በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወጣቶች—ለጥምቀት መዘጋጀት የምትችሉት እንዴት ነው?

ወጣቶች—ለጥምቀት መዘጋጀት የምትችሉት እንዴት ነው?

“አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል።”—መዝ. 40:8

መዝሙሮች፦ 51, 58

1, 2. (ሀ) ጥምቀት ትልቅ እርምጃ የሆነው ለምን እንደሆነ አብራራ። (ለ) አንድ ሰው ከመጠመቁ በፊት ስለ ምን ነገር እርግጠኛ መሆን አለበት? ለምንስ?

 ለመጠመቅ እያሰብክ ያለህ ወጣት ነህ? ከሆነ ይህ በሕይወትህ ልታገኘው ከምትችለው መብት ሁሉ እጅግ የላቀው ነው። ሆኖም ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ጥምቀት ትልቅ እርምጃ ነው። የይሖዋን ፈቃድ በሕይወትህ ውስጥ ከማንኛውም ነገር በላይ በማስቀደም እሱን ለዘላለም ለማገልገል ቃል መግባትህን በሌላ አባባል ራስህን መወሰንህን ያሳያል። መጠመቅ የሚኖርብህ ይህን ውሳኔ ለማድረግ ብቃቱን ስታሟላ፣ በራስህ ተነሳሽነት ለመጠመቅ ፍላጎቱ ሲኖርህ እንዲሁም ራስን መወሰን ምን ትርጉም እንዳለው ስትረዳ እንደሆነ ግልጽ ነው።

2 ለመጠመቅ ዝግጁ እንደሆንክ የማይሰማህ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? አሊያም ደግሞ አንተ መጠመቅ ብትፈልግም ወላጆችህ ግን መቆየት እንዳለብህ የሚሰማቸው ቢሆንስ? ምናልባትም እንዲህ ያሉት በክርስቲያናዊ ሕይወት ትንሽ ተሞክሮ እንድታገኝ አስበው ሊሆን ይችላል። ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ተስፋ አትቁረጥ። ከዚህ ይልቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመጠመቅ ብቁ እንድትሆን አጋጣሚውን እድገት ለማድረግ ተጠቀምበት። ይህን ነጥብ በአእምሮህ ይዘህ (1) ከምታምንባቸው ነገሮች፣ (2) ከምግባርህ እንዲሁም (3) ከምታሳየው አድናቆት ጋር በተያያዘ ምን ግቦች ማውጣት እንደምትችል አስብ።

የምታምንባቸው ነገሮች

3, 4. ወጣቶች፣ ጢሞቴዎስ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

3 ለሚከተሉት ጥያቄዎች ምን መልስ እንደምትሰጥ ቆም ብለህ አስብ፦ በአምላክ መኖር የማምነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በመንፈስ መሪነት ያስጻፈው እንደሆነ እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው? በአምላክ የሥነ ምግባር ደንቦች መመራት የዓለምን አኗኗር ከመከተል የተሻለ እንደሆነ የማምነው ለምንድን ነው? የእነዚህ ጥያቄዎች ዓላማ በውስጥህ ጥርጣሬ መፍጠር አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ “ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ [አረጋግጡ]” በማለት የሰጠውን ማሳሰቢያ ለመከተል ይረዱሃል። (ሮም 12:2) ሆኖም በሮም የሚገኙ ክርስቲያኖች ቀድሞውኑ የተቀበሉትን ነገር ማረጋገጥ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?

4 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንመልከት። ጢሞቴዎስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። እናቱና አያቱ “ከጨቅላነት” ዕድሜው አንስቶ አስተምረውታል። ያም ቢሆን ጳውሎስ “በተማርካቸውና አምነህ በተቀበልካቸው ነገሮች ጸንተህ ኑር” በማለት አሳስቦት ነበር። (2 ጢሞ. 3:14, 15) አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ‘መቀበል’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል በበኩረ ጽሑፉ “አንድ ነገር እውነት መሆኑን ማመንና እርግጠኛ መሆን” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ጢሞቴዎስ እውነትን የራሱ አድርጓል። እንዲህ ያደረገው እናቱና አያቱ ስላስገደዱት ሳይሆን በተማረው ነገር ላይ በሚገባ ካሰበበት በኋላ አምኖ ስለተቀበለው ነው።—ሮም 12:1ን አንብብ።

5, 6. ከልጅነት ዕድሜህ አንስቶ ‘የማሰብ ችሎታህን’ ማሠራትህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

