የጥናት ርዕስ 36
አርማጌዶን—በጉጉት የምንጠብቀው ክንውን!
“አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።”—ራእይ 16:16
መዝሙር 150 ትድኑ ዘንድ አምላክን ፈልጉ
ማስተዋወቂያ a
1-2. (ሀ) የአርማጌዶን መምጣት ለሰው ዘር ምሥራች ነው የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
ሰዎች “አርማጌዶን” የሚለውን ቃል ከኑክሌር ጦርነት ወይም አካባቢን ከሚያወድም የተፈጥሮ አደጋ ጋር አያይዘው ሲጠቅሱት ሰምተህ ታውቃለህ? እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አርማጌዶን የሚገልጸው ነገር ለሰው ልጆች ምሥራች የሚያበስር ነው! (ራእይ 1:3) የአርማጌዶን ጦርነት የሰውን ዘር የሚያጠፋ ሳይሆን የሚታደግ ክንውን ነው! እንዴት?
2 የአርማጌዶን ጦርነት ሰብዓዊ አገዛዝን በማስወገድ የሰውን ዘር እንደሚያድን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ይህ ጦርነት ክፉዎች እንዲጠፉና ጻድቃን በሕይወት እንዲተርፉ በማድረግ ለሰዎች መዳን ያስገኛል። በተጨማሪም ግዑዟን ምድራችንን ከጥፋት በመታደግ የሰው ልጆችን ያድናል። (ራእይ 11:18) እነዚህን ነጥቦች ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ እስቲ የሚከተሉትን አራት ጥያቄዎች እንመርምር፦ አርማጌዶን ምንድን ነው? ከአርማጌዶን በፊት ምን ነገሮች ይከናወናሉ? ከአርማጌዶን ጦርነት በሕይወት ከሚተርፉት መካከል መሆን የምንችለው እንዴት ነው? አርማጌዶን እየቀረበ ሲሄድ ታማኝነታችንን ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
አርማጌዶን ምንድን ነው?
3. (ሀ) “አርማጌዶን” የሚለው ቃል ምን ያመለክታል? (ለ) በራእይ 16:14, 16 መሠረት አርማጌዶን ቃል በቃል በምድር ላይ ያለን ቦታ አያመለክትም የምንለው ለምንድን ነው?
3 ራእይ 16:14, 16ን አንብብ። “አርማጌዶን” የሚለው ቃል በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሰው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን “የመጊዶ ተራራ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው። (ራእይ 16:16 ግርጌ) መጊዶ በጥንቷ እስራኤል የምትገኝ ከተማ ነበረች። (ኢያሱ 17:11) ሆኖም አርማጌዶን ቃል በቃል በምድር ላይ ያለን ቦታ አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ ‘የዓለም ነገሥታት ሁሉ’ ይሖዋን ተቃውመው የሚሰበሰቡበትን ሁኔታ ያመለክታል። (ራእይ 16:14) ይሁንና በዚህ ርዕስ ውስጥ “አርማጌዶን” የሚለው ቃል የዓለም ነገሥታት ከተሰበሰቡ በኋላ ወዲያውኑ የሚከተለውን ጦርነት ለማመልከትም ተሠርቶበታል። አርማጌዶን ምሳሌያዊ ቦታን እንደሚያመለክት እንዴት እናውቃለን? አንደኛ፣ የመጊዶ ተራራ የሚባል ቦታ የለም። ሁለተኛ፣ በመጊዶ አካባቢ ያለው ቦታ ‘የዓለምን ነገሥታት ሁሉ’ ከወታደሮቻቸውና ከጦር መሣሪያዎቻቸው ጋር ለመያዝ አይበቃም። ሦስተኛ፣ በኋላ ላይ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንደምንመለከተው የአርማጌዶን ጦርነት የሚጀምረው የዓለም “ነገሥታት” በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ነው፤ የአምላክ ሕዝቦች የሚገኙት ደግሞ በተለያዩ የምድር ክፍሎች ውስጥ ነው።
4. ይሖዋ እሱ የሚያካሂደውን ታላቅ ጦርነት ከመጊዶ ጋር ያያያዘው ለምንድን ነው?
