‘በቃላት ሊገለጽ የማይችለው የአምላክ ነፃ ስጦታ’ ግድ ይበላችሁ
“በቃላት ሊገለጽ ለማይችለው ነፃ ስጦታው አምላክ የተመሰገነ ይሁን።”—2 ቆሮ. 9:15
1, 2. (ሀ) ‘በቃላት ሊገለጽ የማይችለው የአምላክ ነፃ ስጦታ’ ምን ነገሮችን ያካትታል? (ለ) በዚህ ርዕስ ሥር የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
ይሖዋ፣ አንድያ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ከሁሉ የላቀውን ስጦታ በፍቅር ተነሳስቶ ሰጥቶናል! (ዮሐ. 3:16፤ 1 ዮሐ. 4:9, 10) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን የአምላክ ስጦታ “በቃላት ሊገለጽ [የማይችል] ነፃ ስጦታ” በማለት ገልጾታል። (2 ቆሮ. 9:15) ይህን አገላለጽ የተጠቀመው ለምንድን ነው?
2 ጳውሎስ፣ አምላክ ቃል የገባቸው አስደናቂ ተስፋዎች በሙሉ እንደሚፈጸሙ ዋስትና የሚሆነው የክርስቶስ ፍጹም መሥዋዕት እንደሆነ ስለሚያውቅ ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:20ን አንብብ።) ‘በቃላት ሊገለጽ የማይችለው ይህ ነፃ ስጦታ’ ይሖዋ በኢየሱስ በኩል የሚያደርግልንን መልካም ነገሮች በሙሉ እንዲሁም የሚያሳየንን ታማኝ ፍቅር ያካትታል። በእርግጥም ስጦታው እጅግ አስደናቂ በመሆኑ የሰው ልጆች ሙሉ በሙሉ በሚረዱት መንገድ መግለጽ አስቸጋሪ ነው። እንዲህ ያለ ልዩ ስጦታ በመቀበላችን ምን ሊሰማን ይገባል? ደግሞስ ከይሖዋ ያገኘነው ስጦታ ረቡዕ፣ መጋቢት 23, 2016 የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ለማክበር ስንዘጋጅ ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?
ከአምላክ ያገኘነው ልዩ ስጦታ
3, 4. (ሀ) አንድ ስጦታ ሲሰጥህ ምን ይሰማሃል? (ለ) አንድ ሰው በፍቅር ተነሳስቶ ልዩ ስጦታ ቢሰጥህ ይህ በአኗኗርህ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
3 አንድ ስጦታ ሲሰጥህ እንደምትደሰት የታወቀ ነው። አንዳንድ ስጦታዎች ግን በጣም ልዩ ወይም ትልቅ ትርጉም ያላቸው በመሆናቸው በሕይወታችን ላይ ጉልህ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንጀል በመፈጸምህ የተነሳ ሞት ተፈርዶብሃል እንበል። ይሁንና ፈጽሞ የማታውቀው አንድ ሰው ከተሰበሰበው ሰው መሃል በድንገት ወጥቶ በአንተ ፋንታ ቅጣቱን ለመቀበል ራሱን አቀረበ። እስቲ አስበው፣ ግለሰቡ በአንተ ምትክ የሞትን ጽዋ ለመጎንጨት ፈቃደኛ ነው! ይህ ሰው የሰጠህ የላቀ ስጦታ ምን ስሜት ያሳድርብሃል?
4 ይህ ግለሰብ እንዲህ ያለ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያሳየህ መሆኑ፣ አኗኗርህን መለስ ብለህ እንድታጤንና ሕይወትህን የምትመራበትን መንገድ እንድትቀይር እንደሚያነሳሳህ የታወቀ ነው። ይበልጥ ለጋስና አፍቃሪ እንድትሆን አልፎ ተርፎም የበደሉህን እንኳ ይቅር እንድትል ያነሳሳህ ይሆናል። በአንተ ፋንታ ለመሞት ፈቃደኛ ለሆነው ሰው ምንጊዜም ባለዕዳ እንደሆንክ ይሰማሃል።
5. ከአምላክ ያገኘነው የቤዛው ስጦታ ከሌላ ከማንኛውም ስጦታ የሚልቀው እንዴት ነው?
