በየዕለቱ ከይሖዋ ጋር ሥሩ
“ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን።”—1 ቆሮ. 3:9
1. ከይሖዋ ጋር መሥራት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
የፈጣሪ ዓላማ፣ ፍጹም የሆኑ ሰዎች የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም አብረውት እንዲሠሩ ነበር። በእርግጥ በዛሬው ጊዜ የሰው ልጆች ፍጹማን አይደሉም፤ ያም ቢሆን ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከይሖዋ ጋር በየዕለቱ መሥራት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በመካፈል “ከአምላክ ጋር አብረን [መሥራት]” እንችላለን። (1 ቆሮ. 3:5-9) የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪና ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከፍ አድርጎ በሚመለከተው በዚህ ሥራ፣ ከእሱ ጋር አብረን ለመሥራት ብቁ ሆነን መቆጠራችን ምን ያህል ታላቅ መብት እንደሆነ እስቲ አስበው! እርግጥ ነው፣ ከይሖዋ ጋር መሥራት የምንችለው ምሥራቹን በመስበክና ደቀ መዛሙርት በማድረግ ብቻ አይደለም። ይህን ማድረግ የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶች በዚህ ርዕስ ውስጥ ይብራራሉ፤ እነዚህም ቤተሰቦቻችንንና የእምነት አጋሮቻችንን መርዳት፣ እንግዳ ተቀባይ መሆን፣ በቲኦክራሲያዊ ሥራዎች ላይ ለመካፈል ራስን ማቅረብ እንዲሁም አገልግሎታችንን ማስፋት ናቸው።—ቆላ. 3:23
2. በይሖዋ አገልግሎት ማከናወን የምንችለውን ነገር ሌሎች ከሚያከናውኑት ጋር ማወዳደር የሌለብን ለምንድን ነው?
2 ይህን ርዕስ ስናጠና፣ በይሖዋ አገልግሎት ማከናወን የምንችለውን ነገር ሌሎች ከሚያከናውኑት ጋር ማወዳደር የለብንም። የእያንዳንዱ ሰው ዕድሜ፣ ጤንነት፣ ያለበት ሁኔታ እንዲሁም አቅም እንደሚለያይ እናስታውስ። ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።”—ገላ. 6:4
ቤተሰቦቻችንንና የእምነት አጋሮቻችንን መርዳት
3. ቤተሰቡን የሚንከባከብ ማንኛውም ሰው ከአምላክ ጋር ተባብሮ እየሠራ ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
3 ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ የቤተሰባቸውን አባላት እንዲንከባከቡ ይፈልጋል። ለምሳሌ፣ ብዙ ሰዎች የቤተሰባቸው አባላት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት መሥራት አለባቸው። በርካታ እናቶች፣ ሕፃናት ልጆቻቸውን ለመንከባከብ ሲሉ ቤት ይውላሉ። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ አቅመ ደካማ የሆኑ ወላጆቻቸውን መንከባከብ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። እነዚህ አስፈላጊ የሆኑ ተግባሮች ናቸው። የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው የራሱ ለሆኑት በተለይ ደግሞ ለቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማያቀርብ ከሆነ እምነትን የካደ ከመሆኑም በላይ እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው።” (1 ጢሞ. 5:8) አንተም እንዲህ ያሉ ኃላፊነቶች ካሉብህ በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች የምትፈልገውን ያህል ሰፋ ያለ ጊዜ ማሳለፍ አትችል ይሆናል። ያም ቢሆን ተስፋ አትቁረጥ! የቤተሰብህ አባላት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ማቅረብህ ይሖዋን ያስደስተዋል።—1 ቆሮ. 10:31
4. ወላጆች መንፈሳዊ ግቦችን ከራሳቸው ፍላጎት እንደሚያስቀድሙ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? ይህን ማድረጋቸውስ ምን ውጤት ያስገኛል?
