የጥናት ርዕስ 5
“የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ” ነው
“የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ [ነው]።”—1 ቆሮ. 11:3
መዝሙር 12 ታላቁ አምላክ ይሖዋ
ማስተዋወቂያ *
1. አንድ ወንድ ስለ ራስነት ሥርዓት ባለው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት አንዳንድ ነገሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
“የራስነት ሥርዓት” ሲባል ወደ አእምሮህ የሚመጣው ምንድን ነው? አንዳንድ ወንዶች ሚስታቸውንና ልጆቻቸውን የሚይዙበት መንገድ ያደጉበትን ባሕል፣ ልማድ ወይም የራሳቸውን አስተዳደግ የሚያንጸባርቅ ነው። በአውሮፓ የምትኖር ያኒታ የተባለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በምኖርበት አካባቢ ‘ሴቶች ከወንዶች ያንሳሉ’ እንዲሁም ‘እንደ አገልጋይ ሊታዩ ይገባል’ የሚል ሥር የሰደደ አመለካከት አለ።” በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር ሉክ የተባለ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ አባቶች ወንዶች ልጆቻቸውን ለሴቶች ጆሮ ሊሰጡ እንደማይገባ እንዲሁም የሴቶች ሐሳብ ምንም ጥቅም እንደሌለው ያስተምሯቸዋል።” ይሁንና ይሖዋ የራስነት ሥርዓትን ያቋቋመው ወንዶች ለሚስቶቻቸው እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲኖራቸው አስቦ አይደለም። (ከማርቆስ 7:13 ጋር አወዳድር።) ታዲያ አንድ ወንድ ጥሩ የቤተሰብ ራስ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?
2. አንድ የቤተሰብ ራስ ምን ማወቅ ይኖርበታል? ለምንስ?
2 አንድ ወንድ ጥሩ የቤተሰብ ራስ ለመሆን በመጀመሪያ ይሖዋ የሚጠብቅበትን ማወቅ ይኖርበታል። በተጨማሪም ይሖዋ የራስነት ሥርዓትን ያቋቋመበትን ምክንያት በተለይ ደግሞ ይሖዋና ኢየሱስ የተዉትን ምሳሌ መከተል የሚችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገዋል። አንድ ወንድ እነዚህን ነገሮች ማወቅ የሚጠበቅበት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ ለቤተሰብ ራሶች የተወሰነ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፤ እንዲሁም ይህን ሥልጣናቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ይጠብቅባቸዋል።—ሉቃስ 12:48ለ
የራስነት ሥርዓት ምንድን ነው?
3. በአንደኛ ቆሮንቶስ 11:3 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ስለ ራስነት ሥርዓት ምን ያስተምረናል?
3 አንደኛ ቆሮንቶስ 11:3ን አንብብ። ይህ ጥቅስ፣ ይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰቡን እንዴት እንዳደራጀ ይገልጻል። የራስነት ሥርዓት ሁለት ቁልፍ ነገሮችን የያዘ ነው፤ እነሱም ሥልጣንና ተጠያቂነት ናቸው። የሁሉም “ራስ” ወይም የመጨረሻው ባለሥልጣን ይሖዋ ነው፤ ሁሉም ልጆቹ ማለትም መላእክትም ሆኑ የሰው ልጆች በእሱ ፊት ተጠያቂ ናቸው። (ሮም 14:10፤ ኤፌ. 3:14, 15) ይሖዋ ለኢየሱስ በጉባኤው ላይ ሥልጣን ሰጥቶታል፤ ሆኖም ኢየሱስ እኛን የሚይዝበትን መንገድ በተመለከተ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ ነው። (1 ቆሮ. 15:27) ይሖዋ ለባልም በሚስቱና በልጆቹ ላይ ሥልጣን ሰጥቶታል፤ ይሁንና አንድ ባል ቤተሰቡን የሚይዝበትን መንገድ በተመለከተ በይሖዋና በኢየሱስ ፊት ተጠያቂ ነው።—1 ጴጥ. 3:7
4. ይሖዋና ኢየሱስ ምን ሥልጣን አላቸው?
