ወላጆች፣ ልጆቻችሁን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ እየረዳችኋቸው ነው?
“ታዲያ አሁን ምን ትጠብቃለህ? ተነስና ተጠመቅ።”—ሥራ 22:16
1. ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው ከመጠመቃቸው በፊት ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን ይፈልጋሉ?
“አባባንና እማማን ካልተጠመቅሁ እያልኩ ለብዙ ወራት እጨቀጭቃቸው ነበር። እነሱም ብዙ ጊዜ ስለ ጥምቀት ይነግሩኝ ነበር። ውሳኔዬ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንዳውቅ ፈልገው ነበር። ታኅሣሥ 31, 1934 በሕይወቴ ውስጥ ይህን ልዩ እርምጃ የምወስድበት ቀን ደረሰ።” ብሎሰም ብራንት ይህን ሐሳብ የተናገረችው ከመጠመቋ በፊት ስለነበረው ሁኔታ ስትገልጽ ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ወላጆችም ልጆቻቸው ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ እንዲያደርጉ ሊረዷቸው ይፈልጋሉ። ልጆች ለመጠመቅ በሚጠይቁበት ጊዜ ያለበቂ ምክንያት እንዲቆዩ ማድረግ የልጆቹን መንፈሳዊነት ሊጎዳ ይችላል። (ያዕ. 4:17) ያም ሆኖ ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ከመጠመቃቸው በፊት፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመሸከም ዝግጁ እንደሆኑ ማረጋገጥም ይፈልጋሉ።
2. (ሀ) አንዳንድ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የትኛው ሁኔታ አሳስቧቸዋል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
2 አንዳንድ የወረዳ የበላይ ተመልካቶች፣ በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ወይም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ከሚገኙ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ጋር በተያያዘ ያሳሰባቸው ነገር እንዳለ ሲናገሩ ይሰማል፤ እነዚህ ወጣቶች በእውነት
ቤት ውስጥ ያደጉ ቢሆኑም ገና አልተጠመቁም። አብዛኞቹ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሲሆን በአገልግሎትም ይካፈላሉ። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክር እንደሆኑ አድርገው ራሳቸውን ይቆጥራሉ። ይሁን እንጂ ሕይወታቸውን ለይሖዋ ከመወሰንና ከመጠመቅ ወደኋላ ይላሉ። እንዲህ የሚያደርጉት ለምን ሊሆን ይችላል? አንዳንድ ጊዜ፣ ሳይጠመቁ እንዲቆዩ የሚመክሯቸው ወላጆቻቸው ናቸው። እነዚህ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲጠመቁ ከማበረታታት ወደኋላ የሚሉት አንዳንድ የሚያሳስቧቸው ነገሮች ስላሉ ነው፤ በዚህ ርዕስ ውስጥ ከእነዚህ መካከል አራቱን እንመለከታለን።ልጄ ለመጠመቅ ዕድሜው ደርሷል?
3. የብሎሰም ወላጆች ያሳሰባቸው ነገር ምን ነበር?
3 በአንቀጽ አንድ ላይ የተጠቀሰችው የብሎሰም ወላጆች፣ ‘ልጃችን ጥምቀት ያለውን ትርጉም እንዲሁም በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ጉዳይ መሆኑን መረዳት የምትችልበት ዕድሜ ላይ ደርሳለች?’ የሚለው ጥያቄ አሳስቧቸው ነበር። ለመሆኑ ወላጆች፣ ልጃቸው ተቀባይነት ባለው መንገድ ራሱን ለመወሰን ዝግጁ እንደሆነ ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነው?
4. ወላጆች ልጆቻቸውን በሚያስተምሩበት ጊዜ ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ስለሰጠው ትእዛዝ ቆም ብለው ማሰባቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?
4 ማቴዎስ 28:19, 20ን አንብብ። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው በስንት ዓመቱ መጠመቅ እንዳለበት የሚገልጽ መመሪያ አይሰጥም። ይሁንና ወላጆች ደቀ መዝሙር ማድረግ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ቆም ብለው ማሰባቸው ጠቃሚ ነው። በማቴዎስ 28:19 ላይ “ደቀ መዛሙርት አድርጉ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል፣ ሰዎችን ተከታይ ወይም ደቀ መዝሙር የማድረግ ግብ ይዞ ማስተማር የሚል መልእክት ያስተላልፋል። ደቀ መዝሙር የሚባለው፣ ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች የተማረና በሚገባ የተረዳ እንዲሁም ያወቀውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥር ሰው ነው። በመሆኑም ሁሉም ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻቸውን ከሕፃንነታቸው አንስቶ በማስተማር የተጠመቁ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ የመርዳት ግብ ሊኖራቸው ይገባል። እርግጥ ነው፣ ሕፃናት ለመጠመቅ ብቁ አይሆኑም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው ትናንሽ ልጆችም እንኳ የቅዱሳን መጻሕፍትን እውነት መረዳትና ለተማሩት ነገር አድናቆት ማዳበር ይችላሉ።
5, 6. (ሀ) ስለ ጢሞቴዎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናገኘው ሐሳብ የተጠመቀበትን ጊዜ በተመለከተ ምን ይጠቁመናል? (ለ) አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?
