የሕይወት ታሪክ
‘ይሖዋ ደግነት አሳይቶናል’
እኔና ባለቤቴ ዳኒዬል ወደምናርፍበት ሆቴል ገብተን የእንግዳ መቀበያ ጋ የምትሠራውን ሴት ስናነጋግራት ወዲያውኑ “ይቅርታ፣ የድንበር ፖሊሶቹ ጋ ሊደውሉ ይችላሉ?” አለችኝ። በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው ጋቦን የደረስነው ከጥቂት ሰዓታት በፊት ነበር። በ1970ዎቹ በዚህች አገር ውስጥ ሥራችን ታግዶ ነበር።
ዳኒዬል ፈጣን አእምሮ ስላላት “ፖሊሶቹ ጋ መደወል አያስፈልግህም፤ እዚሁ መጥተዋል!” ብላ በጆሮዬ ሹክ አለችኝ። እኛ ከገባን ብዙም ሳይቆይ አንድ መኪና መጥቶ ከሆቴሉ ፊት ለፊት ቆሞ ነበር። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሁለታችንም በወታደሮች ተይዘን ታሰርን። ሆኖም ዳኒዬል አስቀድማ ስላስጠነቀቀችኝ የተወሰኑ ሰነዶችን ለአንድ ወንድም የማቀብልበት ጊዜ አግኝቼ ነበር።
ወደ ፖሊስ ጣቢያው ይዘውን በሚሄዱበት ጊዜ፣ እንዲህ ያለች ደፋርና መንፈሳዊ ሚስት በማግኘቴ ምን ያህል እንደታደልኩ እያሰብኩ ነበር። እኔና ዳንዬል እርስ በርስ ከተረዳዳንባቸው በርካታ አጋጣሚዎች መካከል ይህ አንዱ ነበር። እስቲ የስብከቱ ሥራችን የታገደባቸውን አገሮች መጎብኘት የጀመርነው እንዴት እንደሆነ ልንገራችሁ።
ይሖዋ እውነትን እንዳውቅ በደግነት ዓይኖቼን ከፈተልኝ
የተወለድኩት በሰሜናዊ ፈረንሳይ በምትገኝ ክርዋ የተባለች አነስተኛ ከተማ ውስጥ በ1930 ነው። ቤተሰባችን አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነበር። በየሳምንቱ በቅዳሴ ላይ እንገኝ የነበረ ሲሆን አባቴ ቤተ ክርስቲያኗ በምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደርግ ነበር። ይሁን እንጂ 14 ዓመት ገደማ ሲሆነኝ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የሚታየውን ግብዝነት እንዳስተውል ያደረገኝ አንድ ነገር ተፈጠረ።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ፈረንሳይ በጀርመን ሠራዊት ቁጥጥር ሥር ወድቃ ነበር። የቤተ ክርስቲያናችን ቄስ የናዚ ደጋፊ የነበረውን የቪሺን መንግሥት እንድንደግፍ ዘወትር ያበረታታን ነበር። የሚናገረው ነገር በጣም ያስፈራን ነበር። በፈረንሳይ እንደነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ሁሉ እኛም ስለ ኅብረ ብሔሩ ጦር የሚገልጹ ዘገባዎችን በቢቢሲ ሬዲዮ በድብቅ እናዳምጥ ነበር። ከዚያም ቄሱ በድንገት አቋሙን ቀይሮ መስከረም 1944 የኅብረ ብሔሩ ጦር በናዚ ላይ የተቀዳጀውን ድል ለመደገፍ የምስጋና አገልግሎት እንዲቀርብ ዝግጅት አደረገ። ይህ በጣም ያስደነገጠኝ ሲሆን በቀሳውስት ላይ ያለኝ እምነት በእጅጉ ተዳከመ።
ጦርነቱ ካበቃ ብዙም ሳይቆይ አባቴ ሞተ። በወቅቱ ታላቅ እህቴና ባለቤቷ የሚኖሩት በቤልጅየም ነበር፤ በመሆኑም እናቴን የመንከባከብ ኃላፊነት ያለብኝ እኔ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ስለዚህ በአንድ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጠርኩ። አለቃዬና ወንዶች ልጆቹ አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ነበሩ። በፋብሪካው ውስጥ እድገት የማግኘት አጋጣሚ የነበረኝ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ አንድ ፈታኝ ሁኔታ ገጠመኝ።