5 ይሖዋ በክርስቶስ አማካኝነት የሰጠን ስጦታ በዚህ ምሳሌ ላይ ከተገለጸው ስጦታ በእጅጉ የላቀ ነው። (1 ጴጥ. 3:18) ለምን? በወረስነው ኃጢአት የተነሳ ሁላችንም የሞት ቅጣት ይጠብቀናል። (ሮም 5:12) አፍቃሪ የሆነው ይሖዋ ግን ኢየሱስ ወደ ምድር እንዲመጣና “ለሰው ሁሉ ሲል ሞትን” እንዲቀምስ ዝግጅት አድርጓል። (ዕብ. 2:9) ይሖዋ ይህን በማድረጉ ከሞት የታደገን ከመሆኑም ባሻገር ለሞት መንስኤ የሆነውን ነገር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የሚያስችለውን መሠረት ጥሏል። (ኢሳ. 25:7, 8፤ 1 ቆሮ. 15:22, 26) በኢየሱስ ላይ እምነት ያላቸው ሁሉ በክርስቶስ በሚመራው የአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድር ላይ በሰላምና በደስታ ለዘላለም የሚኖሩ ሲሆን ቅቡዓኑ ደግሞ በዚህ መንግሥት ውስጥ ተባባሪ ገዢዎች ይሆናሉ። (ሮም 6:23፤ ራእይ 5:9, 10) ይሖዋ የሰጠን ይህ ስጦታ የሚያስገኛቸው ሌሎች በረከቶችስ አሉ?
6. (ሀ) ከይሖዋ ያገኘነው ‘በቃላት ሊገለጽ የማይችል ነፃ ስጦታ’ ካስገኘልን በረከቶች መካከል ይበልጥ የምታደንቀው የትኛውን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ላይ የአምላክ ፍቅር ለተግባር ሊያነሳሳን የሚችልባቸውን የትኞቹን ሦስት አቅጣጫዎች እንመለከታለን?
6 ከይሖዋ ያገኘነው ስጦታ ከሚያስገኛቸው ጥቅሞች መካከል ማንኛውም በሽታ ሙሉ በሙሉ መወገዱ፣ ምድራችን ወደ ገነትነት መለወጧ እንዲሁም የሞቱ ሰዎች መነሳታቸው ይገኙበታል። (ኢሳ. 33:24፤ 35:5, 6፤ ዮሐ. 5:28, 29) ይሖዋና ውድ ልጁ ‘በቃላት ሊገለጽ የማይችል ነፃ ስጦታ’ ስለሰጡን እንደምንወዳቸው ጥያቄ የለውም። ሆኖም ‘የአምላክ ፍቅር ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?’ የሚል ጥያቄ ይነሳል። የአምላክ ፍቅር (1) የክርስቶስ ኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ እንድንከተል፣ (2) ለወንድሞቻችን ፍቅር እንድናሳይ እና (3) ሌሎችን ከልብ ይቅር እንድንል ሊያነሳሳን የሚገባው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
“ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል”
7, 8. ክርስቶስ ስላሳየን ፍቅር ምን ሊሰማን ይገባል? ይህ ፍቅር ምን እንድናደርግ ይገፋፋናል?
7 በመጀመሪያ፣ ክርስቶስ ኢየሱስ ያለው ፍቅር ለእሱ እንድንኖር ግድ ይለናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል” በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15ን አንብብ።) ክርስቶስ ላሳየን ተወዳዳሪ የሌለው ፍቅር የምንሰጠው ምላሽ ለእሱ ለመኖር ግድ እንደሚለን ወይም እንደሚያነሳሳን ጳውሎስ ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋ ያደረገልንን ነገር ሙሉ በሙሉ ስንገነዘብና ልባችን ለእሱ ባለን ፍቅር ሲሞላ በሙሉ ነፍሳችን ለክርስቶስ ኢየሱስ የመኖር ፍላጎት ያድርብናል። እንዲህ ያለ ፍላጎት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
8 ለይሖዋ ያለን ፍቅር፣ ክርስቶስን ለመምሰል ይኸውም የእሱን አካሄድ እንዲሁም ፈለጉን በጥብቅ ለመከተል ግድ ይለናል። (1 ጴጥ. 2:21፤ ) ታዛዦች በመሆን ለአምላክና ለክርስቶስ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እኔን የሚወደኝ ትእዛዛቴን የሚቀበልና የሚጠብቅ ነው። እኔን የሚወደኝን ሁሉ ደግሞ አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።”— 1 ዮሐ. 2:6ዮሐ. 14:21፤ 1 ዮሐ. 5:3
9. የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታዮች ምን ጫና ይደርስባቸዋል?
