የሕይወት ታሪክ
ይሖዋ ፈጽሞ አልተወኝም!
አዶልፍ ሂትለር በአንድ ወቅት ንግግር ካቀረበ በኋላ አበባ ካበረከቱለት አራት ትናንሽ ልጆች አንዷ እኔ ነበርኩ። እኔ የተመረጥኩት ለምንድን ነው? አባቴ በናዚ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበረው ሲሆን በአካባቢያችን ያለው የናዚ ፓርቲ ቅርንጫፍ መሪ ለሆነው ሰው በሾፌርነት ይሠራ ነበር። እናቴ ደግሞ አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ስትሆን እኔም እንድመነኩስ ትፈልግ ነበር። አባቴም ሆነ እናቴ ከፍተኛ ተጽዕኖ ቢያሳድሩብኝም የናዚ ደጋፊም ሆነ መነኩሲት አልሆንኩም። ምክንያቱን እስቲ ልንገራችሁ።
ያደግሁት በግራትስ፣ ኦስትሪያ ነው። ሰባት ዓመት ሲሆነኝ ሃይማኖታዊ ትምህርት ወደሚሰጥበት ትምህርት ቤት ተላክሁ። ይሁን እንጂ ቀሳውስቱና ሴቶቹ መነኮሳት የፆታ ብልግና እንደሚፈጽሙ ሳውቅ በጣም ደነገጥኩ። በመሆኑም ከአንድ ዓመት በኋላ እናቴ ከዚህ ትምህርት ቤት እንድወጣ ፈቀደችልኝ።
ከዚያ በኋላ አዳሪ ትምህርት ቤት ገባሁ። አንድ ምሽት፣ ግራትስ በቦምብ እየተደበደበች ስለነበር አባቴ መጥቶ ወሰደኝ። ከቦምብ ድብደባው ለማምለጥ ወደ ሽላድሚንግ ከተማ ሸሸን። ወደ ከተማው ደርሰን አንድ ድልድይ እንደተሻገርን ድልድዩ በቦምብ ተመታ። በሌላ ጊዜ ደግሞ ከሴት አያቴ ጋር ግቢያችን ውስጥ እያለን ዝቅ ብለው የሚበሩ አውሮፕላኖች ተኮሱብን። ጦርነቱ ሲያበቃ፣ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በመንግሥት ላይ እምነት መጣል እንደማንችል ተሰምቶን ነበር።
አስተማማኝ ድጋፍ የሚሰጥ አካል እንዳለ ተማርኩ
በ1950 አንዲት የይሖዋ ምሥክር ለእናቴ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ማካፈል ጀመረች። እኔም ውይይታቸውን እሰማ የነበረ ሲሆን እናቴ ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ስትሄድ አንዳንድ ጊዜ አብሬያት እሄድ ነበር። እናቴ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሩት ነገር እውነት እንደሆነ ስላመነች በ1952 ተጠመቀች።
በዚያን ጊዜ በአካባቢያችን ያለው ጉባኤ የአሮጊቶች ክበብ መስሎ ይታየኝ ነበር። በአንድ ወቅት ግን የሌላ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኘን፤ በዚያ ጉባኤ ውስጥ ብዙ ወጣቶች ስለነበሩ የአሮጊቶች ክበብ እንደሆነ አልተሰማኝም። ወደ ግራትስ ከተመለስን በኋላ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመርኩ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ የምማረው ነገር እውነት እንደሆነ ተገነዘብኩ። በተጨማሪም ይሖዋ ለአገልጋዮቹ አስተማማኝ ድጋፍ የሚሰጥ አምላክ መሆኑን አወቅኩ። ልንቋቋማቸው የማንችላቸው ሁኔታዎች እንዳጋጠሙንና ማንም ከጎናችን እንደሌለ በሚሰማን ጊዜም ጭምር የይሖዋ ድጋፍ አይለየንም።—መዝ. 3:5, 6
እውነትን ለሌሎች የማካፈል ፍላጎት አደረብኝ። እውነትን መጀመሪያ የተናገርኩት ለወንድሜና ለእህቶቼ ነበር። በወቅቱ አራቱ ታላላቅ እህቶቼ ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው በመምህርነት እየሠሩ ነበር። ስለዚህ ወደሚኖሩባቸው
