥ ደስተኛ ያደረገኝ ከመሆኑም ሌላ በየዕለቱ የሚያጋጥሙኝን ፈተናዎች ለመወጣት አስችሎኛል።” ይህን የተናገረችው በካናዳ የምትኖር አንዲት እህት ናት። በብራዚል የሚኖር አንድ ወንድም ደግሞ “መንፈሳዊ አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት በማድረጋችን በትዳር ሕይወት 23 አስደሳች ዓመታት ማሳለፍ ችለናል” በማለት ተናግሯል። በፊሊፒንስ የሚኖር ሌላ ወንድምም እንዲህ ብሏል፦ “መንፈሳዊ ሰው መሆኔ የአእምሮ ሰላም አስገኝቶልኛል፤ ከዚህም በተጨማሪ የተለያየ አስተዳደግ ካላቸው ወንድሞች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረኝ ረድቶኛል።”
2 እነዚህ ክርስቲያኖች የሰጡት ሐሳብ መንፈሳዊ ሰው መሆን ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ያጎላል። ከዚህ አንጻር ‘መንፈሳዊ እድገት ማድረግና እነዚህ ክርስቲያኖች ያገኟቸውን ጥቅሞች ይበልጥ ማጣጣም የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። ለዚህ ጥያቄ መልስ ከማግኘታችን በፊት ግን መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ የሆኑ ወይም መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎችን እንዴት እንደሚገልጻቸው መረዳት ያስፈልገናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ ለሦስት መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን፦ (1) መንፈሳዊ ሰው መሆን ሲባል ምን ማለት ነው? (2) መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የእነማን ምሳሌ ሊረዳን ይችላል? (3) “የክርስቶስ አስተሳሰብ” እንዲኖረን ጥረት ማድረጋችን መንፈሳዊ ሰዎች ለመሆን የሚረዳን እንዴት ነው?
መንፈሳዊ ሰው በምን ተለይቶ ይታወቃል?
3. መጽሐፍ ቅዱስ በዓለማዊ ሰው እና በመንፈሳዊ ሰው መካከል ምን ልዩነት እንዳለ ይገልጻል?
3 ሐዋርያው ጳውሎስ ‘መንፈሳዊ ሰውን’ እና ‘ዓለማዊ ሰውን’ በማነጻጸር ያሰፈረው ሐሳብ መንፈሳዊ ሰው መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል። (1 ቆሮንቶስ 2:14-16ን አንብብ።) ‘በመንፈሳዊ ሰው’ እና ‘በዓለማዊ ሰው’ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ጳውሎስ እንደገለጸው “ዓለማዊ ሰው . . . ከአምላክ መንፈስ የሆኑትን ነገሮች አይቀበልም።” ምክንያቱም “እንዲህ ያሉት ነገሮች ለእሱ ሞኝነት ናቸው”፤ ደግሞም “ሊረዳቸው አይችልም።” በሌላ በኩል ግን “መንፈሳዊ ሰው ሁሉንም ነገር ይመረምራል” እንዲሁም “የክርስቶስ አስተሳሰብ” አለው። ጳውሎስ መንፈሳዊ ሰዎች እንድንሆን አበረታቶናል። ዓለማዊ ሰውን ከመንፈሳዊ ሰው ለመለየት የሚያስችሉን ሌሎች ነገሮችስ የትኞቹ ናቸው?