5 የአንተስ ሁኔታ እንዴት ነው? ምናልባት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ያወቅከው ከረጅም ጊዜ በፊት ይሆናል። ከሆነ ትምህርቶቹን አምነህ እንድትቀበል ያደረጉህን ምክንያቶች ለመመርመር ለምን ግብ አታወጣም? እንዲህ ማድረግህ በምታምንባቸው ነገሮች ላይ ያለህን እምነት የሚያጠናክርልህ ከመሆኑም በላይ በእኩዮች ተጽዕኖ፣ በዚህ ዓለም ፕሮፓጋንዳ አልፎ ተርፎም በራስህ ስሜት እንዳትሸነፍ ይረዳሃል።

6 ከልጅነት ዕድሜህ አንስቶ ‘የማሰብ ችሎታህን’ ማሠራትህ እኩዮችህ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አሳማኝ መልስ መስጠት እንድትችል ያዘጋጅሃል፤ እኩዮችህ እንዲህ ብለው ሊጠይቁህ ይችላሉ፦ ‘አምላክ መኖሩን እንዴት በእርግጠኝነት ማወቅ ትችላለህ? አፍቃሪ የሆነ አምላክ ክፋት እንዲኖር ለምን ይፈቅዳል? አምላክ መጀመሪያ የለውም ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?’ አስቀድመህ ከተዘጋጀህ እንዲህ ያሉት ጥያቄዎች እምነትህን ከማዳከም ይልቅ በግል ጥናትህ ላይ ተጨማሪ ምርምር ለማድረግ ሊያነሳሱህ ይችላሉ።

7-9. ድረ ገጻችን ላይ የሚወጣው “ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?” የሚለው ዓምድ ስለምታምንባቸው ነገሮች ይበልጥ እርግጠኛ እንድትሆን የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ ግለጽ።

7 ትጋት የተሞላበት የግል ጥናት ማድረግህ ለሚቀርቡልህ ጥያቄዎች መልስ እንድትሰጥ፣ ማንኛውንም ጥርጣሬ እንድታስወግድ እንዲሁም እምነትህን እንድታጠናክር ሊረዳህ ይችላል። (ሥራ 17:11) ለዚህ የሚረዱህ በርካታ መሣሪያዎች አሉ። ብዙዎች የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተባለውን ብሮሹርና ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (በአማርኛ አይገኝም) የተሰኘውን መጽሐፍ በግል ማጥናታቸው ጠቅሟቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ብዙ ወጣቶች ኢንተርኔት ላይ የሚወጣውን “ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?” የሚለውን ዓምድ የሚወዱት ከመሆኑም ሌላ ብዙ ጥቅም አግኝተውበታል። እነዚህን በተከታታይ የሚወጡ ማጥኛ ጽሑፎች jw.org ላይ “የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች” በሚለው ክፍል ሥር ልታገኛቸው ትችላለህ። እያንዳንዱ ማጥኛ ጽሑፍ በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያለህን እምነት ማጠናከር እንድትችል ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

8 ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ትውውቅ ስላለህ በማጥኛ ጽሑፎቹ ላይ ለሚገኙት ጥያቄዎች መልስ መስጠት አይከብድህ ይሆናል። ይሁንና መልስህ ትክክለኛ እንደሆነ እርግጠኛ ያደረገህ ምንድን ነው? ማጥኛ ጽሑፎቹ በተለያዩ ጥቅሶች ላይ በጥሞና እንድታስብና ከዚያም ጥቅሶቹን በተመለከተ ያለህን አመለካከት እንድትጽፍ ያበረታታሉ። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን እምነትህን ለሌሎች እንዴት ማብራራት እንደምትችል አስቀድመህ እንድታስብ ይረዱሃል። ድረ ገጻችን ላይ የሚወጣው “ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?” የሚለው ዓምድ በርካታ ወጣቶች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ይበልጥ እርግጠኛ እንዲሆኑ እየረዳ ነው። አንተስ ኢንተርኔት የመጠቀም አጋጣሚው ካለህ ይህን ዓምድ በግል ጥናት ፕሮግራምህ ውስጥ ለምን አታካትተውም?

9 ብቃቱን አሟልተህ ለመጠመቅ ልትወስደው የሚገባ አንድ ወሳኝ እርምጃ ስለምታምንባቸው ነገሮች ይበልጥ እርግጠኛ መሆን ነው። በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ለመጠመቅ ከመወሰኔ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናሁ ከመሆኑም ሌላ እውነተኛውን ሃይማኖት እንደያዝኩ እርግጠኛ መሆን ችዬ ነበር። በሕይወት በማሳልፈው በእያንዳንዱ ቀን እምነቴ ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል።”

ምግባርህ

10. አንድ የተጠመቀ ክርስቲያን ከሚያምንበት ነገር ጋር የሚስማማ ምግባር ይኖረዋል ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?