መንደሮች እየሄድኩ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ አበረታታኋቸው። ውሎ አድሮ ወንድሜና ሁሉም እህቶቼ መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።ከቤት ወደ ቤት አገልግሎት ማገልገል በጀመርኩ በሁለተኛው ሳምንት ላይ በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ሴት አገኘሁና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀመርኳት። ይህች ሴት እድገት አድርጋ የተጠመቀች ሲሆን ከጊዜ በኋላ ደግሞ ባሏና ሁለት ወንዶች ልጆቿም ተጠመቁ። ሴትየዋን ማስጠናቴ የእኔንም እምነት በእጅጉ አጠናክሮታል። እንዲህ ያልኩት ለምንድን ነው? እኔን መደበኛ በሆነ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናኝ ሰው ስላልነበረ ነው። በመሆኑም እሷን ከማስጠናቴ በፊት እያንዳንዱን ትምህርት አስቀድሜ በሚገባ መዘጋጀት ነበረብኝ። ይህን የማደርገው በመጀመሪያ ራሴን ከዚያም ጥናቴን ለማስተማር ነበር ማለት ይቻላል! ይህም እውነት በደንብ እንዲገባኝ ረድቶኛል። ሚያዝያ 1954 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ።
“ስደት ቢደርስብንም አልተተውንም”
በ1955 በጀርመን፣ በፈረንሳይና በእንግሊዝ የተደረጉ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎችን ተካፈልኩ። ለንደን እያለሁ ከወንድም አልበርት ሽሮደር ጋር ተገናኘሁ። ወንድም ሽሮደር በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት አስተማሪ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ደግሞ የበላይ አካል አባል ሆኖ አገልግሏል። ብሪትሽ ሙዚየምን ስንጎበኝ ወንድም ሽሮደር በእጅ የተገለበጡ አንዳንድ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎችን አሳየን። እነዚህ ቅጂዎች የአምላክ ስም የሚጻፍባቸውን የዕብራይስጥ ፊደላት ይዘዋል፤ ወንድም ሽሮደር እነዚህ ጥንታዊ ቅጂዎች ምን ያህል ጥቅም እንዳላቸው አስረዳን። ይህን ማወቄ ለይሖዋና ለእውነት ያለኝ ፍቅር እንዲጨምር ያደረገ ሲሆን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ለመስበክ ይበልጥ አነሳሳኝ።
ጥር 1, 1956 አቅኚ ሆኜ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ። ከአራት ወር በኋላ ደግሞ ኦስትሪያ ውስጥ በልዩ አቅኚነት እንዳገለግል ተጋበዝኩ። በተመደብኩባት በሚስትልባኽ ከተማ በወቅቱ አንድም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም። ይሁን እንጂ ሌላ ተፈታታኝ ሁኔታም አጋጥሞኝ ነበር። እኔና በልዩ አቅኚነት አብራኝ የምታገለግለው እህት በጣም የተለያየን ሰዎች ነበርን። እኔ 19 ዓመት እንኳ አልሞላኝም ነበር፤ እሷ ደግሞ 25 ዓመቷ ነበር፤ እኔ የከተማ ልጅ ስሆን እሷ ደግሞ የገጠር ልጅ ነበረች። እኔ የምፈልገው ጠዋት ላይ ረፈድ አድርጌ መነሳት ነው፤ እሷ ግን የምትነሳው ማለዳ ነው። ማታ ላይ እኔ አምሽቼ መተኛት ይቀናኛል፤ እሷ ደግሞ በጊዜ መተኛት ትፈልጋለች። ያም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ልዩነቶቻችንን የፈታን ሲሆን ጥሩ ጓደኛሞች ሆነን በአቅኚነት ማገልገል ችለናል።