9 በመታሰቢያው በዓል ሰሞን፣ ስለ አኗኗራችን በቁም ነገር ማሰላሰላችን ጠቃሚ ነው። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በሕይወቴ ውስጥ የክርስቶስ ኢየሱስን ፈለግ በመከተል ረገድ በየትኞቹ አቅጣጫዎች ተሳክቶልኛል? ማሻሻያ ማድረግ የሚያስፈልገኝስ በየትኞቹ መስኮች ነው?’ በዚህ መንገድ ራሳችንን መመርመራችን አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም የዓለምን አካሄድ እንድንከተል ያለማቋረጥ ጫና ይደርስብናል። (ሮም 12:2) ካልተጠነቀቅን በዓለም ያሉ ፈላስፎች አልፎ ተርፎም በስፖርትና በሌሎች መስኮች ስማቸው የገነነ ሰዎች ደቀ መዛሙርት ልንሆን እንችላለን። (ቆላ. 2:8፤ 1 ዮሐ. 2:15-17) ታዲያ የሚደርስብንን ጫና መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው?
10. በመታሰቢያው በዓል ሰሞን የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን? ይህስ ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ምስል ተመልከት።)
10 በመታሰቢያው በዓል ሰሞን፣ ልብሶቻችንን እንዲሁም ያሉንን ፊልሞችና ሙዚቃዎች አልፎ ተርፎም በኮምፒውተራችን፣ በስልካችንና በታብሌታችን ላይ ያስቀመጥናቸውን ነገሮች መመርመሩ ጥሩ ነው። ልብሶቻችሁን ስትመለከቱ እንደሚከተለው ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦ ‘ኢየሱስ ወደሚገኝበት ቦታ የምሄድ ቢሆን ይህን ልብስ ለብሼ መሄድ ይጨንቀኛል?’ (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10ን አንብብ።) ‘ይህን ለብሼ ብሄድ፣ በቦታው ያሉት ሰዎች የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታይ መሆኔን ከአለባበሴ ማወቅ ይችላሉ?’ የፊልምና የሙዚቃ ምርጫችንን በተመለከተም ራሳችንን ተመሳሳይ ጥያቄዎች መጠየቃችን ተገቢ ነው። ‘ኢየሱስ ይህን ፊልም በመመልከት ወይም ይህን ሙዚቃ በማዳመጥ ሊዝናና ይችላል? ሞባይል ስልኬን ወይም ታብሌቴን ቢዋሰኝ እዚያ ላይ የሚያየው ነገር ያሳፍረኛል?’ የአንድን የቪዲዮ ጨዋታ ይዘት በምትመረምሩበት ወቅት ‘ይህ ጨዋታ ለምን እንደሚያስደስተኝ ለክርስቶስ መግለጽ ያስቸግረኛል?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። ለይሖዋ ያለን ፍቅር፣ አንድ ነገር ለክርስቶስ ደቀ መዝሙር ተገቢ ካልሆነ የቱንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍለን እንድናስወግደው ግድ ሊለን ይገባል። (ሥራ 19:19, 20) ራሳችንን ስንወስን፣ ከዚያ በኋላ ለራሳችን ሳይሆን ለክርስቶስ ለመኖር ቃል ገብተናል። በመሆኑም የክርስቶስን ፈለግ በጥብቅ እንዳንከተል እንቅፋት ሊሆንብን የሚችልን ማንኛውም ነገር ማስወገድ አለብን።—ማቴ. 5:29, 30፤ ፊልጵ. 4:8
11. (ሀ) ለይሖዋና ለኢየሱስ ያለን ፍቅር ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል? (ለ) ፍቅራችን በጉባኤ ውስጥ ሌሎችን በምን መንገድ እንድንረዳ ያነሳሳናል?
