በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ አሁንም ሕይወትህን እየለወጠው ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ አሁንም ሕይወትህን እየለወጠው ነው?

“አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።”—ሮም 12:2

መዝሙሮች፦ 61, 52

1-3. (ሀ) ከተጠመቅን በኋላ የትኞቹን ለውጦች ማድረግ ይከብደን ይሆናል? (ለ) ለውጥ ማድረግ ከጠበቅነው በላይ ከባድ ሲሆንብን የትኞቹ ጥያቄዎች ይፈጠሩብን ይሆናል? (በመግቢያው ላይ ያሉትን ፎቶግራፎች ተመልከት።)

 ኬቨን [1] እውነትን ሲሰማ ከምንም በላይ የተመኘው ነገር ከይሖዋ ጋር የተቀራረበ ዝምድና መመሥረት ነበር። ይሁንና ቁማር መጫወት፣ ማጨስ፣ መስከርና ዕፅ መውሰድ ለዓመታት የሕይወቱ ክፍል ሆኖ ቆይቷል። ኬቨን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ከፈለገ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዛቸውን እነዚህን ልማዶቹን መተው ነበረበት። በይሖዋ በመታመን እንዲሁም ሕይወትን የመለወጥ ኃይል ባለው በአምላክ ቃል እርዳታ ይህን ማድረግ ችሏል።—ዕብ. 4:12

2 ኬቨን ከተጠመቀ በኋላስ በሕይወቱ ውስጥ ለውጥ ማድረጉን አቁሞ ይሆን? በፍጹም፤ ምክንያቱም ክርስቲያናዊ ባሕርያትን በማዳበርና ይበልጥ እያሻሻለ በመሄድ ረገድ ገና ብዙ መሥራት ነበረበት። (ኤፌ. 4:31, 32) ለምሳሌ ያህል፣ ግልፍተኛ በመሆኑ ቁጣውን መቆጣጠር ከጠበቀው በላይ ከባድ ሆኖበት ነበር። ኬቨን “መጥፎ ልማዶችን ከማሸነፍ ይበልጥ የከበደኝ ቁጣዬን መቆጣጠር ነበር!” ብሏል። ሆኖም ልባዊ ጸሎት በማቅረብና መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት በማጥናት አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ ችሏል።

3 እንደ ኬቨን ሁሉ ብዙዎቻችን ከመጠመቃችን በፊት ሕይወታችንን መሠረታዊ ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር ለማስማማት ጉልህ የሆኑ ለውጦችን ማድረግ አስፈልጎናል። ከተጠመቅን በኋላ ደግሞ አምላክንና ክርስቶስን በቅርብ መከተል እንድንችል አንዳንድ ለውጦችን ማድረጋችንን መቀጠል እንደሚያስፈልገን ተገንዝበናል፤ እነዚህ ለውጦች ያን ያህል ጎልተው የማይታዩ ሊሆኑ ይችላሉ። (ኤፌ. 5:1, 2፤ 1 ጴጥ. 2:21) ለምሳሌ ነቃፊዎች እንደሆንን፣ ሰዎችን እንደምንፈራ፣ የሐሜት ልማድ እንዳለን አሊያም ሌላ ድክመት እንዳለብን አስተውለን ይሆናል። ከእነዚህ ድክመቶች ጋር በተያያዘ ለውጥ ማድረግ ከጠበቅነው በላይ ከባድ ሆኖብናል? ከሆነ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ወደ አእምሯችን ይመጡ ይሆናል፦ ‘ትላልቅ ለውጦችን ማድረግ ከቻልኩ ትናንሽ በሆኑ ጉዳዮች ረገድ ለውጥ ማድረጌን መቀጠል የሚያቅተኝ ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወቴን እንዲለውጠው በመፍቀድ ረገድ የበለጠ ማሻሻያ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?’

ከራስህ በምትጠብቀው ነገር ምክንያታዊ ሁን

4. ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት የማንችለው ለምንድን ነው?

