በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 7

‘የጥበበኞችን ቃል አዳምጥ’

‘የጥበበኞችን ቃል አዳምጥ’

“ጆሮህን አዘንብል፤ የጥበበኞችንም ቃል አዳምጥ።”—ምሳሌ 22:17

መዝሙር 123 ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት በታማኝነት መገዛት

ማስተዋወቂያ a

1. ምክር በምን መልኩ ሊመጣ ይችላል? ሁላችንም ምክር የሚያስፈልገንስ ለምንድን ነው?

 ሁላችንም ምክር የሚያስፈልገን ጊዜ አለ። አንዳንድ ጊዜ እኛ ራሳችን ቅድሚያውን ወስደን አንድ የምናከብረውን ሰው ምክር እንጠይቃለን። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ሁኔታችን ያሳሰበው አንድ ወንድም፣ በኋላ ላይ የምንጸጸትበትን “የተሳሳተ ጎዳና” ልንከተል እንደሆነ ይጠቁመን ይሆናል። (ገላ. 6:1) ወይም ደግሞ ከባድ ስህተት ሠርተን እርማት ይሰጠን ይሆናል፤ ይህም ምክር የምናገኝበት አንዱ መንገድ ነው። ምክሩ በምንም መልኩ ቢመጣ ልንሰማ ይገባል። ይህን ማድረጋችን የሚበጀን ከመሆኑም ሌላ ሕይወታችንን ሊታደግልን ይችላል!—ምሳሌ 6:23

2. በምሳሌ 12:15 መሠረት ምክር መስማት ያለብን ለምንድን ነው?

2 ትምህርቱ የተመሠረተበት ጥቅስ ‘የጥበበኞችን ቃል እንድናዳምጥ’ ያበረታታናል። (ምሳሌ 22:17) ሁሉንም ነገር የሚያውቅ ሰው የለም፤ ምንጊዜም ቢሆን ከእኛ የበለጠ እውቀት ወይም ተሞክሮ ያለው ሰው መኖሩ አይቀርም። (ምሳሌ 12:15ን አንብብ።) ስለዚህ ምክር መስማት የትሕትና አንዱ መገለጫ ነው። ያሉብንን ገደቦች እንደምንረዳና ግባችን ላይ ለመድረስ የሌሎች እርዳታ እንደሚያስፈልገን እንደምንገነዘብ ያሳያል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን ‘የታቀደው ነገር በብዙ አማካሪዎች ይሳካል’ በማለት በመንፈስ መሪነት ጽፏል።—ምሳሌ 15:22

ከእነዚህ ሁለት የምክር ዓይነቶች ለመቀበል የሚከብድህ የትኛውን ነው? (ከአንቀጽ 3-4⁠ን ተመልከት)

3. በየትኞቹ መንገዶች ምክር ልናገኝ እንችላለን?

3 ቀጥተኛ በሆነ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ምክር እናገኝ ይሆናል። ቀጥተኛ ያልሆነ ምክር ስንል ምን ማለታችን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ወይም ጽሑፎቻችን ላይ የምናነበው አንድ ነገር ስለ አካሄዳችን ቆም ብለን እንድናስብና ማስተካከያ እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይችላል። (ዕብ. 4:12) እንዲህ ያለው ምክር ቀጥተኛ ያልሆነ ሊባል ይችላል። ቀጥተኛ ምክር ስንልስ ምን ማለታችን ነው? አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ወይም የጎለመሰ ወንድም ማስተካከል ያለብንን ነገር ይነግረን ይሆናል። ይህ ቀጥተኛ ምክር ሊባል ይችላል። አንድ ሰው ለእኛ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ከሰጠን፣ ምክሩን በመስማትና ተግባራዊ በማድረግ አድናቆታችንን ልናሳይ ይገባል።

4. በመክብብ 7:9 መሠረት ምክር ሲሰጠን ምን ማድረግ የለብንም?

4 እውነታውን ካየን፣ ብዙ ጊዜ መቀበል የሚከብደን ቀጥተኛ የሆነን ምክር ነው። እንዲያውም እንበሳጭ ይሆናል። ለምን? ፍጹም አለመሆናችንን መቀበል ባይከብደንም አንድ ሰው ድክመታችንን ለይቶ ሲነግረን፣ ብዙውን ጊዜ ምክሩን መቀበል ይተናነቀናል። (መክብብ 7:9ን አንብብ።) ሰበብ አስባብ እንደረድር ይሆናል። ምክሩን በሰጠን ግለሰብ ዝንባሌ ላይ ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን፤ ወይም ደግሞ ምክሩን በሰጠበት መንገድ እንከፋ ይሆናል። ሌላው ቀርቶ ምክር በሰጠን ሰው ላይ እንከን ወደመፈላለግ ልንሄድ እንችላለን፤ ‘እሱ ማን ሆኖ ነው እንዲህ የሚለኝ? እሱ ራሱ ስንት ነገር ያጠፋ የለ!’ እንል ይሆናል። የተሰጠንን ምክር ካልወደድነው ደግሞ ምክሩን ችላ ልንለው ወይም ሌላ የሚስማማንን ምክር ፍለጋ ልንሄድ እንችላለን።

5. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

5 በዚህ ርዕስ ውስጥ ምክር ያልሰሙና ምክር የተቀበሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመለከታለን። በተጨማሪም ምክር ለመቀበልና ከምክሩ ጥቅም ለማግኘት ምን እንደሚረዳን እናያለን።

ምክር አልሰሙም

6. ንጉሥ ሮብዓም ምክር ሲሰጠው ካደረገው ነገር ምን ትምህርት እናገኛለን?

6 ሮብዓምን እንደ ምሳሌ እንመልከት። የእስራኤል ንጉሥ ሆኖ ሲሾም ሕዝቡ አንድ ጥያቄ አቀረቡለት። ጥያቄያቸው አባቱ ሰለሞን የጫነባቸውን ሸክም እንዲያቀልላቸው ነበር። ሮብዓም ለሕዝቡ ምን ምላሽ መስጠት እንዳለበት የእስራኤልን ሽማግሌዎች አማከረ፤ ይህም የሚያስመሰግነው ነው። ሽማግሌዎቹ፣ ንጉሡ ሕዝቡ የጠየቁትን ካደረገላቸው ምንጊዜም ከጎኑ እንደሚሆኑ ነገሩት። (1 ነገ. 12:3-7) ሮብዓም ግን ይህ ምክር ያረካው አይመስልም፤ ስለዚህ አብሮ አደጎቹን አማከረ። እነዚህ ሰዎች በ40ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ስለሆኑ የተወሰነ የሕይወት ተሞክሮ እንደሚኖራቸው አያጠራጥርም። (2 ዜና 12:13) በዚህ ጊዜ ለሮብዓም የሰጡት ምክር ግን ጥሩ አልነበረም። የሕዝቡን ሸክም እንዲያከብድባቸው መከሩት። (1 ነገ. 12:8-11) ሮብዓም ሁለት የተለያዩ ምክሮች ሲገጥሙት የትኛውን ምክር መከተል እንዳለበት ይሖዋን በጸሎት መጠየቅ ይችል ነበር። እሱ ግን ለጆሮው የሚጥመውን የአብሮ አደጎቹን ምክር ለመቀበል መረጠ። ይህ ያስከተለው መዘዝ ለሮብዓም ብቻ ሳይሆን ለሕዝቡም ተረፈ። እኛም አንዳንድ ጊዜ የሚሰጠን ምክር ብዙም ላያስደስተን ይችላል። ያም ቢሆን በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እስከሆነ ድረስ ልንቀበለው ይገባል።

7. ከንጉሥ ዖዝያ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 ንጉሥ ዖዝያ ምክር አልሰማም። ለካህናቱ ብቻ ወደተፈቀደው የቤተ መቅደሱ ክፍል ገባ፤ በዚያም ዕጣን ለማጠን ሞከረ። የይሖዋ ካህናትም “ዖዝያ ሆይ፣ አንተ ለይሖዋ ዕጣን ማጠንህ ተገቢ አይደለም! ዕጣን ማጠን ያለባቸው ካህናቱ ብቻ ናቸው” አሉት። ታዲያ ዖዝያ ምን አደረገ? የተሰጠውን ምክር በትሕትና ተቀብሎ ወዲያውኑ ከቤተ መቅደሱ ቢወጣ ኖሮ ይሖዋ ይቅር ሊለው ይችል ነበር። “ዖዝያ ግን እጅግ ተቆጣ።” ዖዝያ ምክሩን ያልሰማው ለምንድን ነው? ንጉሥ ስለሆነ የፈለገውን ነገር የማድረግ መብት እንዳለው ተሰምቶት ሳይሆን አይቀርም። ይሖዋ ግን ጉዳዩን እንደዚህ አላየውም። ዖዝያ በእብሪተኝነቱ የተነሳ በሥጋ ደዌ ተመታ፤ “እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሆኖ ኖረ።” (2 ዜና 26:16-21) ከዖዝያ ታሪክ እንደምንማረው ማንም እንሁን ማን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር የማንቀበል ከሆነ የይሖዋን ሞገስ እናጣለን።

ምክር ሰምተዋል

8. ኢዮብ ምክር ሲሰጠው ምን አድርጓል?