11 ለኢየሱስ ያለን ፍቅር በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በሙሉ ነፍሳችን እንድንካፈልም ሊያነሳሳን ይገባል። (ማቴ. 28:19, 20፤ ሉቃስ 4:43) በመታሰቢያው በዓል ወቅት በረዳት አቅኚነት በማገልገል በስብከቱ ሥራ 30 ወይም 50 ሰዓት ለማሳለፍ አጋጣሚ እናገኛለን። አንተስ ሁኔታህን አመቻችተህ እንዲህ ማድረግ ትችላለህ? ባለቤታቸውን በሞት ያጡ አንድ የ84 ዓመት አረጋዊ፣ ዕድሜያቸውና ጤናቸው በረዳት አቅኚነት ለማገልገል እንደማይፈቅድላቸው ተሰምቷቸው ነበር። ይሁንና በአካባቢው የሚገኙ አቅኚዎች እኚህን ወንድም ለመርዳት ፈለጉ። አቅኚዎቹ እኚህን ወንድም በመኪና ይወስዷቸው የነበረ ሲሆን እሳቸው ሊያገለግሉበት የሚችሉ ጥሩ ክልል መረጡላቸው፤ በመሆኑም ወንድም የ30 ሰዓት ግባቸው ላይ መድረስ ቻሉ። አንተስ በጉባኤህ የሚገኝ አንድ ክርስቲያን በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ረዳት አቅኚ ሆኖ በማገልገል የሚገኘውን ደስታ እንዲያጣጥም ልታግዘው ትችላለህ? እርግጥ ነው፣ ረዳት አቅኚ ሆነን ማገልገል የምንችለው ሁላችንም አይደለንም። ያም ቢሆን ያለንን ጊዜና ጉልበት ተጠቅመን ለይሖዋ የምናቀርበውን የውዳሴ መሥዋዕት መጠን ከፍ ማድረግ እንችላለን። እንዲህ ስናደርግ ልክ እንደ ጳውሎስ፣ ለክርስቶስ ያለን ፍቅር ግድ እንደሚለን እናሳያለን። የአምላክ ፍቅር ሌላስ ምን እንድናደርግ ያነሳሳናል?
እርስ በርሳችን የመዋደድ ግዴታ አለብን
12. የአምላክ ፍቅር ምን እንድናደርግ ግድ ይለናል?
12 ሁለተኛ፣ ሐዋርያው ዮሐንስ እንደገለጸው የአምላክ ፍቅር ወንድሞቻችንን እንድንወድ ያነሳሳናል። ዮሐንስ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ አምላክ የወደደን በዚህ መንገድ ከሆነ እኛም እርስ በርሳችን የመዋደድ ግዴታ አለብን” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐ. 4:7-11) አምላክ እንዲወደን ከፈለግን ወንድሞቻችንን የመውደድ ግዴታ እንዳለብን አምነን መቀበል ይኖርብናል። (1 ዮሐ. 3:16) ታዲያ ፍቅራችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
13. ኢየሱስ ሰዎችን በመውደድ ረገድ ምን ምሳሌ ትቷል?
13 ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እንመልከት። በምድር ላይ ባከናወነው አገልግሎቱ ወቅት፣ ዝቅ ተደርገው ለሚታዩ ሰዎች ልዩ ትኩረት ይሰጥ ነበር። የአካል ጉዳተኛ የሆኑትን ለምሳሌ አንካሶችን፣ ዓይነ ስውሮችን፣ መስማት የተሳናቸውንና ዱዳዎችን ፈውሷል። (ማቴ. 11:4, 5) በጊዜው የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ‘የተረገሙ’ አድርገው የሚመለከቷቸውን በመንፈሳዊ የተራቡ ሰዎች ማስተማር ያስደስተው ነበር። (ዮሐ. 7:49) ዝቅ ተደርገው የሚታዩትን እነዚህን ሰዎች ይወዳቸውና እነሱን ለማገልገል በትጋት ይሠራ ነበር።—ማቴ. 20:28
14. ለጉባኤህ አባላት ፍቅርህን ለማሳየት ምን ማድረግ ትችላለህ?