4 ይሖዋን የምናውቅና የምንወድ እንደመሆናችን መጠን እሱን የማስደሰት ልባዊ ፍላጎት አለን። ይህን የማድረግ ፍላጎታችን ምንም ያህል ከፍተኛ ቢሆን፣ ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን አምላክን ማስደሰት የምንችለው ሁልጊዜ አይደለም። እኛም “መልካም የሆነውን ነገር የማድረግ ፍላጎት እንጂ የመፈጸም ችሎታ የለኝም” ብሎ እንደጻፈው እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ይሰማናል።—ሮም 7:18፤ ያዕ. 3:2

5. ከመጠመቃችን በፊት የትኞቹን ለውጦች አድርገናል? ይሁንና የትኞቹ ድክመቶች አሁንም ሊያስቸግሩን ይችላሉ?

5 የክርስቲያን ጉባኤ አባል እንዳንሆን ሊያደርጉን የሚችሉ የኃጢአት ድርጊቶችን አስወግደናል። (1 ቆሮ. 6:9, 10) ይሁን እንጂ አሁንም ፍጹማን አይደለንም። (ቆላ. 3:9, 10) በመሆኑም ከተጠመቅን ሌላው ቀርቶ በእውነት ውስጥ በርካታ ዓመታት ካስቆጠርን በኋላ እንኳ ፈጽመን ስህተት እንደማንሠራ፣ ድክመታችን ሊያሸንፈን እንደማይችል ወይም መጥፎ ስሜትና ዝንባሌ እንደማያስቸግረን ማሰቡ ምክንያታዊ አይሆንም። አንዳንድ ድክመቶችን ለማሸነፍ ለዓመታት መታገል ሊያስፈልገን ይችላል።

6, 7. (ሀ) ፍጹም ባንሆንም እንኳ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ያስቻለን ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ ይቅር እንዲለን ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት የሌለብን ለምንድን ነው?

6 በወረስነው ኃጢአት ምክንያት ፍጽምና የጎደለን ብንሆንም ይህ ከይሖዋ አምላክ ጋር ወዳጅነት እንዳንመሠርት ወይም እሱን ማገልገላችንን እንዳንቀጥል እንቅፋት ሊሆንብን አይገባም። እስቲ አስበው፦ ይሖዋ ወደ ራሱ የሳበን አንዳንድ ጊዜ ስህተት ልንሠራ እንደምንችል እያወቀ ነው። (ዮሐ. 6:44) አምላክ ባሕርያችንን ብሎም በልባችን ውስጥ ያለውን ነገር ስለሚረዳ የትኞቹ የኃጢአት ዝንባሌዎች ይበልጥ እንደሚያስቸግሩን በሚገባ ያውቃል። አልፎ አልፎ እንደምንሳሳትም ይገነዘባል። ይሁንና ይሖዋ ይህንን ሁሉ እያወቀ ወዳጆቹ እንድንሆን ጋብዞናል።

7 አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ እጅግ ውድ ስጦታ ይኸውም የሚወደውን ልጁን ቤዛ አድርጎ ሰጥቶናል። (ዮሐ. 3:16) ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ንስሐ ከገባንና በዋጋ ሊተመን የማይችለውን ይህን ዝግጅት መሠረት በማድረግ ይቅር እንዲለን ይሖዋን ከጠየቅነው፣ ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት እንደሚቀጥል እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ሮም 7:24, 25፤ 1 ዮሐ. 2:1, 2) ይሁንና እንደረከስን ወይም ኃጢአተኞች እንደሆንን ተሰምቶን፣ በቤዛው ዝግጅት አማካኝነት ይቅር እንዲለን ይሖዋን ከመጠየቅ ወደኋላ ልንል ይገባል? በጭራሽ። እንዲህ ማድረግ፣ እጃችን ሲቆሽሽ ለመታጠብ ፈቃደኛ ካለመሆን ጋር ይመሳሰላል። ደግሞም ቤዛው የተዘጋጀው ንስሐ ለሚገቡ ኃጢአተኞች ነው። በመሆኑም የቤዛው ዝግጅት መኖሩ ፍጹም ባንሆንም እንኳ ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረት እንድንችል መንገድ ከፍቶልናል።1 ጢሞቴዎስ 1:15ን አንብብ።

8. ድክመታችንን ችላ ብለን ማለፍ የሌለብን ለምንድን ነው?

