በይሖዋ በመታመን በሕይወት ኑሩ!
“በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ።”—ምሳሌ 3:5
1. ሁላችንም ማጽናኛ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
ሁላችንም ማጽናኛ ያስፈልገናል። የአንዳንዶቻችን ሕይወት በጭንቀት፣ በመከራና ተስፋ በሚያስቆርጡ ነገሮች የተሞላ ሊሆን ይችላል። ሌሎቻችን ደግሞ የዕድሜ መግፋት፣ ሕመም ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ከሚያስከትለው የስሜት ሥቃይ ጋር እየታገልን ይሆናል። የጥላቻ ሰለባ የሆኑ ክርስቲያኖችም አሉ። በዚያ ላይ በዓለማችን ላይ የሚታየው ዓመፅ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ነው። እርግጥ ነው፣ ያለንበት ጊዜ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” መሆኑ “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ውስጥ እንደምንኖር የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነና እያንዳንዱ ቀን ባለፈ ቁጥር ወደ አዲሱ ዓለም ይበልጥ እየቀረብን እንዳለ እናምናለን። (2 ጢሞ. 3:1) ያም ቢሆን ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች የሚፈጸሙበትን ጊዜ ለበርካታ ዓመታት ስንጠባበቅ ቆይተን ይሆናል፤ በተጨማሪም ችግሮቻችን ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሱ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ማጽናኛ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?
2, 3. (ሀ) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዕንባቆም የሚሰጠን መረጃ ምንድን ነው? (ለ) የዕንባቆምን መጽሐፍ መመርመራችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
2 የዕንባቆምን መጽሐፍ መመርመራችን መልሱን ለማግኘት ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዕንባቆም ሕይወትና ስላደረጋቸው ነገሮች በዝርዝር ባይናገርም በስሙ የተሰየመው መጽሐፍ ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ይሆነናል። ዕንባቆም የሚለው ስም “አጥብቆ ማቀፍ” የሚል ትርጉም ሳይኖረው አይቀርም። ይህም ይሖዋ አገልጋዮቹን ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ በእጆቹ አቅፎ እንደሚያጽናናቸው አሊያም ደግሞ አገልጋዮቹ በእሱ በመተማመን የሙጥኝ ብለው እንደሚይዙት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። ዕንባቆም ያስጨነቁትን አንዳንድ ጥያቄዎች ለአምላክ አቅርቧል። ይሖዋ እኛም እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ሊፈጠሩብን እንደሚችሉ ስለሚያውቅ በእሱና በዕንባቆም መካከል የተደረገው ውይይት ተመዝግቦ እንዲቆይ አድርጓል።—ዕን. 2:2
3 በጭንቀት ስለተዋጠው ስለዚህ ነቢይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መረጃ በእሱና በይሖዋ መካከል የተደረገው ይህ ውይይት ብቻ ነው። በስሙ የተሰየመው መጽሐፍ ‘በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ ቀደም ብለው ከተጻፉት’ እንዲሁም የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተካተቱት መጻሕፍት መካከል አንዱ ነው። (ሮም 15:4) ታዲያ ይህ መጽሐፍ በግለሰብ ደረጃ ምን ጥቅም ያስገኝልናል? በይሖዋ መታመን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። በተጨማሪም የዕንባቆም ትንቢት መከራና ችግር ቢደርስብንም ውስጣዊ ሰላም ማግኘትና ይህን ሰላም ይዘን መቀጠል እንደምንችል ያረጋግጥልናል። ይህን በአእምሯችን በመያዝ የዕንባቆምን መጽሐፍ በጥልቀት እንመርምር።
ወደ ይሖዋ ጩኹ
4. ዕንባቆም በጭንቀት የተዋጠው ለምን ነበር?