4 ይሖዋ የጽንፈ ዓለማዊው ቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ልጆቹ የሚመሩባቸውን መሥፈርቶች የማውጣትና የማስፈጸም ሥልጣን አለው። (ኢሳ. 33:22) ኢየሱስም የክርስቲያን ጉባኤ ራስ ስለሆነ መሥፈርቶች የማውጣትና የማስፈጸም መብት አለው።—ገላ. 6:2፤ ቆላ. 1:18-20
5. አንድ ክርስቲያን የቤተሰብ ራስ ምን ሥልጣን አለው? ሥልጣኑስ ምን ገደብ አለው?
5 ከዚሁ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ አንድ የቤተሰብ ራስ ቤተሰቡን የሚመለከቱ ውሳኔዎች የማድረግ ሥልጣን አለው። (ሮም 7:2፤ ኤፌ. 6:4) ሆኖም ሥልጣኑ ገደብ አለው። ለምሳሌ ያህል፣ የሚያወጣቸው ደንቦች በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረቱ መሆን አለባቸው። (ምሳሌ 3:5, 6) እንዲሁም አንድ የቤተሰብ ራስ የቤተሰቡ አባላት ላልሆኑ ሰዎች ደንብ የማውጣት ሥልጣን የለውም። (ሮም 14:4) በተጨማሪም ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆቹ አድገው ከቤት ከወጡ በኋላ አክብሮት እንዲያሳዩት ቢጠበቅባቸውም በእሱ የራስነት ሥርዓት ሥር አይሆኑም።—ማቴ. 19:5
ይሖዋ የራስነት ሥርዓትን ያቋቋመው ለምንድን ነው?
6. ይሖዋ የራስነት ሥርዓትን ያቋቋመው ለምንድን ነው?
6 ይሖዋ የራስነት ሥርዓትን ያቋቋመው ለቤተሰቡ ካለው ፍቅር የተነሳ ነው። የራስነት ሥርዓት የእሱ ስጦታ ነው። የይሖዋ ቤተሰብ ደስተኛና ሥርዓታማ ሊሆን የቻለው የራስነት ሥርዓት ስላለ ነው። (1 ቆሮ. 14:33, 40) ማን ራስ እንደሆነ በግልጽ የተቀመጠ ነገር ባይኖር ኖሮ የይሖዋ ቤተሰብ ሥርዓትና ደስታ የሌለው ይሆን ነበር። ለምሳሌ ‘አንድን ውሳኔ የማድረግና ግንባር ቀደም ሆኖ ውሳኔውን የማስፈጸም ኃላፊነት ያለበት ማን ነው?’ የሚለው ጉዳይ ግራ መጋባት ይፈጥር ነበር።
7. ኤፌሶን 5:25, 28 ላይ በተገለጸው መሠረት ይሖዋ ሚስቶች እንዴት እንዲያዙ ይፈልጋል?
7 አምላክ ያቋቋመው የራስነት ሥርዓት እንዲህ ያለ ጥሩ ዝግጅት ከሆነ በዛሬው ጊዜ ብዙ ሴቶች ባሎቻቸው እንደሚጨቁኗቸው የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ብዙ ወንዶች ይሖዋ ለቤተሰብ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ከመጠበቅ ይልቅ የአካባቢያቸውን ወጎችና ልማዶች ስለሚከተሉ ነው። በራስ ወዳድነት ስሜት ተነሳስተው ሚስቶቻቸውን የሚበድሉም አሉ። ለምሳሌ አንድ ባል፣ ሌሎች ከፍ ያለ ግምት እንዲሰጡት ለማድረግ ወይም ወንድነቱን ለማሳየት ሲል ሚስቱን ሊጨቁን ይችላል። ሚስቴ እንድትወደኝ ማስገደድ ባልችልም እንድትፈራኝ ማድረግ እችላለሁ ብሎ ያስብ ይሆናል። ስለዚህ እያስፈራራ እንደፈለገ ሊቆጣጠራት ይሞክራል። * እንዲህ ያለው አመለካከትና ድርጊት ሴቶች የሚገባቸውን አክብሮት እንዲነፈጉ ያደርጋል፤ በተጨማሪም ይሖዋ ካሰበው ነገር ጋር በቀጥታ የሚቃረን ነው።—ኤፌሶን 5:25, 28ን አንብብ።
አንድ ወንድ ጥሩ የቤተሰብ ራስ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?
8. አንድ ወንድ ጥሩ የቤተሰብ ራስ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?