4 ታዲያ ይሖዋ ታላቁን ጦርነት ከመጊዶ ጋር ያያያዘው ለምንድን ነው? መጊዶና በአቅራቢያው የሚገኘው የኢይዝራኤል ሸለቆ በርካታ ጦርነቶች የተካሄዱባቸው ቦታዎች ናቸው። እንዲያውም በአንዳንዶቹ ጦርነቶች ላይ ይሖዋ ራሱ በቀጥታ ጣልቃ ገብቶ ነበር። ለምሳሌ እስራኤላዊው መስፍን ባርቅ፣ ሲሳራ በተባለ የጦር አዛዥ ከሚመራው የከነአን ሠራዊት ጋር “በመጊዶ ውኃዎች አጠገብ” በተዋጋበት ጊዜ አምላክ ድል እንዲጎናጸፍ ረድቶታል። ባርቅና ነቢዪቱ ዲቦራ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ላገኙት ድል ይሖዋን አመስግነዋል። እንዲህ በማለትም ዘምረዋል፦ “ከዋክብት ከሰማይ . . . ከሲሳራ ጋር ተዋጉ። . . . የቂሾን ወንዝ ጠራርጎ ወሰዳቸው።”—መሳ. 5:19-21
5. በአርማጌዶን ጦርነትና ባርቅ በተዋጋው ጦርነት መካከል ያለው ትልቅ ልዩነት ምንድን ነው?
5 ባርቅና ዲቦራ መዝሙራቸውን የደመደሙት እንዲህ በማለት ነው፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ጠላቶችህ ሁሉ ይጥፉ፣ አንተን የሚወዱ ግን ደምቃ እንደምትወጣ ፀሐይ ይሁኑ።” (መሳ. 5:31) በተመሳሳይም በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት የአምላክ ጠላቶች በሙሉ የሚጠፉ ሲሆን አምላክን የሚወዱ ደግሞ መዳን ያገኛሉ። ሆኖም ባርቅ ባካሄደው ጦርነትና በአርማጌዶን ጦርነት መካከል አንድ ትልቅ ልዩነት አለ። በአርማጌዶን ጦርነት ላይ የአምላክ ሕዝቦች አይዋጉም። መዋጋት ቀርቶ የጦር መሣሪያ እንኳ አይዙም! በይሖዋና በሰማይ ባለው ሠራዊቱ ‘ተማምነው በመኖር ብርቱ መሆናቸውን ያሳያሉ።’—ኢሳ. 30:15፤ ራእይ 19:11-15
6. በአርማጌዶን ጦርነት ላይ አምላክ ጠላቶቹን ድል የሚያደርገው እንዴት ሊሆን ይችላል?
6 በአርማጌዶን ጦርነት ላይ አምላክ ጠላቶቹን የሚያጠፋው እንዴት ነው? የተለያዩ መንገዶችን ሊጠቀም ይችላል። ለምሳሌ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ በረዶ ወይም መብረቅ ሊጠቀም ይችላል። (ኢዮብ 38:22, 23፤ ሕዝ. 38:19-22) አሊያም ጠላቶቹ እርስ በርሳቸው እንዲተላለቁ ያደርግ ይሆናል። (2 ዜና 20:17, 22, 23) መላእክቱ ክፉዎችን እንዲያጠፉ ሊያደርግም ይችላል። (ኢሳ. 37:36) አምላክ የሚጠቀምበት ዘዴ ምንም ሆነ ምን በጠላቶቹ ላይ የተሟላ ድል ይቀዳጃል። ጠላቶቹ ድምጥማጣቸው ይጠፋል። ጻድቃን ሁሉ ደግሞ መዳን ያገኛሉ።—ምሳሌ 3:25, 26
ከአርማጌዶን በፊት ምን ነገሮች ይከናወናሉ?
