የጥናት ርዕስ 8
የምትሰጡት ምክር ‘ልብን ደስ ያሰኛል’?
“ዘይትና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ በቀና ምክር ላይ የተመሠረተ ጥሩ ወዳጅነትም እንዲሁ ነው።”—ምሳሌ 27:9
መዝሙር 102 ‘ደካማ የሆኑትን እርዱ’
ማስተዋወቂያ *
1-2. አንድ ወንድም ምክር ስለመስጠት ምን ተምሯል?
ከብዙ ዓመታት በፊት ሁለት ሽማግሌዎች ለአንዲት እህት የእረኝነት ጉብኝት ሊያደርጉላት ሄዱ፤ ይህች እህት ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከስብሰባዎች ቀርታ ነበር። አንደኛው ሽማግሌ ስብሰባዎች ላይ መገኘትን የሚያበረታቱ ብዙ ጥቅሶች አሳያት፤ ጉብኝቱ እህትን እንዳበረታታት ተሰምቶት ነበር። ሆኖም ሊሄዱ ሲል እህት “ወንድሞች፣ እኔ ያለሁበት ሁኔታ ጨርሶ አልገባችሁም” አለቻቸው። ወንድሞች እህትን የመከሯት ስላጋጠሟት ችግሮችና ስላለችበት ሁኔታ ሳይጠይቋት ነው። በዚህም የተነሳ ምክራቸው እንደሚጠቅማት አልተሰማትም።
2 ጥቅሶቹን ያነበበላት ሽማግሌ የተፈጠረውን ነገር ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በወቅቱ እህት አክብሮት እንደጎደላት ተሰምቶኝ ነበር። ቆም ብዬ ሳስበው ግን ለእህት አስፈላጊ ይሆናሉ ብዬ ያሰብኳቸውን ጥቅሶች እንዳዘጋጀሁ ሁሉ አስፈላጊ ጥያቄዎችን አስቤም ቢሆን ጥሩ ነበር። ለምሳሌ ‘እንዴት ነሽ?’ ‘ልንረዳሽ የምንችለው ነገር አለ?’ ብዬ ብጠይቃት የተሻለ ነበር።” ይህ ሽማግሌ ከዚህ አጋጣሚ ትልቅ ቁም ነገር ተምሯል። በአሁኑ ወቅት አሳቢና የሌሎችን ስሜት የሚረዳ እረኛ ነው።
3. በጉባኤ ውስጥ እነማን ምክር ሊሰጡ ይችላሉ?
3 ሽማግሌዎች እረኞች ስለሆኑ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ምክር የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። ሆኖም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎችም ምክር መስጠት የሚያስፈልጋቸው ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ለጓደኛቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ይሰጡ ይሆናል። (መዝ. 141:5፤ ምሳሌ 25:12) ወይም በዕድሜ ከፍ ያሉ እህቶች በቲቶ 2:3-5 ላይ ከተጠቀሱት ነገሮች ጋር በተያያዘ “ወጣት ሴቶችን” የሚመክሩበት ጊዜ ይኖራል። ወላጆችም ቢሆኑ ብዙውን ጊዜ ለልጆቻቸው ምክርና እርማት መስጠት ያስፈልጋቸዋል። በመሆኑም ይህ ርዕስ በዋነኝነት የተዘጋጀው ለጉባኤ ሽማግሌዎች ቢሆንም ሁላችንንም የሚጠቅም ሐሳብ ይዟል። ጠቃሚ የሆነና ለተግባር የሚያነሳሳ እንዲሁም ‘ልብን ደስ የሚያሰኝ’ ምክር መስጠት የምንችልባቸውን መንገዶች ይጠቁመናል።—ምሳሌ 27:9
4. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
4 በዚህ ርዕስ ላይ ምክር መስጠትን በተመለከተ አራት ጥያቄዎችን እንመለከታለን፦ (1) ምክር ለመስጠት ሊያነሳሳን የሚገባው ትክክለኛ ምክንያት ምንድን ነው? (2) ምክሩ በእርግጥ አስፈላጊ ነው? (3) ምክሩን መስጠት ያለበት ማን ነው? (4) ውጤታማ ምክር መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
ምክር ለመስጠት ሊያነሳሳን የሚገባው ትክክለኛ ምክንያት ምንድን ነው?
5. አንድ ሽማግሌ በትክክለኛው ምክንያት ተነሳስቶ ምክር መስጠቱ ምክሩ ይበልጥ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚረዳው ለምንድን ነው? (1 ቆሮንቶስ 13:4, 7)
5 ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን ይወዷቸዋል። ፍቅራቸውን የሚያሳዩበት አንዱ መንገድ የተሳሳተ ጎዳና የሚከተልን ሰው መምከር ነው። (ገላ. 6:1) ሆኖም አንድ ሽማግሌ ግለሰቡን ከማነጋገሩ በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ ስለጠቀሳቸው የፍቅር ገጽታዎች ቆም ብሎ ማሰቡ ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። . . . ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል።” (1 ቆሮንቶስ 13:4, 7ን አንብብ።) ሽማግሌው በእነዚህ ጥቅሶች ላይ ማሰላሰሉ ምክር የሚሰጥበትን ምክንያት ለመገምገምና የሚመክረውን ወንድም በትክክለኛው መንገድ ለማነጋገር ይረዳዋል። ምክር የሚሰጠው ሰው ሽማግሌው እንደሚያስብለት ከተሰማው ምክሩን መቀበል ላይከብደው ይችላል።—ሮም 12:10
6. ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?
