በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 13

ይሖዋ የሚጠብቀን እንዴት ነው?

ይሖዋ የሚጠብቀን እንዴት ነው?

“ጌታ . . . ታማኝ ነው፤ እሱ ያጠነክራችኋል፤ እንዲሁም ከክፉው ይጠብቃችኋል።”—2 ተሰ. 3:3

መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን

ማስተዋወቂያ a

1. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ይሖዋ እንዲጠብቃቸው የጠየቀው ለምንድን ነው?

 ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ደቀ መዛሙርቱ ወደፊት ስለሚያጋጥሟቸው ችግሮች እያሰበ ነበር። ለወዳጆቹ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ አባቱን ‘ከክፉው እንዲጠብቃቸው’ ጠይቆታል። (ዮሐ. 17:14, 15) ኢየሱስ እሱ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ ይሖዋን ማገልገል በሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን እንደሚቀጥል ያውቅ ነበር። በእርግጥም የይሖዋ ሕዝቦች ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል።

2. ይሖዋ ጸሎታችንን እንደሚመልስልን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

2 ይሖዋ ልጁን ስለሚወደው ለጸሎቱ ምላሽ ሰጥቶታል። እኛም ይሖዋን ለማስደሰት የቻልነውን ሁሉ ጥረት የምናደርግ ከሆነ እሱ ይወደናል። እንዲሁም እርዳታና ጥበቃ ለማግኘት የምናቀርበውን ጸሎት ይመልስልናል። ይሖዋ አሳቢ የሆነ የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ምንጊዜም ለልጆቹ ፍቅራዊ እንክብካቤ ያደርጋል። እንዲህ ሳያደርግ ቢቀር በስሙ ላይ ነቀፋ ይመጣበታል።

3. በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ጥበቃ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

3 ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአሁኑ ወቅት የይሖዋ ጥበቃ ያስፈልገናል። ሰይጣን ከሰማይ የተወረወረ ሲሆን “በታላቅ ቁጣ” ተሞልቷል። (ራእይ 12:12) አንዳንዶች እኛን ሲያሳድዱ “ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት” እያቀረቡ እንዳሉ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። (ዮሐ. 16:2) በአምላክ የማያምኑ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ከዚህ ዓለም የተለየን በመሆናችን ምክንያት ያሳድዱናል። ሰዎች እንዲያሳድዱን የሚያነሳሳቸው ምክንያት ምንም ሆነ ምን መፍራት አይኖርብንም። ለምን? ምክንያቱም የአምላክ ቃል “ጌታ . . . ታማኝ ነው፤ እሱ ያጠነክራችኋል፤ እንዲሁም ከክፉው ይጠብቃችኋል” ይላል። (2 ተሰ. 3:3) ይሖዋ የሚጠብቀን እንዴት ነው? እስቲ ሁለት መንገዶችን እንመልከት።

ይሖዋ የጦር ትጥቅ አዘጋጅቶልናል

4. በኤፌሶን 6:13-17 መሠረት ይሖዋ እኛን ለመጠበቅ ምን አዘጋጅቶልናል?

4 ይሖዋ ከሰይጣን ጥቃቶች ሊጠብቀን የሚችል የጦር ትጥቅ አዘጋጅቶልናል። (ኤፌሶን 6:13-17ን አንብብ።) ይህ መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ ጠንካራና ውጤታማ ነው! ሆኖም የጦር ትጥቁ ጥበቃ የሚያደርግልን እያንዳንዱን ክፍል ከለበስነው እና ካላወለቅነው ነው። የጦር ትጥቁ እያንዳንዱ ክፍል ምን ያመለክታል? እስቲ በዝርዝር እንመልከት።

5. የእውነት ቀበቶ ምንድን ነው? ልንታጠቀው የሚገባውስ ለምንድን ነው?

