ይሖዋ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳላችሁ በተግባር አሳዩ
“እምነት . . . የምናምንበት ነገር በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።”—ዕብ. 11:1
መዝሙሮች፦ 54, 125
1. እምነታችንን እንዴት ልንመለከተው ይገባል?
የክርስቲያኖች እምነት ትልቅ ዋጋ ያለው ባሕርይ ነው። እምነት ያላቸው ሁሉም ሰዎች አይደሉም። (2 ተሰ. 3:2) ይሁንና ይሖዋ ለሁሉም አገልጋዮቹ “እምነት” ሰጥቷቸዋል። (ሮም 12:3፤ ገላ. 5:22) አምላክ፣ እምነት ስለሰጠን አመስጋኞች ልንሆን ይገባል!
2, 3. (ሀ) እምነት ያለው ሰው ምን በረከቶች የማግኘት አጋጣሚ አለው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
2 ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በሰማይ ያለው አባቱ ሰዎችን ወደ ራሱ የሚስበው በወልድ አማካኝነት እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐ. 6:44, 65) አንድ ሰው በኢየሱስ ማመኑ ደግሞ የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ያስችለዋል። ይህም ከይሖዋ ጋር ዘላለማዊ የሆነ ዝምድና ለመመሥረት በር ይከፍታል። (ሮም 6:23) እንዲህ ያለ አስደናቂ በረከት ልናገኝ የቻልነው እንዴት ነው? እንደ ኃጢአታችን ቢሆን የሚገባን ሞት ነበር። (መዝ. 103:10) ይሖዋ ግን ትኩረት ያደረገው በመልካም ጎናችን ላይ ነው። በመሆኑም ምሥራቹን እንድንቀበል በጸጋው ልባችንን ከፈተልን። ስለሆነም በኢየሱስ ላይ እምነት በማዳበር እሱን መከተል ጀመርን፤ ይህ ደግሞ የዘላለም ሕይወት ተስፋ አስገኘልን።—1 ዮሐንስ 4:9, 10ን አንብብ።
3 ይሁንና እምነት ምንድን ነው? አምላክ ለወደፊቱ ጊዜ በረከቶችን እንዳዘጋጀልን ማወቅ ማለት ብቻ ነው? ከሁሉ በላይ ደግሞ እምነታችንን በተግባር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
‘በልብህ እመን’
4. እምነት ከጭንቅላት እውቀት የበለጠ ነገርን ይጨምራል የምንለው ለምንድን ነው?
4 አንድ ሰው እምነት አለው የሚባለው የአምላክን ዓላማዎች ስላወቀ ብቻ አይደለም። እምነት፣ አንድ ሰው ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲኖር የሚገፋፋ ኃይል ነው። ግለሰቡ አምላክ የሰው ልጆችን ለማዳን ባደረገው ዝግጅት ላይ እምነት ካለው ምሥራቹን ለሌሎች ለማካፈል ይነሳሳል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ በይፋ ብትናገር እንዲሁም አምላክ ከሞት እንዳስነሳው በልብህ ብታምን ትድናለህና። ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና፤ በአፉ ደግሞ እምነቱን በይፋ ተናግሮ ይድናል።”—ሮም 10:9, 10፤ 2 ቆሮ. 4:13
5. እምነት በጣም አስፈላጊ ባሕርይ የሆነው ለምንድን ነው? እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።
5 በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ከፈለግን እምነት ሊኖረን የሚገባ ከመሆኑም በላይ እምነታችን ምንጊዜም ጠንካራ መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው። አንድ ተክል እንዳይጠወልግ ውኃ ያስፈልገዋል፤ በተመሳሳይም እምነት ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን እንክብካቤ ሊደረግለት ይገባል። ከሰው ሠራሽ አትክልት በተለየ፣ ሕይወት ያለው ተክል ሁልጊዜ ለውጥ ያደርጋል። ውኃ ካጣ ይጠወልጋል፤ በቋሚነት ውኃ ካገኘ ደግሞ እየለመለመ ይሄዳል። በአንድ ወቅት ጤናማ የነበረ ተክልም እንኳ በቂ ውኃ ካላገኘ ሊደርቅ ይችላል። ከእምነታችን ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። እምነታችንን ችላ ካልነው ጠውልጎ መሞቱ አይቀርም። (ሉቃስ 22:32፤ ዕብ. 3:12) ተገቢውን እንክብካቤ ካደረግንለት ግን ጠንካራ ሆኖ ሊቀጥልና “እያደገ” ሊሄድ ይችላል፤ ይህም “በእምነት . . . ጤናሞች” ለመሆን ያስችለናል።—2 ተሰ. 1:3፤ ቲቶ 2:2
መጽሐፍ ቅዱስ እምነትን እንዴት ይገልጸዋል?