14 በመታሰቢያው በዓል ወቅት በጉባኤያችሁ ስላሉት ወንድሞችና እህቶች ጊዜ ወስዳችሁ ለማሰብና በዚህ መንገድ ኢየሱስን ለመምሰል አጋጣሚ ታገኛላችሁ። ይህን ስታደርጉ ፍቅር ብታሳዩአቸው የሚጠቀሙ ሰዎች እንዳሉ ማስተዋላችሁ አይቀርም። ምናልባትም እርዳታ የሚያሻቸው አረጋውያን ወንድሞችና እህቶች ይኖሩ ይሆናል። እነዚህን ውድ ወንድሞች ሄዳችሁ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ? ምግብ ልትወስዱላቸው፣ የቤት ውስጥ ሥራ ልታግዟቸው፣ ወደ ስብሰባ በመኪና ልትወስዷቸው ወይም አብረዋችሁ እንዲያገለግሉ ልትጋብዟቸው ትችሉ ይሆን? (ሉቃስ 14:12-14ን አንብብ።) የአምላክ ፍቅር ለወንድሞቻችን ፍቅራችንን ለማሳየት ሊያነሳሳን ይገባል።
ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ምሕረት ማሳየት
15. የአዳም ልጆች በመሆናችን ሁላችንም ምን መገንዘብ ይኖርብናል?
15 ሦስተኛ፣ የይሖዋ ፍቅር ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይቅር እንድንል ግድ ሊለን ይገባል። የመጀመሪያው ሰው የአዳም ልጆች በመሆናችን ሁላችንም ኃጢአትንና የኃጢአት ደሞዝ የሆነውን ሞትን ወርሰናል። ማናችንም ብንሆን “ቤዛው አያስፈልገኝም” ማለት አንችልም። በጣም ታማኝ የሆነ የአምላክ አገልጋይም እንኳ ይሖዋ በክርስቶስ በኩል ያሳየን ጸጋ የግድ ያስፈልገዋል። ሁላችንም ከፍተኛ ዕዳ እንደተሰረዘልን መገንዘብ ይኖርብናል። ይህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መልሱን ኢየሱስ በተናገረው አንድ ምሳሌ ላይ እናገኛለን።
16, 17. (ሀ) ኢየሱስ ከፍተኛ ዕዳ ያለበትን ባሪያ ይቅር ስላለው ንጉሥ ከተናገረው ምሳሌ ምን እንማራለን? (ለ) ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ማሰላሰልህ ምን እንድታደርግ አነሳስቶሃል?