10 መጽሐፍ ቅዱስ ‘በሥራ ያልተደገፈ እምነት በራሱ የሞተ ነው’ ይላል። (ያዕ. 2:17) ስለምታምንበት ነገር እርግጠኛ ከሆንክ ይህ በምግባርህ ላይ መንጸባረቁ አይቀርም። ምን ዓይነት ምግባር ታሳያለህ? መጽሐፍ ቅዱስ “ቅዱስ ሥነ ምግባር” ሊኖርህና ‘ለአምላክ ያደሩ መሆንን የሚያሳዩ ተግባሮች’ ልትፈጽም እንደሚገባ ይገልጻል።—2 ጴጥሮስ 3:11ን አንብብ።

11. “ቅዱስ ሥነ ምግባር” የሚለው አገላለጽ ምን ነገሮችን እንደሚያካትት አብራራ።

11 “ቅዱስ ሥነ ምግባር” ሲባል ምን ማለት ነው? ምግባርህ ቅዱስ ከሆነ ከሥነ ምግባር አኳያ ንጹሕ ነህ ማለት ነው። በዚህ ረገድ የአንተ ሁኔታ ምን ይመስላል? ለምሳሌ ያለፉትን ስድስት ወራት መለስ ብለህ አስብ። ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ለመለየት የሠለጠነ “የማስተዋል ችሎታ” እንዳለህ ያሳየኸው እንዴት ነው? (ዕብ. 5:14) ፈተናዎችን ወይም የእኩዮችን ተጽእኖ የተቋቋምክባቸውን አጋጣሚዎች ታስታውሳለህ? በትምህርት ቤት የምታሳየው ምግባር ስለምታምንበት ነገር ጥሩ ምሥክርነት ይሰጣል? ሌሎች እንዳያሾፉብህ ስትል ብቻ አብረውህ ከሚማሩ ልጆች ጋር ለመመሳሰል ከመሞከር ይልቅ ለምታምንበት ነገር ጥብቅና ትቆማለህ? (1 ጴጥ. 4:3, 4) እርግጥ ነው፣ ፍጹም የሆነ ሰው የለም። ይሖዋን ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ሰዎችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ በሕዝብ ፊት ስለሚያምኑበት ነገር በይፋ መናገር ሊያስፈራቸው ይችላል። ይሁንና ራሱን ለይሖዋ የወሰነ አንድ ሰው የአምላክን ስም በመሸከሙ ኩራት ይሰማዋል፤ ይህንንም በምግባሩ ያሳያል።

12. ‘ለአምላክ ያደሩ መሆንን የሚያሳዩ’ አንዳንድ ተግባሮች የትኞቹ ናቸው? ለእነዚህ ተግባሮችስ ምን አመለካከት ሊኖርህ ይገባል?

12 ‘ለአምላክ ያደሩ መሆንን የሚያሳዩ ተግባሮች’ የተባሉት የትኞቹ ናቸው? እነዚህ ተግባሮች በጉባኤ ውስጥ የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሲሆኑ አዘውትሮ በስብሰባ ላይ መገኘትንና በአገልግሎት መካፈልን ያካትታሉ። በግልህ እንደምታቀርበው ጸሎትና የግል ጥናት የመሳሰሉ ሰዎች የማያዩአቸው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችም በዚህ ውስጥ ይጠቃለላሉ። ራሱን ለይሖዋ የወሰነ ግለሰብ እነዚህን ነገሮች እንደ አድካሚ ሥራ አይመለከታቸውም። ከዚህ ይልቅ ንጉሥ ዳዊት የገለጸው የሚከተለው አመለካከት ይኖረዋል፦ “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው።”—መዝ. 40:8

13, 14. ‘ለአምላክ ያደሩ መሆንን የሚያሳዩ ተግባሮችን’ ለማከናወን የሚረዳህ ምን ዝግጅት አለ? አንዳንድ ወጣቶች ከዚህ ዝግጅት ምን ጥቅም አግኝተዋል?