5 ጢሞቴዎስ፣ ገና በልጅነቱ እውነትን የራሱ ያደረገ ደቀ መዝሙር ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ የቅዱሳን መጻሕፍትን እውነት የተማረው ከጨቅላነቱ ጀምሮ እንደሆነ ተናግሯል። ጢሞቴዎስ ያደገው በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ቢሆንም አይሁዳውያን የሆኑት እናቱና አያቱ ለቅዱሳን መጻሕፍት ፍቅር እንዲያዳብር ረድተውታል። በዚህም ምክንያት ጠንካራ እምነት አዳብሯል። (2 ጢሞ. 1:5፤ 3:14, 15) ጢሞቴዎስ በአሥራዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ወይም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ አካባቢ እያለ፣ በጉባኤ ውስጥ ልዩ የአገልግሎት መብቶችን ለመቀበል የሚያስፈልገውን ብቃት አሟልቶ ነበር።—ሥራ 16:1-3
6 በእርግጥ ሁሉም ልጆች የተለያዩ እንደሆኑ ማስታወስ ያስፈልጋል፤ እድገት የሚያደርጉበት ፍጥነት ተመሳሳይ አይደለም። አንዳንዶች በትንሽነታቸው አእምሯዊና ስሜታዊ ብስለት ያዳብራሉ፤ በመሆኑም ገና ልጆች እያሉ መጠመቅ እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ። ሌሎች ደግሞ ለመጠመቅ ዝግጁ የሚሆኑት ከፍ ካሉ በኋላ ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንጻር፣ አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው እንዲጠመቁ ጫና አያደርጉም። ይልቁንም እያንዳንዱን ልጅ በራሱ ፍጥነት መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ ይረዱታል። ወላጆች ልጆቻቸው ጥበብ የሚንጸባረቅበት እርምጃ ሲወስዱ ይደሰታሉ። (ምሳሌ 27:11ን አንብብ።) ያም ቢሆን ግባቸው፣ ልጆቻቸው የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት መሆኑን ሊዘነጉ አይገባም። ስለሆነም ወላጆች ‘ልጄ ራሱን ለአምላክ ለመወሰንና ለመጠመቅ የሚያስችል በቂ እውቀት አለው?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቃቸው አስፈላጊ ነው።
ልጄ በቂ እውቀት አለው?
7. አንድ ሰው ከመጠመቁ በፊት ሁሉንም ነገር ማወቅ አለበት? አብራራ።
7 ወላጆች ልጆቻቸውን በሚያስተምሩበት ጊዜ ልጆቹ እውነትን በሚገባ እንዲያውቁ ሊረዷቸው ይገባል፤ እንዲህ ያለው እውቀት ልጆቹ ራሳቸውን ለአምላክ እንዲወስኑ ያነሳሳቸዋል። ይህ ሲባል ግን አንድ ልጅ ራሱን ለአምላክ ወስኖ ከመጠመቁ በፊት ሁሉንም ነገር ማወቅ አለበት ማለት አይደለም። ሁሉም ደቀ መዛሙርት፣ ከተጠመቁ በኋላም ቢሆን ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደጉ መሄድ ይኖርባቸዋል። (ቆላስይስ 1:9, 10ን አንብብ።) ታዲያ ልጆች ከመጠመቃቸው በፊት ምን ያህል እውቀት ሊኖራቸው ይገባል?
8, 9. ስለ ጳውሎስና ስለ እስር ቤቱ ጠባቂ ከሚገልጸው ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?