8 ይህ ሲባል ግን ድክመታችንን ችላ ብለን እናልፈዋለን ማለት አይደለም። ከይሖዋ ጋር ያለንን ወዳጅነት ለማጠናከር፣ አምላክንና ክርስቶስን ይበልጥ መምሰል እንዲሁም እነሱ የሚፈልጉት ዓይነት ሰው ለመሆን ጥረት ማድረግ አለብን። (መዝ. 15:1-5) በተጨማሪም የኃጢአት ዝንባሌዎቻችንን ለመቆጣጠር፣ የሚቻል ከሆነም ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። የተጠመቅነው በቅርቡም ይሁን ከበርካታ ዓመታት በፊት፣ “መስተካከላችሁን . . . ቀጥሉ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል።—2 ቆሮ. 13:11

9. አዲሱን ስብዕና መልበስ ቀጣይነት ያለው ሂደት መሆኑን እንዴት እናውቃለን?

9 ‘ለመስተካከል’ እና “አዲሱን ስብዕና” ለመልበስ ሁልጊዜ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። ጳውሎስ ለእምነት አጋሮቹ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷል፦ “ከቀድሞ አኗኗራችሁ ጋር የሚስማማውንና አታላይ በሆነው ምኞቱ እየተበላሸ የሚሄደውን አሮጌውን ስብዕናችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ ተምራችኋል። ደግሞም አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ፤ እንዲሁም እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና መልበስ ይኖርባችኋል።” (ኤፌ. 4:22-24) “እየታደሰ ይሂድ” የሚለው አገላለጽ አዲሱን ስብዕና መልበስ ቀጣይነት ያለው ሂደት መሆኑን ይጠቁማል። ይህን ማወቅ የሚያበረታታ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋን በማገልገል ያሳለፍነው ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን፣ አዲሱን ስብዕና ለመልበስ የሚረዱንን ክርስቲያናዊ ባሕርያት ምንጊዜም እያዳበርንና እያሻሻልን መሄድ እንደምንችል ማረጋገጫ ይሰጠናል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ምንጊዜም ለውጥ ማምጣት ይችላል።

ከባድ የሚሆነው ለምንድን ነው?

10. በመጽሐፍ ቅዱስ እርዳታ ለውጥ ማድረጋችንን ለመቀጠል ምን ማድረግ ይኖርብናል? የትኞቹ ጥያቄዎች ይፈጠሩብን ይሆናል?

10 የአምላክ ቃል በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ ማምጣቱን እንዲቀጥል ከፈለግን ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ አለብን። ሆኖም ከፍተኛ ጥረት ማድረግ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ይሖዋ ጥረታችንን የሚባርከው ከሆነ መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ቀላል ሊሆንልን አይገባም? ብዙም ጥረት ሳናደርግ፣ አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያትን ማንጸባረቅ እንድንችል ይሖዋ በውስጣችን ያሉ መጥፎ ምኞቶችን ሊያስወግድልን አይችልም ነበር?

11-13. ይሖዋ ድክመቶቻችንን ለማስወገድ ጥረት እንድናደርግ የሚጠብቅብን ለምንድን ነው?

11 ስለ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ስናስብ ይሖዋ ምን ያህል ታላቅ ኃይል እንዳለው እንገነዘባለን። ለምሳሌ ያህል፣ ፀሐይ በእያንዳንዱ ሴኮንድ አምስት ሚሊዮን ቶን ቁስ አካልን ወደ ኃይል ትለውጣለች። ከዚህ ውስጥ የምድርን ከባቢ አየር አልፎ ወደ ፕላኔታችን የሚደርሰው በጣም ትንሽ መጠን ያለው ኃይል ቢሆንም በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር የሚያስፈልገውን ሙቀትና ብርሃን ለማስገኘት በቂ ነው። (መዝ. 74:16፤ ኢሳ. 40:26) ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ኃይል በሚያስፈልጋቸው ጊዜ በተገቢው መጠን መስጠት ያስደስተዋል። (ኢሳ. 40:29) በእርግጥም ይሖዋ፣ ከድክመታችን ጋር መታገል ወይም ከስህተታችን መማር እንኳ ሳያስፈልገን ማንኛውንም ድክመት ማሸነፍ እንድንችል ኃይል ሊሰጠን ይችላል። ታዲያ ይህን የማያደርገው ለምንድን ነው?