5 የእውነት ቀበቶ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች ያመለክታል። ይህን ቀበቶ መታጠቅ ያለብን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰይጣን “የውሸት አባት” ነው። (ዮሐ. 8:44) በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲዋሽ ስለኖረ በውሸት የተካነ ነው፤ ‘መላውን ዓለምም አሳስቷል!’ (ራእይ 12:9) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት ግን እንዳንታለል ይጠብቀናል። ታዲያ ይህን ምሳሌያዊ ቀበቶ መታጠቅ የምንችለው እንዴት ነው? ስለ ይሖዋ እውነቱን በመማር፣ እሱን “በመንፈስና በእውነት” በማምለክ እንዲሁም በሁሉም ነገር በሐቀኝነት በመኖር ነው።—ዮሐ. 4:24፤ ኤፌ. 4:25፤ ዕብ. 13:18

ቀበቶ፦ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት እውነቶች

6. የጽድቅ ጥሩር ምንድን ነው? ልንለብሰው የሚገባውስ ለምንድን ነው?

6 የጽድቅ ጥሩር የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ያመለክታል። ይህን ጥሩር መልበስ ያለብን ለምንድን ነው? አንድ ወታደር ጥሩር መልበሱ ልቡን ከጉዳት እንደሚጠብቅለት ሁሉ እኛም የጽድቅን ጥሩር መልበሳችን ምሳሌያዊው ልባችን ማለትም ውስጣዊ ማንነታችን በዚህ ዓለም ተጽዕኖ እንዳይበከል ይጠብቅልናል። (ምሳሌ 4:23) ይሖዋ በሙሉ ልባችን እንድንወደውና እንድናገለግለው ይፈልጋል። (ማቴ. 22:36, 37) ሰይጣን ይህን ስለሚያውቅ ይሖዋ የሚጠላቸውን በዚህ ዓለም ላይ ያሉ ነገሮች እንድንወድ በማድረግ ልባችንን ለመከፋፈል ይሞክራል። (ያዕ. 4:4፤ 1 ዮሐ. 2:15, 16) ይህ ካልተሳካለት ደግሞ ኃይል ተጠቅሞ የይሖዋን መሥፈርቶች እንድንጥስ ለማድረግ ይጥራል።

የጽድቅ ጥሩር፦ የይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች

7. የጽድቅን ጥሩር መልበስ የምንችለው እንዴት ነው?

7 የጽድቅን ጥሩር የምንለብሰው፣ ትክክል ወይም ስህተት የሆኑትን ነገሮች በተመለከተ ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች በመቀበልና በእነዚህ መሥፈርቶች መሠረት ሕይወታችንን በመምራት ነው። (መዝ. 97:10) አንዳንዶች የይሖዋ መሥፈርቶች በጣም ጥብቅ እንደሆኑ ይሰማቸዋል። አንድ ወታደር ውጊያ ላይ እያለ ጥሩሩን መሸከም ከበደኝ ብሎ ቢያወልቀው ሞኝነት እንደሚሆንበት የታወቀ ነው፤ እኛም በተመሳሳይ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከባድ እንደሆኑ በማሰብ በእነሱ መመራታችንን ብናቆም ሞኝነት ይሆንብናል። ይሖዋን የምንወደው ከሆነ ትእዛዛቱ “ከባድ” ሸክም አይሆኑብንም፤ ከዚህ ይልቅ ሕይወታችንን ይጠብቁልናል።—1 ዮሐ. 5:3

8. ምሥራቹን ለማወጅ ዝግጁ በመሆን እግሮቻችን ተጫምተው እንዲቆሙ ማድረግ ሲባል ምን ማለት ነው?

8 ጳውሎስ የሰላምን ምሥራች ለማወጅ ዝግጁ በመሆን እግሮቻችን ተጫምተው እንዲቆሙም አሳስቦናል። ይህም ሲባል የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክ ምንጊዜም ዝግጁ መሆን ይኖርብናል ማለት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች ስናካፍል እምነታችን ይጠናከራል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች ያገኙትን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመው ምሥራቹን እንደሚሰብኩ ማየታችን ያበረታታናል። በሥራ ቦታቸው፣ በትምህርት ቤታቸው፣ በመሥሪያ ቤቶች፣ ከቤት ወደ ቤት እንዲሁም በገበያ ቦታ ይሰብካሉ፤ ከዚህም ሌላ ለማያምኑ ዘመዶቻቸውና ለሚያውቋቸው ሰዎች ይመሠክራሉ፤ ከቤት መውጣት በማይችሉበት ጊዜም ጭምር መስበካቸውን አያቆሙም። በፍርሃት ተሸንፈን መስበካችንን ብናቆም፣ በውጊያ ወቅት ጫማውን እንዳወለቀ ወታደር እንሆናለን። እንዲህ ያለው ወታደር እግሩ በቀላሉ ስለሚጎዳ ለጥቃት የተጋለጠ ይሆናል፤ በተጨማሪም የአዛዡን መመሪያ መከተል አይችልም።

ጫማ፦ ምሥራቹን ለመስበክ ዝግጁ መሆን

9. ትልቁን የእምነት ጋሻ ማንሳት ያለብን ለምንድን ነው?