እንደ እውነቱ ከሆነ ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችም ገጥመውናል። በተወሰነ መጠን ስደትም ደርሶብን ነበር፤ ሆኖም “አልተተውንም።” (2 ቆሮ. 4:7-9) በአንድ ወቅት በአንዲት የገጠር መንደር እየሰበክን ሳለ ሰዎቹ ውሾቻቸውን ፈትተው ለቀቁብን። ትላልቅ ውሾች በኃይል እየጮኹ እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬን ከበቡን። ከጓደኛዬ ጋር እጅ ለእጅ ከተያያዝን በኋላ “ይሖዋ እባክህ ሳንሠቃይ ቶሎ እንድንሞት እርዳን!” ብዬ ጸለይኩ። ውሾቹ አጠገባችን ሲደርሱ ግን ጅራታቸውን እያወዛወዙ ቆሙ፤ ከዚያም ተመልሰው ሄዱ። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ጥበቃ እንዳደረገልን ተሰማን። ከዚያ በኋላ በመንደሩ በሙሉ የሰበክን ሲሆን ደስ የሚለው ነገር ሰዎቹ መልእክታችንን ተቀበሉ። ምናልባት ውሾቹ በእኛ ላይ ጉዳት አለማድረሳቸው ወይም እንዲህ የመሰለ አስፈሪ ሁኔታ ካጋጠመን በኋላም በጽናት መቀጠላችን አስገርሟቸው ሊሆን ይችላል። አንዳንዶቹ ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።
ሌላም አስደንጋጭ ሁኔታ አጋጥሞን ነበር። አንድ ቀን ቤት አከራያችን ሰክሮ መጣና አካባቢውን እየበጠበጥን
እንደሆነ በመናገር እንደሚገድለን ይዝት ጀመር። ሚስቱ ልታረጋጋው ብትሞክርም አልተሳካላትም። እኛም ፎቅ ላይ ባለው ክፍላችን ሆነን ሁሉን ነገር እንሰማ ስለነበር በራችን እንዳይከፈት ወንበር ካስደገፍንበት በኋላ ጓዛችንን መሸከፍ ጀመርን። በሩን ስንከፍት አከራያችን ትልቅ ቢላዋ ይዞ ደረጃው ላይ ቆሟል። ስለዚህ በጓሮው በር በኩል ወጣንና ንብረቶቻችንን ሁሉ ይዘን የአትክልት ቦታውን በማቋረጥ ሸሸን፤ ዳግም ወደዚያ ቤት አልተመለስንም።ከዚያም ወደ አንድ ሆቴል ሄድንና ክፍል ያዝን። በዚያ ሆቴል አንድ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ተቀምጠናል፤ ይህም ለአገልግሎታችን ጠቅሞናል። እንዴት? ሆቴሉ የሚገኘው መሃል ከተማ ሲሆን አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን እዚያ ማጥናት ይፈልጉ ነበር። ብዙም ሳይቆይ በሆቴል ክፍላችን ውስጥ የመጽሐፍ ጥናትና ሳምንታዊውን የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ማድረግ ጀመርን፤ በስብሰባዎቹ ላይ 15 የሚያህሉ ተሰብሳቢዎች ይገኙ ነበር።
በሚስትልባኽ ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ቆይተናል። ከዚያም ከግራትስ በስተ ደቡብ ምሥራቅ በምትገኘው በፌልትባኽ ተመደብኩ። እዚያም አብራኝ የምታገለግል ሌላ ልዩ አቅኚ ብትኖርም ከተማዋ ውስጥ ጉባኤ አልነበረም። የምንኖረው በእንጨት በተሠራ ቤት ሁለተኛ ፎቅ ላይ በምትገኝ ትንሽ ክፍል ውስጥ ነበር። በጣውላዎቹ መካከል ባሉት ክፍተቶች ነፋስ ስለሚገባ ቀዳዳዎቹን በጋዜጣ መድፈን ነበረብን። ውኃ የምንቀዳው ደግሞ ከጉድጓድ ነበር። ሆኖም የምንከፍለው መሥዋዕት የሚያስቆጭ አልነበረም። በጥቂት ወራት ውስጥ አንድ ቡድን ተቋቋመ። እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናነው አንድ ቤተሰብ 30 የሚያህሉ አባላት ውሎ አድሮ ወደ እውነት መጥተዋል!