8 አንድ ወንድ፣ ይሖዋና ኢየሱስ የራስነት ሥልጣናቸውን በመጠቀም ረገድ የተዉትን ግሩም ምሳሌ በመከተል ጥሩ የቤተሰብ ራስ መሆን ይችላል። ይሖዋና ኢየሱስ ካሳዩአቸው ባሕርያት መካከል እስቲ ሁለቱን ብቻ እንመልከት፤
ከዚያም አንድ የቤተሰብ ራስ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ባለው ግንኙነት እነዚህን ባሕርያት ማንጸባረቅ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እናያለን።9. ይሖዋ ትሕትናውን ያሳየው እንዴት ነው?
9 ትሕትና። ይሖዋ ከማንም በላይ ጥበበኛ ነው፤ ያም ቢሆን የአገልጋዮቹን ሐሳብ ያዳምጣል። (ዘፍ. 18:23, 24, 32) በእሱ ሥልጣን ሥር ያሉ አገልጋዮቹ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ፈቅዶላቸዋል። (1 ነገ. 22:19-22) ይሖዋ ፍጹም ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከእኛ ፍጽምናን አይጠብቅም። ከዚህ ይልቅ ፍጹማን ያልሆንን የሰው ልጆች እንዲሳካልን ይረዳናል። (መዝ. 113:6, 7) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይሖዋ ‘ረዳት’ ተብሎ ተገልጿል። (መዝ. 27:9፤ ዕብ. 13:6) ንጉሥ ዳዊት፣ ታላቅ ነገር ማከናወን የቻለው በይሖዋ ትሕትና እንደሆነ ተናግሯል።—2 ሳሙ. 22:36
10. ኢየሱስ ትሕትናውን ያሳየው እንዴት ነው?
10 ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እንመልከት። ለደቀ መዛሙርቱ ጌታቸው ቢሆንም እግራቸውን አጥቧል። ይሖዋ ይህ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲሰፍርልን ያደረገበት አንዱ ምክንያት ምንድን ነው? የቤተሰብ ራሶችን ጨምሮ ለሁላችንም ጥሩ ምሳሌ እንዲሆነን አስቦ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ራሱ “እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ” ብሏል። (ዮሐ. 13:12-17) ኢየሱስ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ቢሆንም ሌሎች እንዲያገለግሉት አልጠበቀም። እንዲያውም እሱ ራሱ ሌሎችን አገልግሏል።—ማቴ. 20:28
11. አንድ የቤተሰብ ራስ ትሕትናን በተመለከተ ይሖዋና ኢየሱስ ከተዉት ምሳሌ ምን ሊማር ይችላል?
11 የምናገኘው ትምህርት። አንድ የቤተሰብ ራስ ትሕትናውን የሚያሳይባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ፍጽምና አይጠብቅም። ከእሱ የተለየ አመለካከት በሚኖራቸው ጊዜም እንኳ የቤተሰቡ አባላት የሚሰጡትን ሐሳብ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ማርሊ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ ስለ አንድ ጉዳይ የተለያየ አመለካከት የሚኖረን ጊዜ አለ። ሆኖም ውሳኔ ከማድረጉ በፊት ሐሳብ እንድሰጠው ይጠይቀኛል፤ እንዲሁም የሰጠሁትን ሐሳብ በቁም ነገር ያስብበታል፤ ይህም ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተኝና እንደሚያከብረኝ እንዲሰማኝ ያደርጋል።” በተጨማሪም አንድ ትሑት ባል የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለማከናወን ፈቃደኛ ነው፤ በሚኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ እነዚህ ሥራዎች የሴት ሥራ እንደሆኑ ተደርገው ቢታዩም ይህ ተጽዕኖ አያሳድርበትም። በእርግጥ ማኅበረሰቡ የሚያሳድረውን እንዲህ ያለውን ተጽዕኖ መቋቋም ቀላል ላይሆን ይችላል።
ለምን? ሪቼል የተባለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በአካባቢያችን አንድ ባል ዕቃ በማጠብ ወይም ቤት በማጽዳት ሚስቱን ካገዘ ጎረቤቶቹና ዘመዶቹ ሴታ ሴት አድርገው ሊያስቡት ይችላሉ። ሚስቱን መቆጣጠር እንደማይችል ይሰማቸዋል።” በምትኖርበት አካባቢ ሰዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካላቸው የኢየሱስን ምሳሌ አስታውስ፤ ኢየሱስ የባሪያ ሥራ ተደርጎ ቢቆጠርም የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል። አንድ ጥሩ የቤተሰብ ራስ የሚያሳስበው ሌሎች ለእሱ ያላቸው አመለካከት ሳይሆን የሚስቱና የልጆቹ ስሜት ነው። ታዲያ አንድ የቤተሰብ ራስ ከትሕትና በተጨማሪ የትኛውን ባሕርይ ማዳበር ይኖርበታል?12. ይሖዋና ኢየሱስ በፍቅር ተነሳስተው ምን አድርገውልናል?