9 ትልቁ የእምነት ጋሻ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ያመለክታል። ይሖዋ የገባውን ቃል በሙሉ እንደሚፈጽም እንተማመናለን። እንዲህ ያለው እምነት “የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ [ለማምከን]” ያስችለናል። ይህን ትልቅ ጋሻ መያዝ ያለብን ለምንድን ነው? በከሃዲዎች ትምህርት እንዳንወሰድ ወይም ሰዎች እምነታችንን ሲያጣጥሉ ተስፋ እንዳንቆርጥ ስለሚረዳን ነው። እምነት ከሌለን ሌሎች የይሖዋን መሥፈርቶች ችላ እንድንል የሚያደርሱብንን ግፊት ለመቋቋም አቅም አይኖረንም። በሌላ በኩል ግን በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት የሚያጋጥመንን የእምነት ፈተና በተቋቋምን ቁጥር፣ ጋሻችን ጥበቃ እያደረገልን ነው። (1 ጴጥ. 3:15) ወይም ደግሞ ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚያስገኝ ግን የአምልኮ ፕሮግራማችንን የሚያስተጓጉል የሥራ ግብዣ ቀርቦልን ግብዣውን ላለመቀበል ስንወስን ጋሻችን ጥበቃ እያደረገልን ነው። (ዕብ. 13:5, 6) እንዲሁም ተቃውሞ እየደረሰብንም ይሖዋን ማገልገላችንን ስንቀጥል ጋሻችን ጥበቃ እያደረገልን ነው።—1 ተሰ. 2:2

ጋሻ፦ በይሖዋ እና እሱ በገባው ቃል ላይ ያለን እምነት

10. የመዳን ራስ ቁር ምንድን ነው? ልናጠልቀው የሚገባውስ ለምንድን ነው?

10 የመዳን የራስ ቁር ይሖዋ የሰጠንን ተስፋ ያመለክታል፤ ይህ ተስፋ ይሖዋ ከሞት እንደሚታደገንና ፈቃዱን ለሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ ወሮታ እንደሚከፍላቸው የሚገልጽ ነው። (1 ተሰ. 5:8፤ 1 ጢሞ. 4:10፤ ቲቶ 1:1, 2) የራስ ቁር የአንድን ወታደር ጭንቅላት እንደሚጠብቅለት ሁሉ የመዳን ተስፋችንም የማሰብ ችሎታችንን ይጠብቅልናል። እንዴት? ይህ ተስፋ አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ ምንጊዜም እንድናተኩርና ለሚደርሱብን ችግሮች ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። ይህን የራስ ቁር ማጥለቅ የምንችለው እንዴት ነው? አስተሳሰባችን ምንጊዜም ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የሚስማማ እንዲሆን በማድረግ ነው። ለምሳሌ ተስፋችንን አስተማማኝነት በሌለው ሀብት ላይ ሳይሆን በአምላክ ላይ እንጥላለን።—መዝ. 26:2፤ 104:34፤ 1 ጢሞ. 6:17

የራስ ቁር፦ የዘላለም ሕይወት ተስፋ

11. የመንፈስ ሰይፍ ምንድን ነው? ልንጠቀምበት የሚገባውስ ለምንድን ነው?