7-8. (ሀ) በ1 ተሰሎንቄ 5:1-6 መሠረት የዓለም ገዢዎች ምን ለየት ያለ አዋጅ ያውጃሉ? (ለ) ይህ አዋጅ እጅግ አስከፊ ውሸት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
7 “የይሖዋ ቀን” ከመምጣቱ በፊት “ሰላምና ደህንነት ሆነ” የሚለው አዋጅ ይታወጃል። (1 ተሰሎንቄ 5:1-6ን አንብብ።) በ1 ተሰሎንቄ 5:2 ላይ የተጠቀሰው “የይሖዋ ቀን” የሚያመለክተው “ታላቁን መከራ” ነው። (ራእይ 7:14) ይህ መከራ ሊጀምር መሆኑ የሚታወቀው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ለየት ያለ አዋጅ እንደሚታወጅ ይነግረናል። ይህ አዋጅ ታላቁ መከራ ሊጀምር መሆኑን የሚጠቁም ምልክት ሆኖ ያገለግላል።
8 አዋጁ፣ በትንቢት የተነገረው “ሰላምና ደህንነት ሆነ” የሚለው አዋጅ ነው። የዓለም ገዢዎች ይህን አዋጅ የሚያውጁት ለምንድን ነው? የሃይማኖት መሪዎችስ ይህን አዋጅ በማወጅ ይተባበሯቸው ይሆን? ይተባበሯቸው ይሆናል። የሆነው ሆኖ ግን ይህ አዋጅ አጋንንት ከሚያናፍሷቸው በርካታ ውሸቶች መካከል አንዱ እንደሚሆን የታወቀ ነው። ሆኖም ይህ ውሸት ከሌሎቹ ውሸቶች ሁሉ የከፋ ነው፤ ምክንያቱም በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ መከራ ሊጀምር በተቃረበበት ጊዜ ላይ ሰዎች የተሳሳተ የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል። ከዚያም “ምጥ እርጉዝ ሴትን እንደሚይዛት ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል።” ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችስ? የይሖዋ ቀን ድንገት መጀመሩ ሊያስገርማቸው ቢችልም ዝግጁ ሆነው ስለሚጠብቁ አይደናገጡም።
9. ይሖዋ የሰይጣንን ሥርዓት በአንዴ ያጠፋዋል? አብራራ።
9 ይሖዋ በኖኅ ዘመን ካደረገው በተለየ የሰይጣንን ዓለም የሚያጠፋው በአንድ ጊዜ አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሁለት ምዕራፎች ከፋፍሎ ያጠፋዋል። በመጀመሪያ በዓለም ላይ ያሉትን የሐሰት ሃይማኖቶች በሙሉ የምትወክለውን ታላቂቱ ባቢሎንን ያጠፋታል። ከዚያም የፖለቲካውን፣ የወታደራዊውንና የንግዱን ሥርዓት የሚጨምረውን ቀሪውን የሰይጣን ዓለም ክፍል በአርማጌዶን ጦርነት ያጠፋዋል። እስቲ እነዚህን ሁለት ዋና ዋና ክንውኖች በዝርዝር እንመልከት።
10. በራእይ 17:1, 6 እንዲሁም 18:24 መሠረት ይሖዋ ታላቂቱ ባቢሎንን የሚያጠፋት ለምንድን ነው?
10 “በታላቂቱ አመንዝራ ላይ [የሚበየነው] ፍርድ።” (ራእይ 17:1, 6፤ 18:24ን አንብብ።) ታላቂቱ ባቢሎን በአምላክ ስም ላይ ብዙ ነቀፋ አምጥታለች። ስለ አምላክ በርካታ ውሸቶችን አስተምራለች። ከምድር ገዢዎች ጋር ኅብረት በመፍጠር መንፈሳዊ ምንዝር ፈጽማለች። ሥልጣኗንና ተሰሚነቷን በመጠቀም መንጎቿን በዝብዛለች። እንዲሁም የአምላክን አገልጋዮች ጨምሮ የብዙ ሰዎችን ደም አፍስሳለች። (ራእይ 19:2) ታዲያ ይሖዋ ታላቂቱ ባቢሎንን የሚያጠፋት እንዴት ነው?