4 ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻቸው መንፈሳዊ ግቦችን እንዲያወጡ በመርዳት ከይሖዋ ጋር ተባብረው መሥራት ይችላሉ። በርካታ ወላጆች እንዲህ አድርገዋል፤ በመሆኑም ልጆቻቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል የወሰኑ ሲሆን አንዳንዶቹ ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች እንኳ ሄደው ለማገልገል ፈቃደኞች ሆነዋል። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ሚስዮናውያን ወይም ቤቴላውያን ሆነው ያገለግላሉ፤ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው ቦታዎች በአቅኚነት የሚያገለግሉም አሉ። ልጆቹ ከቤት ርቀው ስለሚያገለግሉ የቤተሰቡ አባላት የሚፈልጉትን ያህል አዘውትረው መገናኘት አይችሉ ይሆናል። ያም ቢሆን የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ ወላጆች፣ ልጆቻቸውን በተመደቡበት ቦታ በጽናት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ያበረታቷቸዋል። ለምን? ልጆቻቸው የአምላክን መንግሥት እያስቀደሙ መሆናቸው ታላቅ ደስታና እርካታ ስለሚያስገኝላቸው ነው። (3 ዮሐ. 4) እንዲህ ያሉት ወላጆች፣ ሳሙኤልን ለይሖዋ ‘እንዳዋሰችው’ አድርጋ እንደተናገረችው እንደ ሐና ዓይነት ስሜት ይኖራቸው ይሆናል። ወላጆች በዚህ መንገድ ከይሖዋ ጋር አብረው መሥራታቸውን እንደ ታላቅ ክብር ይቆጥሩታል። ይህን መብታቸውን በምንም ነገር መለወጥ አይፈልጉም።—1 ሳሙ. 1:28 ግርጌ
5. ለጉባኤህ አባላት ጠቃሚ እርዳታ ማበርከት የምትችለው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
5 ከባድ የቤተሰብ ኃላፊነት ከሌለብህ፣ የቤተሰባቸውን አባላት የሚንከባከቡ የእምነት ባልንጀሮችህን እንዲሁም የታመሙ፣ በዕድሜ የገፉ አሊያም በሌላ ምክንያት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ክርስቲያኖችን ማገዝ ትችላለህ። በጉባኤህ ውስጥ እንዲህ ያለ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ይኖሩ ይሆን? ምናልባትም በዕድሜ የገፉ አባቷን ወይም እናቷን የምትንከባከብ አንዲት እህት፣ ሌሎች ጉዳዮችን ለማከናወን የሚያስችል ጊዜ እንድታገኝ አንተ ከወላጆቿ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ትችል ይሆናል። አሊያም ደግሞ ወደ ስብሰባ ለመሄድ፣ ገበያ ለመውጣት፣ አንዳንድ ጉዳዮችን ለማከናወን ወይም ሆስፒታል ሄደው ሌሎችን ለመጠየቅ እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች መርዳት ትችል ይሆናል። እንዲህ ባሉ እንቅስቃሴዎች መካፈልህ፣ ይሖዋ ለእነዚህ ሰዎች ጸሎት መልስ ሲሰጥ አብረኸው የመሥራት አጋጣሚ ያስገኝልሃል።—1 ቆሮንቶስ 10:24ን አንብብ።
እንግዳ ተቀባይ መሆን
6. እንግዳ ተቀባይ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?
6 ከአምላክ ጋር የሚሠሩ ሰዎች እንግዳ ተቀባይ በመሆናቸው ተለይተው ይታወቃሉ። በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ “እንግዳ መቀበል” ተብሎ የተተረጎመው ቃል “ለእንግዶች ደግነት ማሳየት” የሚል ፍቺ አለው። (ዕብ. 13:2 ግርጌ) የአምላክ ቃል እንግዶችን በመቀበል ፍቅር እንድናሳይ የሚያበረታቱ ዘገባዎችን ይዟል። (ዘፍ. 18:1-5) ‘በእምነት የሚዛመዱንን ሰዎችም’ ሆነ ሌሎችን ለመርዳት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ልንጠቀምባቸው ይገባል።—ገላ. 6:10
7. የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን በእንግድነት መቀበል ምን ጥቅሞች አሉት?
