የጥናት ርዕስ 38
መዝሙር 25 ልዩ ንብረት
ማስጠንቀቂያዎቹን ልብ እያልክ ነው?
“አንዱ ይወሰዳል፤ ሌላው እዚያው ይተዋል።”—ማቴ. 24:40
ዓላማ
ኢየሱስ የተናገራቸውን ሦስት ምሳሌዎች እንመረምራለን፤ በዚህ ሥርዓት መጨረሻ ላይ ከሚከናወነው ፍርድ ጋር ያላቸውን ግንኙነትም እንመለከታለን።
1. በቅርቡ ኢየሱስ ምን ያደርጋል?
የምንኖረው ትላልቅ ለውጦች በሚጠበቁበት ጊዜ ውስጥ ነው። በቅርቡ ኢየሱስ በምድር ላይ በሚኖር በእያንዳንዱ ሰው ላይ ፍርድ ያስተላልፋል። ኢየሱስ ይህ የፍርድ ጊዜ መቃረቡን እንዴት ማወቅ እንደምንችል ገልጾልናል፤ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱንና ‘የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ’ የሚጠቁመውን ትንቢታዊ “ምልክት” ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። (ማቴ. 24:3) ይህ ትንቢት በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25 እንዲሁም በማርቆስ ምዕራፍ 13 እና በሉቃስ ምዕራፍ 21 ላይ ይገኛል።
2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን? ይህስ የሚጠቅመን እንዴት ነው?
2 ኢየሱስ ሦስት ምሳሌዎችን በመጠቀም አስፈላጊ ማስጠንቀቂያዎችን ተናግሯል። እነሱም የበጎቹና የፍየሎቹ፣ የልባሞቹና የሞኞቹ ደናግል እንዲሁም የታላንቱ ምሳሌዎች ናቸው። እያንዳንዱ ምሳሌ፣ ለፍርድ መሠረት የሚሆነው ባሕርይ ምን እንደሆነ ይጠቁመናል። እነዚህን ምሳሌዎች በምንመረምርበት ጊዜ ምን ትምህርት እንደምናገኝና ትምህርቱን እንዴት ተግባራዊ እንደምናደርገውም እንመለከታለን። በመጀመሪያ የምንመረምረው የበጎቹንና የፍየሎቹን ምሳሌ ነው።
የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ
3. ኢየሱስ በሰዎች ላይ ፍርድ የሚያስተላልፈው መቼ ነው?
3 በበጎቹና በፍየሎቹ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ ፍርድ የሚያስተላልፈው ሰዎች ለምሥራቹ በሚሰጡት ምላሽና ለቅቡዓን ወንድሞቹ በሚሰጡት ድጋፍ ላይ ተመሥርቶ እንደሆነ እንመለከታለን። (ማቴ. 25:31-46) ኢየሱስ ፍርድ የሚያስተላልፈው ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ልክ ከአርማጌዶን በፊት ነው። (ማቴ. 24:21) አንድ እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሁሉ ኢየሱስም ቅቡዓን ተከታዮቹን በታማኝነት የደገፉትን ሰዎች ካልደገፉት ሰዎች ይለያል።
4. በኢሳይያስ 11:3, 4 መሠረት ኢየሱስ ፍትሐዊ ፍርድ እንደሚሰጥ እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
4 የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚጠቁመው ኢየሱስ በይሖዋ የተሾመ ፈራጅ እንደመሆኑ መጠን በጽድቅ ይፈርዳል። (ኢሳይያስ 11:3, 4ን አንብብ።) የሰዎችን ድርጊት፣ አመለካከትና አነጋገር ይመለከታል፤ ይህም ሰዎች ቅቡዓን ወንድሞቹን የሚይዙበትን መንገድ ይጨምራል። (ማቴ. 12:36, 37፤ 25:40) ኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞቹንም ሆነ ሥራቸውን የደገፉት እነማን እንደሆኑ ያውቃል። a በበግ የተመሰሉት ሰዎች የክርስቶስን ወንድሞች ከሚደግፉባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዱ በስብከቱ ሥራ እነሱን መርዳት ነው። በዚህ መንገድ ድጋፋቸውን ያሳዩ ሰዎች “ጻድቃን” ተብለው ይፈረድላቸዋል፤ እንዲሁም በምድር ላይ ‘የዘላለም ሕይወት’ የማግኘት ተስፋ ይኖራቸዋል። (ማቴ. 25:46፤ ራእይ 7:16, 17) እንዴት ያለ አስደናቂ ሽልማት ነው! በታላቁ መከራ ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ ታማኞች ሆነው ከቀጠሉ ስማቸው “በሕይወት መጽሐፍ” ላይ ተጽፎ ይቆያል።—ራእይ 20:15
5. የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ የሚያስተላልፈው ትምህርት ምንድን ነው? ይህ ትምህርት የሚመለከተውስ እነማንን ነው?