4 ዕንባቆም 1:2, 3ን አንብብ። ዕንባቆም የኖረው በጣም ከባድና ተፈታታኝ በሆነ ወቅት ላይ ነው። ክፉና ዓመፀኛ በሆኑ ሰዎች መካከል መኖሩ በጥልቅ ሐዘን እንዲዋጥ አድርጎታል። የእነዚህ ሰዎች ክፋት የሚያበቃው መቼ ነው? ይሖዋ እርምጃ ለመውሰድ ይህን ያህል የዘገየው ለምንድን ነው? ዕንባቆም የሚያየው ሁሉ የገዛ አገሩ ሰዎች የሚፈጽሙትን ግፍና ጭቆና ብቻ ነው። ብቻውን እንደተተወ ሳይሰማው አልቀረም። ዕንባቆም ወደ ይሖዋ በመጮኽ ጣልቃ እንዲገባ የጠየቀው እንዲህ ባለ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው። ምናልባትም ይህ ነቢይ ይሖዋ ጉዳዩ እንደማያሳስበውና በቅርቡ እርምጃ እንደማይወስድ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። አንተስ እንደዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ተሰምቶህ ያውቃል?
5. በዕንባቆም መጽሐፍ ውስጥ ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
5 ዕንባቆም በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት አጥቶ ይሆን? አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ ያለው እምነትስ ጠፍቶ ይሆን? በፍጹም! ችግሮቹንና ያሳሰቡትን ነገሮች ለሰዎች ሳይሆን ለይሖዋ መናገሩ በራሱ፣ ተስፋ እንዳልቆረጠ ያሳያል። አምላክ እርምጃ ሳይወስድ የቆየውና አገልጋዩ እንዲህ ያለ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ አለማወቁ አስጨንቆት እንደሚሆን ግልጽ ነው። ይሖዋ፣ ዕንባቆም ያስጨነቀውን ነገር እንዲጽፍ በመንፈሱ በመምራት አንድ ጠቃሚ ትምህርት ሰጥቶናል፦ ስላስጨነቀን ነገር ወይም በውስጣችን ስላደረው ጥርጣሬ ለእሱ መናገር ሊያስፈራን አይገባም። እንዲያውም በጸሎት አማካኝነት ልባችንን በፊቱ እንድናፈስ በደግነት ጋብዞናል። (መዝ. 50:15፤ 62:8) በተጨማሪም ምሳሌ 3:5 ‘በገዛ ራሳችን ማስተዋል ከመመካት’ ይልቅ ‘በሙሉ ልባችን በይሖዋ እንድንታመን’ ያበረታታናል። ዕንባቆም ይህን ምክር እንደሚያውቅና ተግባራዊ አድርጎት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።
6. ጸሎት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
6 ዕንባቆም የቅርብ ወዳጁና አባቱ ወደሆነው ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የሚያስችለውን እርምጃ ወስዷል። ያለበትን ሁኔታ እያሰበ ከመብሰልሰል አሊያም በራሱ ማስተዋል ከመመካት ተቆጥቧል። ከዚህ ይልቅ የተሰማውን ስሜትና ያስጨነቀውን ነገር በጸሎት ለይሖዋ ተናግሯል። በዚህ መንገድ ለእኛ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ጸሎት ሰሚ የሆነው ይሖዋም ቢሆን ያስጨነቁንን ነገሮች ለእሱ በመናገር እንደምንታመንበት እንድናሳይ ግብዣ አቅርቦልናል። (መዝ. 65:2) እንዲህ ስናደርግ ይሖዋ የሚሰጠንን ምላሽ መመልከት እንችላለን፤ ይሖዋ ደግነት የሚንጸባረቅበት አመራር ስለሚሰጠን በእጆቹ እቅፍ እንዳደረገን ሆኖ ይሰማናል። (መዝ. 73:23, 24) ያጋጠመን ተፈታታኝ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አስተሳሰብ እንድናውቅ ይረዳናል። ለአምላክ የምናቀርበው ከልብ የመነጨ ጸሎት በእሱ እንደምንታመን ከምናሳይባቸው ዋነኛ መንገዶች መካከል አንዱ ነው።
ይሖዋን ስሙ
7. ይሖዋ ዕንባቆም ላሰማው ጩኸት ምን ምላሽ ሰጠ?