6. ዕብራውያን 11:1 እምነትን የሚገልጸው በየትኞቹ ሁለት መንገዶች ነው?
6 መጽሐፍ ቅዱስ እምነት ምን እንደሆነ በዕብራውያን 11:1 (ጥቅሱን አንብብ) ላይ ያብራራል። እምነት፣ ልናያቸው በማንችላቸው ሁለት ነገሮች ላይ ያተኮረ ነው፦ (1) ‘ተስፋ የተደረጉት ነገሮች።’ ይህም ወደፊት እንደሚፈጸሙ ተስፋ የተሰጠባቸው ሆኖም ገና ያልተፈጸሙ ነገሮችን፣ ለምሳሌ ክፋት ሁሉ እንደሚወገድና አዲስ ዓለም እንደሚመጣ የተሰጠንን ተስፋ ይጨምራል። (2) ‘በዓይን ባይታዩም እውን የሆኑ ነገሮች።’ እዚህ ጥቅስ ላይ “ተጨባጭ ማስረጃ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አንድ ነገር በዓይን ባይታይም እውን መሆኑን የሚያሳይ ማረጋገጫን ያመለክታል፤ ለምሳሌ ይሖዋ አምላክን፣ ኢየሱስ ክርስቶስንና መላእክትን በዓይን ማየት ባንችልም እውን መሆናቸውን እናውቃለን፤ በሰማይ ያለው የአምላክ መንግሥት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። (ዕብ. 11:3) ታዲያ ተስፋችን እንደሚፈጸም እርግጠኛ እንደሆንን እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተስፋ በተሰጠባቸው የማይታዩ ነገሮች እንደምናምን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? በንግግራችንና በድርጊታችን ነው፤ አለዚያ እምነታችን የተሟላ አይሆንም።
7. ኖኅ የተወው ምሳሌ እምነት ምን ነገሮችን እንደሚጨምር ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
7 ዕብራውያን 11:7 ኖኅ ስላሳየው እምነት ይናገራል፤ “ኖኅ ገና ስላልታዩት ነገሮች መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ከተቀበለ በኋላ አምላካዊ ፍርሃት ያሳየውና ቤተሰቡን ለማዳን መርከብ የሠራው በእምነት ነበር።” ኖኅ በታዘዘው መሠረት ትልቅ መርከብ መሥራቱ እምነት እንዳለው ያሳያል። ጎረቤቶቹ፣ ይህን የሚያህል ግዙፍ መርከብ የሚሠራው ለምን እንደሆነ ጠይቀውት መሆን አለበት። ታዲያ ኖኅ ለጥያቄያቸው መልስ ከመስጠት ተቆጥቦ ወይም ጉዳዩ እንደማይመለከታቸው ነግሯቸው ይሆን? በፍጹም! ኖኅ የነበረው እምነት፣ በድፍረት እንዲመሠክርና በዘመኑ የነበሩትን ሰዎች አምላክ ስለሚያመጣው ፍርድ እንዲያስጠነቅቅ አነሳስቶታል። ይሖዋ የነገረውን የሚከተለውን መልእክት ቃል በቃል ሳይደግምላቸው አልቀረም፦ “በእነሱ የተነሳ ምድር በዓመፅ ስለተሞላች ሥጋ ለባሽ የሆነውን ሁሉ ለማጥፋት ወስኛለሁ፤ . . . ከሰማያት በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃ አመጣለሁ። በምድር ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይጠፋል።” በተጨማሪም ኖኅ መዳን የሚችሉበትን ብቸኛ መንገድ ገልጾላቸው እንደሚሆን ጥያቄ የለውም፤ “ወደ መርከቡ መግባት ይኖርባችኋል” የሚለውን የይሖዋን ትእዛዝ ደግሞላቸዋል። ስለዚህ ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” በመሆንም እምነቱን በተግባር አሳይቷል።—ዘፍ. 6:13, 17, 18፤ 2 ጴጥ. 2:5
8. ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ክርስቲያኖች ያላቸውን እውነተኛ እምነት በመንፈስ መሪነት ያብራራው እንዴት ነው?