4, 5. ዓለማዊ ሰው ተለይቶ የሚታወቅባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
4 እስቲ በመጀመሪያ ዓለማዊ ሰው ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንዳለው እንመልከት። በዓለም ላይ ባሉ በብዙዎች ዘንድ የሚንጸባረቀው አስተሳሰብ ሥጋዊ ፍላጎትን በማርካት ላይ ያተኮረ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ “በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን ተጽዕኖ እያሳደረ ያለ መንፈስ” በማለት ገልጾታል። (ኤፌ. 2:2) ይህ መንፈስ አብዛኞቹ ሰዎች፣ የብዙኃኑን አካሄድ እንዲከተሉ ያደርጋቸዋል። እንዲህ ያሉት ሰዎች ትኩረታቸው በሙሉ ያረፈው በሥጋዊ ነገሮች ላይ ነው። በመሆኑም የሚያደርጉት ለራሳቸው ትክክል መስሎ የታያቸውን ነገር ሲሆን አምላክ ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር ፈጽሞ ጥረት አያደርጉም። ዓለማዊ የሆነ ወይም ሥጋዊ አመለካከት ያለው ሰው ለራሱ ክብር ማግኘትና ቁሳዊ ነገሮችን ማካበት በሕይወቱ ውስጥ ከምንም ነገር በላይ ያሳስበዋል፤ በተጨማሪም መብቴ ነው ብሎ ለሚያስበው ነገር ትልቅ ቦታ ይሰጣል።
5 ዓለማዊ ሰው ተለይቶ የሚታወቅበት ሌላስ ምን ነገር አለ? ዓለማዊ የሆኑ ሰዎች “የሥጋ ሥራዎች” ተብለው የተገለጹትን ነገሮች ይፈጽማሉ። (ገላ. 5:19-21) ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ ሥጋዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ተለይተው የሚታወቁባቸውን ሌሎች ነገሮችም ገልጿል። ከእነዚህም መካከል ክፍፍልና አለመግባባት መፍጠር፣ ወገንተኝነት፣ እርስ በርስ በፍርድ ቤት መካሰስ፣ ለራስነት ሥልጣን አክብሮት አለማሳየት እንዲሁም ከልክ በላይ መብላትና መጠጣት ይገኙበታል። ሥጋዊ አመለካከት ያለው ሰው፣ ትክክል ያልሆነ ነገር ለማድረግ ሲፈተን በቀላሉ ይሸነፋል። (ምሳሌ 7:21, 22) አንዳንድ ሰዎች ዓለማዊ አስተሳሰብ ስለተቆጣጠራቸው ጨርሶ ‘መንፈሳዊ እንዳልሆኑ’ ወይም የአምላክ መንፈስ እንደሌላቸው ደቀ መዝሙሩ ይሁዳ ተናግሯል።—ይሁዳ 18, 19
6. መንፈሳዊ ሰው ተለይቶ የሚታወቅባቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
6 “መንፈሳዊ ሰው” መሆን ሲባልስ ምን ማለት ነው? ከዓለማዊ ሰው በተለየ መልኩ መንፈሳዊ ሰው ከአምላክ ጋር ላለው ዝምድና ትልቅ ቦታ ይሰጣል። መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ‘አምላክን ለመምሰል’ ጥረት ያደርጋሉ። (ኤፌ. 5:1) ይህም ሲባል የይሖዋን አስተሳሰብ ለመረዳት ብሎም ነገሮችን እሱ በሚመለከትበት መንገድ ለመመልከት ይጥራሉ ማለት ነው። ለእነዚህ ሰዎች አምላክ እውን ሆኖ ይታያቸዋል። ሥጋዊ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች በተቃራኒ መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች፣ መላ ሕይወታቸውን ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ለመምራት የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። (መዝ. 119:33፤ 143:10) መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው በሥጋ ሥራዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ “የመንፈስ ፍሬ” ለማፍራት ጥረት ያደርጋል። (ገላ. 5:22, 23) ነጥቡን ግልጽ ለማድረግ፦ ነገሮችን ሁልጊዜ በአዎንታዊ መንገድ የሚመለከት ሰው አዎንታዊ አስተሳሰብ አለው ይባላል፤ በተመሳሳይም ለመንፈሳዊ ነገሮች ትልቅ ቦታ የሚሰጥ ሰው መንፈሳዊ አስተሳሰብ አለው ሊባል ይችላል።
7. መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ አስተሳሰብ መያዝን በተመለከተ ምን ይላል?