13 ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች (ጥራዝ 2) በተባለው መጽሐፍ ገጽ 308 እና 309 ላይ የሚገኘውን የመልመጃ ሣጥን በመጠቀም ግብ ማውጣት ትችላለህ። ይህ የመልመጃ ሣጥን ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ እንድትሰጥ ይጋብዝሃል፦ “ስለ አንድ ጉዳይ ስትጸልይ ሐሳብህን በግልጽ ትናገራለህ ወይስ እንዲያው በደፈናው ታስቀምጠዋለህ? ጸሎትህ ለይሖዋ ስላለህ ፍቅር ምን ያሳያል?” “በግል ጥናትህ ወቅት የትኞቹን ነገሮች ታጠናለህ?” “ወላጆችህ በአገልግሎት ባይካፈሉም እንኳ አንተ እንዲህ ታደርጋለህ?” ከዚህ በተጨማሪ የመልመጃ ሣጥኑ ከጸሎት፣ ከግል ጥናትና ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ማውጣት የምትፈልጋቸውን ግቦች የምትጽፍበት ባዶ ቦታ አለው።

14 ለመጠመቅ እያሰቡ ያሉ በርካታ ወጣቶች ይህን የመልመጃ ሣጥን ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። ቲልዳ የተባለች ወጣት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በዚህ የመልመጃ ሣጥን ተጠቅሜ ግቦች አወጣሁ። አንድ በአንድ እነዚህ ግቦች ላይ ስለደረስኩ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ለመጠመቅ ዝግጁ ሆንኩ።” ፓትሪክ የተባለ ወጣት ወንድምም ተመሳሳይ ጥቅም አግኝቷል። እንዲህ ብሏል፦ “ድሮም ቢሆን ግቦች ነበሩኝ፤ ግቦቼን በጽሑፍ ማስፈሬ ግን እዚያ ላይ ለመድረስ ጠንክሬ እንድሠራ አነሳስቶኛል።”

ወላጆችህ ይሖዋን ማገልገላቸውን ቢያቆሙ አንተ እሱን ማገልገልህን ትቀጥላለህ? (አንቀጽ 15ን ተመልከት)

15. ራስን መወሰን በራስህ ፍላጎት ተነሳስተህ ልታደርገው የሚገባ ውሳኔ የሆነው ለምንድን ነው? አብራራ።

15 በመልመጃ ሣጥኑ ውስጥ ከሚገኙና በጥሞና ልታስብባቸው ከሚገቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ “ወላጆችህና ጓደኞችህ ይሖዋን ማገልገላቸውን ቢያቆሙም እንኳ አንተ ታገለግለዋለህ?” የሚለው ነው። ራስህን የወሰንክና የተጠመቅክ ክርስቲያን ስትሆን በይሖዋ ፊት የምትቆመው ራስህን ችለህ እንደሆነ አስታውስ። ለእሱ የምታቀርበው አገልግሎት በማንም ላይ ሌላው ቀርቶ በወላጆችህ ላይ የተመካ መሆን የለበትም። ቅዱስ ሥነ ምግባር መያዝህ እንዲሁም ለአምላክ ያደርክ መሆንህን የሚያሳይ ተግባር መፈጸምህ እውነትን የራስህ እንዳደረግክና ለመጠመቅ ብቃቱን እያሟላህ እንደሆነ ያሳያል።

የምታሳየው አድናቆት

16, 17. (ሀ) አንድ ሰው ክርስቲያን ለመሆን ሊያነሳሳው የሚገባው ምክንያት ምንድን ነው? (ለ) ለቤዛው ዝግጅት ሊኖረን የሚገባውን አድናቆት በምሳሌ አስረዳ።

16 የሙሴን ሕግ ጠንቅቆ የሚያውቅ አንድ ሰው “ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?” በማለት ኢየሱስን ጠየቀው። ኢየሱስም “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ” በማለት መለሰለት። (ማቴ. 22:35-37) ኢየሱስ የሰጠው ምላሽ እንደሚጠቁመው አንድ ሰው ተጠምቆ ክርስቲያን እንዲሆን የሚያነሳሳው ለይሖዋ ያለው ልባዊ ፍቅር መሆን አለበት። ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ማሳደግ ከምትችልባቸው ከሁሉ የተሻሉ መንገዶች አንዱ ይሖዋ በሰጠን እጅግ የላቀ ስጦታ ማለትም በልጁ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ማሰላሰል ነው። (2 ቆሮንቶስ 5:14, 15ን እና 1 ዮሐንስ 4:9, 19ን አንብብ።) ስለ ቤዛው እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ለአንተ ስላለው ትርጉም ማሰብህ የአድናቆት ስሜት እንዲያድርብህ ያደርጋል።