በ1953 እህቴ ሲሞን ልትጠይቀን መጣች፤ በዚያ ወቅት የይሖዋ ምሥክር ሆና ነበር። እሷም ሲኦል መቃጠያ ቦታ እንደሆነ፣ አምላክ ሥላሴ እንደሆነና ነፍስ እንደማትሞት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምራቸው ትምህርቶች ሐሰት እንደሆኑ መጽሐፍ ቅዱሷን ተጠቅማ በሚገባ አስረዳችን። መጀመሪያ ላይ
ጥቅሶቹን ያነበበችልኝ ከካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዳልሆነ በመናገር ተከራከርኳት፤ ብዙም ሳይቆይ ግን የምትናገረው ነገር እውነት መሆኑን አመንኩ። በኋላም ቆየት ያሉ የመጠበቂያ ግንብ እትሞችን ያመጣችልኝ ሲሆን እኔም ማታ ማታ መኝታ ክፍሌ ውስጥ ሆኜ እነዚህን ጽሑፎች በጉጉት አነብ ነበር። እውነትን እንዳገኘሁ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደብኝም፤ ሆኖም የይሖዋ ምሥክር እንደሆንኩ ብናገር ሥራዬን አጣለሁ ብዬ ፈርቼ ነበር።ለተወሰኑ ወራት ያህል መጽሐፍ ቅዱስንና የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎችን በግሌ አጠና ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ወደ ስብሰባ አዳራሽ ለመሄድ ወሰንኩ። በጉባኤው ውስጥ ያየሁት ፍቅር ልቤን በጥልቅ ነካው። ተሞክሮ ካለው አንድ ወንድም ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለስድስት ወራት ካጠናሁ በኋላ መስከረም 1954 ተጠመቅሁ። ብዙም ሳይቆይ እናቴና ታናሽ እህቴም የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸው በጣም አስደስቶኛል።
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ስንካፈል በይሖዋ መታመን
በ1958 በኒው ዮርክ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የመካፈል መብት አግኝቼ ነበር፤ የሚያሳዝነው ስብሰባው ከመድረሱ ከጥቂት ሳምንታት በፊት እናቴ ሞተች። ከስብሰባው ስመለስ ምንም ዓይነት የቤተሰብ ኃላፊነት ስላልነበረብኝ ሥራዬን አቁሜ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ። ዳኒዬል ዴሊ ከምትባል አንዲት ቀናተኛ አቅኚ ጋር የተጫጨሁት በዚህ ወቅት ነበር፤ ግንቦት 1959 ከዳንዬል ጋር ተጋባን።
ዳኒዬል የሙሉ ጊዜ አገልግሎቷን የጀመረችው ቤተሰቦቿ ካሉበት በጣም ርቆ በሚገኘው በገጠራማው ብሪታኒ ነበር። የካቶሊክ እምነት ተከታዮች በሚበዙበት በዚያ አካባቢ መስበክና በብስክሌት ተጉዛ ገጠራማ ወደሆኑት ክልሎች መሄድ ድፍረት ይጠይቅባት ነበር። ልክ እንደ እኔ እሷም በጥድፊያ ስሜት ታገለግል ነበር፤ ምክንያቱም ሁለታችንም መጨረሻው በጣም ቅርብ እንደሆነ ይሰማን ነበር። (ማቴ. 25:13) ዳንዬል የነበራት የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድንጸና ረድቶናል።
ከተጋባን ከጥቂት ቀናት በኋላ በወረዳ ሥራ እንድናገለግል ተመደብን። በዚህ ሥራ ላይ ስንካፈል አኗኗራችንን ቀላል ለማድረግ ጥረት አድርገናል። ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኘነው ጉባኤ 14 አስፋፊዎች ያሉት ሲሆን ወንድሞች እኛን በቤታቸው ተቀብለው ለማስተናገድ አቅም አልነበራቸውም። በመሆኑም በስብሰባ አዳራሹ መድረክ ላይ ፍራሽ ዘርግተን ተኛን። እርግጥ መኝታው ምቹ አልነበረም፤ ለጀርባ ግን በጣም ጥሩ ነው!