11. ‘ደማቁ ቀይ አውሬ’ ማንን ያመለክታል? ይህ አውሬ፣ አምላክ በታላቂቱ ባቢሎን ላይ የበየነውን ፍርድ በማስፈጸም ረገድ ምን ሚና ይጫወታል?
11 ይሖዋ ‘በደማቁ ቀይ አውሬ ላይ ባሉት አሥር ቀንዶች’ አማካኝነት ‘ታላቂቱን አመንዝራ’ ያጠፋታል። ይህ ምሳሌያዊ አውሬ የተባበሩት መንግሥታትን ያመለክታል። አሥሩ ቀንዶች በአሁኑ ጊዜ ይህን ድርጅት እየደገፉ ያሉትን የፖለቲካ ኃይሎች ያመለክታሉ። አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች በታላቂቱ ባቢሎን ላይ ይነሳሉ። ሀብቷን በመዝረፍና ክፋቷን በማጋለጥ “ይበዘብዟታል፤ ራቁቷንም ያስቀሯታል።” (ራእይ 17:3, 16) በአንድ ቀን ውስጥ የተከናወነ ያህል በአፋጣኝ የሚመጣባት ይህ ጥፋት፣ ደጋፊዎቿን በእጅጉ ያስደነግጣቸዋል። ምክንያቱም ይህች አመንዝራ “ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ፤ መበለትም አይደለሁም፤ ሐዘንም ፈጽሞ አይደርስብኝም” እያለች ትኩራራ ነበር።—ራእይ 18:7, 8
12. አምላክ ብሔራት ምን እንዲያደርጉ አይፈቅድላቸውም? ለምንስ?
12 አምላክ ብሔራት ሕዝቡን እንዲያጠፉ አይፈቅድም። ምክንያቱም ሕዝቡ በእሱ ስም የሚጠሩ ከመሆኑም ሌላ ከታላቂቱ ባቢሎን እንዲወጡ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ጠብቀዋል። (ሥራ 15:16, 17፤ ራእይ 18:4) በተጨማሪም ሌሎች ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን እንዲወጡ ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በመሆኑም የይሖዋ አገልጋዮች በዚህች አመንዝራ ላይ የሚመጣው “መቅሰፍት ተካፋይ” አይሆኑም። ያም ሆኖ እምነታቸውን የሚፈትን ሁኔታ ያጋጥማቸዋል።
13. (ሀ) ጎግ ማን ነው? (ለ) በሕዝቅኤል 38:2, 8, 9 መሠረት ጎግን አርማጌዶን ተብሎ ወደሚጠራው ምሳሌያዊ ቦታ የሚያመጣው ምንድን ነው?
13 የጎግ ጥቃት። (ሕዝቅኤል 38:2, 8, 9ን አንብብ።) የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች በሙሉ ተጠራርገው ከጠፉ በኋላ የአምላክ ሕዝቦች ከከባድ አውሎ ነፋስ ብቻዋን እንደተረፈች ዛፍ አውላላ ሜዳ ላይ ተጋልጠው ይታያሉ። ይህ ሰይጣንን እንደሚያስቆጣው የታወቀ ነው። ‘በመንፈስ የተነገሩ ርኩሳን ቃላትን’ ማለትም አጋንንታዊ ፕሮፓጋንዳዎችን ተጠቅሞ ብሔራት ግንባር ፈጥረው በአምላክ ሕዝቦች ላይ እንዲነሱ በማድረግ ቁጣውን ይገልጻል። (ራእይ 16:13, 14) ይህ የብሔራት ጥምረት ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ ይባላል። ብሔራት በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር ሲጀምሩ፣ አርማጌዶን ተብሎ ወደሚጠራው ምሳሌያዊ ቦታ እንደደረሱ ይቆጠራል።—ራእይ 16:16
14. ጎግ የትኛውን እውነታ ይገነዘባል?