7 ዕንባቆም 1:5-7ን አንብብ። ዕንባቆም ያስጨነቀውንና ያሳሰበውን ነገር ለይሖዋ ከተናገረ በኋላ ይሖዋ ምን እርምጃ እንደሚወስድ ለማወቅ ጓጉቶ መሆን አለበት። ይሖዋ ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት ስሜታችንን ስለሚረዳ ዕንባቆም የተሰማውን ቅሬታ በመግለጹ አልገሠጸውም። ዕንባቆም ይህን ጩኸት ያሰማው ከደረሰበት ሥቃይና ሐዘን የተነሳ እንደሆነ ተረድቶለት ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ ታማኝ ያልሆኑት አይሁዳውያን በቅርቡ ምን እንደሚያጋጥማቸው ለዕንባቆም ገለጸለት። እንዲያውም በወቅቱ የነበሩት ዓመፀኛ ሰዎች በቅርቡ እንደሚጠፉ ለመጀመሪያ ጊዜ የነገረው ለዕንባቆም ሳይሆን አይቀርም።
8. ይሖዋ የሰጠው ምላሽ ዕንባቆምን ግራ ያጋባው ለምንድን ነው?
8 ይሖዋ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ እንደሆነ ለዕንባቆም ገልጾለታል። ያ ዓመፀኛና ክፉ ትውልድ ከቅጣት አያመልጥም። ይሖዋ “በዘመናችሁ” የሚለውን አገላለጽ በመጠቀም ፍርዱ በዕንባቆም አሊያም በወቅቱ በነበሩት እስራኤላውያን ዘመን መፈጸሙ እንደማይቀር ጠቁሟል። ይሁንና ይሖዋ የሚወስደው እርምጃ ዕንባቆም ከጠበቀው ፈጽሞ የተለየ ነበር። ይሖዋ የነገረው ነገር በመላው ይሁዳ ላይ የከፋ መከራ እንደሚመጣ የሚጠቁም ነበር። ከለዳውያን (ባቢሎናውያን) ከአይሁዳውያን የበለጠ ጨካኞችና ርኅራኄ የሌላቸው ነበሩ፤ ምክንያቱም አይሁዳውያኑ ቢያንስ የይሖዋን መሥፈርቶች ያውቁ ነበር። ታዲያ ይሖዋ በራሱ ሕዝብ ላይ ጥፋት ለማምጣት ይህን በጭካኔው የሚታወቅ አረማዊ ብሔር የሚጠቀመው ለምንድን ነው? አንተ ብትሆን ኖሮ ይህን መለኮታዊ ፍርድ ስትሰማ ምን ምላሽ ትሰጥ ነበር?
9. ዕንባቆም የትኞቹን ጥያቄዎች ራሱን ጠይቆ ሊሆን ይችላል?
9 ዕንባቆም 1:12-14, 17ን አንብብ። ዕንባቆም፣ ይሖዋ በባቢሎናውያን ተጠቅሞ በዙሪያው ባሉት ክፉ አድራጊዎች ላይ የፍርድ እርምጃ እንደሚወስድና እንደሚቀጣቸው ቢያውቅም ግልጽ ያልሆኑለት ብዙ ነገሮች ነበሩ። ያም ቢሆን፣ ይሖዋ ምንጊዜም ‘ዓለቱ’ እንደሆነ በትሕትና ተናግሯል። (ዘዳ. 32:4፤ ኢሳ. 26:4) ዕንባቆም አምላክ አፍቃሪና ደግ እንደሆነ በመተማመን በትዕግሥት መጠበቁን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። ይህም ለይሖዋ ድጋሚ ጥያቄ ለማቅረብ ድፍረት ሰጥቶታል። ይሖዋ ‘ቅዱስ የሆነ አምላክ’ እንደሆነና ‘ዓይኖቹ ክፉ የሆነውን ነገር እንዳያዩ እጅግ ንጹሐን እንደሆኑ’ ዕንባቆም ያውቃል። ታዲያ በይሁዳ የነበረው ሁኔታ እንዲባባስ የሚፈቅደው ለምንድን ነው? ወዲያውኑ እርምጃ የማይወስደው ለምንድን ነው? ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ከቀድሞው የከፋ ሁኔታ ሲፈጠርና ምድሪቱ በክፋት ስትሞላ ‘ዝም ብሎ የሚመለከተውስ’ ለምንድን ነው?