11 የመንፈስ ሰይፍ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እንደ ሰይፍ የሆነው የአምላክ ቃል ማንኛውንም ዓይነት ማታለያ የማጋለጥ እንዲሁም በሐሰት ትምህርቶችና ጎጂ በሆኑ ልማዶች የተተበተቡ ሰዎችን ነፃ የማውጣት ኃይል አለው። (2 ቆሮ. 10:4, 5፤ 2 ጢሞ. 3:16, 17፤ ዕብ. 4:12) በግል ጥናት እንዲሁም ከአምላክ ድርጅት በምናገኘው ሥልጠና አማካኝነት፣ ይህን ሰይፍ በአግባቡ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። (2 ጢሞ. 2:15) ይሖዋ የጦር ትጥቅ ከመስጠት በተጨማሪ ጥበቃ የሚያስገኝልን ሌላ ዝግጅት አድርጎልናል። ይህ ዝግጅት ምንድን ነው?

ሰይፍ፦ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ

የምንዋጋው ብቻችንን አይደለም

12. ከጦር ትጥቅ በተጨማሪ ምን ያስፈልገናል? ለምንስ?

12 ልምድ ያለው አንድ ወታደር፣ ከግዙፍ ሠራዊት ጋር ብቻውን ተዋግቶ ማሸነፍ እንደማይችል ያውቃል። አብረውት የተሰለፉት ወታደሮች ድጋፍ ያስፈልገዋል። እኛም በተመሳሳይ ብቻችንን ሰይጣንን እና ተከታዮቹን ማሸነፍ አንችልም፤ የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችን ድጋፍ ያስፈልገናል። ይሖዋ እኛን ለመርዳት ዓለም አቀፋዊ “የወንድማማች ማኅበር” ሰጥቶናል።—1 ጴጥ. 2:17

13. በዕብራውያን 10:24, 25 መሠረት በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ምን ጥቅሞች ያስገኝልናል?

13 ድጋፍ የምናገኝበት አንዱ መንገድ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው። (ዕብራውያን 10:24, 25ን አንብብ።) ሁላችንም አልፎ አልፎ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን፤ በዚህ ጊዜ ስብሰባዎች መንፈሳችንን ያድሱታል። ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የሚሰጧቸው ከልብ የመነጩ ሐሳቦች ያበረታቱናል። የሚያቀርቧቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ንግግሮችና ሠርቶ ማሳያዎችም ይሖዋን ለማገልገል ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክሩልናል። በተጨማሪም ከስብሰባዎች በፊትና በኋላ የምናደርጋቸው የሚያንጹ ጭውውቶች ያበረታቱናል። (1 ተሰ. 5:14) ከዚህም ሌላ ስብሰባዎች ሌሎችን በመርዳት የሚገኘውን ደስታ የምናጣጥምበት አጋጣሚ ይሰጡናል። (ሥራ 20:35፤ ሮም 1:11, 12) ስብሰባዎቻችን በሌሎች መንገዶችም ይረዱናል። የመስበክና የማስተማር ችሎታችንን እንድናሻሽል ስለሚረዱን የውጊያ ክህሎታችንን ያሳድጉልናል ሊባል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የማስተማሪያ መሣሪያዎቻችንን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። እንግዲያው ለጉባኤ ስብሰባዎች በሚገባ ተዘጋጁ። በስብሰባ ወቅት በጥሞና አዳምጡ። ከስብሰባው በኋላ ደግሞ ያገኛችሁትን ሥልጠና በተግባር አውሉ። እንዲህ ካደረጋችሁ “የክርስቶስ ኢየሱስ ምርጥ ወታደር” መሆን ትችላላችሁ።—2 ጢሞ. 2:3

14. ከእምነት ባልንጀሮቻችን በተጨማሪ የእነማን እርዳታ አለን?

14 በተጨማሪም እልፍ አእላፋት ኃያላን መላእክት ከጎናችን አሉ። አንድ መልአክ ብቻ እንኳ ምን ያህል ኃይል እንዳለው አስቡት! (ኢሳ. 37:36) እጅግ ብዙ መላእክትን ያቀፈ ሠራዊትማ ምን ያህል ኃይል እንደሚኖረው መገመት አያዳግትም። ከይሖዋ ኃያል ሠራዊት ጋር ሊወዳደር የሚችል ኃይል ያለው ሰውም ሆነ ጋኔን የለም! አንድ ታማኝ ክርስቲያን ይሖዋ ከጎኑ ካለ ከየትኛውም ጭፍራ የሚበልጥ ኃይል ይኖረዋል። (መሳ. 6:16) የሥራ ባልደረባችሁ፣ አብሯችሁ የሚማር ልጅ ወይም የማያምን ዘመዳችሁ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ሲናገር ወይም ሲያደርግ እነዚህን ነገሮች ማስታወሳችሁ ይረዳችኋል። በዚህ ውጊያ ላይ ብቻችሁን እንዳልሆናችሁ አስታውሱ። የይሖዋን አመራር እየተከተላችሁ ስለሆነ እሱ ይደግፋችኋል።