8 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የሚኖር አንድ ቤተሰብ የወሰደው እርምጃ ለወላጆች ጥሩ ትምህርት ይዟል። (ሥራ 16:25-33) ጳውሎስ በ50 ዓ.ም. ገደማ በሁለተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ላይ ፊልጵስዩስን ጎብኝቶ ነበር። በዚያ ሳለም እሱና ጓደኛው ሲላስ በሐሰት ተከስሰው ወደ ወህኒ ተጣሉ። ሌሊት ላይ ከባድ የምድር ነውጥ በመከሰቱ የእስር ቤቱ መሠረት ተናጋ፤ በተጨማሪም በሮቹ በሙሉ ተከፈቱ። የእስር ቤቱ ጠባቂ፣ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ለመግደል ሰይፉን መዘዘ፤ በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ድምፁን ከፍ አድርጎ በመጣራት አስቆመው። ከዚያም ጳውሎስና ሲላስ ለጠባቂውና ለቤተሰቡ መሠከሩላቸው። ታዲያ ይህ ቤተሰብ፣ ስለ ኢየሱስ የተማረው እውነት ምን እንዲያደርግ አነሳሳው? ጠባቂውና ቤተሰቡ ወዲያውኑ ተጠመቁ። ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት እናገኛለን?
9 የእስር ቤቱ ጠባቂ ጡረታ የወጣ የሮም ወታደር ሳይሆን አይቀርም። ይህ ሰው የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት አልነበረውም። ስለዚህ ክርስቲያን ለመሆን፣ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን መማርና አምላክ ከአገልጋዮቹ ምን እንደሚጠብቅ መረዳት እንዲሁም የኢየሱስን ትምህርት ለመታዘዝ ፈቃደኛ መሆን ነበረበት። መሠረታዊ ስለሆኑ የቅዱሳን መጻሕፍት እውነቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ያገኘው እውቀት ብሎም ለተማረው ነገር ያደረበት አድናቆት ለመጠመቅ አነሳስቶታል። ይህ ሰው ከተጠመቀ በኋላም እውቀት መቅሰሙን እንደቀጠለ ጥያቄ የለውም። ወላጆች ከዚህ ታሪክ ትምህርት ማግኘት ትችላላችሁ፤ ልጃችሁ መሠረታዊ የሆኑ የቅዱሳን መጻሕፍት ትምህርቶችን በሚገባ ስለተረዳ እንዲሁም ራስን መወሰንና ጥምቀት ምን ትርጉም እንዳላቸው ስለተገነዘበ መጠመቅ እንደሚፈልግ ቢነግራችሁ ምን ማድረግ ይኖርባችኋል? ልጃችሁ ለመጠመቅ የሚያስፈልገውን ብቃት ማሟላቱን ለማወቅ የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲያነጋግሩት ዝግጅት ማድረግ ትችላላችሁ። * እንደ ማንኛውም የተጠመቀ ደቀ መዝሙር ሁሉ ልጃችሁም በመላ ሕይወቱ እንዲያውም ለዘላለም ስለ ይሖዋ ዓላማዎች እውቀት መቅሰሙን ይቀጥላል።—ሮም 11:33, 34
ልጄ የተሳካ ሕይወት እንዲኖረው የሚረዳው ምንድን ነው?
10, 11. (ሀ) አንዳንድ ወላጆች ምን ዓይነት አመለካከት አላቸው? (ለ) አንድ ወላጅ በዋነኝነት ሊያሳስበው የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
10 አንዳንድ ወላጆች፣ ልጃቸው ከመጠመቁ በፊት በትምህርቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢደርስና ጥሩ ሥራ ቢይዝ የተሻለ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ወላጆች እንዲህ ዓይነት ሐሳብ የሚያቀርቡት ለልጃቸው መልካም ስለሚያስቡ ነው፤ ሆኖም እንደሚከተለው ብለው ራሳቸውን መጠየቃቸው ጠቃሚ ነው፦ ‘ይህ አካሄድ ልጄ በሕይወቱ እውነተኛ ስኬት እንዲያገኝ ይረዳዋል? ደግሞስ እንዲህ ያለው አመለካከት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው ሐሳብ ጋር ይስማማል? ይሖዋ የሚፈልገው ሕይወታችንን በምን መንገድ እንድንጠቀምበት ነው?’—መክብብ 12:1ን አንብብ።
11 ዓለምም ሆነ በዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች ከይሖዋ ፈቃድ ጋር እንደሚጋጩ መዘንጋት የለብንም። (ያዕ. 4:7, 8፤ 1 ዮሐ. 2:15-17፤ 5:19) ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም እንዲሁም ይህ ዓለም የሚያራምደው መጥፎ አስተሳሰብ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ልጃችሁ መቋቋም እንዲችል የሚረዳው ከሁሉ የተሻለው መከላከያ ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረቱ ነው። ወላጆች ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ነገር ትምህርትና ጥሩ ሥራ ከሆነ ግን ልጁ እነዚህ ነገሮች ከይሖዋ ጋር ዝምድና ከመመሥረት ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆኑ ሊሰማው ይችላል፤ ይህ ደግሞ አደገኛ ነው። ደግሞስ አፍቃሪ የሆኑ ክርስቲያን ወላጆች፣ የተሳካ ሕይወት ማግኘት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ልጃቸው በዓለም ላይ ያለውን አመለካከት እንዲያዳብር ይፈልጋሉ? እውነተኛ ደስታና ስኬት ማግኘት የምንችለው በሕይወታችን ውስጥ ለይሖዋ አንደኛ ቦታ ስንሰጠው ብቻ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም።—መዝሙር 1:2, 3ን አንብብ።
ልጄ ኃጢአት ቢፈጽምስ?