እንደነዚህ ያሉት ተሞክሮዎች ይሖዋ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለሚያስቀድሙ ሰዎች የሚያደርገውን የማያቋርጥ ድጋፍ ይበልጥ እንዳደንቅ አድርገውኛል። የሰው እርዳታ ማግኘት በማንችልበት ቦታ ብንሆንም እንኳ የይሖዋ ድጋፍ ምንጊዜም አይለየንም።—መዝ. 121:1-3
የአምላክ ‘የጽድቅ ቀኝ እጅ’ ደግፎናል
በ1958 በኒው ዮርክ ሲቲ በያንኪ ስታዲየምና በፖሎ ግራውንድስ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ሊደረግ ፕሮግራም ወጥቶ ነበር። እኔም በስብሰባው ላይ ለመገኘት ሳመለክት የኦስትሪያ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ በጊልያድ ትምህርት ቤት በ32ኛው ክፍል መማር እፈልግ እንደሆነ ጠየቀኝ። እንዲህ የመሰለውን መብት እንዴት እምቢ እላለሁ? ወዲያውኑ “እንዴታ!” ብዬ መልስ ሰጠሁ።
በጊልያድ ስማር ክፍል ውስጥ የምቀመጠው ከወንድም ማርቲን ፖትጺንገር አጠገብ ነበር። ወንድም ፖትጺንገር በናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የደረሰበትን አሰቃቂ
መከራ በጽናት የተቋቋመ ክርስቲያን ነው። እሱም ከጊዜ በኋላ የበላይ አካል አባል ሆኖ አገልግሏል። ክፍል ውስጥ ስንማር፣ ማርቲን አንዳንድ ጊዜ “ኤሪካ፣ ይህ በጀርመንኛ ምን ማለት ነው?” ብሎ በሹክሹክታ ይጠይቀኝ ነበር።በጊልያድ የሚኖረንን ቆይታ ስናጋምስ ወንድም ናታን ኖር ምድባችንን አሳወቀን። እኔ የተመደብኩት ፓራጓይ ነበር። ሆኖም በዕድሜዬ ምክንያት፣ ወደ ፓራጓይ ለመግባት ከአባቴ ፈቃድ ማግኘት ያስፈልገኝ ነበር። ፈቃዱን ካገኘሁ በኋላ መጋቢት 1959 ፓራጓይ መግባት ቻልኩ። አሱንሲዮን ከተማ ውስጥ በሚገኝ የሚስዮናውያን ቤት እየኖርኩ ከአንዲት ሚስዮናዊት ጋር እንዳገለግል ተመደብኩ።
ብዙም ሳይቆይ፣ ከጊልያድ ትምህርት ቤት 30ኛው ክፍል ከተመረቀ ዎልተር ብራይት የተባለ ሚስዮናዊ ጋር ተዋወቅሁ። ከጊዜ በኋላ ከዎልተር ጋር ተጋባንና የሕይወትን ውጣ ውረድ አብረን መጋፈጥ ጀመርን። አንድ ተፈታታኝ ችግር ሲያጋጥመን ይሖዋ በኢሳይያስ 41:10 ላይ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ። እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ” በማለት የገባውን ቃል እናነባለን። ይህ ጥቅስ ለአምላክ ታማኝ ሆነን ለመኖርና መንግሥቱን ለማስቀደም እስከጣርን ድረስ እሱ ፈጽሞ እንደማይተወን ማረጋገጫ ሆኖናል።
ከጊዜ በኋላ በብራዚል ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ አካባቢ እንድናገለግል ተመደብን። በዚያ ያሉት ቀሳውስት ወጣቶችን በማነሳሳት ቀድሞውንም ይዞታው ጥሩ ባልነበረው የሚስዮናውያን ቤታችን ላይ ድንጋይ እንዲወረውሩብን አደረጉ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዎልተር የፖሊስ አዛዡን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመረ። የፖሊስ አዛዡም ለአንድ ሳምንት ያህል ፖሊሶች ቤታችን አቅራቢያ እንዲቆሙ አደረገ፤ ተቃዋሚዎቻችን ከዚያ በኋላ አልረበሹንም። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የብራዚልን ድንበር ተሻግሮ በሚገኝ ተስማሚ ቤት መኖር ጀመርን። ይህም በፓራጓይም ሆነ በብራዚል ስብሰባዎችን ለማድረግ ስላስቻለን ጠቅሞናል። ያንን ምድብ ከመልቀቃችን በፊት በአካባቢው ሁለት ትናንሽ ጉባኤዎች ተመሥርተው ነበር።