5 ታማኝ መሆንህን አስመሥክር። ኢየሱስ ስለ በጎቹና ፍየሎቹ የተናገረው ምሳሌ በዋነኝነት የሚመለከተው ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖች ነው። የክርስቶስን ወንድሞች በስብከቱ ሥራ በመደገፍ ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ የሾመውን ‘የታማኝና ልባም ባሪያ’ አመራር በታማኝነት በመከተልም እምነት እንዳላቸው ያስመሠክራሉ። (ማቴ. 24:45) ሆኖም ሰማያዊ ውርሻ ያላቸው ክርስቲያኖችም ይህ ምሳሌ የሚሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ ሊሉ ይገባል። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ የእነሱንም ድርጊት፣ አመለካከትና አነጋገር ይመዝናል። እነሱም ታማኝ መሆናቸውን ማስመሥከር አለባቸው። እንዲያውም ኢየሱስ ለቅቡዓኑ ቀጥተኛ ማስጠንቀቂያ የያዙ ሁለት ሌሎች ምሳሌዎችን ተናግሯል። እነዚህን ምሳሌዎችም በማቴዎስ ምዕራፍ 25 ላይ እናገኛቸዋለን። ቀጥሎ የልባሞቹንና የሞኞቹን ደናግል ምሳሌ እንመለከታለን።
የልባሞቹና የሞኞቹ ደናግል ምሳሌ
6. አምስቱ ደናግል ልባሞች መሆናቸውን ያስመሠከሩት እንዴት ነው? (ማቴዎስ 25:6-10)
6 ኢየሱስ በደናግሉ ምሳሌ ላይ አንድን ሙሽራ ሊቀበሉ ስለወጡ አሥር ደናግል ተናግሯል። (ማቴ. 25:1-4) ሁሉም ሙሽራውን አጅበው ወደ ሠርጉ ድግስ ለመግባት እየተጠባበቁ ነበር። ኢየሱስ አምስቱ “ልባሞች፣” አምስቱ ደግሞ “ሞኞች” እንደሆኑ ተናግሯል። ልባሞቹ ደናግል ዝግጁ እና ንቁ ነበሩ። ሙሽራው ምንም ያህል ቢዘገይ እሱን ለመጠበቅ ተዘጋጅተው ነበር። በጨለማ እንዲያበራላቸው መብራት ይዘዋል። ሙሽራው ከታሰበው በላይ ቢዘገይ ሊጠቀሙበት የሚችሉት ትርፍ ዘይት እንኳ ይዘዋል። ስለዚህ መብራቶቻቸውን እንደበሩ ለማቆየት ተዘጋጅተው ነበር። (ማቴዎስ 25:6-10ን አንብብ።) ሙሽራው ሲመጣ ልባሞቹ ደናግል ከእሱ ጋር አብረው ወደ ድግሱ ገቡ። በተመሳሳይም፣ ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ ንቁና ታማኝ በመሆን ዝግጁ መሆናቸውን ያስመሠከሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሙሽራው ኢየሱስ ጋር ወደ ሰማያዊ መንግሥቱ ለመግባት ብቁ እንደሆኑ ይፈረድላቸዋል። b (ራእይ 7:1-3) አምስቱ ሞኝ ደናግልስ?
7. ሞኞቹ ደናግል ምን ደረሰባቸው? ለምንስ?
7 ከልባሞቹ ደናግል በተቃራኒ አምስቱ ሞኝ ደናግል ሙሽራው ለሚመጣበት ጊዜ ዝግጁ አልነበሩም። መብራታቸው ሊጠፋ ተቃርቦ ነበር፤ ትርፍ ዘይት ደግሞ አልያዙም። ሙሽራው እየመጣ መሆኑን ሲያውቁ ዘይት ለመግዛት ሄዱ። ሙሽራው ሲደርስ እነሱ አልተመለሱም ነበር። በዚህ መሃል “ተዘጋጅተው የነበሩት [ደናግል] ወደ ሠርጉ ድግስ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ።” (ማቴ. 25:10) ሞኞቹ ደናግል ተመልሰው መጥተው ወደ ድግሱ ለመግባት ሲሞክሩ ሙሽራው “አላውቃችሁም” አላቸው። (ማቴ. 25:11, 12) እነዚህ ደናግል፣ ሙሽራው ምንም ያህል ቢዘገይ እሱ እስኪመጣ ድረስ ለመጠበቅ ዝግጁ አልነበሩም። ይህ ለቅቡዓኑ ምን ትምህርት ይዟል?