16 ኢየሱስ፣ አንድ ንጉሥ 10,000 ታላንት ወይም 60,000,000 ዲናር ዕዳ የነበረበትን ባሪያውን ይቅር እንዳለው የሚገልጽ ምሳሌ ተናግሯል። ይህን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ዕዳ ይቅር የተባለለት ባሪያ ግን ከእሱ በጣም ያነሰ ዕዳ ይኸውም 100 ዲናር የነበረበትን ባልንጀራው የሆነውን ባሪያ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ አልሆነም። ንጉሡ፣ ምሕረት የተደረገለት ባሪያ የፈጸመውን ጭካኔ ሲሰማ በጣም ተቆጣ። ንጉሡ እንዲህ አለው፦ “አንተ ክፉ ባሪያ፣ ስለተማጸንከኝ ያን ሁሉ ዕዳ ተውኩልህ። ታዲያ እኔ ምሕረት እንዳደረግኩልህ ሁሉ አንተስ ባልንጀራህ ለሆነው ባሪያ ምሕረት ልታደርግለት አይገባም ነበር?” (ማቴ. 18:23-35 ግርጌ) ንጉሡ ለባሪያው ያሳየው አስደናቂ ምሕረት፣ ያ ባሪያ ባልንጀራው ለሆነው ባሪያ ምሕረት እንዲያሳይ ሊገፋፋው ይገባ ነበር። እኛስ የይሖዋ ፍቅርና ምሕረት ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
17 በመታሰቢያው በዓል ሰሞን፣ በወንድሞቻችን ወይም በእህቶቻችን ላይ ቂም ይዘን እንደሆነ ቆም ብለን ማሰብ ይኖርብናል። ቂም ይዘን ከሆነ “ይቅር ለማለት ዝግጁ” የሆነውን ይሖዋን ለመምሰል ይህ ወቅት ግሩም አጋጣሚ ነው። (ነህ. 9:17፤ መዝ. 86:5) ይሖዋ ከፍተኛ መጠን ያለውን ዕዳችንን በመሰረዝ ላደረገልን ነገር አድናቆት ካለን እኛም ሌሎችን ከልባችን ይቅር ለማለት እንነሳሳለን። ለሌሎች ፍቅርና ምሕረት የማናሳይ ከሆነ አምላክ ሊወደን ወይም ይቅር ሊለን አይችልም። (ማቴ. 6:14, 15) ይቅር ማለታችን የደረሰብንን በደል ባያስቀረውም በወደፊት ሕይወታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጥርጥር የለውም።
18. አንዲት እህት በጉባኤዋ የነበሩ አረጋዊት እህትን ባሕርይ ችላ ለመኖር የአምላክ ፍቅር የረዳት እንዴት ነው?
18 ብዙዎቻችን ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር በየዕለቱ ‘መቻቻል’ ይከብደን ይሆናል። (ቆላስይስ 3:13, 14ን እና ኤፌሶን 4:32ን አንብብ።) አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ሊሊ የተባለች አንዲት ያላገባች እህት ካሮል የተባሉ በጉባኤዋ የነበሩ አንዲት መበለትን በራሷ ተነሳስታ ታግዛቸዋለች። [1] ሊሊ እህት ካሮልን በመኪና የሚፈልጉበት ቦታ ታደርሳቸዋለች፣ ገበያ ወጥታ ዕቃ ትገዛላቸዋለች እንዲሁም በሌሎች መንገዶች ደግነት ታሳያቸዋለች። ሊሊ ይህን ሁሉ ብታደርግም እህት ካሮል ሁልጊዜ ነቃፊና አስቸጋሪ ነበሩ። ያም ሆኖ ሊሊ ትኩረት ያደረገችው በእህት ካሮል መልካም ባሕርያት ላይ ነው። እህት ካሮል በጠና ታመው ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ሊሊ ለዓመታት ረድታቸዋለች። ሊሊ እንዲህ ብላለች፦ “እህት ካሮልን በትንሣኤ ለማግኘት እጓጓለሁ። ፍጹም ሆነው ማየት እፈልጋለሁ።” በእርግጥም የአምላክ ፍቅር ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ተቻችለን እንድንኖርና ሰብዓዊ አለፍጽምና ጨርሶ የሚወገድበትን ጊዜ ለማየት እንድንጓጓ ግድ ይለናል።
19. ‘በቃላት ሊገለጽ የማይችለው የአምላክ ነፃ ስጦታ’ ምን እንድታደርግ ግድ ይልሃል?
19 በእርግጥም ይሖዋ ‘በቃላት ሊገለጽ የማይችል ነፃ ስጦታ’ ሰጥቶናል። ይህን ውድ ስጦታ መቼም ቢሆን አቅልለን አንመልከተው። በተለይ የመታሰቢያው በዓል በሚከበርበት በዚህ ወቅት፣ ይሖዋና ኢየሱስ ባደረጉልን ነገር ሁሉ ላይ በአድናቆት እናሰላስል። ይሖዋና ኢየሱስ ያሳዩን ፍቅር የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ እንድንከተል፣ ለወንድሞቻችን ፍቅር እንድናሳይ እንዲሁም ወንድሞቻችንን ከልብ ይቅር እንድንል ግድ ይበለን።
^ [1] (አንቀጽ 18) በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።