የይሖዋ ድጋፍ አልተለየኝም
ሐኪሞች ልጅ መውለድ እንደማልችል ነግረውኝ ስለነበር በ1962 እንዳረገዝኩ ስናውቅ በጣም ተገረምን! ከጊዜ በኋላም በሆሊውድ ፍሎሪዳ በዎልተር ቤተሰቦች አቅራቢያ መኖር ጀመርን። ከዚያ በኋላ ላሉት በርካታ ዓመታት እኔና ዎልተር ቤተሰባችንን መንከባከብ ስለነበረብን በአቅኚነት ማገልገል አልቻልንም። ያም ሆኖ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ምንጊዜም ቅድሚያ እንሰጥ ነበር።—ማቴ. 6:33
ወደ ፍሎሪዳ የሄድነው ኅዳር 1962 ነው፤ በዚያም የአካባቢው ሰዎች ነጮችና ጥቁሮች እንዲቀላቀሉ ስለማይፈልጉ ጥቁር ወንድሞች ከነጭ ወንድሞች ጋር እንደማይሰበሰቡና የሚሰብኩባቸውም አካባቢዎች የተለያዩ እንደሆኑ መመልከታችን በጣም አስገረመን። ይሁንና ይሖዋ የተለያየ ዘር ባላቸው ሰዎች መካከል ልዩነት እንዲኖር አይፈልግም፤ በመሆኑም ብዙም ሳይቆይ በጉባኤዎቻችን ውስጥ ጥቁሮችም ሆኑ ነጮች አንድ ላይ ተቀላቅለው መሰብሰብ ጀመሩ። በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው ብዙ ጉባኤዎች የሚገኙ መሆኑ በዚህ አሠራር ላይ የይሖዋ እጅ እንዳለበት በግልጽ ያሳያል።
የሚያሳዝነው፣ ዎልተር በ2015 በካንሰር ምክንያት ሕይወቱ አለፈ። ከዎልተር ጋር በትዳር 55 ዓመታት አሳልፈናል፤ ይሖዋን የሚወድና ብዙ ወንድሞችን የረዳ ግሩም ባል ነበር። በትንሣኤ ሙሉ ጤንነቱ ተመልሶለት እንደገና ላየው እናፍቃለሁ።—ሥራ 24:15
ከ40 የሚበልጡ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ማሳለፍ በመቻሌ በጣም አመስጋኝ ነኝ፤ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ይህ ነው የማይባል ደስታና በረከት አስገኝቶልኛል። ለምሳሌ ያህል፣ እኔና ዎልተር መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናናቸው ሰዎች መካከል 136ቱ ሲጠመቁ ማየት ችለናል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ችግሮችም ገጥመውናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ችግሮች ታማኙን አምላካችንን ማገልገላችንን ለማቆም ምክንያት እንዲሆኑ አልፈቀድንላቸውም። ይሖዋ ችግሮቻችንን በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ እንደሚፈታቸው በመተማመን ወደ እሱ ይበልጥ ቀርበናል። እሱም አላሳፈረንም!—2 ጢሞ. 4:16, 17
ዎልተር በጣም ይናፍቀኛል፤ ናፍቆቱን ለመቋቋም የሚረዳኝ በአቅኚነት ማገልገሌ ነው። በተለይ ደግሞ ሌሎችን ማስተማሬና ስለ ትንሣኤ ተስፋ መናገሬ በጣም ጠቅሞኛል። በእርግጥም ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይተወኝ የተመለከትኩባቸውን መንገዶች ዘርዝሬ መጨረስ አልችልም። ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት ደግፎኛል፤ አበርትቶኛል፤ እንዲሁም ‘በጽድቅ ቀኝ እጁ’ አጥብቆ ይዞኛል።—ኢሳ. 41:10