8 ከላይ ከተመለከትናቸው የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ ምክር በመስማታቸው የተባረኩ ሰዎችንም ይጠቅሳል። ኢዮብን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኢዮብ ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው ቢሆንም ፍጹም አልነበረም። ኢዮብ ውጥረት ውስጥ ሲገባ አንዳንድ የተሳሳቱ ነገሮችን ተናግሯል። በዚህም የተነሳ ኤሊሁም ሆነ ይሖዋ ቀጥተኛ ምክር ሰጥተውታል። ታዲያ ኢዮብ ምን ምላሽ ሰጠ? ምክሩን በትሕትና ተቀብሏል። እንዲህ ብሏል፦ “ማስተዋል በጎደለው መንገድ ተናግሬአለሁ። . . . በተናገርኩት ነገር እጸጸታለሁ፤ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬም ንስሐ እገባለሁ።” ኢዮብ ትሕትና በማሳየቱ ይሖዋ ባርኮታል።—ኢዮብ 42:3-6, 12-17

9. ሙሴ ምክር ከመቀበል ጋር በተያያዘ ምን ጥሩ ምሳሌ ትቷል?

9 ሙሴ ከባድ ስህተት ከሠራ በኋላ የተሰጠውን እርማት በመቀበል ጥሩ ምሳሌ ትቷል። በአንድ ወቅት ይሖዋን ማክበር እስኪያቅተው ድረስ ቁጣውን መቆጣጠር አቅቶት ነበር። በዚህም የተነሳ ሙሴ ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳይገባ ተከለከለ። (ዘኁ. 20:1-13) ሙሴ፣ ውሳኔውን እንደገና እንዲያስብበት ለይሖዋ ጥያቄ ሲያቀርብ “ዳግመኛ ስለዚህ ጉዳይ እንዳታነሳብኝ” አለው። (ዘዳ. 3:23-27) ሙሴ በዚህ አልተበሳጨም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋን ውሳኔ ተቀብሏል፤ ይሖዋም እስራኤላውያንን ለመምራት በእሱ መጠቀሙን ቀጥሏል። (ዘዳ. 4:1) ምክር ከመቀበል ጋር በተያያዘ ኢዮብ እና ሙሴ ግሩም ምሳሌ ትተውልናል። ኢዮብ አመለካከቱን አስተካክሏል፤ ሰበብ አስባብ አልደረደረም። ሙሴም ቢሆን የሚጓጓለትን ነገር ቢያጣም ታማኝ ሆኖ በመቀጠል የይሖዋን ምክር እንደተቀበለ አሳይቷል።

10. (ሀ) ምሳሌ 4:10-13 ምክር መቀበል ስላለው ጥቅም ምን ይላል? (ለ) አንዳንዶች ምክር ሲሰጣቸው ምን ጥሩ ዝንባሌ አሳይተዋል?

10 እንደ ኢዮብ እና ሙሴ ያሉ ታማኝ ሰዎች የተዉትን ምሳሌ መከተላችን ይጠቅመናል። (ምሳሌ 4:10-13ን አንብብ።) ብዙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንም እንዲሁ አድርገዋል። በኮንጎ የሚኖር ኢማኑኤል የተባለ ወንድም የተሰጠውን ማሳሰቢያ በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “በጉባኤያችን ያሉ የጎለመሱ ወንድሞች መንፈሳዊ አደጋ ሊደርስብኝ እንደሆነ ሲያስተውሉ ወዲያውኑ ሊታደጉኝ መጡ። የሰጡኝን ምክር ተግባራዊ አደረግኩ፤ ይህም ከብዙ ጣጣ ጠብቆኛል።” b በካናዳ የምትኖር ሜጋን የተባለች አቅኚ ምክርን በተመለከተ እንዲህ ብላለች፦ “ሁሌ የሚነግሩኝ መስማት የምፈልገውን ነው ማለት አይደለም፤ መስማት የሚያስፈልገኝን ምክር ግን ይሰጡኛል።” በክሮኤሺያ የሚኖር ማርኮ የተባለ ወንድምም እንዲህ ብሏል፦ “የነበረኝን መብት አጣሁ፤ መለስ ብዬ ሳስበው ግን ያ ምክር መንፈሳዊነቴን መልሼ እንዳገኝ እንደረዳኝ ይሰማኛል።”

11. ወንድም ካርል ክላይን ምክር ስለ መቀበል ምን ተገንዝቧል?