8-9. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከደናግሉ ምሳሌ ምን ትምህርት ያገኛሉ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
8 ዝግጁ መሆንህን አስመሥክር። ኢየሱስ ሁለት የቅቡዓን ቡድን እንደሚኖር ይኸውም አንደኛው እስከ ሥርዓቱ መጨረሻ ድረስ ለመጠበቅ ዝግጁ እንደሚሆን፣ ሌላኛው ደግሞ እንዲህ እንደማያደርግ ትንቢት መናገሩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ቅቡዓኑ እስከ መጨረሻው በታማኝነት ለመጽናት ዝግጁ ካልሆኑ ምን እንደሚደርስባቸው ማስጠንቀቁ ነበር። ዝግጁ ሆነው ካልጠበቁ ሽልማታቸውን አያገኙም። (ዮሐ. 14:3, 4) ይህ በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ተስፋችን ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ፣ የደናግሉ ምሳሌ የያዘውን ማስጠንቀቂያ ልብ ልንለው ይገባል። እያንዳንዳችን እስከ መጨረሻው መጽናት እንድንችል ንቁና ዝግጁ መሆን ይኖርብናል።—ማቴ. 24:13
9 ኢየሱስ ዝግጁና ንቁ መሆን ያለውን አስፈላጊነት ከሚያጎላው ከደናግሉ ምሳሌ በኋላ የታላንቱን ምሳሌ ተናገረ። ይህ ምሳሌ ደግሞ ታታሪ የመሆንን አስፈላጊነት የሚያጎላ ነው።
የታላንቱ ምሳሌ
10. ሁለቱ ባሪያዎች ታማኝ መሆናቸውን ያስመሠከሩት እንዴት ነው? (ማቴዎስ 25:19-23)
10 ኢየሱስ በታላንቱ ምሳሌ ላይ የጠቀሳቸው ሁለት ባሪያዎች ለጌታቸው ታማኝ ነበሩ፤ አንደኛው ግን አልነበረም። (ማቴ. 25:14-18) ሁለቱ ባሪያዎች የጌታቸውን ሀብት ለማሳደግ ተግተው በመሥራት ታማኝ መሆናቸውን አሳይተዋል። ጌታቸው ወደ ሌላ አገር ከመሄዱ በፊት ታላንት ማለትም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በአደራ ሰጣቸው። ሁለቱ ባሪያዎች ታታሪ ነበሩ፤ ገንዘቡንም በጥበብ ተጠቅመውበታል። ውጤቱስ ምን ሆነ? ጌታቸው ሲመለስ፣ በአደራ የሰጣቸው ሀብት በእጥፍ አድጎ ነበር። በመሆኑም አመሰገናቸው፤ እንዲሁም ‘ወደ ጌታቸው ደስታ ገቡ።’ (ማቴዎስ 25:19-23ን አንብብ።) ሦስተኛው ባሪያስ? ጌታው የሰጠውን ገንዘብ ምን አደረገበት?
11. ‘ሰነፉ’ ባሪያ ምን ደረሰበት? ለምንስ?
11 አንድ ታላንት የተሰጠው ሦስተኛ ባሪያ “ሰነፍ” ነበር። የተሰጠውን ታላንት በጥበብ እንዲጠቀምበት ጌታው ይጠብቅበት ነበር። እሱ ግን መሬት ውስጥ ቀበረው። ጌታው ሲመለስ ባሪያው በገንዘቡ ምንም አላተረፈም። ይህ ባሪያ የልቡ ዝንባሌ ጥሩ አልነበረም። የጌታውን ሀብት ባለማሳደጉ ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው ጌታውን “ኃይለኛ ሰው” ብሎ በመጥራት ያለስሙ ስም ሰጠው። ይህ ባሪያ በጌታው ዘንድ ምስጋና አላተረፈም። እንዲያውም የተሰጠውን ታላንት ተነጠቀ፤ እንዲሁም ከጌታው ቤት ተባረረ።—ማቴ. 25:24, 26-30
12. ሁለቱ ታማኝ ባሪያዎች እነማንን ያመለክታሉ?
