የሕይወት ታሪክ
መማሬን አቁሜ አላውቅም
‘ከታላቁ አስተማሪ’ ከይሖዋ የመማር መብት በማግኘቴ እሱን ሁልጊዜ አመሰግነዋለሁ። (ኢሳ. 30:20) ይሖዋ አገልጋዮቹን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ዕጹብ ድንቅ በሆኑት ፍጥረታቱ እንዲሁም በድርጅቱ አማካኝነት ያስተምራቸዋል። እኛን ለማስተማር ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንንም ይጠቀማል። ዕድሜዬ ወደ መቶ ዓመት እየተጠጋ ቢሆንም አሁንም በእነዚህ መንገዶች ከይሖዋ መማሬን ቀጥያለሁ። ይህ የሆነው እንዴት እንደሆነ ልንገራችሁ።
የተወለድኩት በ1927 ሲሆን ቦታውም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በቺካጎ፣ ኢሊኖይ አቅራቢያ የሚገኝ አንድ አነስተኛ ከተማ ነው። አባዬና እማዬ አምስት ልጆች አሏቸው፦ ጄታ፣ ዶን፣ እኔ፣ ካርል እና ጆይ። ሁላችንም በሙሉ ነፍሳችን ይሖዋን ለማገልገል ቆርጠን ነበር። ጄታ በ1943 በጊልያድ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ክፍል ተምራለች። ዶን በ1944፣ ካርል በ1947፣ ጆይ ደግሞ በ1951 በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ቤቴል ማገልገል ጀመሩ። እነሱም ሆኑ ወላጆቼ የተዉልኝ መልካም ምሳሌ በጣም አበረታቶኛል።
ቤተሰባችን እውነትን የሰማበት መንገድ
አባዬና እማዬ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡና አምላክን የሚወዱ ሰዎች ነበሩ። ይህን ፍቅር በእኛ ውስጥም ተክለውብናል። ይሁንና አባዬ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት አውሮፓ ውስጥ ወታደር ሆኖ ካገለገለ በኋላ ለአብያተ ክርስቲያናቱ ያለውን አክብሮት አጣ። እማዬ፣ አባዬ ከጦርነቱ በሰላም በመመለሱ ከፍተኛ የአመስጋኝነት ስሜት ስለተሰማት “ካርል፣ እንደ በፊቱ ቤተ ክርስቲያን እንሂድ” አለችው። አባዬ ግን “ከፈለግሽ እሸኝሻለሁ፤ ግን ውስጥ አልገባም” አላት። እሷም “ለምን?” አለችው። በዚህ ጊዜ እንዲህ አላት፦ “በጦርነቱ ወቅት በሁለቱም ወገኖች ያሉ የተመሳሳይ ሃይማኖት ቄሶች ወታደሮቻቸውን ይባርኩ ነበር። ታዲያ አምላክ ከማን ወገን ሊሆን ነው?”
በኋላ ላይ እማዬ ቤተ ክርስቲያን ሄዳ ሳለ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችን መጡ። ለአባቴ ስለ ራእይ መጽሐፍ የሚያብራራውን ብርሃን (እንግሊዝኛ) የተባለ ባለ ሁለት ጥራዝ መጽሐፍ ሰጡት። አባዬ ትኩረቱ ስለተሳበ መጽሐፎቹን ተቀበላቸው። እማዬ መጽሐፎቹን ካየቻቸው በኋላ ማንበብ ጀመረች። ከዚያም አንድ ቀን ጋዜጣ ላይ፣ እነዚህን መጽሐፎች በመጠቀም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ለሚፈልጉ ሰዎች ግብዣ የሚያቀርብ ማስታወቂያ አየች። በጥናቱ ላይ ለመገኘት ወሰነች። እዚያ ስትደርስ አንዲት አረጋዊት ሴት በሩን ከፈተችላት። እማዬም አንዱን መጽሐፍ አውጥታ “ይህን መጽሐፍ የምታጠኑት እዚህ ነው?” ብላ ጠየቀቻት። ሴትየዋም “አዎ የእኔ ቆንጆ፣ ግቢ” አለቻት። በቀጣዩ ሳምንት እማዬ እኛንም ይዛን ሄደች። ከዚያ በኋላ በየሳምንቱ መሄድ ጀመርን።
በአንደኛው ስብሰባ ላይ፣ ስብሰባውን የሚመራው ወንድም መዝሙር 144:15ን እንዳነብ ጠየቀኝ፤ ጥቅሱ ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ደስተኛ እንደሆኑ ይናገራል። ይህ ጥቅስ ልቤን ነካው። ልቤን የነኩት ሌሎች ሁለት ጥቅሶች ደግሞ ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ እንደሆነ የሚናገረው 1 ጢሞቴዎስ 1:11 እና ‘አምላክን እንድንመስል’ የሚያበረታታው ኤፌሶን 5:1 ናቸው። ፈጣሪዬን በማገልገል ደስታ ማግኘት እንዳለብኝ እንዲሁም ይህን መብት ስለሰጠኝ እሱን ማመስገን እንደሚገባኝ ተገነዘብኩ። እነዚህ እውነቶች ለሕይወቴ መርህ ሆነውልኛል።
ለእኛ የሚቀርበን ጉባኤ 32 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ በቺካጎ ያለ ጉባኤ ነበር። ያም ቢሆን በስብሰባ ላይ እንገኝ ነበር። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለኝ እውቀትም እያደገ መጣ። በአንድ ወቅት ጄታ እጇን አውጥታ ሐሳብ ስትሰጥ “እኔም እኮ መልሱን አውቀው ነበር። እጄን አውጥቼ መመለስ እችል ነበር” ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ ለስብሰባ መዘጋጀትና ሐሳብ መስጠት ጀመርኩ። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ እኔም ሆንኩ ወንድሞቼና እህቶቼ መንፈሳዊ እድገት አደረግን። በ1941 ተጠመቅኩ።
በትላልቅ ስብሰባዎች ወቅት ከይሖዋ መማር
በተለይ በ1942 በክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ የተደረገውን ትልቅ ስብሰባ መቼም አልረሳውም። ስብሰባው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ወደሚገኙ ሌሎች 50 ቦታዎች በስልክ ተሰራጭቷል። የእኛ ቤተሰብም ሆነ ሌሎች በርካታ ቤተሰቦች በስብሰባ ቦታው አቅራቢያ በሚገኝ ትላልቅ መኪኖች የሚቆሙበት ሰፊ ግቢ ውስጥ ድንኳን ጥለን እናድር ነበር። በወቅቱ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተካሄደ ነበር። በወንድሞች ላይ የሚደርሰው ተቃውሞም እየጨመረ መጥቷል። ምሽት ላይ ወንድሞች የመኪናቸውን ፊት ከግቢው ወደ ውጭ አዙረው ሲያቆሙ አየሁ። በእያንዳንዱ መኪና ውስጥ አንድ አንድ ሰው ሲጠብቅ እንዲያድር ተስማምተው ነበር። ችግር ከተፈጠረ እነዚያ ወንድሞች ጥቃት የሚሰነዝሩት ሰዎች ማየት እንዲከብዳቸው ለማድረግ የመኪናቸውን መብራት ማብራትና ጥሩንባቸውን መንፋት ነበረባቸው። ከዚያም ሌሎቹ ወንድሞች ቶሎ መጥተው እገዛ ማበርከት ይችላሉ። ‘የይሖዋ ሕዝቦች ለሁሉም ዓይነት ሁኔታ ዝግጁ ናቸው’ ብዬ አሰብኩ። በመሆኑም ምንም ስጋት ሳያድርብኝ ለጥ ብዬ ተኝቼ አደርኩ። ደስ የሚለው፣ ምንም ዓይነት ችግር አልተፈጠረም።
ከዓመታት በኋላ ስለዚያ ስብሰባ መለስ ብዬ ሳስብ እናቴ ምንም ዓይነት የጭንቀትም ሆነ የፍርሃት ስሜት እንዳልነበራት አስታወስኩ። በይሖዋና በድርጅቱ ሙሉ በሙሉ ተማምና ነበር። እሷ የተወችልኝን መልካም ምሳሌ መቼም አልረሳውም።
ያ ስብሰባ ከመካሄዱ ጥቂት ቀደም ብሎ እማዬ የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል ጀምራ ነበር። በመሆኑም የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን የሚመለከቱ ንግግሮችን ልዩ ትኩረት ሰጥታ ታዳምጥ ነበር። ወደ ቤት እየተመለስን ሳለ እንዲህ አለችን፦ “በአቅኚነት ማገልገሌን መቀጠል እፈልጋለሁ። ግን በአቅኚነት እያገለገልኩ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ሁሉ ማከናወን አልችልም።” ከዚያም ልንረዳት ፈቃደኞች መሆናችንን ጠየቀችን። እኛም ፈቃደኛ ሆንን፤ ስለዚህ እያንዳንዳችን ከቁርስ በፊት የምናጸዳው አንድ ወይም ሁለት ክፍል መደበችልን። ወደ ትምህርት ቤት ከሄድን በኋላ ቤቱ ንጹሕ መሆኑን ታረጋግጥና ወደ አገልግሎት ትሄዳለች። ብዙ ሥራ ቢኖራትም ልጆቿን ችላ ብላ አታውቅም። ለምሳና ከትምህርት በኋላ ስንመለስ ቤት ውስጥ አጥተናት አናውቅም። አንዳንድ ጊዜ ከትምህርት በኋላ አብረናት አገልግሎት እንወጣ ነበር። ይህም አቅኚ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስገንዝቦናል።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መጀመር
በ16 ዓመቴ አቅኚነት ጀመርኩ። አባዬ ገና የይሖዋ ምሥክር ባይሆንም ስለ አገልግሎቴ ይጠይቀኝ ነበር። አንድ ምሽት፣ የቻልኩትን ሁሉ ጥረት ባደርግም መጽሐፍ ቅዱስን
ማጥናት የሚፈልግ ሰው እንዳላገኘሁ ነገርኩት። ከዚያም “አንተ ከእኔ ጋር ለማጥናት ፈቃደኛ ነህ?” አልኩት። እሱም ጥቂት አሰብ አደረገና “እንቢ ለማለት የሚያበቃ አጥጋቢ ምክንያት አላገኘሁም” አለኝ። ስለዚህ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ አባቴ ነበር። ይህ ለእኔ ልዩ መብት ነው።“ነፃ የሚያወጣው እውነት” (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ አጠናን። ጥናታችንን እየቀጠልን ስንሄድ አባዬ ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪና አስተማሪ እንድሆን እየረዳኝ እንዳለ ተገነዘብኩ። ለምሳሌ አንድ ምሽት አንቀጹን ካነበብን በኋላ “መጽሐፉ ምን እንደሚል ገብቶኛል። ግን መጽሐፉ የሚለው ነገር ትክክል እንደሆነ በምን ታውቃለህ?” አለኝ። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ዝግጁ አልነበርኩም። ስለዚህ “መልሱን አሁን ልነግርህ አልችልም። በቀጣዩ ጥናታችን ላይ ግን መልሱን አዘጋጅልሃለሁ” አልኩት። ደግሞም መልሱን ተዘጋጀሁ። እየተወያየን የነበርነውን ነጥብ የሚደግፉ ጥቅሶችን አገኘሁ። ከዚያ በኋላ ለጥናታችን በደንብ መዘጋጀት ጀመርኩ፤ ምርምር ማድረግ የሚቻልበትንም መንገድ ተማርኩ። እንዲህ ማድረጌ ለእኔም ሆነ ለአባቴ መንፈሳዊ እድገት አስተዋጽኦ አበርክቷል። አባቴ የተማረውን ነገር ተግባራዊ አደረገ፤ ከዚያም በ1952 ተጠመቀ።
ተጨማሪ ትምህርት እንዳገኝ የረዱኝ ግቦች
በ17 ዓመቴ ራሴን ችዬ መኖር ጀመርኩ። በወቅቱ ጄታ a ሚስዮናዊ፣ ዶን ደግሞ ቤቴላዊ ሆነው ነበር። ሁለቱም የአገልግሎት ምድባቸውን በጣም ይወዱት ነበር፤ ይህም በእጅጉ አበረታቶኛል። ስለዚህ ለቤቴልም ለጊልያድ ትምህርት ቤትም ካመለከትኩ በኋላ ጉዳዩን ለይሖዋ ተውኩት። ከዚያም በ1946 በቤቴል እንዳገለግል ተጋበዝኩ።
ባለፉት ዓመታት ቤቴል ውስጥ በተለያዩ ምድቦች አገልግያለሁ። በመሆኑም ብዙ አዳዲስ ነገሮችን መማር ችያለሁ። በቤቴል ባሳለፍኳቸው 75 ዓመታት ውስጥ መጻሕፍትን ማተም የሚቻልበትን መንገድና የሒሳብ አያያዝ ተምሬያለሁ። ዕቃዎችን ከውጭ ማስገባትና ወደ ውጭ አገር መላክ ስለሚቻልበት መንገድም ትምህርት አግኝቻለሁ። በዋነኝነት ግን፣ ቤቴል ውስጥ በማለዳ አምልኮና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ንግግሮች አማካኝነት የሚሰጠውን ያልተቋረጠ ትምህርት በጣም እወደዋለሁ።
ከታናሽ ወንድሜ ከካርልም ትምህርት አግኝቻለሁ። እሱ ቤቴል የገባው በ1947 ነው። ካርል ጎበዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪና አስተማሪ ነበር። በአንድ ወቅት፣ ከማቀርበው ንግግር ጋር በተያያዘ እንዲረዳኝ ጠየቅኩት። ከጽሑፎች ላይ ብዙ ሐሳቦችን ባሰባስብም ሐሳቦቹን እንዴት መጠቀም እንዳለብኝ ግራ እንደገባኝ ነገርኩት። እሱም አንድ ጥያቄ በመጠየቅ መፍትሔ እንዳገኝ ረዳኝ። “ጆኤል፣ ጭብጥህ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። ነጥቡ ወዲያውኑ ገባኝ፤ ጭብጡን ለማዳበር የሚረዱኝን ሐሳቦች ብቻ መጠቀም፣ የቀረውን ደግሞ መተው አለብኝ ማለት ነው። ያንን ትምህርት እስካሁን አልረሳሁትም።
ቤቴል ውስጥ ደስተኛ ሆነን መኖር ከፈለግን በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ ይኖርብናል፤ ይህም የሚያበረታቱ
ተሞክሮዎችን እንድናገኝ ሊረዳን ይችላል። ከማልረሳቸው ተሞክሮዎች አንዱ ያጋጠመኝ አንድ ምሽት በኒው ዮርክ ሲቲ ስናገለግል ነው። ከአንድ ወንድም ጋር ሆነን ከዚህ በፊት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔት የወሰደችን ሴት ልናነጋግር ሄድን። ራሳችንን ካስተዋወቅን በኋላ “ዛሬ የመጣነው ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ አበረታች ሐሳቦችን እንዲማሩ መርዳት ስለፈለግን ነው” አልናት። እሷም “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ከሆነ ግቡ” አለችን። ስለ አምላክ መንግሥትና ስለ አዲሱ ዓለም የሚናገሩ ብዙ ጥቅሶችን አንብበን ተወያየን። ውይይቱ በጣም አስደሰታት፤ ስለዚህ በቀጣዩ ሳምንት አንዳንድ ጓደኞቿን በውይይቱ ላይ እንዲገኙ ጋበዘቻቸው። ከጊዜ በኋላ እሷና ባለቤቷ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ሆነዋል።ከትዳር አጋሬ ያገኘሁት ትምህርት
ከባለቤቴ ጋር ከመገናኘታችን በፊት ለአሥር ዓመት ገደማ የትዳር አጋር ስፈልግ ቆይቻለሁ። ጥሩ ሚስት ለማግኘት የረዳኝ ምንድን ነው? ‘ካገባሁ በኋላ መምራት የምፈልገው ምን ዓይነት ሕይወት ነው?’ የሚለውን ጥያቄ በጸሎት ታግዤ አሰብኩበት።
በ1953 በያንኪ ስታዲየም ከተደረገው ትልቅ ስብሰባ በኋላ ሜሪ አኒዮል ከተባለች እህት ጋር ተዋወቅኩ። እሷና ጄታ በጊልያድ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ክፍል አብረው ተምረዋል። በተጨማሪም አብረው በሚስዮናዊነት አገልግለዋል። ሜሪ በካሪቢያን ስለነበረው የሚስዮናዊ ምድቧ እንዲሁም ባለፉት ዓመታት ስላስጠናቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በከፍተኛ ቅንዓት ትነግረኝ ነበር። ይበልጥ እየተዋወቅን ስንሄድ ተመሳሳይ መንፈሳዊ ግብ እንዳለን ተገነዘብን። ይበልጥ እየተዋደድን መጣን፤ ከዚያም ሚያዝያ 1955 ተጋባን። ሜሪ በብዙ መንገዶች የይሖዋ ስጦታ እንዲሁም ግሩም ምሳሌ ሆናልኛለች። የተሰጣትን ማንኛውንም ሥራ በደስታ ታከናውን ነበር። በትጋት ትሠራለች፤ ለሌሎች ከልቧ ታስባለች፤ እንዲሁም ምንጊዜም የመንግሥቱን ጉዳዮች ታስቀድማለች። (ማቴ. 6:33) ለሦስት ዓመት ያህል በወረዳ ሥራ አገለገልን። ከዚያም በ1958 አብረን በቤቴል እንድናገለግል ተጋበዝን።
ከሜሪ ብዙ ትምህርት አግኝቻለሁ። ለምሳሌ ገና እንደተጋባን አካባቢ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንን አብረን ለማድረግ ወሰንን። በአንድ ጊዜ 15 ቁጥር ገደማ እናነባለን። አንዳችን የተወሰነውን ክፍል ካነበብን በኋላ ስለ ጥቅሱ ሐሳብ እንሰጣለን፤ እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ልናደርገው እንደምንችል እንወያያለን። ሜሪ በጊልያድ ወይም በሚስዮናዊ አገልግሎቷ ወቅት የተማረቻቸውን ነገሮች ብዙ ጊዜ ትነግረኝ ነበር። እነዚህ ውይይቶች ጥልቅ ማስተዋል ሰጥተውኛል፤ እንዲሁም ንግግሮቼንና ለእህቶች የምሰጠውን ማበረታቻ እንዳሻሽል ረድተውኛል።—ምሳሌ 25:11
ውዷ ባለቤቴ ሜሪ በ2013 አረፈች። በአዲሱ ዓለም እሷን ለማግኘት በጣም እጓጓለሁ። እስከዚያው ድረስ ግን መማሬንና በሙሉ ልቤ በይሖዋ መታመኔን ለመቀጠል ቆርጫለሁ። (ምሳሌ 3:5, 6) የይሖዋ ሕዝቦች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ስለሚያከናውኑት ሥራ ማሰብ ማጽናኛና ደስታ ይሰጠኛል። በዚያ ወቅት ከታላቁ አስተማሪያችን ብዙ አዳዲስ ነገሮችን እንደምንማር ምንም ጥያቄ የለውም፤ ስለ እሱም ብዙ የምንማረው ነገር ይኖራል። አዎ፣ ይሖዋ እስካሁን ብዙ ትምህርቶችን ስላስተማረኝ እንዲሁም ጸጋውን በተለያዩ መንገዶች ስላሳየኝ በእጅጉ አመሰግነዋለሁ።
a የጄታ ሱነል የሕይወት ታሪክ በመጋቢት 1, 2003 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 23-29 ላይ ይገኛል።