11 ምክርን በመስማት የተጠቀመ ሌላም ምሳሌ እንመልከት፤ ይህ ሰው የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ካርል ክላይን ነው። ወንድም ክላይን በሕይወት ታሪኩ ላይ፣ የቅርብ ጓደኛው የሆነው ወንድም ራዘርፎርድ በአንድ ወቅት ጠንከር ያለ ምክር እንደሰጠው ጠቅሷል። ወንድም ክላይን መጀመሪያ ላይ ምክሩ ቅር እንዳሰኘው በሐቀኝነት ተናግሯል። እንዲህ ሲል ተርኳል፦ “በኋላ ላይ ወንድም ራዘርፎርድ ሲያገኘኝ ፈገግ ብሎ ‘ታዲያስ ካርል!’ አለኝ። እኔ ግን ተቀይሜው ስለነበር እያጉተመተምኩ ሰላም አልኩት። በዚህ ጊዜ ‘ካርል ተጠንቀቅ! ዲያብሎስ ሊያጠምድህ ነው!’ አለኝ። እኔም አፍሬ ‘ኧረ ምንም አልሆንኩም ወንድም ራዘርፎርድ’ አልኩት። እሱ ግን እንዳኮረፍኩ ስለገባው ‘ለማንኛውም ተጠንቀቅ። ዲያብሎስ ሊያጠምድህ ነው!’ ብሎ ማስጠንቀቂያውን ደገመልኝ። ደግሞም ትክክል ነበር! አንድ ወንድም በተናገረው ሐሳብ በተለይም . . . ኃላፊነት ኖሮት አስተያየት በሚሰጠን ጊዜ የምንቀየም ከሆነ ዲያብሎስ መግቢያ ቀዳዳ እንዲያገኝ በር እንከፍትለታለን።” c (ኤፌ. 4:25-27) ወንድም ክላይን ወንድም ራዘርፎርድ የሰጠውን ምክር ተቀብሏል፤ ወዳጅነታቸውም ቀጥሏል።

ምክር ለመቀበል ምን ይረዳናል?

12. ትሕትና ምክር ለመቀበል የሚረዳን እንዴት ነው? (መዝሙር 141:5)

12 ምክር ለመቀበል ምን ይረዳናል? ትሑት መሆን ይኖርብናል፤ ፍጹማን እንዳልሆንንና አንዳንድ ጊዜ የሞኝነት ድርጊት ልንፈጽም እንደምንችል ማስታወሳችን በዚህ ረገድ ይረዳናል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ኢዮብ የተሳሳተ አመለካከት ነበረው። በኋላ ላይ ግን አመለካከቱን አስተካከለ፤ ይሖዋም ባርኮታል። ለምን? ኢዮብ ትሑት ስለነበረ ነው። በዕድሜ በጣም የሚያንሰው ቢሆንም የኤሊሁን ምክር መስማቱ ትሑት እንደሆነ የሚያሳይ ነው። (ኢዮብ 32:6, 7) እኛም ምክሩ ለእኛ እንደማይሠራ ሲሰማን ወይም ምክሩን የሰጠን ሰው በዕድሜ ከእኛ በጣም የሚያንስ በሚሆንበት ጊዜ ትሕትና ምክሩን ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳናል። በካናዳ ያለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ራሳችንን የምናየው ሌሎች እኛን በሚያዩን መንገድ ስላልሆነ የሚመክረን ሰው ከሌለ እንዴት መሻሻል እንችላለን?” ደግሞም የመንፈስ ፍሬ ከማፍራት እንዲሁም ክርስቲያናዊ አገልግሎታችንን ከምናከናውንበት መንገድ ጋር በተያያዘ ማሻሻያ ማድረግ የማያስፈልገው ማን አለ?መዝሙር 141:5ን አንብብ።

13. የሚሰጠንን ምክር እንዴት ልንመለከተው ይገባል?

13 የሚሰጣችሁን ምክር የአምላክ ፍቅር መገለጫ አድርጋችሁ ተመልከቱት። ይሖዋ የሚመኝልን የሚጠቅመንን ነገር ነው። (ምሳሌ 4:20-22) በቃሉ፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ወይም በአንድ የጎለመሰ የእምነት ባልንጀራችን ተጠቅሞ ሲመክረን ፍቅሩን እየገለጸልን ነው። ዕብራውያን 12:9, 10 “ለጥቅማችን ሲል ይገሥጸናል” ይላል።

14. ምክር ሲሰጠን ማተኮር ያለብን ምን ላይ ነው?