12 ሁለቱ ታማኝ ባሪያዎች ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖችን ያመለክታሉ። ጌታቸው ኢየሱስ ‘ወደ ጌታቸው ደስታ እንዲገቡ’ ይጋብዛቸዋል። ‘በመጀመሪያው ትንሣኤ’ ተካፋይ በመሆን ሰማያዊ ሽልማታቸውን ያገኛሉ። (ማቴ. 25:21, 23፤ ራእይ 20:5ለ) በሌላ በኩል ደግሞ ሰነፉ ባሪያ የተወው መጥፎ ምሳሌ ለቅቡዓኑ ማስጠንቀቂያ ይሆናል። እንዴት?
13-14. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከታላንቱ ምሳሌ ምን ትምህርት ያገኛሉ? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
13 ታታሪ እና ትጉ መሆንህን አስመሥክር። እንደ ደናግሉ ምሳሌ ሁሉ ኢየሱስ የታላንቱን ምሳሌ ሲናገር ቅቡዓኑ ሰነፍ እንደሚሆኑ መተንበዩ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ቅንዓታቸው ቢቀዘቅዝ ምን እንደሚያጋጥማቸው ማስጠንቀቁ ነበር። ‘መጠራታቸውንና መመረጣቸውን አስተማማኝ ማድረግ’ አይችሉም፤ ወደ ሰማያዊ መንግሥቱ እንዲገቡም አይፈቀድላቸውም።—2 ጴጥ. 1:10
14 ኢየሱስ ስለ ደናግሉ እና ስለ ታላንቱ የተናገራቸው ምሳሌዎች ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ዝግጁና ንቁ እንዲሁም ታታሪና ትጉ መሆን እንዳለባቸው የሚያሳዩ ናቸው። ይሁንና ኢየሱስ ለቅቡዓኑ ማስጠንቀቂያ የሚሆን ሌላ ሐሳብስ ተናግሮ ይሆን? አዎ፣ ተናግሯል። ኢየሱስ በማቴዎስ 24:40, 41 ላይ የተናገረው ሐሳብ በቅቡዓኑ ላይ ከሚተላለፈው የመጨረሻ ፍርድ ጋር የተያያዘ ነው።
‘የሚወሰዱት’ እነማን ናቸው?
15-16. ማቴዎስ 24:40, 41 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ነቅተው መጠበቅ እንዳለባቸው የሚያጎላው እንዴት ነው?
15 ኢየሱስ ሦስቱን ምሳሌዎች ከመናገሩ በፊት ቅቡዓኑ በግለሰብ ደረጃ ስለሚሰጣቸው የመጨረሻ ፍርድ ተናግሮ ነበር። በእርሻ ቦታ ስለሚሠሩ ሁለት ወንዶችና በወፍጮ ስለሚፈጩ ሁለት ሴቶች ተናግሯል። ሁለቱ ወንዶችም ሆኑ ሁለቱ ሴቶች ተመሳሳይ ሥራ እየሠሩ ያሉ ይመስላል፤ ሆኖም ኢየሱስ ‘አንዳቸው እንደሚወሰዱ፣ ሌላኛቸው ደግሞ እዚያው እንደሚተዉ’ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:40, 41ን አንብብ።) ከዚያም ተከታዮቹን እንዲህ በማለት አሳሰባቸው፦ “ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ።” (ማቴ. 24:42) ኢየሱስ የደናግሉን ምሳሌ ከተናገረ በኋላም ተመሳሳይ ነገር ብሏል። (ማቴ. 25:13) እነዚህ ሐሳቦች ተያያዥ ናቸው? እንደዚያ ይመስላል። ወደ ኢየሱስ ሰማያዊ መንግሥት ‘የሚወሰዱት’ እውነተኛና ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው።—ዮሐ. 14:3
16 ንቁ መሆንህን አስመሥክር። በመንፈሳዊ ንቁ ያልሆነ ማንኛውም ቅቡዕ ክርስቲያን ‘ከተመረጡት’ ጋር አይሰበሰብም። (ማቴ. 24:31) ይህ ማስጠንቀቂያ በተዘዋዋሪ መንገድ ለሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ይሠራል፤ ተስፋችን ምንም ይሁን ምን ሁላችንም ነቅተን መጠበቅና ታማኞች መሆን ይኖርብናል።
17. ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ክርስቲያኖችን በመንፈሱ ለመቀባት ቢመርጥ ጉዳዩ ሊያሳስበን የማይገባው ለምንድን ነው?
