ከታሪክ ማኅደራችን
ፖርቱጋል ውስጥ የመንግሥቱ ዘሮች የተዘሩበት መንገድ
መርከቧ የአትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጣ ወደ አውሮፓ እያቀናች ነው፤ ከተሳፋሪዎቹ አንዱ የሆነው ጆርጅ ያንግ፣ በብራዚል የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክ ስላከናወነው ሥራ መለስ ብሎ ሲያስብ ውስጡ በእርካታ ተሞላ። a ወንድም ያንግ ጉዞውን እየቀጠለ ሲሄድ ግን ትኩረቱን በአዲሱ ምድቡ ይኸውም ምሥራቹ እምብዛም ባልተሰበከባቸው የስፔንና የፖርቱጋል ክልሎች ላይ አደረገ። እዚያ ከደረሰ በኋላ፣ ወንድም ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ለሚያቀርባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮች ዝግጅት ለማድረግ እንዲሁም 300,000 ትራክቶችን ለማሰራጨት አስቧል!
ወንድም ያንግ በ1925 ጸደይ ላይ ሊዝበን ሲደርስ በአገሪቱ ሁከት ነግሦ ነበር። በ1910 የተካሄደው የሪፑብሊካኖች አብዮት የዘውድ አገዛዙን ስለገረሰሰው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያላት ኃይል ተዳክሟል። ሕዝቡ የበለጠ ነፃነት ያገኘ ቢሆንም አገሪቱ በሕዝባዊ ዓመፅ ትናወጥ ነበር።
ወንድም ያንግ ለወንድም ራዘርፎርድ ንግግር ዝግጅት እያደረገ ሳለ፣ በፖርቱጋል የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ በመካሄዱ አገሪቱ በወታደራዊ ሕግ መተዳደር ጀመረች። የብሪታንያና የሌሎች አገራት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ዋና ጸሐፊ፣ ወንድም ያንግን ብዙ ተቃውሞ ሊያጋጥመው እንደሚችል አስጠነቀቀው። ያም ቢሆን ወንድም ያንግ በካሞይሽ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስፖርት ማዕከል ውስጥ ለመሰብሰብ ፈቃድ የጠየቀ ሲሆን ፈቃዱንም አገኘ!
ወንድም ራዘርፎርድ ንግግር የሚያቀርብበት ቀን ግንቦት 13 ነበር። ብዙዎች ንግግሩን ለመስማት በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቁ ነበር! “በምድር ላይ ለዘላለም መኖር የሚቻለው እንዴት ነው?” በሚል ርዕስ የሕዝብ ንግግር እንደሚቀርብ የሚገልጹ ማስታወቂያዎች በሕንፃዎች ላይ ተለጥፈው እንዲሁም በጋዜጦች ላይ ወጥተው ነበር። ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎችም አዲስ ስለመጡት “ሐሰተኛ ነቢያት” የሚያስጠነቅቅ አንድ ርዕስ በፍጥነት በጋዜጣቸው ላይ አሳተሙ። በተጨማሪም ተቃዋሚዎች፣ ወንድም ራዘርፎርድ የሚያቀርባቸውን ትምህርቶች የሚቃወሙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ብሮሹሮችን በስፖርት ማዕከሉ መግቢያ ላይ ለሕዝብ አደሉ።
ያም ቢሆን አዳራሹ ወደ 2,000 በሚሆኑ ሰዎች ከዳር እስከ ዳር ግጥም ብሎ ሞላ፤ በቦታ ጥበት ምክንያት 2,000 ገደማ የሚሆኑ ሌሎች ሰዎች ወደ አዳራሹ መግባት አልቻሉም። አንዳንዶች በአዳራሹ ውስጥ የሚካሄደውን ነገር ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ስላደረባቸው በአዳራሹ ጎንና ጎን በሚገኙ የገመድ መሰላሎች ላይ ተንጠላጥለው ወደ ውስጥ ይመለከቱ ነበር፤ ሌሎች ደግሞ በስፖርት መሣሪያዎች ላይ ወጥተው ተቀመጡ።
በስብሰባው ዕለት አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ነበሩ። ተቃዋሚዎች ይጮኹ እንዲሁም ወንበሮችን ይሰባብሩ ነበር። ይሁን እንጂ ወንድም ራዘርፎርድ ተረጋግቶ ንግግሩን የቀጠለ ሲሆን ድምፁ በደንብ እንዲሰማ ሲል ጠረጴዛ ላይ ወጣ። ንግግሩ ያበቃው እኩለ ሌሊት ገደማ ነው፤ ከ1,200 የሚበልጡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ እንዲደርሳቸው እንደሚፈልጉ በመግለጽ ስማቸውንና አድራሻቸውን ሰጥተው ሄዱ። ኦ ሴኩሉ የተሰኘው ጋዜጣ በማግስቱ ስለ ወንድም ራዘርፎርድ ንግግር የሚያወሳ ርዕስ ይዞ ወጣ።
መስከረም 1925 በፖርቱጋልኛ የተዘጋጀ መጠበቂያ ግንብ ፖርቱጋል ውስጥ መታተም ጀመረ። (ቀደም ሲል የፖርቱጋልኛ