14 በምክሩ ላይ እንጂ በአሰጣጡ ላይ አታተኩሩ። አንዳንድ ጊዜ ምክሩ የተሰጠበት መንገድ ችግር እንዳለው ይሰማን ይሆናል። እርግጥ፣ ምክር የሚሰጥ ማንኛውም ሰው በተቻለ መጠን የሚመከረው ሰው ምክሩን መቀበል ቀላል እንዲሆንለት ሊያደርግ ይገባል። d (ገላ. 6:1) ተመካሪዎቹ እኛ ከሆንን ግን ምክሩ የተሰጠበት መንገድ ባያስደስተንም እንኳ በመልእክቱ ላይ ማተኮራችን ጠቃሚ ነው። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ምክሩ የተሰጠበትን መንገድ ባልወደውም እንኳ ከተናገረው ነገር የማገኘው ትምህርት ይኖር ይሆን? ምክር ሰጪው ያሉትን ድክመቶች በማለፍ ከምክሩ ጥቅም ማግኘት እችል ይሆን?’ ምንም ዓይነት ምክር ቢሰጠን ከምክሩ ጥቅም ለማግኘት ጥረት ማድረጋችን የጥበብ እርምጃ ነው።—ምሳሌ 15:31

ምክር በመጠየቅ ተጠቃሚዎች ሁኑ

15. ምክር መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው?

15 መጽሐፍ ቅዱስ ምክር እንድንጠይቅ ያበረታታናል። ምሳሌ 13:10 “ምክር በሚሹ ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል። ይህ በእርግጥም እውነት ነው! አንድ ሰው ቀርቦ እስኪያነጋግራቸው ከመጠበቅ ይልቅ ራሳቸው ሄደው ምክር የሚጠይቁ ሰዎች፣ ብዙውን ጊዜ ይህን ከማያደርጉ ሰዎች የበለጠ መንፈሳዊ እድገት ያደርጋሉ። እንግዲያው ቅድሚያውን ወስዳችሁ ምክር ጠይቁ።

ወጣቷ እህት የጎለመሰችውን እህት ምክር የጠየቀቻት ለምንድን ነው? (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት)

16. ምክር መጠየቅ የሚያስፈልገን መቼ ሊሆን ይችላል?

16 የእምነት አጋሮቻችን ምክር እንዲሰጡን የምንጠይቀው መቼ ሊሆን ይችላል? እስቲ አንዳንድ ሁኔታዎችን እንመልከት። (1) አንዲት እህት፣ ተሞክሮ ያላትን አንዲት አስፋፊ ጥናቷ ላይ ጋበዘቻት፤ በኋላ ላይ ከማስተማር ችሎታዋ ጋር በተያያዘ ማሻሻል የሚኖርባት ነገር ካለ ምክር ጠየቀቻት። (2) አንዲት ያላገባች እህት ልብስ መግዛት ፈልጋለች፤ ስለዚህ ምርጫዋን በተመለከተ በሐቀኝነት አስተያየት እንድትሰጣት አንዲትን የጎለመሰች እህት ጠየቀቻት። (3) አንድ ወንድም ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ንግግር ሊያቀርብ ነው። አንድን ተሞክሮ ያለው ተናጋሪ፣ ንግግሩን አዳምጦ የሚያሻሽላቸው ነገሮች ካሉ እንዲነግረው ይጠይቀዋል። ለብዙ ዓመታት ንግግር የሰጠ ወንድምም እንኳ ተሞክሮ ያላቸውን ወንድሞች ምክር መጠየቁና ምክሩን ተግባራዊ ማድረጉ ይጠቅመዋል።

17. ከምክር ተጠቃሚ ለመሆን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

17 በቀጣዮቹ ሳምንታት ወይም ወራት ሁላችንም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ምክር ማግኘታችን አይቀርም። ይህ በሚሆንበት ጊዜ፣ በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱትን ነጥቦች አስታውስ። ምንጊዜም ትሑት ሁን። በምክሩ ላይ እንጂ በአሰጣጡ ላይ አታተኩር። ደግሞም የተሰጠህን ምክር ተግባራዊ አድርግ። ጥበበኛ ሆኖ የተወለደ ማንም የለም። ምክርን የምንሰማና ተግሣጽን የምንቀበል ከሆነ ግን ‘ጥበበኛ እንደምንሆን’ የአምላክ ቃል ይናገራል።—ምሳሌ 19:20

መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን

a የይሖዋ አገልጋዮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር መስማት ያለውን ጥቅም በሚገባ ይረዳሉ። ሆኖም ምክርን መቀበል ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ደግሞስ ከሚሰጠን ምክር ጥቅም ለማግኘት ምን ይረዳናል?

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

d በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምክር የሚሰጡ ሰዎች በዘዴ መምከር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።