ምንጊዜም የይሖዋ ጥበቃ አይለየንም

15. በኢሳይያስ 54:15, 17 መሠረት የአምላክን ሕዝቦች ዝም ማሰኘት የማይቻለው ለምንድን ነው?

15 በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም እኛን የሚጠላበት ብዙ ምክንያት አለው። በፖለቲካ ጉዳዮች ረገድ ሙሉ በሙሉ ገለልተኞች ነን፤ እንዲሁም በጦርነት አንካፈልም። የአምላክን ስም እናውጃለን፤ ለሰው ልጆች ሰላም የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ እንሰብካለን፤ እንዲሁም የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች እናከብራለን። የዚህ ዓለም ገዢ ጨካኝ፣ ውሸታምና ነፍሰ ገዳይ መሆኑን እናጋልጣለን። (ዮሐ. 8:44) በተጨማሪም የሰይጣን ዓለም በቅርቡ እንደሚጠፋ እናውጃለን። ያም ቢሆን ሰይጣንና ተከታዮቹ ዝም ሊያሰኙን አይችሉም። እንዲያውም ባገኘናቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ተጠቅመን ይሖዋን ማወደሳችንን እንቀጥላለን! ሰይጣን በጣም ኃያል ቢሆንም የመንግሥቱ መልእክት በዓለም ዙሪያ ወዳሉ ሰዎች እንዳይደርስ ማገድ አልቻለም። የይሖዋ ጥበቃ ባይኖረን ኖሮ ይህ ሊሆን አይችልም ነበር።ኢሳይያስ 54:15, 17ን አንብብ።

16. ይሖዋ በታላቁ መከራ ወቅት ሕዝቦቹን የሚያድናቸው እንዴት ነው?

16 ወደፊት ምን ይጠብቀናል? በታላቁ መከራ ወቅት ይሖዋ በሁለት አስደናቂ መንገዶች ያድነናል። አንደኛ፣ ይሖዋ የዓለም ነገሥታት ታላቂቱ ባቢሎንን ማለትም በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ እንዲያጠፉ በሚያደርግበት ወቅት ታማኝ አገልጋዮቹን ያድናቸዋል። (ራእይ 17:16-18፤ 18:2, 4) ቀጥሎም በአርማጌዶን ቀሪዎቹን የሰይጣን ዓለም ክፍሎች ጠራርጎ ሲያጠፋ ሕዝቦቹን ያድናቸዋል።—ራእይ 7:9, 10፤ 16:14, 16

17. ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን መኖራችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

17 ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ከኖርን ሰይጣን ምንም ዓይነት ዘላቂ ጉዳት ሊያደርስብን አይችልም። እንዲያውም ለዘለቄታው የሚደመሰሰው እሱ ነው። (ሮም 16:20) እንግዲያው ሙሉውን የጦር ትጥቅ ልበሱ፤ እንዲሁም ፈጽሞ አታውልቁት! ብቻችሁን ለመዋጋት አትሞክሩ። ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ደግፉ። የይሖዋን አመራርም ተከተሉ። እንዲህ ካደረጋችሁ በሰማይ ያለው አፍቃሪ አባታችሁ እንደሚያጠነክራችሁና እንደሚጠብቃችሁ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ።—ኢሳ. 41:10

መዝሙር 149 የድል መዝሙር

a መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ እንደሚያጠነክረን እንዲሁም ከመንፈሳዊ ጉዳት ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ጉዳት ሊያደርስብን ከሚችል ከማንኛውም ነገር እንደሚጠብቀን ቃል ገብቶልናል። በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን፦ ጥበቃ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ይሖዋ የሚጠብቀን እንዴት ነው? የይሖዋን እርዳታ ለማግኘትስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?