17 ለቤዛው ስጦታ የምትሰጠውን ምላሽ ለማስረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ አንድ ሰው ከመስመጥ አዳነህ እንበል። ቤት ሄደህ ሰውነትህን ካደራረቅክ በኋላ የተደረገልህን ነገር በሙሉ ትረሳለህ? በጭራሽ! ከሞት ላዳነህ ሰው ትልቅ ውለታ እንዳለብህ እንደሚሰማህ ጥርጥር የለውም። እንደ እውነቱ ከሆነ ያ ሰው በሕይወት እንድትቀጥል አስችሎሃል! ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ከዚህ የላቀ ውለታ ውለውልናል። የቤዛው ዝግጅት ባይኖር ኖሮ ሁላችንም በኃጢአትና በሞት ባሕር ውስጥ ሰምጠን እንቀር ነበር። ሆኖም ይሖዋ ባደረገልን በዚህ ታላቅ የፍቅር መግለጫ የተነሳ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ወደር የለሽ ተስፋ ተከፍቶልናል!

18, 19. (ሀ) የይሖዋ ንብረት መሆን ሊያስፈራህ የማይገባው ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋን ማገልገል የተሻለ ሕይወት እንድትመራ የሚረዳህ እንዴት ነው?

18 ይሖዋ ላደረገልህ ነገር አድናቆት አለህ? ከሆነ ራስህን ለይሖዋ መወሰንና መጠመቅ ይኖርብሃል። ራስን መወሰን የይሖዋን ፈቃድ በሕይወትህ ውስጥ ከማንኛውም ነገር በላይ በማስቀደም እሱን ለዘላለም ለማገልገል የምትገባው ቃል ኪዳን እንደሆነ አስታውስ። ታዲያ እንዲህ ያለ ከባድ እርምጃ መውሰድ ሊያስፈራህ ይገባል? በፍጹም! ይሖዋ ምንጊዜም በሕይወትህ ደስተኛ እንድትሆን እንደሚፈልግ፣ “ከልብ ለሚፈልጉትም ወሮታ ከፋይ መሆኑን” አትርሳ። (ዕብ. 11:6) ራስህን ለይሖዋ መወሰንህና መጠመቅህ ሕይወትህ እንዲበላሽ አያደርግም። ከዚህ በተቃራኒ ይሖዋን ማገልገል የተሻለ ሕይወት እንድትመራ ያስችልሃል። በአሥራዎቹ ዕድሜ የተጠመቀ አንድ የ24 ዓመት ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ዕድሜዬ ከፍ እስኪል ብጠብቅ ኖሮ የተሻለ እውቀት ይኖረኝ ይሆናል፤ ያም ሆኖ ራሴን ለይሖዋ መወሰኔ ዓለማዊ ነገሮችን ከማሳደድ ጠብቆኛል።”

19 ይሖዋ ከሰይጣን ምንኛ የተለየ ነው! የሰይጣን ፍላጎት አንተን መጠቀሚያ ማድረግ ብቻ ነው። ከእሱ ጎን ለሚቆሙ ሰዎች የሚሰጣቸው ዘላቂ ጥቅም የለም። ደግሞስ እንዲህ ማድረግ ይችላል? ሰይጣን የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ መልካም ነገር አይታየውም፤ ተስፋው የጨለመ ነው። ታዲያ እሱ ራሱ የሌለውን ነገር እንዴት ሊሰጥህ ይችላል? ሰይጣን ሊሰጥህ የሚችለው ልክ እሱ እንደሚጠብቀው ያለ አስከፊ ነገር ነው!—ራእይ 20:10

20. አንድ ወጣት ራሱን ለመወሰንና ለመጠመቅ እድገት ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? (“ መንፈሳዊ እድገት እንድታደርግ የሚረዱ ርዕሶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

20 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ራስህን ለይሖዋ መወሰንህ ትክክለኛ እርምጃ ነው። ታዲያ ይህን እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተሃል? ከሆነ ወደኋላ አትበል። በሌላ በኩል ደግሞ ተጨማሪ ጊዜ የሚያስፈልግህ ከሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን ምክሮች ሥራ ላይ በማዋል እድገት ማድረግህን ቀጥል። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች “ምንም ያህል እድገት ያደረግን ብንሆን በዚሁ መንገድ በአግባቡ ወደፊት መጓዛችንን እንቀጥል” ሲል ጽፎላቸዋል። (ፊልጵ. 3:16) ይህን ምክር በሥራ ላይ ካዋልክ ብዙም ሳይቆይ ራስህን ለይሖዋ ለመወሰንና ለመጠመቅ መነሳሳትህ አይቀርም።