7 ጉባኤያችሁን የሚጎበኙ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን በእንግድነት ተቀብላችሁ በማሳረፍ ከአምላክ ጋር መሥራት ትችሉ ይሆን? (3 ዮሐንስ 5, 8ን አንብብ።) እንዲህ ማድረጋችሁ ከእንግዶቻችሁ ጋር ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ይከፍትላችኋል። (ሮም 1:11, 12) ኦላፍ ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኦላፍ ልጅ እያለ አንድ ያላገባ የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉባኤያቸውን ጎብኝቶ ነበር፤ በወቅቱ የወረዳ የበላይ ተመልካቹን በቤቱ ተቀብሎ ሊያስተናግድ የሚችል ሰው በጉባኤያቸው አልነበረም። ኦላፍ፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በቤታቸው ማረፍ ይችል እንደሆነ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑትን ወላጆቹን ጠየቃቸው። ወላጆቹም ፈቀዱለት፤ ሆኖም ኦላፍ አልጋውን ለቅቆ ሶፋ ላይ መተኛት እንደሚኖርበት ነገሩት። ኦላፍ ይህን በማድረጉ በእጅጉ ተክሷል። እንዲህ ብሏል፦ “በጣም አስደሳች ሳምንት አሳለፍን! እኔና የወረዳ የበላይ ተመልካቹ በየዕለቱ ጠዋት ላይ ቁርስ ስንበላ በርካታ ጉዳዮችን አንስተን ግሩም ውይይት እናደርግ ነበር። ከእሱ ያገኘሁት ማበረታቻ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድካፈል አነሳስቶኛል።” ኦላፍ ላለፉት 40 ዓመታት ሚስዮናዊ ሆኖ በተለያዩ ቦታዎች አገልግሏል።
8. ሰዎች ላሳየናቸው ደግነት መጀመሪያ ላይ አመስጋኝ ባይሆኑም እንኳ ይህን ማድረጋችንን እንድንቀጥል የሚያነሳሳን ምንድን ነው? በምሳሌ አስረዳ።
8 ለእንግዶች ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸው በርካታ መንገዶች አሉ፤ ለምናደርገው ጥረት መጀመሪያ ላይ ጥሩ ምላሽ ባናገኝም እንኳ ይህን ማድረጋችን ጠቃሚ ነው። አንድ ምሳሌ እንመልከት። በስፔን የምትኖር አንዲት አስፋፊ ዬሲካ የተባለችን ከኢኳዶር የመጣች ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠና ነበር። አንድ ቀን እያጠኑ እያለ ዬሲካ ማልቀስ ጀመረች። አስፋፊዋ ዬሲካን የምታለቅሰው ለምን እንደሆነ ጠየቀቻት። ዬሲካም ከአገሯ ከመሰደዷ በፊት በጣም ድሃ እንደነበረች ገለጸችላት። እንዲያውም አንድ ቀን ቤቷ ውስጥ አንዳች የሚላስ የሚቀመስ ነገር ስላልነበራት ለልጇ ከውኃ በቀር ሌላ ነገር ልትሰጣት እንዳልቻለች ነገረቻት። ዬሲካ ልጇን ለማስተኛት እያባበለቻት ሳለ አምላክ እንዲረዳት ትጸልይ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ቤቷን አንኳኩ፤ ዬሲካ ግን ያመናጨቀቻቸው ሲሆን የሰጧትን መጽሔትም ቀዳደደችው። “ይሄ ለልጄ ምግብ ይሆናል?” አለቻቸው። እህቶች ሊያረጋጓት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። እነዚህ እህቶች በኋላ ላይ ምግብ ይዘው መጥተው ደጃፏ ላይ አስቀመጡላት። እህቶች ባሳዩዋት ደግነት ዬሲካ ልቧ የተነካ ሲሆን አምላክ ለጸሎቷ የሰጣትን ምላሽ እንዳላስተዋለች ስታስታውስ በጣም አዘነች። አሁን ግን ዬሲካ ይሖዋን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አድርጋለች። እህቶች ያሳዩት ልግስና ግሩም ውጤት አስገኝቷል!—መክ. 11:1, 6
በቲኦክራሲያዊ ሥራዎች ላይ ለመካፈል ራስን ማቅረብ
9, 10. (ሀ) በጥንት ዘመን የአምላክ ሕዝቦች ራሳቸውን በፈቃደኝነት እንዲያቀርቡ የተጠየቁባቸው አጋጣሚዎች የትኞቹ ናቸው? (ለ) በዛሬው ጊዜ በጉባኤ ያሉ ፈቃደኛ ወንድሞች የትኞቹን ሥራዎች እንዲያከናውኑ ይጠየቃሉ?