12 ይሖዋ በዋጋ ሊተመን የማይችል ስጦታ ይኸውም የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። በራሳችን ተነሳስተን የአምላክን ፈቃድ ስንፈጽምና ይህን ለማድረግ ከልባችን ስንጥር ለይሖዋ ያለን ፍቅርና እሱን ለማስደሰት ያለን ፍላጎት ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ እናሳያለን። ሉዓላዊነቱን እንደምንደግፍም እናሳያለን። ይሖዋ ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበት መንገድ ትክክል ስለመሆኑ ሰይጣን ጥያቄ አስነስቷል፤ በመሆኑም ደግና አድናቂ የሆነው የሰማዩ አባታችን፣ የእሱን ሉዓላዊነት ለመደገፍ በፈቃዳችን ተነሳስተን ለምናደርገው ከፍተኛ ጥረት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ጥርጥር የለውም። (ኢዮብ 2:3-5፤ ምሳሌ 27:11) ይሁንና ይሖዋ እሱን ለማስደሰት ስንል ካለብን አለፍጽምና ጋር የምናደርገውን ትግል ሙሉ በሙሉ ቢያስወግድልን ኖሮ ለሉዓላዊነቱ ታማኝ እንደሆንንና ሉዓላዊነቱን እንደምንደግፍ መናገር አንችልም ነበር።

13 በመሆኑም ይሖዋ እሱን የሚያስደስቱ ባሕርያትን ለማዳበር “ልባዊ ጥረት” እንድናደርግ ይመክረናል። (2 ጴጥሮስ 1:5-7ን አንብብ፤ ቆላ. 3:12) አስተሳሰባችንንና ስሜታችንን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እንድናደርግ ይፈልጋል። (ሮም 8:5፤ 12:9) በዚህ ረገድ ከልባችን ጥረት ካደረግን በኋላ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አሁንም ሕይወታችንን እየለወጠው እንዳለ ስንገነዘብ ይበልጥ እርካታ እናገኛለን።

የአምላክ ቃል ሕይወትህን መለወጡን እንዲቀጥል ፍቀድ

14, 15. ይሖዋ የሚወዳቸውን ባሕርያት ለማዳበር ምን ማድረግ ያስፈልገናል? (“ መጽሐፍ ቅዱስና ጸሎት ሕይወታቸውን ለውጦታል” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

14 አምላክ የሚፈልጋቸውን ባሕርያት ለማዳበርና ይሖዋን ለማስደሰት ምን ሊረዳን ይችላል? የምንፈልጋቸውን ነገሮች ብቻ እየመረጥን ለውጥ ከማድረግ ይልቅ ለውጥ ማድረግ ያለብን በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሆነ አምላክ እንዲመራን መፍቀድ አለብን። ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረጋችንን መቀጠልና በሮም 12:2 ላይ የሚገኘውን አምላክ የሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።” ይሖዋ በቃሉና በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ፈቃዱን እንድናስተውል፣ እንድንፈጽምና እሱ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ለማሟላት በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ እንድናደርግ ይረዳናል። በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ማሰላሰልና መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት መጸለይ ያስፈልገናል። (ሉቃስ 11:13፤ ገላ. 5:22, 23) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንዲመራን ስንፈቅድ እንዲሁም በአምላክ ቃል ውስጥ ከሰፈረው የይሖዋ አመለካከት ጋር የሚስማማ አመለካከት ስናዳብር አስተሳሰባችን፣ ንግግራችንና ድርጊታችን አምላክን የሚያስደስት ይሆናል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ እያደረግንም ቢሆን በድክመቶቻችን ላለመሸነፍ መጠንቀቅ ያስፈልገናል።—ምሳሌ 4:23

ድክመቶችህን ለማሸነፍ ሊረዱህ የሚችሉ ጥቅሶችንና ርዕሶችን መሰብሰብ እንዲሁም በየጊዜው መከለስ ጠቃሚ ነው (አንቀጽ 15ን ተመልከት)

15 መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ከማንበብ በተጨማሪ በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን እየታገዝን የአምላክን ቃል ማጥናት ያስፈልገናል፤ ይህም የይሖዋን አስደናቂ ባሕርያት ለማዳበር ይረዳናል። አንዳንዶች ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ለማዳበር ወይም አንዳንድ ድክመቶችን ለማሸነፍ የሚረዱ ጥቅሶችን እንዲሁም መጠበቂያ ግንብ ወይም ንቁ! ላይ የወጡ ርዕሶችን በማሰባሰብ አልፎ አልፎ መከለሳቸው ጠቅሟቸዋል።

16. የምናደርገው ለውጥ ፈጣን እንዳልሆነ ቢሰማን ተስፋ መቁረጥ የሌለብን ለምንድን ነው?

