በዛሬው ጊዜ ከይሖዋ መመሪያ ተጠቃሚ መሆን
ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ በፖላንድ
“የተጠመቅኩት በ15 ዓመቴ ነው፤ ከስድስት ወር በኋላ ረዳት አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ የዘወትር አቅኚ ለመሆን አመለከትኩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ሳጠናቅቅ፣ የመንግሥቱ ምሥራች ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄጄ ለማገልገል ጥያቄ አቀረብኩ። ያደግኩበትን አካባቢ ለቅቄ መሄድ እንዲሁም አብሬያት ከምኖረው የይሖዋ ምሥክር ያልሆነች አያቴ መለየት ፈልጌ ነበር። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ፣ እዚያው የተወለድኩበት ከተማ ውስጥ እንዳገለግል መመደቤን ሲነግረኝ በጣም አዘንኩ! ምን ያህል እንዳዘንኩ እንዲያውቅብኝ ግን አልፈለግኩም። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የነገረኝን እያውጠነጠንኩ አንገቴን አቀርቅሬ ሄድኩ። የአገልግሎት ጓደኛዬን እንዲህ አልኳት፦ “እንደ ዮናስ እየሆንኩ ነው መሰለኝ። ዮናስ ግን በስተ መጨረሻ ወደ ነነዌ ሄዷል። ስለዚህ እኔም በተመደብኩበት ቦታ አገለግላለሁ።”
“በተወለድኩበት ከተማ በአቅኚነት ማገልገል ከጀመርኩ አሁን አራት ዓመት ሆኖኛል፤ የተሰጠኝን መመሪያ መቀበሌ ጥበብ የተንጸባረቀበት እርምጃ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ዋነኛው ችግሬ አሉታዊ አመለካከት የነበረኝ መሆኑ ነው። አሁን ይበልጥ ደስተኛ ነኝ። በአንድ ወር ውስጥ 24 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መምራት ችያለሁ። በይሖዋ እርዳታ፣ ተቃዋሚ የነበረችውን አያቴን ጭምር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ችያለሁ።”
አስደሳች ውጤት በፊጂ
በፊጂ የምትገኝ አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ በአንድ ትልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ከመገኘትና በዘመዳቸው የልደት ሥነ ሥርዓት ላይ ከባለቤቷ ጋር ከመገኘት አንዱን መምረጥ ነበረባት። ባለቤቷ ወደ ስብሰባው እንድትሄድ ፈቀደላት። እሷም ከስብሰባው በኋላ በግብዣው ላይ እንደምትገኝ ነገረችው። ከስብሰባው ስትመለስ ግን መንፈሳዊነቷን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ውስጥ አለመግባቷ እንደሚሻል ተሰማት፤ ስለሆነም ሳትሄድ ቀረች።
ባለቤቷ በግብዣው ላይ እያለ፣ ሚስቱ “የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዋን” ስትጨርስ እንድትመጣ ስለጠየቃት በልደት ዝግጅቱ ላይ እንደምትገኝ ለዘመዶቹ ነገራቸው፤ እነሱ ግን “አትመጣም፤ የይሖዋ ምሥክሮች ልደት አያከብሩም!” a ብለው መለሱለት።
በኋላ ላይ ባልየው፣ ሚስቱ ከእምነቷና ከሕሊናዋ ጋር የሚስማማ አቋም እንደወሰደች ሲመለከት በጣም ኮራባት። የወሰደችው የታማኝነት እርምጃ ከጊዜ በኋላ ለባሏ እንዲሁም ለሌሎች መመሥከር የምትችልበት አጋጣሚ ፈጠረላት። ውጤቱ ምን ሆነ? ባለቤቷ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና የቀረበለትን ግብዣ የተቀበለ ሲሆን ከሚስቱ ጋር በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ።
a በታኅሣሥ 15, 2001 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።