10. አንዳንድ ጊዜ እኛም እንደ ዕንባቆም ምን ሊሰማን ይችላል?
10 አንዳንድ ጊዜ እኛም እንደ ዕንባቆም ይሰማን ይሆናል። ይሖዋ የሚለንን እንሰማለን እንዲሁም በእሱ እንተማመናለን። በተጨማሪም ቃሉን የምናነብና የምናጠና ሲሆን ይህም ተስፋ ይሰጠናል። ከዚህም በላይ ይሖዋ ቃል ስለገባቸው ነገሮች በድርጅቱ አማካኝነት እንማራለን። ይህን ሁሉ እያደረግንም ‘የሚደርስብን መከራ የሚያበቃው መቼ ነው?’ የሚል ጥያቄ ሊፈጠርብን ይችላል። ታዲያ ዕንባቆም ቀጥሎ ካደረገው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?
ይሖዋን በትዕግሥት ጠብቁ
11. ዕንባቆም ይሖዋ የተናገረውን ከሰማ በኋላ ምን ለማድረግ ወስኗል?
11 ዕንባቆም 2:1ን አንብብ። ዕንባቆም ከይሖዋ ጋር ያደረገው ውይይት ውስጣዊ ሰላም እንዲያገኝ ረድቶታል። በመሆኑም በይሖዋ በመታመን አምላክ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ በትዕግሥት ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። ዕንባቆም ይህን ውሳኔ ያደረገው ስሜታዊ ሆኖ አይደለም፤ ምክንያቱም ከጊዜ በኋላም “የጭንቀትን ቀን ዝም ብዬ እጠብቃለሁ” በማለት በድጋሚ ተናግሯል። (ዕን. 3:16) ሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም እንዲህ ያለውን እምነትና በትዕግሥት የመጠበቅ ዝንባሌ አሳይተዋል፤ ይህም ይሖዋ እርምጃ የሚወስድበትን ጊዜ ተስፋ ሳንቆርጥ እንድንጠብቅ ያበረታታናል።—ሚክ. 7:7፤ ያዕ. 5:7, 8
12. ከዕንባቆም ምን እንማራለን?
12 ዕንባቆም ካደረገው ቁርጥ ውሳኔ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንደኛ፣ ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስብን ወደ ይሖዋ መጸለያችንን ማቆም የለብንም። ሁለተኛ፣ ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ በኩል የሚነግረንን መስማት ያስፈልገናል። ሦስተኛ፣ ይሖዋ ችግራችንን ራሱ በወሰነው ጊዜ እንደሚፈታልን ሙሉ በሙሉ በመተማመን እሱን በትዕግሥት መጠባበቅ አለብን። ልክ እንደ ዕንባቆም የልባችንን አውጥተን ለይሖዋ የምንነግረውና በትዕግሥት በመጠባበቅ እሱ የሚለንን የምንሰማ ከሆነ እኛም ውስጣዊ ሰላም ይኖረናል፤ ይህም እንድንጸና ያደርገናል። ይሖዋ የሰጠን ተስፋ ይበልጥ ታጋሾች እንድንሆን ይረዳናል፤ ትዕግሥት ደግሞ በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ደስተኞች እንድንሆን ያስችለናል። በተጨማሪም ተስፋ፣ በሰማይ ያለው አባታችን እርምጃ መውሰዱ እንደማይቀር እርግጠኞች እንድንሆን ያደርገናል።—ሮም 12:12
13. በዕንባቆም 2:3 ላይ ይሖዋ ለዕንባቆም ምን ማረጋገጫ ሰጥቶታል?
