ይህን ያውቁ ኖሯል?
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ዓመታትና ወራት የሚቆጠሩት እንዴት ነበር?
በተስፋይቱ ምድር ይኖሩ ለነበሩት ዕብራውያን አዲሱ የሥራ ዓመት የሚጀምረው መሬቱ በሚታረስበትና ዘር በሚዘራበት ወቅት ነበር። ይህም ያርፍ የነበረው በአሁኑ መስከረም/ጥቅምት ላይ ነው።
በጨረቃ የቀን አቆጣጠር መሠረት 12 ወራትን (እያንዳንዱ ወር 29 ወይም 30 ቀን አለው) ያቀፈው ዓመት በፀሐይ የቀን አቆጣጠር መሠረት ካለው ዓመት ያጥራል። በወቅቱ የጨረቃ ዓመት ከፀሐይ ዓመት ጋር እንዲጋጠም ለማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀሙ ነበር። ይህን የሚያደርጉት በወራቱ ውስጥ ተጨማሪ ቀናትን በመጨመር ወይም በየተወሰነ ዓመቱ አንድ ተጨማሪ ወር በመጨመር ነው፤ ብዙውን ጊዜ ይህ ወር የሚጨመረው አዲሱ ዓመት ከመጀመሩ በፊት ነው። በዚህ መንገድ የቀን መቁጠሪያውን ሰብል ከሚዘራበት ወይም ከሚሰበሰብበት ወቅት ጋር ማጣጣም ይቻላል።
ሆኖም በሙሴ ዘመን አምላክ ሃይማኖታዊውን የቀን መቁጠሪያ አቋቋመ፤ እንዲሁም በዚህ የቀን መቁጠሪያ መሠረት ዓመቱ መጀመር ያለበት በጸደይ ወቅት በሚገኘው የአቢብ ወይም የኒሳን ወር እንደሆነ ለሕዝቦቹ ገለጸላቸው። (ዘፀ. 12:2፤ 13:4) እስራኤላውያን በዚያ ወር የሚያከብሩት በዓል ከገብስ መከር ጋር የተያያዘ ነበር።—ዘፀ. 23:15, 16
ኤሚል ሹረር የተባሉት ምሁር የአይሁዳውያን ታሪክ በኢየሱስ ክርስቶስ ዘመን (175 ዓ.ዓ.–135 ዓ.ም.) በተባለው መጽሐፋቸው (በአማርኛ አይገኝም) ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ተጨማሪ ወር ይጨመር ወይ የሚለው ጉዳይ የሚወሰንበት መንገድ በጣም ቀላል ነበር። በኒሳን ወር (ኒሳን 14) ሙሉ ጨረቃ በምትታይበት ዕለት የሚከበረው የፋሲካ በዓል ማረፍ ያለበት [በጸደይ ወቅት] የቀኑና የሌሊቱ ርዝመት እኩል የሚሆንበት ዕለት ካለፈ በኋላ ነው። ስለዚህ የፋሲካ በዓል የሚያርፈው ቀኑና ሌሊቱ እኩል ከሚሆንበት ዕለት በፊት እንደሆነ በዓመቱ መጨረሻ አካባቢ ከታወቀ ከኒሳን በፊት [13ኛ] ወር እንደሚጨመር ይታወጃል።”
የይሖዋ ምሥክሮች የጌታ ራት መቼ እንደሚከበር በሚወስኑበት ጊዜ ይህን ደንብ ከግምት ያስገባሉ፤ ይህ በዓል የሚከበረው በጸደይ ወቅት ሲሆን በዕብራውያን የቀን መቁጠሪያ መሠረት ኒሳን 14 ላይ ያርፋል። በመላው ዓለም ያሉ ጉባኤዎች በዓሉ የሚከበርበት ዕለት አስቀድሞ ይነገራቸዋል። a
ይሁንና ዕብራውያን አንድ ወር የሚያልቅበትንና አዲሱ ወር የሚጀምርበትን ጊዜ የሚያውቁት እንዴት ነበር? በዛሬው ጊዜ፣ የታተመ ወይም በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ላይ ያለ የቀን መቁጠሪያ በመመልከት በቀላሉ ማወቅ እንችላለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ግን እንደዚህ ቀላል አልነበረም።