12 ፍቅር። ይሖዋ ሁሉንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። (1 ዮሐ. 4:7, 8) በፍቅር ተነሳስቶ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ያሟላልናል፤ ይህን የሚያደርገው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስና በድርጅቱ አማካኝነት ነው። እንደሚወደን በመግለጽ ስሜታዊ ፍላጎታችንንም ያሟላልናል። ቁሳዊ ፍላጎቶቻችንን በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋ “የሚያስደስቱንን ነገሮች ሁሉ አትረፍርፎ” ይሰጠናል። (1 ጢሞ. 6:17) ስህተት ስንሠራ እርማት ይሰጠናል፤ ሆኖም ስህተት መሥራታችን ለእኛ ያለውን ፍቅር ይቀንሰዋል ማለት አይደለም። ይሖዋ ለእኛ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ ቤዛውን አዘጋጅቶልናል። ኢየሱስም ቢሆን ሕይወቱን ለእኛ የሰጠው በጣም ስለሚወደን ነው። (ዮሐ. 3:16፤ 15:13) ይሖዋና ኢየሱስ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ያላቸውን ፍቅር የሚበጥሰው ምንም ነገር የለም።—ዮሐ. 13:1፤ ሮም 8:35, 38, 39
13. አንድ የቤተሰብ ራስ ለቤተሰቡ ፍቅር ማሳየቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (“ በቅርቡ ትዳር የመሠረተ አንድ ወንድ የሚስቱን አክብሮት ማትረፍ የሚችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)
13 የምናገኘው ትምህርት። አንድ የቤተሰብ ራስ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ መሆን አለበት። ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ የጻፈው ሐሳብ መልሱን ይሰጠናል፤ እንዲህ ብሏል፦ “ያየውን ወንድሙን [ወይም ቤተሰቡን] የማይወድ ያላየውን አምላክ ሊወድ አይችልም።” (1 ዮሐ. 4:11, 20) ቤተሰቡን የሚወድ እንዲሁም ይሖዋንና ኢየሱስን መምሰል የሚፈልግ አንድ ባል የቤተሰቡን መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላት የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። (1 ጢሞ. 5:8) ለልጆቹ ሥልጠናና ተግሣጽ ይሰጣል። በተጨማሪም ይሖዋን የሚያስከብርና ቤተሰቡን የሚጠቅም ውሳኔ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል። እስቲ እነዚህን ነገሮች በተናጠል በመመልከት አንድ የቤተሰብ ራስ ይሖዋንና ኢየሱስን መምሰል የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንመርምር።
አንድ የቤተሰብ ራስ ምን ማድረግ ይጠበቅበታል?
14. አንድ የቤተሰብ ራስ የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎት የሚያሟላው እንዴት ነው?