13 ዕንባቆም 2:3ን አንብብ። ዕንባቆም በትዕግሥት ለመጠበቅ ባደረገው ውሳኔ ይሖዋ እንደተደሰተ ምንም ጥያቄ የለውም። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ዕንባቆም ያለበትን አሳሳቢ ሁኔታ በሚገባ ያውቃል። በመሆኑም በፍቅር ተነሳስቶ ዕንባቆምን ያጽናናው ከመሆኑም ሌላ ለጥያቄዎቹ መልስ እንደሚሰጠው አረጋግጦለታል። ዕንባቆምን ያስጨነቁት ነገሮች በሙሉ በቅርቡ መፍትሔ ያገኛሉ። አምላክ ዕንባቆምን “በትዕግሥት ጠብቅ፤ በእኔ ታመን። የሚዘገይ ቢመስልህም ለጥያቄህ መልስ እሰጣለሁ!” ያለው ያህል ነበር። ይሖዋ ቃል የገባቸውን ነገሮች የሚፈጽምበትን ጊዜ እንደወሰነ ለዕንባቆም አስታውሶታል። በተጨማሪም ይህን ጊዜ በትዕግሥት እንዲጠባበቅ መክሮታል። ዕንባቆም እንዲህ በማድረጉ ፈጽሞ አይቆጭም።
14. በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?
14 ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቃችንና እሱ የሚነግረንን ነገር በትኩረት ማዳመጣችን በእሱ ላይ ያለንን እምነት የሚጨምርልን ከመሆኑም ሌላ መከራና ችግር ቢያጋጥመንም ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረን ይረዳናል። ኢየሱስ፣ “ጊዜያትንና ወቅቶችን” በተመለከተ አምላክ ለእኛ ያላሳወቀን ነገር እንዳለ ተናግሯል፤ በመሆኑም በዚያ ላይ ከማተኮር ይልቅ የቀጠረውን ጊዜ በመጠበቅ ረገድ ወደር በማይገኝለት በይሖዋ ላይ እምነት እንድንጥል መክሮናል። (ሥራ 1:7) እንግዲያው ተስፋ አንቁረጥ፤ ከዚህ ይልቅ ትሕትና፣ እምነትና ትዕግሥት እያሳየን ይሖዋን እንጠባበቅ። እስከዚያው ድረስ ግን ጊዜያችንን አቅማችን የፈቀደውን ያህል ይሖዋን ለማገልገል እንጠቀምበት።—ማር. 13:35-37፤ ገላ. 6:9
በይሖዋ መታመን ሕይወትና ክብራማ ተስፋ ያስገኛል
15, 16. (ሀ) በዕንባቆም መጽሐፍ ውስጥ ምን አስደናቂ ተስፋዎች እናገኛለን? (ለ) እነዚህ ተስፋዎች ምን ያስገነዝቡናል?
15 ይሖዋ በእሱ ለሚታመኑ ጻድቅ አገልጋዮቹ “ጻድቅ . . . በታማኝነቱ በሕይወት ይኖራል” እንዲሁም “ምድር . . . የይሖዋን ክብር በማወቅ ትሞላለች” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል። (ዕን. 2:4, 14) አዎ፣ አምላክን በትዕግሥትና በእምነት የሚጠባበቁ ሁሉ ሕይወት ያገኛሉ።
16 በዕንባቆም 2:4 ላይ ያለውን ተስፋ፣ ላይ ላዩን ስናየው ትልቅ ቁም ነገር የያዘ አይመስለን ይሆናል። ሆኖም እዚህ ጥቅስ ላይ ያለው ይሖዋ የገባው ቃል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ከመሆኑ የተነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ ሦስት ጊዜ ጠቅሶታል! (ሮም 1:17፤ ገላ. 3:11፤ ዕብ. 10:38) ጻድቅ ሰው ምንም ዓይነት መከራ ቢደርስበት እምነት እስካለው ድረስ የአምላክ ዓላማ ሲፈጸም ያያል። ይሖዋ አሁን ካለው ጊዜ ባሻገር ያለውን ነገር እንድናይ ይፈልጋል።
17. የዕንባቆም መጽሐፍ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል?