እትም ብራዚል ውስጥ መውጣት ጀምሮ ነበር።) በዚያው ጊዜ አካባቢ ቬርዚሊዮ ፈርግሰን የሚባል ብራዚል ውስጥ የነበረ ወንድም፣ ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩ ሥራ ለማገዝ ሲል ወደ ፖርቱጋል ለመዛወር አሰበ። ወንድም ፈርግሰን ብራዚል በሚገኘው አነስተኛ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ከወንድም ያንግ ጋር ይሠራ ነበር። ወንድም ፈርግሰን ከወንድም ያንግ ጋር በድጋሚ አብሮ ለመሥራት ከባለቤቱ ከሊዚ ጋር ወደ ፖርቱጋል መጣ። ወንድም ፈርግሰን ፖርቱጋል የደረሰው ጥሩ ጊዜ ላይ ነበር፤ ምክንያቱም ብዙም ሳይቆይ ወንድም ያንግ፣ ሶቪየት ኅብረትን ጨምሮ በሌሎች አገሮች ለመስበክ ሄደ።ፖርቱጋል ውስጥ ወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣ ተካሂዶ አምባገነናዊ መሪ ሲሾም በስብከቱ ሥራ ላይ የሚደርሰው ተቃውሞም እየተባባሰ ሄደ። ይሁንና ወንድም ፈርግሰን በድፍረት እዚያው ቆየ፤ እንዲሁም አነስተኛ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድን ለማበረታታትና እንቅስቃሴያቸውን ለማጠናከር የሚያስችሉ እርምጃዎችን ወሰደ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በቋሚነት ለሚያደርጓቸው ስብሰባዎች መኖሪያ ቤቱን እንዲጠቀሙበት ፈቃድ ጠየቀ። ጥቅምት 1927 ይህን ለማድረግ ፈቃድ ተሰጠው።
በአምባገነናዊው አገዛዝ የመጀመሪያው ዓመት ላይ ፖርቱጋል ውስጥ 450 ገደማ የሚሆኑ ሰዎች የመጠበቂያ ግንብ ኮንትራት ገብተው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በትራክቶችና በቡክሌቶች አማካኝነት የእውነት ቃል የፖርቱጋል ቅኝ ግዛቶች ወደነበሩት ወደ አንጎላ፣ ኤዞርዝ፣ ኬፕ ቨርድ፣ ምሥራቅ ቲሞር፣ ጎኣ፣ ማዴይራ እና ሞዛምቢክ ደረሰ።
በ1920 ማብቂያ ላይ ማንዌል ዳ ሲልቫ ዦርዳው የሚባል አንድ ትሑት ፖርቱጋላዊ አትክልተኛ ወደ ሊዝበን መጣ። ማኑዌል ብራዚል ውስጥ እያለ ወንድም ያንግ የሰጠውን የሕዝብ ንግግር ሰምቶ ነበር። የሰማው ነገር እውነት መሆኑን ወዲያውኑ ስለተገነዘበ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ወንድም ፈርግሰንን የማገዝ ጉጉት አደረበት። ማኑዌል ይህን ለማድረግ ሲል ኮልፖርተር (አቅኚዎች ቀደም ሲል የሚጠሩበት ስም ነው) ሆኖ ማገልገል ጀመረ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን የማተሙና የማሰራጨቱ ሥራ በዚህ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ተደራጅቶ ስለነበር በሊዝበን የተቋቋመው አዲስ ጉባኤ እያደገ ሄደ!
በ1934 ወንድም ፈርግሰንና ባለቤቱ ወደ ብራዚል መመለስ አስፈለጋቸው። ይሁንና ፖርቱጋል ውስጥ የእውነት ዘር ተዘርቶ ነበር። በስፔን የእርስ በርስ ጦርነት እንዲሁም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አውሮፓ ውስጥ ሁከት በነገሠበት ጊዜም እንኳ በፖርቱጋል የነበሩት ታማኝ ወንድሞች በአቋማቸው ጸንተዋል። እርግጥ ነው፣ ለተወሰነ ጊዜ ያህል እነዚህ ክርስቲያኖች እንደተዳፈነ ፍም ነበሩ፤ በጊልያድ ሠልጥኖ ወደ ፖርቱጋል የሄደ የመጀመሪያ ሚስዮናዊ የሆነው ጆን ኩክ በ1947 ሲመጣ ግን ሥራው እንደገና ተቀጣጠለ። ከዚያ በኋላ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት ጨመረ። የፖርቱጋል መንግሥት በ1962 የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ ባገደበት ጊዜም እንኳ የአስፋፊዎቹ ቁጥር ማደጉን ቀጥሎ ነበር። ታኅሣሥ 1974 የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ሲያገኙ በአገሪቱ ውስጥ ከ13,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች ነበሩ።
በዛሬው ጊዜ ከ50,000 የሚበልጡ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በፖርቱጋልና ፖርቱጋልኛ በሚነገርባቸው የተለያዩ ደሴቶች ውስጥ (ኤዞርዝንና ማዴይራን ጨምሮ) የአምላክን መንግሥት ምሥራች ይሰብካሉ። ከእነዚህ አስፋፊዎች አንዳንዶቹ በ1925 ወንድም ራዘርፎርድ ያቀረበውን ታሪካዊ ንግግር ያዳመጡት ሰዎች የልጅ ልጆች ናቸው።
ይሖዋን እንዲሁም “ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ አገልጋይ” በመሆን ሥራውን በድፍረትና በግንባር ቀደምትነት የመሩትን እነዚያን የቀድሞ ታማኝ ወንድሞችና እህቶች እናመሰግናለን።—ሮም 15:15, 16—በፖርቱጋል ካለው የታሪክ ማኅደራችን
a በግንቦት 15, 2014 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 31-32 ላይ የሚገኘውን “ገና መሠራት ያለበት ብዙ የመከር ሥራ አለ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።