14 የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት። ኢየሱስ በእሱ ኃላፊነት ሥር ያሉ ሁሉ በቂ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘታቸው ያሳስበው ነበር፤ ይህም የአባቱን ምሳሌ እንደሚከተል ያሳያል። (ማቴ. 5:3, 6፤ ማር. 6:34) በተመሳሳይም አንድ የቤተሰብ ራስ ከምንም ነገር በላይ ሊያሳስበው የሚገባው የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት ነው። (ዘዳ. 6:6-9) ይህን ለማድረግ ደግሞ እሱም ሆነ ቤተሰቡ የአምላክን ቃል የሚያነቡበትንና የሚያጠኑበትን፣ በስብሰባ ላይ የሚገኙበትን እንዲሁም ምሥራቹን የሚሰብኩበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት ይኖርበታል፤ በተጨማሪም የቤተሰቡ አባላት ከይሖዋ ጋር ዝምድና እንዲመሠርቱና ይህን ዝምድና ጠብቀው እንዲቀጥሉ መርዳት ይኖርበታል።
15. አንድ የቤተሰብ ራስ የቤተሰቡን ስሜታዊ ፍላጎት ማሟላት የሚችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
15 የቤተሰቡን ስሜታዊ ፍላጎት ማሟላት። ይሖዋ ለኢየሱስ እንደሚወደው በግልጽ ነግሮታል። (ማቴ. 3:17) ኢየሱስ በቃልም ሆነ በድርጊት ለተከታዮቹ ያለውን ፍቅር ከመግለጽ ወደኋላ ብሎ አያውቅም። እነሱም በምላሹ እንደሚወዱት ገልጸውለታል። (ዮሐ. 15:9, 12, 13፤ 21:16) አንድ የቤተሰብ ራስ በድርጊቱ ሚስቱንና ልጆቹን እንደሚወድ ማሳየት ይችላል፤ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስን አብሯቸው ያጠናል። ከዚህም በተጨማሪ ግን እንደሚወዳቸውና እንደሚያደንቃቸው ሊነግራቸው ይገባል፤ ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ በሌሎች ፊት እነሱን ከማመስገን ወደኋላ ማለት የለበትም።—ምሳሌ 31:28, 29
16. አንድ የቤተሰብ ራስ ምን ማድረግ ይኖርበታል? በዚህ ረገድ ሚዛኑን መጠበቅ የሚችለውስ እንዴት ነው?
16 የቤተሰቡን ቁሳዊ ፍላጎት ማሟላት። ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር በመስጠት ይንከባከባቸው ነበር፤ ባለመታዘዛቸው ምክንያት እየቀጣቸው በነበረበት ወቅትም እንኳ እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ አላለም። (ዘዳ. 2:7፤ 29:5) በዛሬው ጊዜም የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች ይሰጠናል። (ማቴ. 6:31-33፤ 7:11) ኢየሱስም ቢሆን ይከተሉት የነበሩትን ሰዎች መግቧል። (ማቴ. 14:17-20) የታመሙትን በመፈወስ ስለ ጤንነታቸው እንደሚያስብም አሳይቷል። (ማቴ. 4:24) አንድ የቤተሰብ ራስ ይሖዋን ማስደሰት ከፈለገ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ማቅረብ አለበት። ሆኖም በዚህ ረገድ ሚዛኑን መጠበቅ ይኖርበታል። ቤተሰቡን ለማስተዳደር ሲል በሰብዓዊ ሥራ ከልክ በላይ ከመጠመዱ የተነሳ የቤተሰቡን መንፈሳዊና ስሜታዊ ፍላጎት ችላ ማለት የለበትም።
17. ይሖዋና ኢየሱስ ሥልጠናና ተግሣጽ በመስጠት ረገድ ምን ምሳሌ ትተውልናል?
17 ሥልጠና መስጠት። ይሖዋ ለራሳችን ጥቅም ሲል ሥልጠናና ተግሣጽ ይሰጠናል። (ዕብ. 12:7-9) ኢየሱስም ልክ እንደ አባቱ በእሱ ሥልጣን ሥር ያሉትን ሰዎች ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ያሠለጥናቸዋል። (ዮሐ. 15:14, 15) ጠንከር ያለ ምክር መስጠት የሚያስፈልገው ጊዜ ቢኖርም ይህን የሚያደርገው በደግነት ነው። (ማቴ. 20:24-28) ፍጹማን እንዳልሆንንና ስህተት መሥራት እንደሚቀናን ይረዳል።—ማቴ. 26:41
18. አንድ ጥሩ የቤተሰብ ራስ ምን አይዘነጋም?
18 የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተል የቤተሰብ ራስ፣ የቤተሰቡ አባላት ፍጹማን እንዳልሆኑ አይዘነጋም። በሚስቱ ወይም በልጆቹ ላይ ‘መራራ ቁጣ አይቆጣም።’ (ቆላ. 3:19) ከዚህ ይልቅ እሱ ራሱ ፍጹም እንዳልሆነ በማስታወስ ገላትያ 6:1 እንደሚለው “በገርነት መንፈስ” ሊያስተካክላቸው ይሞክራል። ኢየሱስ እንዳደረገው፣ ከሁሉ የተሻለው የማስተማሪያ ዘዴ ምሳሌ ሆኖ መገኘት እንደሆነ ይገነዘባል።—1 ጴጥ. 2:21
19-20. ውሳኔ ከማድረግ ጋር በተያያዘ አንድ የቤተሰብ ራስ የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችለው እንዴት ነው?