14 ጎግ ‘በሥጋ ክንዱ’ ማለትም በወታደራዊ ኃይሉ ይታመናል። (2 ዜና 32:8) እኛ ግን በአምላካችን በይሖዋ እንታመናለን። እርግጥ ይህ በብሔራት ዓይን እንደ ሞኝነት የሚቆጠር ነገር ነው፤ ምክንያቱም በአንድ ወቅት ኃያል የነበረችው የታላቂቱ ባቢሎን አማልክት ‘ከአውሬው’ እንዲሁም ‘ከአሥሩ ቀንዶች’ ሊታደጓት አልቻሉም! (ራእይ 17:16) በመሆኑም ጎግ የአምላክን ሕዝቦች በቀላሉ ሊያጠፋቸው እንደሚችል ያስባል። “ምድርን እንደሚሸፍን ደመና” በመሆን በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። (ሕዝ. 38:16) ብዙም ሳይቆይ ግን ወጥመድ ውስጥ እንደገባ ይረዳል። ፈርዖን በቀይ ባሕር እንዳጋጠመው ጎግም ከይሖዋ ጋር እየተዋጋ እንዳለ ይገነዘባል።—ዘፀ. 14:1-4፤ ሕዝ. 38:3, 4, 18, 21-23
15. ኢየሱስ ሙሉ በሙሉ ድል የሚቀዳጀው እንዴት ነው?
15 ክርስቶስና በሰማይ ያለው ሠራዊቱ ጎግን በማጥፋት የአምላክን ሕዝቦች ይታደጋሉ። (ራእይ 19:11, 14, 15) ሆኖም በውሸት ፕሮፓጋንዳው ብሔራት ወደ አርማጌዶን እንዲሰበሰቡ ያደረገው የአምላክ ቀንደኛ ጠላት ሰይጣንስ ምን ያጋጥመዋል? ኢየሱስ እሱንም ሆነ አጋንንቱን ወደ ጥልቁ ወርውሮ ለሺህ ዓመት ይዘጋባቸዋል።—ራእይ 20:1-3
ከአርማጌዶን ጦርነት መትረፍ የምንችለው እንዴት ነው?
16. (ሀ) ‘አምላክን እንደምናውቅ’ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋን ማወቃችን በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ትልቅ በረከት ያስገኝልናል የምንለው ለምንድን ነው?
16 በእውነት ቤት ውስጥ ለብዙ ዓመታት የቆየንም ሆንን አዲሶች ከአርማጌዶን ጦርነት መትረፍ ከፈለግን ‘አምላክን እንደምናውቅ’ እና ‘ስለ ጌታችን ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች እንደምንታዘዝ’ ማሳየት አለብን። (2 ተሰ. 1:7-9) ‘አምላክን ማወቅ’ እሱ የሚወዳቸውንና የሚጠላቸውን ነገሮች እንዲሁም መሥፈርቶቹን ማወቅን ያካትታል። በተጨማሪም አምላክን በመውደድና በመታዘዝ እንዲሁም እሱን ብቻ በማምለክ እሱን እንደምናውቀው እናሳያለን። (1 ዮሐ. 2:3-5፤ 5:3) አምላክን ማወቃችን ደግሞ ‘በእሱ ዘንድ የመታወቅ’ ልዩ መብት ይሰጠናል፤ ይህም ከአርማጌዶን ጦርነት ለመትረፍ ያስችለናል! (1 ቆሮ. 8:3) እንዴት? ምክንያቱም ‘በአምላክ ዘንድ መታወቅ’ ማለት የእሱን ሞገስ ማግኘት ማለት ነው።
17. ‘ስለ ጌታችን ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች’ መታዘዝ ምን ነገሮችን ይጨምራል?