የጥፋት ውኃው በደረሰበት ዘመን እያንዳንዱ ወር 30 ቀን እንዳለው ተደርጎ ይቆጠር ነበር። (ዘፍ. 7:11, 24፤ 8:3, 4) በኋላ ግን በዕብራውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት 30 ቀን የሚኖራቸው ሁሉም ወራት አልነበሩም። በዕብራውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት አንድ ወር የሚጀምረው አዲስ ጨረቃ መታየት በምትጀምርበት ጊዜ ነው። ይህ የሚሆነው ያለፈው ወር ከጀመረ ከ29 ወይም ከ30 ቀን በኋላ ነበር።
በአንድ ወቅት ዳዊትም ሆነ ዮናታን አዲስ ወር ስለሚጀምርበት ጊዜ ሲናገሩ “ነገ አዲስ ጨረቃ የምትወጣበት ቀን ነው” ብለው ነበር። (1 ሳሙ. 20:5, 18) ከዚህ አንጻር በ11ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ወሩ የሚጀምርበት ቀን አስቀድሞ ይሰላ የነበረ ይመስላል። ታዲያ ተራ እስራኤላውያን አዲስ ወር መጀመሩን የሚያውቁት እንዴት ነበር? የአይሁዳውያን የቃል ሕጎችና ወጎች ስብስብ የሆነው ሚሽና ስለዚህ ጉዳይ መረጃ ይሰጠናል። ሚሽና እስራኤላውያን ከግዞት ከተመለሱ በኋላ ባለው ዘመን ይህን የሚወስነው የሳንሄድሪን ሸንጎ (የአይሁዳውያን ከፍተኛ ፍርድ ቤት) እንደነበረ ይጠቁማል። በዓላት በሚከበሩባቸው ሰባት ወራት ላይ ሸንጎው በወሩ 30ኛ ቀን ይሰበሰብ ነበር። የሸንጎው አባላት ቀጣዩ ወር መቼ እንደሚጀምር ይወስኑ ነበር። ይህን የሚያደርጉት ምንን መሠረት አድርገው ነው?
ጠባቂዎች በኢየሩሳሌም ዙሪያ በሚገኙ ከፍ ያሉ ቦታዎች ላይ ሆነው አዲሷ ጨረቃ መውጣቷን ይከታተላሉ። ከዚያም ቶሎ ብለው ጉዳዩን ለሳንሄድሪን ሸንጎ ያሳውቃሉ። የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት አዲሷ ጨረቃ መታየቷን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ እንዳገኙ ሲሰማቸው አዲስ ወር መጀመሩን ያሳውቃሉ። ይሁንና በደመና ወይም በጉም ምክንያት ጠባቂዎቹ አዲሷን ጨረቃ ማየት ቢያቅታቸውስ? እንደዚያ ከሆነ አሁን ያሉበት ወር 30 ቀን እንዳለው ተደርጎ ይቆጠራል። ከዚያም በማግስቱ አዲሱ ወር ይጀምራል።
ሚሽና እንደሚገልጸው አዲሱ ወር መጀመሩን ለማሳወቅ በኢየሩሳሌም አቅራቢያ በሚገኘው የደብረ ዘይት ተራራ ላይ እሳት እንዲቀጣጠል ይደረግ ነበር። በሌሎች የእስራኤል ክፍሎችም ከፍ ባሉ ቦታዎች ላይ እሳት በማንደድ መረጃው እንዲዳረስ ይደረጋል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ መረጃውን ለማሰራጨት መልእክተኞችን መጠቀም ጀመሩ። በኢየሩሳሌም፣ በመላው እስራኤል እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው የሚኖሩ አይሁዳውያን በዚህ መንገድ አዲስ ወር መጀመሩን ያውቃሉ። በመሆኑም ሁሉም በዓላቱን በተመሳሳይ ጊዜ ማክበር ይችላሉ።
በዕብራውያን የቀን መቁጠሪያ ላይ ስላሉት ወሮች፣ በዓላትና ወቅቶች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ሰንጠረዡን መመልከት ትችላለህ።
a የየካቲት 15, 1990 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 15ን እና በሰኔ 15, 1977 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።