8 የያዕቆብ ደብዳቤ የተጻፈው ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ስለ እምነት ማብራሪያ ከሰጠ ብዙም ሳይቆይ ይመስላል። እንደ ጳውሎስ ሁሉ ያዕቆብም ክርስቲያኖች ያላቸው እውነተኛ እምነት፣ ተግባርንም እንደሚጨምር ገልጿል። ያዕቆብ “እምነትህን ከሥራ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔ ደግሞ እምነቴን በሥራ አሳይሃለሁ” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 2:18) ያዕቆብ ቀጥሎ የተናገረው ሐሳብ አንድን ነገር እንዲሁ አምኖ በመቀበልና እምነትን በተግባር በማሳየት መካከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ ይጠቁማል። ለምሳሌ አጋንንት አምላክ እንዳለ ያምናሉ፤ ሆኖም እውነተኛ እምነት አላቸው ሊባል አይችልም። እንዲያውም የአምላክ ዓላማዎች እንዳይፈጸሙ ለማድረግ የሚጥሩ መሆኑ እምነት እንደሌላቸው የሚያሳይ ነው። (ያዕ. 2:19, 20) ያዕቆብ አክሎም በጥንት ዘመን የኖረን የእምነት ሰው በመጥቀስ እንዲህ ብሏል፦ “አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያ ላይ ካቀረበ በኋላ የጸደቀው በሥራ አይደለም? እምነቱ ከሥራው ጋር አብሮ ይሠራ እንደነበረና ሥራው እምነቱን ፍጹም እንዳደረገው ትገነዘባለህ።” ከዚያም ያዕቆብ እምነት በሥራ መገለጽ እንዳለበት ለማሳየት “በእርግጥም አካል ያለ መንፈስ የሞተ እንደሆነ ሁሉ እምነትም ያለ ሥራ የሞተ ነው” በማለት ጽፏል።—ያዕ. 2:21-23, 26
9, 10. ሐዋርያው ዮሐንስ የጻፈው ሐሳብ እምነታችንን በተግባር ማሳየት አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?
9 ያዕቆብ ደብዳቤውን ከጻፈ ከ30 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ሐዋርያው ዮሐንስ ወንጌሉንና ሦስት ደብዳቤዎችን ጻፈ። ዮሐንስ፣ ክርስቲያኖች ያላቸውን እውነተኛ እምነት በተመለከተ የነበረው ግንዛቤ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በመንፈስ መሪነት ካሰፈሩት ሐሳብ ጋር ተመሳሳይ ነበር? “እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ” ተብሎ አንዳንድ ጊዜ የሚተረጎመውን የግሪክኛ ግስ ከሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ይበልጥ የተጠቀመበት ዮሐንስ ነው።
10 ለምሳሌ ያህል፣ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በወልድ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ የዘላለም ሕይወት አለው፤ ወልድን የማይታዘዝ ግን የአምላክ ቁጣ በላዩ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” (ዮሐ. 3:36 ግርጌ) ክርስቲያኖች ያላቸው እምነት የኢየሱስን መመሪያ እንዲታዘዙ ያነሳሳቸዋል። ኢየሱስ እምነታችንን በቀጣይነት በተግባር ማሳየት አስፈላጊ እንደሆነ የተናገረ ሲሆን ዮሐንስም የኢየሱስን ሐሳብ በተደጋጋሚ ጠቅሶታል።—ዮሐ. 3:16፤ 6:40፤ 11:25, 26፤ 14:12
11. እውነትን በማወቃችን አመስጋኞች መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
11 ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እውነትን ስለገለጠልንና በምሥራቹ እንድናምን ስላስቻለን ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ሉቃስ 10:21ን አንብብ።) ይሖዋ፣ “የእምነታችን ዋና ወኪል እና ፍጹም አድራጊ” በሆነው በልጁ በኩል ወደ ራሱ ስለሳበን ምንጊዜም ልናመሰግነው ይገባል። (ዕብ. 12:2) እንዲህ ላለው ጸጋ ያለንን አመስጋኝነት ለማሳየት በጸሎትና የአምላክን ቃል በማጥናት እምነታችንን ማጠናከራችንን መቀጠል ይኖርብናል።—ኤፌ. 6:18፤ 1 ጴጥ. 2:2