17 “ስለ ጌታችን ኢየሱስ [የሚገልጸው] ምሥራች” ኢየሱስ ያስተማራቸውን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ እውነቶች በሙሉ ያጠቃልላል። ምሥራቹን ታዘናል የሚባለው በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ስናደርገው ነው። ይህም ለመንግሥቱ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠትን፣ ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖርንና ስለ አምላክ መንግሥት ማወጅን ያካትታል። (ማቴ. 6:33፤ 24:14) እንዲሁም የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች የተጣለባቸውን ከባድ ኃላፊነት ሲወጡ ለእነሱ ድጋፍ መስጠትን ይጨምራል።—ማቴ. 25:31-40
18. የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች፣ ሌሎች በጎች ያሳዩአቸውን ደግነት መልሰው የሚከፍሉት እንዴት ነው?
18 በቅርቡ ቅቡዓን የአምላክ አገልጋዮች “ሌሎች በጎች” ያሳዩአቸውን ደግነት መልሰው የሚከፍሉበት አጋጣሚ ያገኛሉ። (ዮሐ. 10:16) እንዴት? የአርማጌዶን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት 144,000ዎቹ ቅቡዓን በሙሉ ወደ ሰማይ ሄደው የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት ያገኛሉ። ከዚያም ጎግን የሚደመስሰውና ‘ለእጅግ ብዙ ሕዝብ’ ማለትም በግ መሰል ለሆኑት የአምላክ አገልጋዮች ጥበቃ የሚያደርገው ሰማያዊ ሠራዊት ክፍል ይሆናሉ። (ራእይ 2:26, 27፤ 7:9, 10) የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት፣ ቅቡዓን የይሖዋ አገልጋዮች ገና ምድር ላይ በነበሩበት ጊዜ እነሱን መደገፍ የሚችሉበት አጋጣሚ በማግኘታቸው ከፍተኛ ደስታ ይሰማቸዋል!
መጨረሻው እየቀረበ ሲሄድ ታማኝነታችንን መጠበቅ
19-20. ወደ መጨረሻው እየቀረብን ስንሄድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም ታማኝነታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
19 ለመቋቋም አስቸጋሪ በሆኑት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በርካታ የይሖዋ ሕዝቦች የተለያዩ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል። ያም ቢሆን ደስታችንን ሳናጣ ፈተናዎቹን በጽናት መወጣት እንችላለን። (ያዕ. 1:2-4) ቁልፉ ከልብ የመነጨ ጸሎት ማቅረብ ነው። (ሉቃስ 21:36) ከዚህም በተጨማሪ በዘመናችን ፍጻሜያቸውን የሚያገኙ አስገራሚ ትንቢቶችን የያዘውን የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማጥናትና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። (መዝ. 77:12) ለእነዚህ ነገሮች ትኩረት መስጠታችንና በአገልግሎት ሙሉ ተሳትፎ ማድረጋችን እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን እንዲሁም ተስፋችን ብሩህ ሆኖ እንዲታየን ይረዳናል።
20 ታላቂቱ ባቢሎን ስትጠፋና የአርማጌዶን ጦርነት ሲደመደም ምን ያህል እንደምትደሰት እስቲ አስበው! ከሁሉ በላይ የሚያስደስትህ ግን የይሖዋ ስም መቀደሱና ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበት መንገድ ትክክል መሆኑ መረጋገጡ እንደሆነ ምንም አያጠራጥርም! (ሕዝ. 38:23) በእርግጥም አርማጌዶን አምላክን ለሚያውቁ፣ ልጁን ለሚታዘዙና እስከ መጨረሻው ለሚጸኑ ሰዎች በጉጉት የሚጠበቅ ክንውን ነው።—ማቴ. 24:13
መዝሙር 143 ነቅተን በተስፋ እንጠብቃለን
a አርማጌዶን፣ የይሖዋ ሕዝቦች ከረጅም ጊዜ አንስቶ በጉጉት የሚጠብቁት ክንውን ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ አርማጌዶን ምን እንደሆነ፣ ከአርማጌዶን በፊት ምን ነገሮች እንደሚከናወኑና መጨረሻው እየተቃረበ ሲሄድ ታማኝነታችንን ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንዳለብን እንመለከታለን።