12. አንዳንድ ወላጆች ልጃቸው ሳይጠመቅ እንዲቆይ የሚፈልጉት ለምንድን ነው?
12 አንዲት ክርስቲያን እናት ልጇ ሳትጠመቅ እንድትቆይ የፈለገችው ለምን እንደሆነ ስትገልጽ “ዋነኛው ምክንያቴ ልጄ እንዳትወገድ ያለኝ ፍርሃት ነው፤ በእርግጥ እንዲህ ብዬ ማሰቤ ያሳፍረኛል” በማለት ተናግራለች። እንደዚህች እህት ሁሉ አንዳንድ ወላጆችም ልጃቸው የሞኝነት ድርጊት ሊፈጽም ስለሚችል ልጅነቱ እስኪያልፍ ድረስ ሳይጠመቅ ቢቆይ የተሻለ እንደሆነ ይሰማቸዋል። (ዘፍ. 8:21፤ ምሳሌ 22:15) ‘ልጄ እስካልተጠመቀ ድረስ ሊወገድ አይችልም’ ብለው ያስቡ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ያለው አስተሳሰብ አታላይ ነው፤ ለምን?—ያዕ. 1:22
13. አንድ ልጅ አለመጠመቁ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ እንዳይሆን ያደርገዋል? አብራራ።
13 ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጃቸው ተቀባይነት ባለው መንገድ ራሱን ለመወሰን የሚያስችል ብስለት ላይ ሳይደርስ እንዲጠመቅ አለመፈለጋቸው ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ አንድ ልጅ እስካልተጠመቀ ድረስ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ አይደለም ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። ለምን? አንድ ሰው በይሖዋ ዘንድ ተጠያቂ የሚሆነው ስለተጠመቀ ብቻ አይደለም። አንድ ልጅ በይሖዋ ፊት ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር እስካወቀ ድረስ ከተጠያቂነት አያመልጥም። (ያዕቆብ 4:17ን አንብብ።) ስለሆነም ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ልጃቸውን ሳይጠመቅ እንዲቆይ አይመክሩትም። ከዚህ ይልቅ ከሕፃንነቱ ጀምሮ በማስተማር ለይሖዋ የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ልባዊ አድናቆት እንዲያዳብር ይረዱታል፤ እንዲሁም እነሱ ራሳቸው ጥሩ ምሳሌ ለመሆን ይጥራሉ። (ሉቃስ 6:40) ልጃችሁ ኃጢአት ከመፈጸም እንዲቆጠብ የሚረዳው ከሁሉ የተሻለው ነገር እንዲህ ዓይነት አድናቆት ማዳበሩ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው አድናቆት የይሖዋን የጽድቅ ጎዳና እንዲከተል ያነሳሳዋል።—ኢሳ. 35:8
ሌሎችም እርዳታ ማበርከት ይችላሉ
14. ልጆቻቸው እድገት አድርገው እንዲጠመቁ ለመርዳት ጥረት የሚያደርጉ ወላጆችን ሽማግሌዎች ሊያግዟቸው የሚችሉት እንዴት ነው?
14 የጉባኤው መንፈሳዊ እረኞች የሆኑት ሽማግሌዎች፣ መንፈሳዊ ግቦች ማውጣት ያለውን ጥቅም ጎላ አድርገው በመግለጽ ወላጆችን ማገዝ ይችላሉ። ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለች አንዲት እህት የስድስት ዓመት ልጅ እያለች ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስል የነገራት ነገር በሕይወቷ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ታስታውሳለች። ይህች እህት “ለ15 ደቂቃ ያህል ስለ መንፈሳዊ ግቦቼ አዋራኝ” ብላለች። በእርግጥም የሚያበረታታ ሐሳብ መናገር በሌሎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። (ምሳሌ 25:11) በተጨማሪም ሽማግሌዎች፣ በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ እንዲካፈሉ ወላጆችንና ልጆችን ሊጋብዟቸው እንዲሁም የልጆቹን ዕድሜና ችሎታ ያገናዘቡ ሥራዎችን ሊሰጧቸው ይችላሉ።
15. ሌሎች የጉባኤው አባላት ልጆችን ማበረታታት የሚችሉት በየትኞቹ መንገዶች ነው?