7 መንፈሳዊ አስተሳሰብ መያዝን የሚያበረታቱ ሐሳቦችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። ለምሳሌ ማቴዎስ 5:3 “መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው፤ መንግሥተ ሰማያት የእነሱ ነውና” ይላል። ሮም 8:6 ደግሞ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ማዳበር ያለውን ጥቅም ሲገልጽ “በሥጋዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ሞት ያስከትላልና፤ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር ግን ሕይወትና ሰላም ያስገኛል” ይላል። በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ትኩረት ካደረግን በአሁኑ ጊዜ ከአምላክ ጋር ያለንን ሰላም ጠብቀን መኖርና ውስጣዊ ሰላም ማግኘት እንችላለን፤ ወደፊት ደግሞ የዘላለም ሕይወት እናገኛለን።
8. መንፈሳዊ ሰው ለመሆንና መንፈሳዊነታችንን ጠብቀን ለማቆየት ትግል ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
8 ይሁንና የምንኖረው አደገኛ በሆነ ዓለም ውስጥ ነው። ሥጋዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ስለምንኖር መንፈሳዊ ሰው ለመሆንና መንፈሳዊነታችንን ጠብቀን ለማቆየት ብርቱ ትግል ማድረግ ያስፈልገናል። አንድ ሰው መንፈሳዊነቱን ካጣ የዚህ ዓለም የተበከለ ‘አየር’ አእምሮውንና አስተሳሰቡን በቀላሉ ይቆጣጠረዋል። ታዲያ ከዚህ አደጋ ራሳችንን ለመጠበቅ ምን ሊረዳን ይችላል? መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?
ለትምህርታችን የሚሆኑ ምሳሌዎች
9. (ሀ) መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል? (ለ) የእነማንን መልካም ምሳሌ እንመለከታለን?
9 አንድ ልጅ የወላጆቹን ድርጊት ማስተዋሉና የእነሱን መልካም ምሳሌ መከተሉ ብስለት ለማዳበር ያስችለዋል። እኛም በተመሳሳይ ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ያላቸውን ሰዎች ምግባር በማስተዋልና ምሳሌያቸውን በመከተል በመንፈሳዊ ማደግ እንችላለን። በሌላ በኩል ደግሞ ሥጋዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆኑናል። (1 ቆሮ. 3:1-4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መልካምም ሆነ መጥፎ ምሳሌዎችን እናገኛለን። ሆኖም ዓላማችን መንፈሳዊ እድገት ማድረግ የምንችልበትን መንገድ ማወቅ ስለሆነ ጥሩ ምሳሌ ስለሚሆኑን አንዳንድ ሰዎች መመልከታችን ጠቃሚ ነው። ከዚህ ቀጥሎ የያዕቆብን፣ የማርያምንና የኢየሱስን ምሳሌ እንመረምራለን።
10. ያዕቆብ መንፈሳዊ ሰው መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
10 በመጀመሪያ የያዕቆብን ምሳሌ እንመልከት። በዛሬው ዘመን እንደምንኖረው እንደ አብዛኞቻችን ሁሉ የያዕቆብም ሕይወት አስቸጋሪ ነበር። ሥጋዊ አስተሳሰብ የነበረውን ወንድሙን ኤሳውን ችሎ መኖር ቀላል አልነበረም፤ በዚያ ላይ ደግሞ ኤሳው ሊገድለው ይፈልግ ነበር። ያዕቆብ ይህም እንዳይበቃው፣ በተደጋጋሚ ጊዜ ሊያታልለው የሞከረው አማቹ የሚያደርስበትን በደል መቋቋም ነበረበት። በዙሪያው ያሉት ሰዎች “ዓለማዊ” ቢሆኑም ያዕቆብ ግን መንፈሳዊ ሰው ነበር። ይህ የአምላክ አገልጋይ፣ ይሖዋ ለአብርሃም በገባው ቃል ላይ እምነት ነበረው፤ በተጨማሪም ቤተሰቡ በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ የሚጫወተው ልዩ ሚና እንዳለ ስለተገነዘበ ዘፍ. 28:10-15) ያዕቆብ ለአምላክ ዓላማና ለመሥፈርቶቹ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ኤሳው ጥቃት ሊሰነዝርበት እንደሆነ በተሰማው ወቅት ወደ አምላክ እንዲህ ሲል ጸልዮአል፦ “እንድታድነኝ እለምንሃለሁ፤ . . . አንተው ራስህ ‘በእርግጥ መልካም አደርግልሃለሁ፤ ዘርህንም ከብዛቱ የተነሳ ሊቆጠር እንደማይችል የባሕር አሸዋ አደርገዋለሁ’ ብለኸኛል።” (ዘፍ. 32:6-12) ያዕቆብ፣ ይሖዋ ለእሱም ሆነ ለአባቶቹ በገባው ቃል ላይ እምነት እንደነበረው እንዲሁም ከአምላክ ፈቃድና ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ ይፈልግ እንደነበር በግልጽ ማየት ይቻላል።
ቤተሰቡን ለመንከባከብ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል። (11. ማርያም መንፈሳዊ ሰው እንደነበረች እንዴት ማወቅ እንችላለን?