12. እምነታችንን በተግባር ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
12 ይሖዋ ቃል በገባቸው ተስፋዎች ላይ እምነት እንዳለን ምንጊዜም ማሳየት ይኖርብናል። ይህንንም የምናደርገው ሌሎች በግልጽ ሊያዩት በሚችሉት መንገድ ሊሆን ይገባል። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ሁልጊዜ እንሳተፋለን። በተጨማሪም “ለሁሉም፣ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች መልካም” ማድረጋችንን አናቋርጥም። (ገላ. 6:10) ከዚህም ሌላ ‘አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፍፈን በመጣል’ በመንፈሳዊ ሊያዳክሙን የሚችሉ ነገሮችን ለመከላከል ብርቱ ጥረት እናደርጋለን።—ቆላ. 3:5, 8-10
በአምላክ ማመን ለእምነታችን መሠረት ከሆኑት ነገሮች አንዱ ነው
13. ‘በአምላክ ማመን’ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ከምን ጋር ተመሳስሏል? ለምንስ?
13 መጽሐፍ ቅዱስ “ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ ወደ አምላክ የሚቀርብ ሁሉ እሱ መኖሩንና ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን ማመን ይኖርበታልና” ይላል። (ዕብ. 11:6) አንድ ሰው እውነተኛ ክርስቲያን እንዲሆንና በክርስትና ጎዳና መጓዙን እንዲቀጥል በሚያስፈልገው “መሠረት” ውስጥ ከሚካተቱት ነገሮች አንዱ “በአምላክ . . . ማመን” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዕብ. 6:1) ይህን መሠረት የጣሉ ክርስቲያኖች ደግሞ ‘ከአምላክ ፍቅር ሳይወጡ መኖር’ እንዲችሉ ‘በእምነታቸው ላይ’ ሌሎች አስፈላጊ ባሕርያትን መጨመር ያስፈልጋቸዋል።—2 ጴጥሮስ 1:5-7ን አንብብ፤ ይሁዳ 20, 21
14, 15. እምነት ከፍቅር ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
14 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች እምነትን በመቶዎች በሚቆጠሩ ጊዜያት መጥቀሳቸው ይህ ባሕርይ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል። የእምነትን ያህል በተደጋጋሚ የተጠቀሰ ሌላ ክርስቲያናዊ ባሕርይ የለም። ይህ ሲባል ታዲያ ከሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው ክርስቲያናዊ ባሕርይ እምነት ነው ማለት ነው?
15 ጳውሎስ፣ እምነትን ከፍቅር ጋር በማወዳደር “ተራራን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማንቀሳቀስ የሚያስችል እምነት ቢኖረኝ፣ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮ. 13:2) ኢየሱስ “ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?” ለሚለው ጥያቄ የሰጠው መልስ ለአምላክ ያለን ፍቅር በጣም አስፈላጊ ባሕርይ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ያሳያል። (ማቴ. 22:35-40) ፍቅር፣ እምነትን ጨምሮ አስፈላጊ የሆኑ በርካታ ክርስቲያናዊ ባሕርያትን አካትቶ ይዟል። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር . . . ሁሉን ያምናል” ይላል። ፍቅር ያለው ሰው፣ አምላክ እውነት በሆነው ቃሉ ውስጥ በተናገራቸው ነገሮች ያምናል።—1 ቆሮ. 13:4, 7
16, 17. እምነትና ፍቅር በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አንድ ላይ ጎላ ተደርገው የተገለጹት እንዴት ነው? ከሁለቱ የሚበልጠው የትኛው ነው? ለምንስ?