16 መንፈሳዊ እድገትህ አዝጋሚ እንደሆነ ከተሰማህ እንዲህ ያለ እድገት ማድረግ ጊዜ እንደሚወስድ ማስታወስህ ጠቃሚ ነው። መንፈሳዊ ባሕርያትን ማዳበር ቀጣይነት ያለው ሂደት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ምንጊዜም በሕይወታችን ውስጥ ጠቃሚ ለውጦች ለማድረግ እንዲረዳን ስንጥር ትዕግሥተኞች መሆን አለብን። ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚስማማ ነገር ለማድረግ መጀመሪያ ላይ ራሳችንን መገሠጽ ያስፈልገን ይሆናል። ውሎ አድሮ በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ይሖዋ አምላክን መምሰል ስንችል ግን አምላክን በሚያስደስት መንገድ ማሰብና መመላለስ ይበልጥ ቀላል ሊሆንልን ይችላል።—መዝ. 37:31፤ ምሳሌ 23:12፤ ገላ. 5:16, 17

ከፊታችን በተዘረጋልን ግሩም ተስፋ ላይ ትኩረት አድርግ

17. ለይሖዋ ታማኝ ከሆንን ወደፊት ምን ዓይነት አስደሳች ሕይወት ይጠብቀናል?

17 የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች፣ ወደፊት ፍጽምናን ተላብሰው እሱን ለዘላለም የማገልገል አጋጣሚ ያገኛሉ። በዚያን ጊዜ አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያትን ማንጸባረቅ የሚያታግል ሳይሆን በጣም አስደሳች ነገር ይሆናል። እስከዚያው ድረስ ግን የቤዛው ዝግጅት በመኖሩ አፍቃሪውን አምላካችንን የማምለክ መብት አለን። በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ ለማድረግ ምንጊዜም የምንጥርና ከአምላክ ቃል የምናገኘውን ትምህርት በሥራ ላይ የምናውል ከሆነ ፍጽምና የጎደለን ብንሆንም እንኳ ይሖዋን ማስደሰት እንችላለን።

18, 19. መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወታችንን የመለወጥ ኃይል እንዳለው እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

18 ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኬቨን ቁጣውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት አደረገ። በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ያሰላሰለ ከመሆኑም ሌላ ያገኘውን ትምህርት በተግባር አዋለ፤ እንዲሁም የእምነት ባልንጀሮቹ የሰጡትን እርዳታና ምክር ተቀበለ። በመሆኑም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ኬቨን ጉልህ ለውጥ አደረገ። ውሎ አድሮ የጉባኤ አገልጋይ ሆነ፤ ላለፉት 20 ዓመታት የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ያም ቢሆን ድክመቶቹ እንዳያገረሹበት ሁልጊዜ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ይገነዘባል።

19 የኬቨን ተሞክሮ እንደሚያሳየው የአምላክ ሕዝቦች በሕይወታቸው ውስጥ ጠቃሚ ለውጦች ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይረዳቸዋል። እንግዲያው የአምላክ ቃል በሕይወታችን ውስጥ ለውጥ ማምጣቱን እንዲቀጥል ብሎም ከይሖዋ ጋር ያለንን የጠበቀ ወዳጅነት ይዘን ለመቀጠል እንዲረዳን ምንጊዜም እንፍቀድ። (መዝ. 25:14) ይሖዋ ጥረታችንን እንደባረከው ስንመለከት መጽሐፍ ቅዱስ ሕይወታችንን የመለወጥ ኃይል እንዳለው እርግጠኞች እንሆናለን።—መዝ. 34:8

^ [1] (አንቀጽ 1) ስሙ ተቀይሯል።