11 አሁን ደግሞ የማርያምን ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ የኢየሱስ እናት እንድትሆን ማርያምን የመረጣት ለምንድን ነው? መንፈሳዊ አስተሳሰብ ስለነበራት እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ይህን እንዴት ማወቅ እንችላለን? በአንድ ወቅት ማርያም ዘመዶቿ የሆኑትን ዘካርያስንና ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ ሄዳ ነበር፤ በዚያ እያለች ይሖዋን ለማወደስ የተጠቀመችባቸው አገላለጾች መንፈሳዊ ሰው እንደነበረች በግልጽ ያሳያሉ። (ሉቃስ 1:46-55ን አንብብ።) ማርያም የተናገረችው ነገር ለአምላክ ቃል ጥልቅ ፍቅር እንደነበራትና የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቃ ታውቅ እንደነበር ይጠቁማል። (ዘፍ. 30:13፤ 1 ሳሙ. 2:1-10፤ ሚል. 3:12) ከዚህም ሌላ ማርያምና ዮሴፍ አዲስ ተጋቢዎች ቢሆኑም እንኳ ኢየሱስን እስክትወልድ ድረስ የፆታ ግንኙነት እንዳልፈጸሙ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከዚህ ምን መረዳት እንችላለን? ማርያምም ሆነች ዮሴፍ የግል ፍላጎታቸውን ከማርካት ይበልጥ ያሳሰባቸው ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖራቸው ነበር። (ማቴ. 1:25) ከዚህም ሌላ ማርያም በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ የተከናወኑትን ነገሮች በትኩረት ትከታተል እንዲሁም የሚናገራቸውን ጥበብ ያዘሉ ሐሳቦች ታስተውል ነበር። በተጨማሪም “የተባሉትን ነገሮች ሁሉ በልቧ ትይዝ [እንደነበር]” መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሉቃስ 2:51) አምላክ ከመሲሑ ጋር በተያያዘ የተናገራቸው ነገሮች እንዴት እንደሚፈጸሙ የማወቅ ጉጉት እንደነበራት ግልጽ ነው። ማርያም የተወችው ምሳሌ በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ ፈቃድ ቅድሚያ መስጠት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ቆም ብለን እንድናስብ አያነሳሳንም?