19 የራሱን ሳይሆን የቤተሰቡን ጥቅም ግምት ውስጥ ያስገባ ውሳኔ ማድረግ። ይሖዋ የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ሌሎችን የሚጠቅሙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ሕይወት ለመፍጠር የተነሳሳው ራሱን ለመጥቀም ሳይሆን ሌሎችም ሕይወት የሚያስገኘውን ደስታ እንዲቀምሱ ሲል ነው። ለኃጢአታችን ሲል ልጁን የሰጠውም ማንም አስገድዶት አይደለም። ለእኛ ጥቅም ሲል እንዲህ ያለውን መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ሆኗል። ኢየሱስ ያደረጋቸው ውሳኔዎችም በዋነኝነት የሌሎችን ጥቅም የሚያስቀድሙ ናቸው። (ሮም 15:3) ለምሳሌ ያህል፣ የተሰበሰበውን ሕዝብ ለማስተማር ሲል እረፍት የሚያደርግበትን ጊዜ መሥዋዕት አድርጓል።—ማር. 6:31-34
20 አንድ የቤተሰብ ራስ ካሉበት ከባድ ኃላፊነቶች አንዱ ቤተሰቡን የሚጠቅም ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ እንደሆነ ይረዳል፤ ይህን ኃላፊነቱንም በቁም ነገር ይመለከተዋል። ስለዚህ ሳያስብበት ወይም በስሜት ተነሳስቶ ውሳኔ ከማድረግ ይቆጠባል። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንዲያሠለጥነው ይፈቅዳል። * (ምሳሌ 2:6, 7) በዚህ መንገድ ስለ ራሱ ሳይሆን ስለ ሌሎች ጥቅም እንደሚያስብ ያሳያል።—ፊልጵ. 2:4
21. በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
21 ይሖዋ ለቤተሰብ ራሶች ከባድ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል፤ ይህን ኃላፊነታቸውን ስለሚወጡበት መንገድም በእሱ ፊት ተጠያቂ ናቸው። ሆኖም አንድ ባል የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት የሚያደርግ ከሆነ ጥሩ የቤተሰብ ራስ መሆን ይችላል። ሚስቱም የራሷን ድርሻ ከተወጣች ትዳራቸው አስደሳች ይሆናል። ታዲያ አንዲት ሚስት ለራስነት ሥርዓት ምን አመለካከት ሊኖራት ይገባል? ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎችስ ያጋጥሟታል? ቀጣዩ ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
መዝሙር 16 ያህ ልጁን ሾሟል አወድሱት
^ አን.5 አንድ ወንድ ትዳር ሲመሠርት የቤተሰቡ ራስ ይሆናል። በዚህ ርዕስ ላይ የራስነት ሥርዓት ምን እንደሆነና ይሖዋ ይህን ሥርዓት ያቋቋመው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን፤ በተጨማሪም ይሖዋና ኢየሱስ ከተዉት ምሳሌ ወንዶች ምን እንደሚማሩ እናያለን። ቀጣዩ ርዕስ ባልም ሆነ ሚስት ከኢየሱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ሌሎች ሰዎች ምን ትምህርት እንደሚያገኙ ያብራራል። በሦስተኛው ርዕስ ላይ ደግሞ በጉባኤው ውስጥ ስላለው የራስነት ሥርዓት እንመረምራለን።
^ አን.7 ፊልሞች፣ ቲያትሮችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ወንዶች ሚስቶቻቸውን መበደላቸው ሌላው ቀርቶ መደብደባቸው ተቀባይነት ያለው ነገር እንደሆነ አድርገው የሚያቀርቡበት ጊዜ አለ። ‘ወንድ የሚስቱ የበላይ ነው’ የሚለው አመለካከት በሰዎች አእምሮ ውስጥ እንዲሰርጽ ያደረገው አንዱ ነገር ይህ የሚዲያዎች ተጽዕኖ ሊሆን ይችላል።
^ አን.20 ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ስለሚቻልበት መንገድ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በሚያዝያ 15, 2011 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 13-17 ላይ የሚገኘውን “አምላክን የሚያስከብር ውሳኔ አድርጉ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።