17 ይሖዋን በደንብ ስለምናውቀው ፍርዱ ትክክል እንደሆነ እንተማመናለን። ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ክርስቲያኖችን በመንፈስ ቅዱስ ለመቀባት ቢመርጥ ጉዳዩ አያስጨንቀንም። c ኢየሱስ በወይን እርሻው ምሳሌ ላይ በ11ኛው ሰዓት ስለተቀጠሩት ሠራተኞች የተናገረውን ሐሳብ እናስታውሳለን። (ማቴ. 20:1-16) በቀኑ መገባደጃም ሆነ ቀደም ብለው የተቀጠሩት ሠራተኞች ክፍያቸው ተመሳሳይ ነበር። በተመሳሳይም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተመረጡት መቼም ይሁን መች ታማኝነታቸውን እስከጠበቁ ድረስ ሽልማታቸውን ያገኛሉ።
ማስጠንቀቂያዎቹን ልብ በል
18-19. የትኞቹን ትምህርቶችና ማስጠንቀቂያዎች ተመልክተናል?
18 እስካሁን ምን ተመልክተናል? የበጎቹና የፍየሎቹ ምሳሌ፣ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች አሁንም ሆነ በታላቁ መከራ ወቅት ለይሖዋ ታማኝ ሆነው መቀጠል እንዳለባቸው ያጎላል። በታላቁ መከራ ወቅት ኢየሱስ ታማኝነታቸውን የጠበቁትን ሰዎች “ወደ ዘላለም ሕይወት” ለመግባት ብቁ ናቸው ብሎ ይፈርድላቸዋል።—ማቴ. 25:46
19 ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ የያዙ ሁለት ምሳሌዎችንም ተመልክተናል። ኢየሱስ ስለ ልባሞቹና ሞኞቹ ደናግል በተናገረው ምሳሌ ላይ አምስቱ ጥበበኞች መሆናቸውን አስመሥክረዋል። ሙሽራው ምንም ያህል ቢዘገይ እሱን ለመጠበቅ ዝግጁ ነበሩ። ሞኞቹ ደናግል ግን ዝግጁ አልነበሩም። ስለዚህ ሙሽራው ወደ ሠርጉ ድግስ እንዲገቡ አልፈቀደላቸውም። እኛም በተመሳሳይ፣ ኢየሱስ ይህን ሥርዓት የሚያጠፋው መቼም ይሁን መች እስከ መጨረሻው ለመጠበቅ ዝግጁ መሆን አለብን። በታላንቱ ምሳሌ ላይ ደግሞ ሁለቱ ባሪያዎች ታታሪ እና ትጉ እንደነበሩ ተመልክተናል። የጌታቸውን ሀብት ለማሳደግ ጠንክረው ሠርተዋል። በዚህም የእሱን ምስጋና አትርፈዋል። ሰነፉ ባሪያ ግን ተባሯል። ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? እስከ መጨረሻው ድረስ በይሖዋ አገልግሎት ተግተን ልንሠራ ይገባል። በመጨረሻ እንደተመለከትነው ደግሞ ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ኢየሱስ ወደ ሰማያዊ ውርሻቸው ‘እንዲወስዳቸው’ እስከ መጨረሻው ንቁ መሆን አለባቸው። እነዚህ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ጋር ለመሆን በሰማይ ‘አንድ ላይ የሚሰበሰቡበትን’ ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። ከአርማጌዶን ጦርነት በኋላ የኢየሱስ ሙሽራ በመሆን በበጉ ሠርግ ላይ ይካፈላሉ።—2 ተሰ. 2:1፤ ራእይ 19:9
20. ይሖዋ ማስጠንቀቂያዎቹን ልብ ለሚሉ ሰዎች ምን ያደርግላቸዋል?
20 ፍርድ የሚሰጥበት ጊዜ በፍጥነት እየተቃረበ ቢሆንም የሚያስፈራን ነገር የለም። ታማኝ ሆነን ከጸናን አፍቃሪ የሆነው የሰማዩ አባታችን ‘በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድንችል’ ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ ይሰጠናል። (2 ቆሮ. 4:7፤ ሉቃስ 21:36) ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ፣ በኢየሱስ ምሳሌዎች ውስጥ የሚገኙትን ማስጠንቀቂያዎች ልብ ካልን አባታችን ይደሰትብናል። በይሖዋ ጸጋ ስማችን በሕይወት “መጽሐፍ ላይ ተጽፎ” ይገኛል።—ዳን. 12:1፤ ራእይ 3:5
መዝሙር 26 ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል
a በግንቦት 2024 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ይሖዋ ወደፊት ስለሚወስዳቸው የፍርድ እርምጃዎች ምን እናውቃለን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በመጋቢት 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ነቅታችሁ ትጠብቃላችሁ?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c የጥር 2020 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 29-30 አን. 11-14ን ተመልከት።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት ቅቡዕ እህት በአገልግሎት ላይ ያገኘቻትን ወጣት ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ስታስጠና።