12. (ሀ) ኢየሱስ የአባቱን ምሳሌ የተከተለው እንዴት ነው? (ለ) እኛስ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
12 መንፈሳዊ አስተሳሰብ በመያዝ ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ የሚሆነን ማን ነው? ኢየሱስ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። የኢየሱስ ሕይወትም ሆነ አገልግሎቱን ያከናወነበት መንገድ አባቱን ይሖዋን መምሰል እንደሚፈልግ የሚያሳይ ነው። የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብና ስሜት የነበረው ሲሆን በድርጊቱም አባቱን መስሏል፤ እንዲሁም ከአምላክ ፈቃድና መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወቱን መርቷል። (ዮሐ. 8:29፤ 14:9፤ 15:10) ነቢዩ ኢሳይያስ የይሖዋን ርኅራኄ የገለጸበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህን ጥቅስ የወንጌል ጸሐፊው ማርቆስ ስለ ኢየሱስ ከጻፈው ሐሳብ ጋር ማወዳደር እንችላለን። (ኢሳይያስ 63:9ን እና ማርቆስ 6:34ን አንብብ።) ታዲያ እኛስ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ምንጊዜም ርኅራኄ በማሳየት የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን? ልክ እንደ ኢየሱስ ምሥራቹን በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ራሳችንን እናስጠምዳለን? (ሉቃስ 4:43) መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የርኅራኄ ስሜት ያላቸው ከመሆኑም ባሻገር ሌሎችን ለመርዳት ጥረት ያደርጋሉ።
13, 14. (ሀ) መንፈሳዊ አስተሳሰብ በማዳበር ረገድ ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑ በዘመናችን ያሉ ክርስቲያኖች ምን እንማራለን? (ለ) አንድ ምሳሌ ጥቀስ።
13 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ምሳሌዎች በተጨማሪ በዘመናችንም መንፈሳዊ አስተሳሰብ በማዳበር ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑ በርካታ ክርስቲያኖች አሉ፤ እነዚህ ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ውስጥ ማስተካከያዎችን በማድረግ ክርስቶስን መምሰል ችለዋል። እንደነዚህ ያሉት ክርስቲያኖች በአገልግሎት ቀናተኞች፣ እንግዳ ተቀባዮችና ሩኅሩኆች እንደሆኑ ብሎም ሌሎች ግሩም ባሕርያትን እንደሚያንጸባርቁ አስተውለህ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ እነዚህን መልካም ባሕርያት ለማዳበር ጥረት በሚያደርጉበት ጊዜ እንደ ማንኛውም ሰው ከድክመቶቻቸውና ካለባቸው አለፍጽምና ጋር መታገል አስፈልጓቸዋል። በብራዚል የምትኖረውን ሬቸል የተባለች እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ እንዲህ ብላለች፦ “አዳዲስ ፋሽኖችን መከተል እወድ ነበር። በመሆኑም አለባበሴ ልከኝነት
የሚንጸባረቅበት አልነበረም። እውነትን ሳውቅ ግን መንፈሳዊ ሰው ለመሆን ስል አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ተነሳሳሁ። እንዲህ ያለ ለውጥ ማድረግ ቀላል ባይሆንልኝም ይበልጥ ደስተኛ እንድሆንና ዓላማ ያለው ሕይወት እንድመራ አስችሎኛል።”14 በፊሊፒንስ የምትኖረው የሬሊን ሁኔታ ደግሞ ከዚህ የተለየ ነበር። ከፍተኛ ትምህርት ተምራ ጥሩ ሥራ በመያዝ ትልቅ ደረጃ ላይ የመድረስ ግብ ነበራት። እንዲህ ብላለች፦ “ለመንፈሳዊ ግቦቼ የምሰጠው ቦታ እየቀነሰ መጣ። ይሁንና በሕይወቴ ውስጥ አንድ የጎደለኝ ነገር እንዳለ ይሰማኝ ጀመር፤ ከሥራዬ የበለጠ ላስቀድመው የሚገባ ነገር እንዳለ ተገነዘብኩ። በመሆኑም በይሖዋ አገልግሎት ላይ ይበልጥ ትኩረት ለማድረግ ወሰንኩ።” ከዚያ ጊዜ አንስቶ ሬሊን ይሖዋ በማቴዎስ 6:33, 34 ላይ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳላት በሕይወቷ እያሳየች ነው። ሬሊን “ይሖዋ ምንጊዜም እንደሚንከባከበኝ ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም!” ብላለች። እኛም በየጉባኤያችን ያሉ በዚህ ረገድ ምሳሌ የሚሆኑ ክርስቲያኖችን እናውቅ ይሆናል። ታዲያ የክርስቶስን አርዓያ የሚከተሉትን እነዚህን ታማኝ ክርስቲያኖች ለመምሰል አንነሳሳም?—1 ቆሮ. 11:1፤ 2 ተሰ. 3:7