በወረዳ ሥራ ላይ እያለን ፕሮግራማችን በጣም የተጣበበ ቢሆንም ዳኒዬል ራሷን ከሁኔታዎች ጋር ለማስማማት አልተቸገረችም። አንዳንድ ጊዜ ከሽማግሌዎች ጋር ድንገተኛ ስብሰባ እናደርጋለን፤ በዚህ ጊዜ ዳኒዬል ትንሿ መኪናችን ውስጥ ቁጭ ብላ ትጠብቀኛለች። ሆኖም አንድም ቀን አማርራ አታውቅም። በወረዳ ሥራ ላይ የቆየነው ለሁለት ዓመት ብቻ ነበር፤ እነዚያ ሁለት ዓመታት ባለትዳሮች በሐቀኝነት መነጋገራቸውና ተባብረው መሥራታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስተምረውናል።—መክ. 4:9
አዲስ የአገልግሎት ምድብ
በ1962 በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የጊልያድ ትምህርት ቤት 37ኛ ክፍል ገብተን ለአሥር ወር ያህል እንድንሠለጥን ተጋበዝን። ከተጋበዙት 100 ተማሪዎች ውስጥ 13ቱ ጥንዶች ሲሆኑ እኔና ዳንዬልም ከእነሱ መካከል የመሆን መብት በማግኘታችን በጣም ተደሰትን። እንደ ፍሬድሪክ ፍራንዝ፣ ዩሊሴዝ ግላስና አሌክሳንደር ማክሚላን ካሉ የእምነት ዓምድ የሆኑ ወንድሞች ጋር ያሳለፍነውን አስደሳች ጊዜ አሁንም ድረስ አስታውሰዋለሁ።
በሥልጠናው ወቅት አስተማሪዎቹ በትኩረት የመመልከት ችሎታችንን እንድናዳብር ያበረታቱን ነበር። አልፎ አልፎ ቅዳሜ ከሰዓት ትምህርት ከጨረስን በኋላ በኒው ዮርክ ሲቲ ውስጥ እየተዘዋወርን አንዳንድ ቦታዎችን እንጎበኝ ነበር፤ ይህ የሥልጠናው
ክፍል ነበር። ከዚያም በጉብኝቱ ላይ የተመለከትነውን ነገር ሰኞ በጽሑፍ እንድናቀርብ እንጠየቃለን። ብዙውን ጊዜ ቅዳሜ ማታ የምንመለሰው በጣም ደክሞን ነበር፤ ሆኖም ቤቴል ውስጥ የሚያገለግለው አስጎብኚያችን ለጽሑፍ ፈተናው ቁልፍ ነጥቦችን እንድናስታውስ ለመርዳት የክለሳ ጥያቄዎች ይጠይቀን ነበር። አንድ ቅዳሜ ሙሉውን ከሰዓት በከተማዋ ውስጥ በእግር ስንዞር ዋልን። ያን ዕለት አንድ የጠፈር ምርምር ጣቢያ ስንጎበኝ ስለ ተወርዋሪ ኮከቦች (ሚቲዮሮች) እና ምድር ላይ ስለሚያርፉ የጠፈር አካላት (ሚቲዮራይቶች) ተምረን ነበር። የአሜሪካ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየምን ስንጎበኝ ደግሞ በአርጃኖና በአዞ መካከል ስላለው ልዩነት ተምረን ነበር። ቤቴል ከደረስን በኋላ አስጎብኚያችን “በሚቲዮሮች እና በሚቲዮራይቶች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀን። ዳኒዬል በጣም ደክሟት ስለነበር “ያው ሚቲዮራይቶች ረጃጅም ጥርሶች አላቸው” ብላ መለሰች!ከሥልጠናው በኋላ በፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ እንድናገለግል መመደባችንን ስናውቅ በጣም ተገረምን። በዚያ ከ53 ዓመታት በላይ አብረን አገልግለናል። በ1976 የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አስተባባሪ ሆኜ የተሾምኩ ከመሆኑም ሌላ በአፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የስብከት ሥራችን የታገደባቸውን አገሮች እንድጎበኝ ተመደብኩ። ወደ ጋቦን የሄድነውና መግቢያው ላይ የጠቀስኩት ተሞክሮ ያጋጠመን በዚህ ወቅት ነበር። እውነቱን ለመናገር፣ የተሰጡኝን ያልተጠበቁ ኃላፊነቶችን ለመቀበል ብቁ እንደሆንኩ ተሰምቶኝ አያውቅም። ዳኒዬል ግን ማንኛውንም ኃላፊነት እንድወጣ ትልቅ ድጋፍ አድርጋልኛለች።
ከባድ ፈተና አጋጠመን
ቤቴል ማገልገል ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ በዚያ ያለውን ሕይወት በጣም ወደነው ነበር። ዳኒዬል ጊልያድ ከመግባታችን በፊት ባሉት አምስት ወራት ውስጥ እንግሊዝኛ የተማረች ሲሆን በኋላም ጎበዝ ተርጓሚ ሆነች። የቤቴል ሥራችን ከፍተኛ እርካታ ይሰጠን ነበር፤ በጉባኤ እንቅስቃሴዎች የምናደርገው ተሳትፎ ደግሞ ደስታችን እጥፍ ድርብ እንዲሆን አድርጓል። እኔና ዳንዬል ጥሩ እድገት እያደረጉ ያሉ ጥናቶችን ከመራን በኋላ ምሽት ላይ የፓሪሱን የምድር ውስጥ ባቡር ተሳፍረን እንመለስ ነበር፤ ውሏችን አድካሚ ቢሆንም ከፍተኛ ደስታ ይሰማን ነበር። አሁንም ድረስ ስለዚያ ጊዜ ጥሩ ትዝታ አለኝ። የሚያሳዝነው ግን ዳኒዬል፣ ድንገተኛ የጤና ችግር ስላጋጠማት የምትፈልገውን ያህል መንቀሳቀስ አልቻለችም።
በ1993 ዳንዬል የጡት ካንሰር እንዳለባት በምርመራ ታወቀ። ሕክምናው ቀዶ ጥገናንና ኬሞቴራፒን ስለሚያካትት ለመቋቋም በጣም ከባድ ነው። ከአሥራ አምስት ዓመት በኋላ በድጋሚ ካንሰር የያዛት ሲሆን ይሄኛው ከበፊቱ የበለጠ በፍጥነት የመሰራጨት አቅም ነበረው። ያም ሆኖ የትርጉም ሥራዋን በጣም ስለምትወደው ሁኔታዋ ሲፈቅድላት እንደ ምንም ብላ ሥራዋን ትቀጥል ነበር።
ዳኒዬል ሕመሟ በጣም ያሠቃያት የነበረ ቢሆንም አንድም ቀን ከቤቴል ለመውጣት አስበን አናውቅም። እርግጥ ቤቴል ውስጥ ሆኖ መታመም የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉት፤ በተለይ ደግሞ ሌሎች ሰዎች ሕመማችሁ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ካላወቁ ሁኔታው የበለጠ ከባድ ይሆናል። (ምሳሌ 14:13) ዳኒዬል በ70ዎቹ መጨረሻ ላይ እያለች እንኳ ውበቷ ስላልጠፋና የደስ ደስ ስለነበራት ያን ያህል የታመመች አትመስልም ነበር። ያለችበትን ሁኔታ እያሰበች ከመቆዘም ይልቅ ሌሎችን በመርዳት ላይ ታተኩር ነበር። በሥቃይ ላይ ያሉ ሰዎች ሰሚ ጆሮ ማግኘታቸው ምን ያህል እንደሚረዳቸው ታውቅ ነበር። (ምሳሌ 17:17) ዳኒዬል ራሷን እንደ አማካሪ አድርጋ ባትቆጥርም ካንሰር የያዛቸው በርካታ እህቶች በሽታውን እንዳይፈሩ የራሷን ተሞክሮ በማካፈል ትረዳቸዋለች።
በተጨማሪም ከዚህ በፊት አጋጥመውን የማያውቁ ተፈታታኝ ምሳሌ 18:22
ሁኔታዎችን መቋቋም ነበረብን። ዳኒዬል በጤናዋ ምክንያት የሙሉ ጊዜ ሥራ መሥራት ካቃታት በኋላ በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ታደርግልኝ ነበር። ሕይወቴን ቀላል ለማድረግ ብዙ ጥረት ያደረገች ሲሆን ይህም ለ37 ዓመታት ያህል በቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አስተባባሪነት ማገልገሌን እንድቀጥል አስችሎኛል። ለምሳሌ በየቀኑ ምሳችንን ክፍላችን ውስጥ መብላትና ዘና ማለት እንድንችል አስፈላጊውን ነገር ታዘጋጅ ነበር።—“እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው”
ዳኒዬል ምንጊዜም አዎንታዊ አመለካከት የነበራት ሲሆን ሁሌም በሕይወት ለመቀጠል ትጓጓ ነበር። ከዚያም ለሦስተኛ ጊዜ ካንሰር ያዛት። በዚህ ጊዜ ምንም አቅም እንደሌለን ተሰማን። ዳንዬል በየተወሰነ ጊዜ የምትወስደው የኬሞቴራፒና የራዲዮቴራፒ ሕክምና አንዳንዴ መራመድ እንኳ እስኪያቅታት ድረስ ኃይሏን ያሟጥጠው ነበር። ጎበዝ ተርጓሚ የነበረችው ውዷ ባለቤቴ፣ የምትናገራቸውን ቃላት ማውጣት አቅቷት ስትታገል ማየት ልብ የሚሰብር ነበር።
ኃይላችን እንደተሟጠጠ ቢሰማንም ይሖዋ ከምንችለው በላይ መከራ እንዲደርስብን ፈጽሞ እንደማይፈቅድ እርግጠኞች በመሆን አዘውትረን እንጸልይ ነበር። (1 ቆሮ. 10:13) ይሖዋ በቃሉ፣ በቤቴል የሕክምና ቡድን አባላትና መንፈሳዊ ቤተሰባችን በሚያደርግልን ፍቅራዊ ድጋፍ አማካኝነት ለሚሰጠን እርዳታ ምንጊዜም አድናቆት ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን።
የትኛውን የሕክምና ዓይነት መቀበል እንዳለብን ለመወሰን ይሖዋ እንዲረዳን በተደጋጋሚ እንለምነው ነበር። በአንድ ወቅት ምንም ዓይነት ሕክምና ማግኘት አልቻልንም ነበር። ለ23 ዓመታት ያህል ዳኒዬልን ሲረዳት የነበረው ሐኪም ዳንዬል ከእያንዳንዱ የኬሞቴራፒ ሕክምና በኋላ ራሷን የምትስተው ለምን እንደሆነ ግራ ገብቶት ነበር። አማራጭ ሕክምናም ሊጠቁመን አልቻለም። በዚህ ጊዜ ምንም ረዳት እንደሌለንና የሚመጣውን ነገር ዝም ብለን ከመጠበቅ ውጭ ምንም ማድረግ እንደማንችል ተሰማን። ከዚያም አንድ ሌላ የካንሰር ሐኪም ዳኒዬልን ለማከም ተስማማ። ይሖዋ ጭንቀታችንን መቋቋም እንድንችል መውጫ መንገዱን ያዘጋጀልን ያህል ነበር።
የነበርንበትን አስከፊ ሁኔታ ለመቋቋም የረዳን ስለ ነገ አለመጨነቃችን ነው። ኢየሱስ እንደተናገረው “እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው።” (ማቴ. 6:34) በተጨማሪም አዎንታዊ አመለካከት መያዛችንና በሁኔታችን ቀልደን ማለፋችን ረድቶናል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት ዳኒዬል ለሁለት ወራት ያህል ኬሞቴራፒ ሳትወስድ ቆይታ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ፈገግ ብላ በራሷ ላይ እያሾፈች “ታውቃለህ፣ የአሁኑን ያህል ጤንነት ተሰምቶኝ አያውቅም!” አለችኝ። (ምሳሌ 17:22) ዳኒዬል ከባድ ሥቃይ ቢኖርባትም አዲሶቹን የመንግሥቱን መዝሙሮች ጮክ ብላ በልበ ሙሉነት እየዘመረች መለማመድ ያስደስታት ነበር።
ዳኒዬል አዎንታዊ አመለካከት ያላት መሆኗ እኔም ድክመቶቼን እንዳሸንፍ ረድቶኛል። እውነቱን ለመናገር በትዳር ሕይወት ባሳለፍናቸው 57 ዓመታት ውስጥ የሚያስፈልጉኝን የተለያዩ ነገሮች የምታሟላልኝ እሷ ነበረች። እንቁላል እንድጠብስ እንኳ አትፈቅድልኝም ነበር! ስለዚህ ሕመሙ ሙሉ በሙሉ አቅም ባሳጣት ጊዜ ዕቃና ልብስ ማጠብ እንዲሁም ቀለል ያሉ ምግቦችን ማዘጋጀት መማር ነበረብኝ። በዚያ ሂደት ጥቂት ብርጭቆዎችን ብሰብርም እሷን የሚያስደስቱ ሥራዎችን መሥራቴ ከፍተኛ እርካታ ያስገኝልኝ ነበር። a
ይሖዋ ላሳየኝ ፍቅራዊ ደግነት አመስጋኝ ነኝ
ሕይወቴን መለስ ብዬ ሳስብ፣ የጤና ችግርና የዕድሜ መግፋት ካስከተለብን የአቅም ገደብ ብዙ ትምህርት እንዳገኘሁ ይሰማኛል። አንደኛ፣ በተለያዩ ነገሮች ከመጠመዳችን የተነሳ ለትዳር አጋራችን አድናቆታችንን የምንገልጽበት ጊዜ እንዳናጣ መጠንቀቅ አለብን። ጠንካራና ጤናማ የሆንበትን ጊዜ የምንወዳቸውን ሰዎች ለመንከባከብ ልንጠቀምበት ይገባል። (መክ. 9:9) ሁለተኛ፣ ጥቃቅን ስለሆኑ ነገሮች እያሰብን ከልክ በላይ መጨነቅ የለብንም፤ አለዚያ በእያንዳንዱ ቀን የምናገኛቸውን በረከቶች ማስተዋል ሊያቅተን ይችላል።—ምሳሌ 15:15
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፍነውን ሕይወት መለስ ብዬ ሳስብ ይሖዋ ከጠበቅነው በላይ እንደባረከን አንዳች ጥርጥር የለኝም። ልክ እንደ መዝሙራዊው እኔም “ይሖዋ ደግነት አሳይቶኛል” ብዬ መናገር እችላለሁ።—መዝ. 116:7
a እህት ዳኒዬል ይህ ተሞክሮ በመዘጋጀት ላይ እያለ በ78 ዓመቷ በሞት አንቀላፍታለች።