9 በጥንቷ እስራኤል ፈቃደኛ ሠራተኞች ያስፈለጉባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች ነበሩ። (ዘፀ. 36:2፤ 1 ዜና 29:5፤ ነህ. 11:2) ዛሬም ቢሆን ጊዜያችንን፣ ገንዘባችንን ብሎም ችሎታችንን ተጠቅመን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በፈቃደኝነት መርዳት የምንችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። በዚህ መልኩ ራሳችንን ማቅረባችን ታላቅ ደስታና ብዙ በረከት ያስገኝልናል።
10 የአምላክ ቃል በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንዶች፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለማገልገልና የበላይ ተመልካችነት ኃላፊነትን ለመሸከም በመጣጣር ከይሖዋ ጋር እንዲሠሩ ያበረታታል። (1 ጢሞ. 3:1, 8, 9፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3) እንዲህ የሚያደርጉ ወንድሞች የእምነት አጋሮቻቸውን በመንፈሳዊም ሆነ በሌሎች መንገዶች ይረዳሉ። (ሥራ 6:1-4) ሽማግሌዎች አስተናጋጅ ሆነህ እንድታገለግል ወይም ከጽሑፍ፣ ከክልል፣ ከጥገናና ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር የተያያዙ ሥራዎችን እንድታከናውን ጠይቀውሃል? እንደነዚህ ያሉ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ወንድሞች ሌሎችን መርዳታቸው ታላቅ ደስታ እንዳስገኘላቸው ይናገራሉ።
11. አንዲት ክርስቲያን በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ሥራዎች ላይ ስትካፈል ወዳጆች በማፍራቷ የተጠቀመችው እንዴት ነው?
11 በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ሥራዎች ላይ የሚካፈሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች አዳዲስ ጓደኞች ማፍራት ችለዋል። ከስብሰባ አዳራሾች ግንባታ ጋር በተያያዙ ሥራዎች ላይ ለ18 ዓመታት የተካፈለችውን ማርጂን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህች እህት ባለፉት ዓመታት ውስጥ በርካታ ወጣት እህቶችን አሠልጥናለች። ማርጂ በእነዚህ የግንባታ ሥራዎች ላይ የሚካፈሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች፣ እርስ በርስ በመንፈሳዊ ለመበረታታት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ እንደሚያገኙ ተናግራለች። (ሮም 1:12) ማርጂ በሕይወቷ ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ባጋጠሟት ወቅት፣ በግንባታ ሥራዎች ላይ ስትካፈል ያፈራቻቸው ወዳጆቿ አበረታተዋታል። አንተስ በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ሥራዎች ላይ ለመካፈል ራስህን በፈቃደኝነት አቅርበህ ታውቃለህ? የግንባታ ችሎታ ኖረህም አልኖረህ ራስህን ማቅረብ ትችላለህ።
12. አደጋ ለደረሰባቸው እርዳታ በመስጠቱ ሥራ መካፈል የምትችለው እንዴት ነው?
12 አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ወንድሞቻቸውን በመርዳት ከአምላክ ጋር የመሥራት አጋጣሚ ያገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በአደጋው ለተጎዱት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንችላለን። (ዮሐ. 13:34, 35፤ ሥራ 11:27-30) ወንድሞቻችንን መርዳት የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ በጽዳት ወይም በመልሶ ግንባታ ሥራ መካፈል ነው። ጋብርኤላ የተባለች በፖላንድ የምትኖር አንዲት እህት በጎርፍ ምክንያት ቤቷ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ነበር፤ ይህች እህት በአቅራቢያዋ በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ወንድሞች ሊረዷት ሲመጡ በጣም ተደሰተች። ጋብርኤላ ስላጣቻቸው ቁሳዊ ነገሮች ከመጨነቅ ይልቅ ባገኘቻቸው ነገሮች ላይ ትኩረት ታደርጋለች። እንዲህ ብላለች፦ “ይህ አጋጣሚ፣ የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆን ልዩ መብት እንደሆነና ታላቅ ደስታ እንደሚያስገኝ እንዳስታውስ ረድቶኛል።” አደጋ አጋጥሟቸው የወንድሞችን እርዳታ ያገኙ በርካታ ክርስቲያኖች፣ ካጡት የበለጠ እንዳገኙ ተሰምቷቸዋል። እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ በማበርከት ከይሖዋ ጋር የሚሠሩ ወንድሞችም ይህን ማድረጋቸው ላቅ ያለ እርካታ ያስገኝላቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35፤ 2 ቆሮንቶስ 9:6, 7
13. ራሳችንን በፈቃደኝነት ማቅረባችን ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያጠናክረው እንዴት ነው? ምሳሌ ጥቀስ።
13 ስቴፈኒ የተባለች እህትና ሌሎች ክርስቲያኖች፣ በስደት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የመጡ የይሖዋ ምሥክሮችን የመርዳት አጋጣሚ አግኝተዋል፤ በዚህ መንገድ ከይሖዋ ጋር መሥራት መቻላቸው ታላቅ ደስታ አምጥቶላቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች በጦርነት ከሚታመሱ አገሮች የመጡ ቤተሰቦች ቤት እንዲያገኙ በመርዳቱ እንዲሁም የሚያስፈልጓቸውን የቤት ዕቃዎች በማሟላቱ ሥራ ተካፍለዋል። ስቴፈኒ እንዲህ ብላለች፦ “እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ወንድሞቻቸው ያሳዩአቸውን ፍቅር ሲመለከቱ ምን ያህል እንደተደሰቱና በአድናቆት እንደተዋጡ ማየታችን ልባችንን ነክቶታል። እነዚህ ቤተሰቦች እኛ እንደረዳናቸው ይሰማቸዋል፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይበልጥ የረዱን እነሱ ናቸው። ወንድሞች ያላቸውን ፍቅር፣ አንድነትና እምነት እንዲሁም በይሖዋ ምን ያህል እንደሚመኩ ስናይ እኛም ለይሖዋ ያለን ፍቅር ጨምሯል፤ ይህ ደግሞ በድርጅቱ በኩል ያገኘናቸውን ነገሮች በሙሉ ይበልጥ እንድናደንቅ አድርጎናል።”
አገልግሎታችንን ማስፋት
14, 15. (ሀ) ነቢዩ ኢሳይያስ ምን ዓይነት መንፈስ አሳይቷል? (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉ የመንግሥቱ ሰባኪዎች የኢሳይያስ ዓይነት አመለካከት እንዳላቸው ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
14 ከይሖዋ ጋር ይበልጥ አብረህ መሥራት ትፈልጋለህ? ለምሳሌ፣ በድርጅቱ ውስጥ ሠራተኞች የበለጠ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረህ ይሖዋን ለማገልገል ፈቃደኛ ነህ? እርግጥ ነው፣ የአምላክ አገልጋዮች ልግስና ለማሳየት የግድ ከአካባቢያቸው ርቀው መሄድ አያስፈልጋቸውም። ሆኖም አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ሄደው ለማገልገል ሁኔታቸው ፈቅዶላቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች የነቢዩ ኢሳይያስ ዓይነት አመለካከት አላቸው። ይሖዋ “ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?” በማለት ላቀረበው ጥያቄ ኢሳይያስ “እነሆኝ! እኔን ላከኝ!” የሚል ምላሽ ሰጥቷል። (ኢሳ. 6:8) አንተስ የይሖዋን ድርጅት ለማገዝ ፈቃደኛ ነህ? ሁኔታህ እንዲህ ለማድረግ ይፈቅድልሃል? ለመሆኑ በየትኞቹ ሥራዎች መካፈል ትችላለህ?