“የክርስቶስ አስተሳሰብ” ይኑራችሁ
15, 16. (ሀ) ክርስቶስን ለመምሰል ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
15 እያንዳንዳችን ክርስቶስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ቆሮንቶስ 2:16 ላይ ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ስለመያዝ ይናገራል። ሮም 15:5 ደግሞ “ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ዓይነት አስተሳሰብ” ስለማዳበር ይገልጻል። በመሆኑም ክርስቶስን ለመምሰል፣ እሱ የሚያስብበትን መንገድ ማወቅና ማንነቱን በደንብ መረዳት ያስፈልገናል። ከዚያም የእሱን ፈለግ መከተል ይኖርብናል። ኢየሱስ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ከአምላክ ጋር ላለው ዝምድና ነው። ስለዚህ ኢየሱስን መምሰላችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ያስችለናል። የኢየሱስን አስተሳሰብ ማዳበራችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለዚህ ነው።
16 ታዲያ ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ክርስቶስ ተአምራት ሲፈጽም የማየት፣ ሲያስተምር የመስማት፣ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች የሚይዝበትን መንገድ የመመልከት እንዲሁም አምላክ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርግ የማስተዋል አጋጣሚ ነበራቸው። በመሆኑም “ላደረጋቸው ነገሮች ሁሉ እኛ ምሥክሮች ነን” በማለት ተናግረዋል። (ሥራ 10:39) እኛ ግን እንደ እነሱ ክርስቶስን የማየት አጋጣሚ የለንም። ይሁን እንጂ ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ የወንጌል ዘገባዎችን አስጽፎልናል፤ እነዚህ ዘገባዎች ኢየሱስን በአካል የምናውቀው ያህል ሆኖ እንዲሰማን ያደርጉናል። የማቴዎስን፣ የማርቆስን፣ የሉቃስንና የዮሐንስን መጻሕፍት ማንበባችን ብሎም በዘገባዎቹ ላይ ማሰላሰላችን የክርስቶስን አስተሳሰብ ለማወቅ ያስችለናል። ይህን ማድረጋችን “የእሱን ፈለግ በጥብቅ [ለመከተል]” እንዲሁም የክርስቶስን “አስተሳሰብ ለማንጸባረቅ” ይረዳናል።—1 ጴጥ. 2:21፤ 4:1
17. የክርስቶስን አስተሳሰብ ማዳበራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
17 የክርስቶስን አስተሳሰብ ማዳበራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው? ገንቢ ምግብ መመገብ ሰውነታችንን እንደሚያጠነክረው ሁሉ አእምሯችንን በክርስቶስ አስተሳሰብ መሙላታችንም መንፈሳዊነታችንን ያጠነክረዋል። በጊዜ ሂደት ደግሞ ክርስቶስ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ምን እንደሚያደርግ ማወቅ የምንችልበት ደረጃ ላይ እንደርሳለን። ይህም ሕሊናችንን የማይረብሽና አምላክን የሚያስደስት ውሳኔ ለማድረግ ያስችለናል። እነዚህ ጥቅሞች ‘ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመልበስ’ እንድንነሳሳ ያደርጉናል ቢባል አትስማማም?—ሮም 13:14
18. መንፈሳዊ ሰው ስለመሆን ከዚህ ርዕስ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
18 መንፈሳዊ ሰው መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ ተመልክተናል። በተጨማሪም መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች ከተዉት ጥሩ ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል ተወያይተናል። በመጨረሻም ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ማዳበራችን መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ እንዴት እንደሚረዳን አይተናል። ሆኖም ከመንፈሳዊነት ጋር በተያያዘ ልናውቃቸው የሚገቡ ሌሎች ነገሮችም አሉ። ለምሳሌ፣ በመንፈሳዊ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆንን መገምገም የምንችለው እንዴት ነው? መንፈሳዊነታችንን ይበልጥ ለማጠናከር ምን ማድረግ እንችላለን? መንፈሳዊነት በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል? በሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን።