በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አለመግባባቶችን በፍቅር መፍታት

አለመግባባቶችን በፍቅር መፍታት

‘እርስ በርሳችሁ ሰላም ይኑራችሁ።’—ማር. 9:50

መዝሙሮች፦ 39, 77

1, 2. በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ አንዳንዶች ያጋጠሟቸው ምን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተጠቅሰዋል? ይህስ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት በግለሰቦች መካከል ስለተፈጠሩ ግጭቶች አስበህ ታውቃለህ? እስቲ በዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ምዕራፎች ላይ የተገለጹትን ብቻ እንመልከት። ቃየን አቤልን ገድሎታል (ዘፍ. 4:3-8)፤ ላሜህም የመታውን አንድ ወጣት ገድሏል (ዘፍ. 4:23)፤ በአብርሃም (በአብራም) እና በሎጥ እረኞች መካከል ጠብ ተፈጥሯል (ዘፍ. 13:5-7)፤ ሣራ (ሦራ) አጋር ስለናቀቻት በአብርሃም ላይ ተቆጥታለች (ዘፍ. 16:3-6)፤ እስማኤል ባገኘው ሰው ሁሉ ላይ እጁን ያነሳል፤ ያገኘውም ሰው ሁሉ እጁን ያነሳበታል።—ዘፍ. 16:12

2 እነዚህ ግጭቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩት ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ፍጽምና የሚጎድላቸው የሰው ልጆች፣ በመካከላቸው ያለው ሰላም እንዳይደፈርስ መጠንቀቅ ያለባቸው ለምን እንደሆነ እንዲማሩ ለመርዳት ነው። በተጨማሪም ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስገነዝበናል። በገሃዱ ዓለም የነበሩ ሰዎች ስለገጠሟቸው ችግሮች የሚያወሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን በማንበብ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ያስገኘላቸውን ውጤት መመልከታችን እኛም በሕይወታችን ውስጥ ተመሳሳይ ሁኔታ ሲያጋጥመን የእነሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል። በእርግጥም እነዚህ ዘገባዎች እንዲህ ያሉ ችግሮች ሲያጋጥሙን ምን ማድረግ እንዳለብንና እንደሌለብን ለመወሰን ይረዱናል።—ሮም 15:4

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ የይሖዋ አገልጋዮች አለመግባባቶችን መፍታት ያለባቸው ለምን እንደሆነና በዚህ ረገድ ጥሩ ውጤት ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን። በተጨማሪም አለመግባባቶችን ለመፍታት እንዲሁም ከባልንጀሮቻቸውም ሆነ ከይሖዋ አምላክ ጋር ያላቸውን ጥሩ ግንኙነት ይዘው ለመቀጠል የሚረዷቸውን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመለከታለን።

የአምላክ አገልጋዮች አለመግባባቶችን መፍታት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?

4. በዚህ ዓለም ውስጥ የተስፋፋው ምን ዓይነት አስተሳሰብ ነው? ይህስ ምን አስከትሏል?

4 በሰዎች መካከል ለሚፈጠሩት ግጭቶችና አለመግባባቶች ዋነኛው ተጠያቂ ሰይጣን ነው። ሰይጣን በኤደን ገነት ያነሳው ክርክር፣ ‘እያንዳንዱ ግለሰብ ያለ አምላክ እርዳታ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መወሰን ይችላል እንዲሁም ይህን ማድረግ ያለበት ራሱ ግለሰቡ ነው’ የሚል ነበር። (ዘፍ. 3:1-5) ይህ ያስከተለው ውጤት በግልጽ የሚታይ ነው። በራስ የመመራት መንፈስ ሰዎች የኩራት፣ የራስ ወዳድነትና የፉክክር መንፈስ እንዲያሳዩ ያደርጋል፤ ይህ ዓለም የተሞላው ደግሞ እንዲህ ባሉ ሰዎች ነው። በዚህ መንፈስ መመራት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው፣ አንድ ግለሰብ የሚያደርገው ነገር በሌሎች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንም ይሁን ምን የራሱን ፍላጎት ብቻ ማርካቱ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጸውን የሰይጣንን ሐሳብ በተዘዋዋሪ መንገድ እየደገፈ ነው። ይህ ዓይነቱ የራስ ወዳድነት አካሄድ ጠብ እንዲፈጠር ያደርጋል። “በቀላሉ የሚቆጣ ሰው ጠብ ያስነሳል፤ ግልፍተኛ የሆነም ብዙ በደል ይፈጽማል” የሚለውን ጥቅስ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው።—ምሳሌ 29:22

5. ኢየሱስ፣ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚረዳ ምን ምክር ሰጥቷል?

5 ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስ፣ የግል ጥቅማቸውን የሚነካ ቢሆንም እንኳ ሰላምን እንዲፈልጉ ሰዎችን አስተምሯል። ኢየሱስ አለመግባባቶችን ወይም ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን መፍታት ስለሚቻልበት መንገድ በተራራው ስብከቱ ላይ ግሩም ምክር ሰጥቷል። ለምሳሌ ደቀ መዛሙርቱ ገሮችና ሰላም ፈጣሪዎች እንዲሆኑ፣ ተቆጥተው እንዳይቆዩ፣ አለመግባባቶችን ቶሎ እንዲፈቱ እንዲሁም ጠላቶቻቸውን እንዲወዱ አሳስቧቸዋል።—ማቴ. 5:5, 9, 22, 25, 44

6, 7. (ሀ) አለመግባባቶችን ወዲያውኑ መፍታት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች የትኞቹን ጥያቄዎች ራሳቸውን ሊጠይቁ ይገባል?

6 ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር ፈቃደኞች ካልሆንን መጸለያችን፣ መሰብሰባችን፣ ማገልገላችንም ሆነ በሌሎች የአምልኮ እንቅስቃሴዎች መካፈላችን ከንቱ ነው። (ማር. 11:25) ሌሎች የፈጸሙብንን በደል ይቅር ለማለት ፈቃደኞች ካልሆንን የአምላክ ወዳጆች መሆን አንችልም።—ሉቃስ 11:4ን እና ኤፌሶን 4:32ን አንብብ።

7 እያንዳንዱ ክርስቲያን ሌሎችን ይቅር ስለ ማለትም ሆነ ከሌሎች ጋር ስላለው ሰላማዊ ግንኙነት በቁም ነገር ሊያስብበት ይገባል፤ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በሐቀኝነት ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል፦ የእምነት ባልንጀሮቼን በነፃ ይቅር እላለሁ? ከእነሱ ጋር መሆን ያስደስተኛል? ይሖዋ አገልጋዮቹ ሌሎችን ይቅር እንዲሉ ይጠብቅባቸዋል። በመሆኑም ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብህ ሕሊናህ የሚነግርህ ከሆነ በዚህ ረገድ እንዲረዳህ ይሖዋን በጸሎት ጠይቀው። የሰማዩ አባታችን በትሕትና የቀረቡ እንዲህ ያሉ ጸሎቶችን ሰምቶ ምላሽ ይሰጣል።—1 ዮሐ. 5:14, 15

የተፈጸመብህን በደል ችላ ብለህ ማለፍ ትችላለህ?

8, 9. ቅር ሊያሰኝ የሚችል ነገር ሲያጋጥመን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

8 ሁላችንም ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም ይዋል ይደር እንጂ አንድ ግለሰብ ስሜትህን የሚጎዳ ነገር ሊናገር ወይም ሊያደርግ ይችላል። ይህ ሊያጋጥም የሚችል ነገር ነው። (መክ. 7:20፤ ማቴ. 18:7) በዚህ ወቅት ምን ታደርጋለህ? የሚከተለውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት፦ አንዲት እህት፣ የተወሰኑ የይሖዋ ምሥክሮች በተገኙበት ግብዣ ላይ የነበሩ ሁለት ወንድሞችን ሰላም አለቻቸው፤ ሆኖም ሰላም ያለችበት መንገድ አንደኛውን ወንድም አላስደሰተውም። ሁለቱ ወንድሞች ብቻቸውን ሲሆኑ፣ በእህት ቅር የተሰኘው ወንድም የተናገረችውን ነገር አንስቶ ይነቅፋት ጀመረ። ሌላኛው ወንድም ግን ይህች እህት ለ40 ዓመታት ያህል በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ይሖዋን በታማኝነት እንዳገለገለች ካስታወሰው በኋላ ይህን ያለችው እሱን ለመጉዳት አስባ እንዳልሆነ አስረግጦ ነገረው። የመጀመሪያው ወንድም ነገሩን ለአፍታ ካሰበበት በኋላ “ልክ ነህ” ብሎ መለሰለት። በመሆኑም ጉዳዩ በዚያው ተቋጨ።

9 ከዚህ ተሞክሮ ምን ትምህርት ማግኘት ይቻላል? ቅር ሊያሰኝህ የሚችል ሁኔታ ሲፈጠር ምላሽ የምትሰጥበት መንገድ ጉዳዩ እንዲባባስ ወይም በአጭሩ እንዲቀጭ ሊያደርግ ይችላል። አፍቃሪ የሆነ ሰው ጥቃቅን ስህተቶችን ችላ ብሎ ያልፋል። (ምሳሌ 10:12ን እና 1 ጴጥሮስ 4:8ን አንብብ።) ‘በደልን የሚተው’ ሰው በይሖዋ ፊት ‘ውብ’ ነው። (ምሳሌ 19:11፤ መክ. 7:9) በመሆኑም አንድ ሰው ደግነት ወይም አክብሮት የጎደለው ነገር እንዳደረገብህ ከተሰማህ በቅድሚያ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ጉዳዩን ችላ ብዬ ማለፍ እችላለሁ? ያን ያህል አክብጄ ልመለከተው የሚገባ ነገር ነው?’

10. (ሀ) አንዲት እህት አሉታዊ አስተያየት ሲሰነዘርባት መጀመሪያ ምን አደረገች? (ለ) ይህች እህት ሰላሟን እንዳታጣ የረዳት የትኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ ነው?

10 ሌሎች ስለ እኛ የሚናገሩትን አሉታዊ ነገር ችላ ብሎ ማለፍ ቀላል ላይሆን ይችላል። ሉሲ የተባለችን አቅኚ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ስለ አገልግሎቷና ጊዜዋን ስለምትጠቀምበት መንገድ አሉታዊ አስተያየት ተሰንዝሮባት ነበር። ሉሲ ሁኔታው ስላበሳጫት የጎለመሱ ወንድሞችን አማከረች። እንዲህ ብላለች፦ “የሰጡኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር፣ ሌሎች ስለሚሰነዝሩት አስተያየት ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረኝና ከሁሉ በላይ ሊያሳስበኝ የሚገባው ይሖዋ ለእኔ ያለው አመለካከት መሆኑን እንድገነዘብ ረድቶኛል።” ሉሲ በማቴዎስ 6:1-4 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ማንበቧ አበረታቷታል። (ጥቅሱን አንብብ።) ይህ ጥቅስ ግቧ ይሖዋን ማስደሰት ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝቧታል። “ሰዎች ስለማደርገው ነገር አሉታዊ አስተያየት ቢሰጡም ደስታዬን አላጣሁም፤ ምክንያቱም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት አቅሜ የፈቀደውን ያህል ጥረት እያደረግኩ እንደሆነ አውቃለሁ” በማለት ተናግራለች። ሉሲ እዚህ መደምደሚያ ላይ ከደረሰች በኋላ የሚሰነዘርባትን አሉታዊ አስተያየት ችላ ብላ በማለፍ ጥበበኛ መሆኗን አሳይታለች።

የተፈጸመው በደል ከባድ ሲሆን

11, 12. (ሀ) አንድ ክርስቲያን፣ ወንድሙ በእሱ ላይ “ቅር የተሰኘበት ነገር” እንዳለ ከተሰማው ምን ማድረግ ይኖርበታል? (ለ) አብርሃም የተፈጠረውን ችግር ከፈታበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

11 “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን።” (ያዕ. 3:2) አንድ ወንድም፣ አንተ በተናገርከው ወይም ባደረግከው ነገር ቅር እንደተሰኘ ብታውቅ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “መባህን ወደ መሠዊያው ባመጣህ ጊዜ ወንድምህ በአንተ ቅር የተሰኘበት ነገር እንዳለ ትዝ ካለህ መባህን በመሠዊያው ፊት ትተህ ሂድ። በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።” (ማቴ. 5:23, 24) ኢየሱስ በሰጠው በዚህ ምክር መሠረት ከወንድምህ ጋር ተነጋገር። ግብህ ምን እንደሆነ አትርሳ። ዓላማህ ወንድምህም ጥፋት እንዳለበት ማሳመን ሳይሆን ስህተትህን አምነህ በመቀበል ሰላም መፍጠር ነው። ከሁሉ በላይ ሊያሳስበን የሚገባው ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ማድረግ ነው።

12 በመግቢያችን ላይ፣ በአብርሃምና የወንድሙ ልጅ በሆነው በሎጥ መካከል ክፍፍል ሊፈጥር የሚችል ጉዳይ ተከስቶ እንደነበር የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ተመልክተናል፤ ይሁንና እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ችግሩን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ፈተውታል። ሁለቱም ሰዎች ከብቶች ነበሯቸው፤ በግጦሽ መሬት ምክንያት ሳይሆን አይቀርም በእረኞቻቸው መካከል ጠብ ተነሳ። ሆኖም አብርሃም የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ሲል፣ ሎጥ ለእሱና ለቤተሰቡ መኖሪያ የሚሆነውን ቦታ መርጦ እንዲወስድ ቅድሚያውን ሰጠው። (ዘፍ. 13:1, 2, 5-9) እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! አብርሃም የራሱን ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ሰላም የሚሰፍንበትን መንገድ ፈልጓል። እንዲህ ያለ ደግነት በማሳየቱ ተጎድቷል? በፍጹም። ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ ታላቅ በረከት እንደሚያፈስለት ቃል ገብቶለታል። (ዘፍ. 13:14-17) አምላክ፣ አገልጋዮቹ ከመለኮታዊ መመሪያዎች ጋር የሚስማማ እርምጃ ለመውሰድና አለመግባባቶችን በፍቅር ለመፍታት ጥረት በማድረጋቸው ምክንያት ዘላቂ ጉዳት እንዲደርስባቸው ፈጽሞ አይፈቅድም። [1]

13. አንድ የበላይ ተመልካች፣ አንድ ወንድም ደግነት በጎደለው መንገድ ሲያናግረው ምን አደረገ? ከዚህ ተሞክሮ ምን ትምህርት እናገኛለን?

13 እስቲ በዘመናችን የተከሰተን አንድ ሁኔታ እንመልከት። አዲስ የተሾመ አንድ የትላልቅ ስብሰባዎች የበላይ ተመልካች፣ በአንድ የሥራ ክፍል ውስጥ መሥራት ይችል እንደሆነ ለመጠየቅ ለአንድ ወንድም ስልክ ደወለ፤ ሆኖም የተደወለለት ወንድም ደዋዩን ደግነት በጎደለው መንገድ ካናገረው በኋላ ስልኩን ዘጋበት። ቀደም ሲል በዚህ ቦታ ላይ የነበረው የበላይ ተመልካች የዚህን ወንድም ስሜት ጎድቶት ነበር። አዲሱ የበላይ ተመልካች፣ ወንድም በቁጣ ሲገነፍልበት አልተበሳጨም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሁኔታውን ችላ ብሎ አልተወውም። ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ ይህ የበላይ ተመልካች ለወንድም በድጋሚ ደወለለት፤ ከዚያም ከዚህ በፊት ተገናኝተው እንደማያውቁ ከገለጸለት በኋላ ጉዳዩን ለመፍታት ተገናኝተው እንዲወያዩ ሐሳብ አቀረበለት። በዚህም መሠረት ከሳምንት በኋላ አንድ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ተገናኙ። ከጸለዩ በኋላ ለአንድ ሰዓት ያህል ተነጋገሩ፤ በዚህ ወቅት ወንድም ከዚህ ቀደም ስላጋጠመው ሁኔታ አጫወተው። የበላይ ተመልካቹ በደግነት ካዳመጠው በኋላ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦችን አካፈለው፤ በዚህ መንገድ ችግሩን በሰላማዊ ሁኔታ ፈቱት። ቅር ተሰኝቶ የነበረው ወንድም፣ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ማገልገሉን የቀጠለ ሲሆን የበላይ ተመልካቹ ጉዳዩን በተረጋጋና ደግነት በተሞላበት መንገድ በመያዙ አመስጋኝ ነው።

ለሽማግሌዎች መንገር ይኖርብሃል?

14, 15. (ሀ) ማቴዎስ 18:15-17 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ የሚሆነው መቼ ነው? (ለ) ኢየሱስ የጠቀሳቸው ሦስት እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው? ግባችንስ ምን መሆን ይኖርበታል?

14 በክርስቲያኖች መካከል የሚፈጠሩ አብዛኞቹ አለመግባባቶች በራሳቸው በግለሰቦቹ ብቻ መፈታት ይችላሉ፤ ደግሞም እንዲህ መደረግ አለበት። ይሁንና ኢየሱስ እንደተናገረው አንዳንድ ጉዳዮችን ለጉባኤው መንገር ሊያስፈልግ ይችላል። (ማቴዎስ 18:15-17ን አንብብ።) አንድ ግለሰብ የበደለውን ወንድም፣ ምሥክሮችን እንዲሁም ጉባኤውን ለመስማት ፈቃደኛ ባይሆንስ? ይህ ሰው “እንደ አሕዛብና እንደ ቀረጥ ሰብሳቢ” መቆጠር ይኖርበታል። ይህም በዛሬው ጊዜ ውገዳ ብለን የምንጠራው እርምጃ ነው። እንዲህ ዓይነት ከባድ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑ የተፈጸመው ‘በደል’ ቀላል አለመግባባት ብቻ እንዳልሆነ ያሳያል። ከዚህ ይልቅ ጉዳዩ (1) የሚመለከታቸው ግለሰቦች ከተስማሙ እነሱ ራሳቸው ሊፈቱት የሚችሉ (2) ካልፈቱት ግን ለውገዳ የሚያበቃ ከባድ በደል መሆን አለበት። እንዲህ ያለው በደል፣ ከማጭበርበር ወይም የአንድን ሰው ስም ሆን ብሎ ከማጥፋት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ የጠቀሳቸው ሦስቱም እርምጃዎች ተግባራዊ የሚደረጉት ከላይ ያሉት ሁለት ሁኔታዎች ከተሟሉ ብቻ ነው። እንዲህ ያለው በደል እንደ ምንዝር፣ ግብረ ሰዶም፣ ክህደት፣ ጣዖት አምልኮ ወይም እነዚህን የመሳሰሉ ከባድ ኃጢአቶችን እንደማይጨምር ግልጽ ነው፤ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን የግድ ለጉባኤ ሽማግሌዎች ማሳወቅ ይገባል።

የበደለህን ወንድምህን ለማትረፍ ስትል እሱን በተደጋጋሚ ማነጋገር ሊያስፈልግህ ይችላል (አንቀጽ 15ን ተመልከት)

15 ኢየሱስ ይህን ምክር የሰጠው ወንድማችንን በፍቅር ተነሳስተን እንድንረዳ በማሰብ ነው። (ማቴ. 18:12-14) በመጀመሪያ፣ ሌሎች ጣልቃ ሳይገቡ ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት ማድረግ ተገቢ ነው። በደል የፈጸመውን ሰው በተደጋጋሚ ጊዜ ማነጋገር አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ይህ ጥረት ካልተሳካ በደል የፈጸመውን ሰው ስለ ጉዳዩ በሚያውቁ ምሥክሮች ፊት ወይም ግለሰቡ በደል መፈጸም አለመፈጸሙን ለመወሰን በሚችሉ ሌሎች ሰዎች ፊት ማነጋገር አስፈላጊ ነው። ከእነሱ ጋር ሆነህ ጉዳዩን መፍታት ከቻልክ “ወንድምህን ታተርፋለህ።” ጉዳዩን ለሽማግሌዎች ማቅረብ የሚኖርብህ፣ ከበደለህ ሰው ጋር ያለህን አለመግባባት ለመፍታት ያደረግከው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ከቀረ ብቻ ነው።

16. ኢየሱስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ አለመግባባቶችን ውጤታማና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ያስችላል የምንለው ለምንድን ነው?

16 በማቴዎስ 18:15-17 ላይ የተገለጹትን ሦስቱንም እርምጃዎች መውሰድ የሚጠይቁ ሁኔታዎች ብዙ ጊዜ አያጋጥሙም። ይህ ደግሞ ደስ የሚል ነገር ነው፤ ብዙ ጊዜ ኃጢአተኛው ስህተቱን አምኖ የተፈጠረውን አለመግባባት ያስተካክላል፤ በመሆኑም ከጉባኤ አይወገድም። የተበደለው ግለሰብ፣ ከዚህ በኋላ ወንድሙን ለመክሰስ የሚያበቃ ምክንያት አይኖረውም፤ እንዲያውም ወንድሙን ይቅር ለማለት ሊመርጥ ይችላል። ሆኖም አለመግባባት ሲፈጠር ጉዳዩን ቶሎ ወደ ሽማግሌዎች መውሰድ ተገቢ እንዳልሆነ ኢየሱስ የሰጠው ምክር ይጠቁማል። ሽማግሌዎች ጣልቃ ሊገቡ የሚችሉት የመጀመሪያዎቹ ሁለት እርምጃዎች ከተወሰዱና በደል መፈጸሙን የሚያሳምን ተጨባጭ ማስረጃ ከተገኘ ብቻ ነው።

17. እርስ በርስ ባለን ግንኙነት ‘ሰላምን ስንፈልግ’ ምን በረከቶች እናገኛለን?

17 በዚህ ሥርዓት ውስጥ እስካለን ድረስ ፍጹም ባለመሆናችን ምክንያት ሌሎችን ማስቀየማችን አይቀርም። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ መጻፉ ተገቢ ነው፦ “በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር ይህ ሰው መላ ሰውነቱንም መቆጣጠር የሚችል ፍጹም ሰው ነው።” (ያዕ. 3:2) አለመግባባቶችን ለመፍታት ከፈለግን ‘ሰላምን ለመፈለግና ለመከተል’ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (መዝ. 34:14) ሰላም ፈጣሪዎች ከሆንን ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት ይኖረናል፤ እንዲሁም የጉባኤው አንድነት እንዲጠናከር እናደርጋለን። (መዝ. 133:1-3) ከሁሉ በላይ ደግሞ ‘ሰላም ከሚሰጠው’ ከይሖዋ አምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ይኖረናል። (ሮም 15:33) አለመግባባቶችን በፍቅር የሚፈቱ ሰዎች እንዲህ ያሉ በረከቶችን ማግኘት ይችላሉ።

^ [1] (አንቀጽ 12) ቀጥሎ የተጠቀሱት ሰዎችም በመካከላቸው የተፈጠረውን አለመግባባት ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት ችለዋል፦ ያዕቆብና ኤሳው (ዘፍ. 27:41-45፤ 33:1-11)፤ ዮሴፍና ወንድሞቹ (ዘፍ. 45:1-15) እንዲሁም ጌድዮንና የኤፍሬም ሰዎች። (መሳ. 8:1-3) ምናልባት አንተም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሌሎች ምሳሌዎችን ታስታውስ ይሆናል።