15 ኢየሱስ የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ኃላፊ ወደ መከሩ፣ ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።” (ማቴ. 9:37, 38) ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል ምናልባትም በዚያ ክልል አቅኚ ሆነህ መሥራት ትችል ይሆን? አሊያም ደግሞ እንዲህ እንዲያደርግ ልትረዳው የምትችለው ሰው ይኖር ይሆን? በርካታ ወንድሞችና እህቶች፣ ለአምላክና ለባልንጀሮቻቸው ፍቅር ማሳየት የሚችሉበት ከሁሉ የተሻለ መንገድ የመከሩ ሠራተኞች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ ወይም ክልል ውስጥ በአቅኚነት ማገልገል እንደሆነ ተሰምቷቸዋል። አንተስ አገልግሎትህን ማስፋት የምትችልባቸው ሌሎች መንገዶች ይኖሩ ይሆን? ይህን ማድረግ ታላቅ ደስታ ያስገኛል።
16, 17. አገልግሎትህን ይበልጥ ማስፋት የምትችልባቸው ምን ተጨማሪ አጋጣሚዎች አሉ?
16 በጊዜያዊነት ወይም በሳምንት ውስጥ ለተወሰኑ ቀናት በቤቴል ለማገልገል አሊያም በቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎች ግንባታ ላይ እገዛ ለማበርከት ፈቃደኛ ነህ? በተመደቡበት በማንኛውም ቦታ ወይም የሥራ መስክ ይሖዋን ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ክርስቲያኖች ምንጊዜም ያስፈልጋሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች በአንድ መስክ ጥሩ ችሎታ ወይም ልምድ ቢኖራቸውም እንኳ ሠራተኞች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ሌላ መስክ እንዲያገለግሉ ሲጠየቁ ይህን ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው። በተፈለጉበት ቦታ ሁሉ ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች የሚያሳዩትን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ይሖዋ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—መዝ. 110:3
17 ቅዱስ አገልግሎት ለማከናወን የበለጠ ብቁ እንድትሆን የሚረዳ ተጨማሪ ሥልጠና ማግኘት ትፈልጋለህ? ከሆነ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት መሠልጠን ትችል ይሆናል። ይህ ትምህርት ቤት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ያሉ መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ወንዶችና ሴቶች በመስኩ ላይ ይበልጥ መሥራት እንዲችሉ የሚያስፈልጋቸውን ሥልጠና ይሰጣል። በዚህ ትምህርት ቤት ለመሠልጠን የሚያመለክቱ ሁሉ፣ ከተመረቁ በኋላ በተመደቡበት በማንኛውም ቦታ ለማገልገል ፈቃደኞች መሆን አለባቸው። አንተስ በዚህ መንገድ ይሖዋን ይበልጥ ለማገልገል ፈቃደኛ ነህ?—1 ቆሮ. 9:23
18. በየዕለቱ ከይሖዋ ጋር ከሠራህ ምን በረከት ታገኛለህ?
18 የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን የጥሩነት፣ የደግነትና የፍቅር መገለጫ የሆነውን ልግስናን እናሳያለን፤ እንዲሁም በየዕለቱ ለሌሎች አሳቢነት ለማሳየት እንጥራለን። ይህን ስናደርግ ደስታና ሰላም እናገኛለን። (ገላ. 5:22, 23) በእርግጥም ሁኔታህ ምንም ይሁን ምን እንደ ይሖዋ ለጋስ በመሆን እንዲሁም ከእሱ ጋር አብረህ በመሥራት ደስታ ማግኘት ትችላለህ!—ምሳሌ 3:9, 10