የአንባቢያን ጥያቄዎች
ሁለተኛ ሳሙኤል 21:7-9 ዳዊት “ለሜፊቦስቴ ራራለት” ካለ በኋላ እንዲገደል አሳልፎ እንደሰጠው የሚናገረው ለምንድን ነው?
ይህን ዘገባ እንዲሁ ላይ ላዩን የሚያነብቡ አንዳንዶች እንዲህ ያለ ጥያቄ ያነሳሉ። ሆኖም እዚህ ዘገባ ላይ ሜፊቦስቴ የተባሉት ሁለት የተለያዩ ሰዎች ናቸው፤ ዘገባውን በመመርመርም የምናገኘው ትምህርት አለ።
የእስራኤል ንጉሥ የሆነው ሳኦል ሰባት ወንዶች ልጆችና ሁለት ሴቶች ልጆች ነበሩት። የበኩር ልጁ ዮናታን ነው። ከጊዜ በኋላ ሳኦል፣ ሪጽፋ ከተባለች ቁባቱ ሜፊቦስቴ የተባለ ወንድ ልጅ ወለደ። የሚገርመው ዮናታንም ሜፊቦስቴ የተባለ ልጅ ነበረው። በመሆኑም የንጉሥ ሳኦል ልጅም ሆነ የልጅ ልጅ ሜፊቦስቴ የተባለ ስም ነበራቸው።
በአንድ ወቅት ንጉሥ ሳኦል በእስራኤላውያን መካከል በሚኖሩት ገባኦናውያን ላይ በመነሳት ሊያጠፋቸው ሞክሮ ነበር። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው የተወሰኑ ገባኦናውያን ተገድለዋል። ይህ በጣም የተሳሳተ እርምጃ ነበር። ለምን? ምክንያቱም በኢያሱ ዘመን የእስራኤል አለቆች ከገባኦናውያን ጋር የሰላም ቃል ኪዳን ተጋብተው ነበር።—ኢያሱ 9:3-27
ይህ ቃል ኪዳን በንጉሥ ሳኦል ዘመንም ይሠራ ነበር። ንጉሡ ግን ቃል ኪዳኑን በማፍረስ ገባኦናውያንን ሊያጠፋቸው ሞከረ። ይህም ‘በሳኦልና በቤቱ ላይ የደም ዕዳ’ አመጣ። (2 ሳሙ. 21:1) በኋላ ላይ ዳዊት ንጉሥ ሆነ። በሕይወት የተረፉት ገባኦናውያን ስለተፈጸመባቸው ከባድ በደል ለዳዊት ነገሩት። ዳዊትም ሳኦል ለፈጸመባቸው በደል ማስተሰረይ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ይሖዋ ምድሪቱን እንዲባርክ ምን ቢያደርግላቸው የተሻለ እንደሚሆን ጠየቃቸው። ገባኦናውያኑ ገንዘብ አልጠየቁም፤ ከዚህ ይልቅ ‘እንዲደመሰሱ ሴራ የጠነሰሰባቸው ሰው’ ሰባት ወንዶች ልጆች በእጃቸው እንዲሰጧቸው ጠየቁ። (ዘኁ. 35:30, 31) ዳዊትም ያሉትን አደረገላቸው።—2 ሳሙ. 21:2-6
ይህ በሆነበት ወቅት ሳኦልና ዮናታን ጦር ሜዳ ላይ ተገድለው ነበር፤ የዮናታን ልጅ ሜፊቦስቴ ግን በሕይወት ነበር። ሜፊቦስቴ ገና በልጅነቱ በደረሰበት አደጋ ሽባ ሆነ፤ በገባኦናውያን ላይ በተሰነዘረው ጥቃት ውስጥም እጁ የለበትም። ዳዊትና ዮናታን ቃል ኪዳን ተጋብተው ነበር፤ ይህ ቃል ኪዳን ሜፊቦስቴን ጨምሮ የዮናታንን ዘሮችም ያካትት ነበር። (1 ሳሙ. 18:1፤ 20:42) ታሪኩ እንዲህ ይላል፦ “ንጉሡ [ዳዊት] እሱና የሳኦል ልጅ ዮናታን በይሖዋ ፊት በተማማሉት መሐላ የተነሳ የሳኦል ልጅ ለሆነው ለዮናታን ልጅ ለሜፊቦስቴ ራራለት።”—2 ሳሙ. 21:7
እንደዚያም ሆኖ ዳዊት ገባኦናውያን የጠየቁትን አድርጎላቸዋል። ከሳኦል ወንዶች ልጆች መካከል ሁለቱን (አንደኛው ሜፊቦስቴ ተብሎ ይጠራል) እንዲሁም ከልጅ ልጆቹ መካከል አምስቱን አሳልፎ ሰጣቸው። (2 ሳሙ. 21:8, 9) ዳዊት የወሰደው እርምጃ ምድሪቱ ከደም ዕዳ ነፃ እንድትሆን አድርጓል።
ይህ ዘገባ ከታሪክነት ባለፈ የያዘው ቁም ነገር አለ። የአምላክ ሕግ “[ልጆች] አባቶቻቸው በሠሩት ነገር መገደል የለባቸውም” በማለት በግልጽ ይናገራል። (ዘዳ. 24:16) ሁለቱ የሳኦል ልጆችና አምስቱ የልጅ ልጆቹ እጃቸው ንጹሕ ቢሆን ኖሮ ይሖዋ እንዲገደሉ አይፈቅድም ነበር። ሕጉ “አንድ ሰው መገደል ያለበት በገዛ ኃጢአቱ ብቻ ነው” በማለትም ይናገራል። የተገደሉት ሰባቱ የሳኦል ዘሮች ሳኦል በገባኦናውያን ላይ በቃጣው የዘር ማጥፋት ዘመቻ እጃቸው የነበረበት ይመስላል። በመሆኑም ሰባቱ ላይ የደረሰው ነገር የሥራቸው ውጤት ነው።
ይህ ታሪክ እንደሚያስተምረን፣ አንድ ሰው መጥፎ ነገር ካደረገ በኋላ ‘የታዘዝኩትን ነው ያደረግኩት’ ብሎ ሰበብ ሊያቀርብ አይችልም። ለድርጊቱ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት። በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የሚገኝ አንድ ጥበብ ያዘለ ሐሳብ እንዲህ ይላል፦ “የእግርህን መንገድ ደልዳላ አድርግ፤ መንገድህም ሁሉ አስተማማኝ ይሆናል።”—ምሳሌ 4:24-27፤ ኤፌ. 5:15