15 ሌሎች የጉባኤው አባላትም ለልጆች ተገቢ በሆነ መንገድ ትኩረት በመስጠት ወላጆችን ማገዝ ይችላሉ። ይህም ልጆቹ የሚያደርጉትን መንፈሳዊ እድገት ለማስተዋል ንቁ መሆንን ይጨምራል። አንድ ልጅ በሳምንቱ መካከል በሚደረገው ስብሰባ ላይ ክፍል አቅርቦ ወይም ከልብ የመነጨና ጥሩ ዝግጅት መዝ. 35:18
የተደረገበት ሐሳብ ሰጥቶ ይሆናል። አሊያም ደግሞ ያጋጠመውን ፈተና በታማኝነት ተወጥቶ ወይም በትምህርት ቤት ስለ እምነቱ መሥክሮ ሊሆን ይችላል። በእነዚህ ጊዜያት ለልጁ አድናቆታችሁን ከመግለጽ ወደኋላ አትበሉ። ከዚህም ሌላ ከስብሰባ በፊት ወይም በኋላ አንድን ወጣት ትኩረት ሰጥታችሁ ለማነጋገር ጥረት ማድረግ ትችላላችሁ። እነዚህንና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም ልጆች ‘በታላቁ ጉባኤ’ ውስጥ ቦታ እንዳላቸው እንዲሰማቸው ማድረግ እንችላለን።—ልጃችሁ እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ እርዱት
16, 17. (ሀ) አንድ ሰው መጠመቁ ከወደፊት ሕይወቱ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? (ለ) ሁሉም ክርስቲያን ወላጆች የሚያስደስታቸው ምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
16 ልጆችን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” ማሳደግ ክርስቲያን ወላጆች ካሏቸው ውድ መብቶች አንዱ ነው። (ኤፌ. 6:4፤ መዝ. 127:3) በጥንቷ እስራኤል የነበሩ ልጆች የተወለዱት ራሱን ለይሖዋ በወሰነ ብሔር ውስጥ ነው፤ በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ የሚወለዱ ልጆች ግን በግለሰብ ደረጃ ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰን አለባቸው። ከዚህም በተጨማሪ ወላጆች፣ ለአምላክና ለእውነት ያላቸውን ፍቅር ለልጆቻቸው በውርስ መስጠት አይችሉም። ወላጆች ልጃቸው ራሱን ለይሖዋ ወስኖ በመጠመቅ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን፣ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ሊረዱት ይገባል። ከዚህ የበለጠ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ምን ነገር አለ? ደግሞም ማንኛውም ሰው በቅርቡ ከሚመጣው ታላቅ መከራ ለመዳን ምልክት የሚደረግበት በግለሰብ ደረጃ ራሱን ለአምላክ ከወሰነ፣ ከተጠመቀና ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግል ከሆነ ብቻ ነው።—ማቴ. 24:13
17 ብሎሰም ብራንት ለመጠመቅ ስትወስን ወላጆቿ በሕይወቷ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ይህን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኗን ማረጋገጥ ፈልገው ነበር። ይህን ካረጋገጡ በኋላ ውሳኔዋን ደግፈዋል። ከመጠመቋ በፊት ባለው ምሽት ላይ አባቷ አንድ ጥሩ ነገር አደረገ። ብሎሰም እንዲህ ብላለች፦ “ሁላችንም እንድንንበረከክ ካደረገ በኋላ ጸሎት አቀረበ። ትንሿ ልጁ ሕይወቷን ለይሖዋ በመወሰኗ በጣም የተደሰተ መሆኑን ለይሖዋ ነገረው።” ይህ ከሆነ ከ60 ዓመታት በኋላ ብሎሰም “መቼም ቢሆን ያን ምሽት በፍጹም አልረሳውም!” በማለት ተናግራለች። እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ራሳቸውን ወስነው የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች ሲሆኑ ማየት የሚያስገኘውን ደስታና እርካታ እንድታጣጥሙ ምኞታችን ነው።
^ አን.9 ወላጆች፣ ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች ጥራዝ 2 በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 304-310 ላይ የሚገኘውን ጠቃሚ ሐሳብ ከልጃቸው ጋር ሊከልሱት ይችላሉ። በተጨማሪም በሚያዝያ 2011 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 2 ላይ ያለውን “የጥያቄ ሣጥን” ተመልከቱ።