16 እምነትና ፍቅር አስፈላጊ ባሕርያት በመሆናቸው ክርስቲያን የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እነዚህን ሁለት ባሕርያት በተደጋጋሚ ጊዜያት፣ አብዛኛውን ጊዜም በአንድ ዓረፍተ ነገር ወይም ሐረግ ውስጥ ጎላ አድርገው ገልጸዋቸዋል። ጳውሎስ “የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር እንልበስ” በማለት ወንድሞቹን አሳስቧቸዋል። (1 ተሰ. 5:8) ጴጥሮስም “[ኢየሱስን] አይታችሁት ባታውቁም ትወዱታላችሁ። አሁን ባታዩትም እንኳ በእሱ ላይ እምነት እያሳያችሁ . . . ነው” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥ. 1:8) ያዕቆብ ደግሞ ቅቡዓን ወንድሞቹን “አምላክ በእምነት ባለጸጋ እንዲሆኑና እሱን ለሚወዱ ቃል የገባውን መንግሥት እንዲወርሱ ከዓለም አመለካከት አንጻር ድሆች የሆኑትን አልመረጠም?” በማለት ጠይቋቸዋል። (ያዕ. 2:5) ዮሐንስም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በእርግጥም [የአምላክ ትእዛዝ] ይህ ነው፦ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንድናምንና እሱ ባዘዘን መሠረት እርስ በርሳችን እንድንዋደድ ነው።”—1 ዮሐ. 3:23
17 እምነት አስፈላጊ ባሕርይ ቢሆንም አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች ከተፈጸሙና ክርስቲያኖች ተስፋ የሚያደርጓቸው ነገሮች እውን ከሆኑ በኋላ በእነዚህ ተስፋዎች ላይ እምነት ማሳደር አያስፈልገንም። ለአምላክና ለባልንጀራችን ያለን ፍቅር ግን ምንጊዜም እያደገ መሄድ ይኖርበታል። ጳውሎስ “እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ እነዚህ ሦስቱ ይቀጥላሉ፤ ከእነዚህ መካከል የሚበልጠው ግን ፍቅር ነው” ብሎ የጻፈው ለዚህ ነው።—1 ቆሮ. 13:13
ታላቅ የእምነት መገለጫ
18, 19. በዘመናችን ያለው ታላቅ የእምነት መገለጫ ምንድን ነው? ለዚህስ ሊመሰገን የሚገባው ማን ነው?
18 በዘመናችን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች በአምላክ መንግሥት ላይ ያላቸውን እምነት በተግባር አሳይተዋል። ይህም ከስምንት ሚሊዮን በላይ ዜጎች ያሉትን ዓለም አቀፋዊ መንፈሳዊ ገነት አስገኝቷል። በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ የአምላክ መንፈስ ፍሬ ጎልቶ ይታያል። (ገላ. 5:22, 23) በእርግጥም መንፈሳዊው ገነት የእውነተኛ እምነትና ፍቅር ታላቅ መገለጫ ነው!
19 ለዚህ ሊመሰገኑ የሚገባቸው ሰዎች ሳይሆኑ አምላካችን ነው። ይህ አስደናቂ ክንውን “የይሖዋ ስም እንዲገን” እያደረገ ነው፤ “እንዲሁም ፈጽሞ የማይጠፋ የዘላለም ምልክት ይሆናል።” (ኢሳ. 55:13) በእርግጥም ‘በእምነት አማካኝነት መዳን’ ማግኘታችን “የአምላክ ስጦታ” ነው። (ኤፌ. 2:8) መላዋ ምድር ፍጹም፣ ጻድቅና ደስተኛ በሆኑ የሰው ልጆች እስክትሞላ ድረስ መንፈሳዊ ገነታችን እየሰፋና እየለመለመ ይሄዳል፤ ይህም ለይሖዋ ስም ዘላለማዊ ውዳሴ ያመጣል። እንግዲያው ይሖዋ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳለን በተግባር ማሳየታችንን እንቀጥል!