17 የዕንባቆም መጽሐፍ በመጨረሻዎቹ ቀናት ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ትልቅ ትምህርት ይዟል። ይሖዋ በእሱ ላይ እምነት ላላቸው ጻድቃን በሙሉ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ ሰጥቷቸዋል። እንግዲያው በማንኛውም ዓይነት መከራ ወይም ችግር ውስጥ ብንሆን ምንጊዜም በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ይኑረን። ይሖዋ፣ እንደሚደግፈንና እንደሚያድነን የሚገልጽ ማረጋገጫ በዕንባቆም አማካኝነት ሰጥቶናል። በተጨማሪም በእሱ እንድንተማመንና የወሰነውን ጊዜ በትዕግሥት እንድንጠብቅ በደግነት ጠይቆናል፤ በዚያን ጊዜ የአምላክ መንግሥት መላዋ ምድር ደስተኛና ገር በሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች እንድትሞላ ያደርጋል።—ማቴ. 5:5፤ ዕብ. 10:36-39
ደስ እያላችሁ በይሖዋ ታመኑ
18. ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት በዕንባቆም ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድረዋል?
18 ዕንባቆም 3:16-19ን አንብብ። ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት በዕንባቆም ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ዕንባቆም፣ ይሖዋ ከዚህ ቀደም ለሕዝቦቹ ሲል በወሰዳቸው አስደናቂ እርምጃዎች ላይ አሰላስሏል። ይህም እምነቱን እንደ አዲስ እንዲያጠናክር ረድቶታል። ይሖዋ በቅርቡ እርምጃ እንደሚወስድ እርግጠኛ መሆን ችሏል! ይህን መገንዘቡ፣ በእሱ ላይ የሚደርሰው መከራ ለተወሰነ ጊዜ እንደሚቀጥል ቢያውቅም መጽናናት እንዲችል አድርጎታል። ዕንባቆም ያደረበት ጥርጣሬ ተወግዶ በይሖዋ የማዳን ኃይል ላይ የማይናወጥ እምነት ማሳደርና ደስተኛ መሆን ችሏል። እንዲያውም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በአምላክ ላይ ያላቸውን እምነት ለመግለጽ ከተጠቀሙባቸው ፈጽሞ የማይረሱ አገላለጾች መካከል አንዱን ተናግሯል። አንዳንድ ምሁራን በቁጥር 18 ላይ ያለው አገላለጽ ቃል በቃል “በጌታ በሐሴት እዘላለሁ፤ በአምላክ በደስታ እጨፍራለሁ” የሚል ትርጉም እንዳለው ይናገራሉ። በእርግጥም ከቁጥር 16 እስከ 19 ላይ ያለው ሐሳብ ለሁላችንም ትልቅ ማረጋገጫ ይሰጠናል! ይሖዋ አስደናቂ ተስፋዎችን ከመስጠት ባለፈ ታላቁን ዓላማውን ለመፈጸም ፈጣን እርምጃ እየወሰደ እንዳለ አረጋግጦልናል።
19. ልክ እንደ ዕንባቆም መጽናኛ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
19 የዕንባቆም መጽሐፍ የሚያስተላልፈው ዋነኛ መልእክት ‘በይሖዋ ታመኑ’ የሚል እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። (ዕን. 2:4) እንዲህ ያለውን እምነት ማዳበርና ይዘን መቀጠል የምንችለው የሚከተሉትን ነገሮች በማድረግ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ካጠናከርን ነው፦ (1) ያስጨነቀንንና ያሳሰበንን ነገር ሁሉ ለይሖዋ ምንጊዜም በጸሎት መንገር፣ (2) ይሖዋ በቃሉ በኩል የሚያስተምረንን ትምህርትና በድርጅቱ አማካኝነት የሚሰጠንን ማንኛውንም መመሪያ በትኩረት መስማት፣ (3) ይሖዋን በእምነትና በትዕግሥት መጠበቅ። ዕንባቆምም ያደረገው ይህንኑ ነው። መጽሐፉን የጀመረው በእሮሮ ቢሆንም የደመደመው በደስታና በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት በመግለጽ ነው። እኛም ይሖዋ ልክ እንደ አባት እቅፍ እንዳደረገን እንዲሰማን ከፈለግን ዕንባቆም የተወልንን ግሩም ምሳሌ እንከተል! በጨለማ በተዋጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ከዚህ የበለጠ መጽናኛ ከየት ይገኛል?