6 ሐዋርያው ጳውሎስ ለሽማግሌዎች ግሩም ምሳሌ ትቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በተሰሎንቄ ያሉ ወንድሞች ምክር ባስፈለጋቸው ወቅት ጳውሎስ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አላለም። ሆኖም ጳውሎስ ለእነሱ በጻፋቸው ደብዳቤዎች ላይ በቅድሚያ ለእምነት ሥራቸው፣ ከፍቅር ለመነጨ ድካማቸውና ለጽናታቸው አመስግኗቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ያሉበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብቷል፤ ሕይወታቸው አልጋ በአልጋ እንዳልሆነና ስደትን እየተጋፈጡ እንዳሉ ተናግሯል። (1 ተሰ. 1:3፤ 2 ተሰ. 1:4) እንዲያውም ለሌሎች ክርስቲያኖች ጥሩ ምሳሌ እንደሆኑ ገልጾላቸዋል። (1 ተሰ. 1:8, 9) እነዚህ ክርስቲያኖች ጳውሎስ ከልቡ ስላመሰገናቸው ተደስተው መሆን አለበት። ጳውሎስ እነዚህን ወንድሞቹን በጣም እንደሚወዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፋቸው ሁለት ደብዳቤዎች ላይ ውጤታማ ምክር መስጠት የቻለው ለዚህ ነው።—1 ተሰ. 4:1, 3-5, 11፤ 2 ተሰ. 3:11, 12
7. አንዳንዶች ለምክር አሉታዊ ምላሽ የሚሰጡት ለምን ሊሆን ይችላል?
7 ምክር የምንሰጥበት መንገድ ትክክል ካልሆነ ምን ሊፈጠር ይችላል? ተሞክሮ ያለው አንድ ሽማግሌ ያስተዋለውን ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንዶች ለምክር አሉታዊ ምላሽ የሚሰጡት ምክሩ በራሱ ችግር ስላለበት ሳይሆን ምክሩ የተሰጣቸው በፍቅር ስላልሆነ ነው።” ይህ ምን ያስተምረናል? በብስጭት ሳይሆን በፍቅር የሚሰጥን ምክር መቀበል በጣም ይቀላል።
ምክሩ በእርግጥ አስፈላጊ ነው?
8. አንድ ሽማግሌ ሌሎችን ከመምከሩ በፊት ራሱን ምን ብሎ ሊጠይቅ ይገባል?
8 ሽማግሌዎች ምክር ለመስጠት መቸኮል የለባቸውም። አንድ ሽማግሌ ከመምከሩ በፊት ራሱን እንዲህ እያለ መጠየቅ ይኖርበታል፦ ‘ይህን ጉዳይ ማንሳት የግድ አስፈላጊ ነው? ግለሰቡ ያደረገው ነገር ስህተት እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ? የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጥሷል? ወይስ ከእኔ የተለየ አመለካከት ስላለው ነው?’ ሽማግሌዎች ‘ለመናገር አለመቸኮላቸው’ ጥበብ ነው። (ምሳሌ 29:20) አንድ ሽማግሌ ምክር ልስጥ ወይስ አልስጥ የሚል ጥርጣሬ ከተፈጠረበት ሌላን ሽማግሌ ቀርቦ ሊያማክረው ይችላል፤ በእርግጥ የተጣሰ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ መኖር አለመኖሩን ሊነጋገሩበት ይችላሉ።—2 ጢሞ. 3:16, 17
9. ከአለባበስና ከፀጉር አያያዝ ጋር የተያያዘ ምክር መስጠትን በተመለከተ ከጳውሎስ ምን እንማራለን? (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10)
9 አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ሽማግሌ የአንድ የእምነት ባልንጀራው አለባበስ ወይም የፀጉር አያያዝ አሳስቦታል እንበል። በዚህ ጊዜ ሽማግሌው ‘ጉዳዩን ለማንሳት የሚያበቃ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት አለኝ?’ ብሎ ራሱን ሊጠይቅ ይችላል። የግሉን አመለካከት በሌሎች ላይ መጫን ስለማይፈልግ ስለ ጉዳዩ ሌላን ሽማግሌ ወይም የጎለመሰ አስፋፊ ያማክራል። ከዚያም አለባበስንና የፀጉር አያያዝን በተመለከተ ጳውሎስ የሰጠውን ምክር አብረው ይከልሳሉ። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10ን አንብብ።) ጳውሎስ ክርስቲያኖች በልከኝነት፣ በማስተዋልና ተገቢ በሆነ መንገድ ሊለብሱ እንደሚገባ በመግለጽ ጠቅለል ያለ መሠረታዊ ሥርዓት አስፍሯል። ይሁንና ጳውሎስ ይህን ልበሱ ወይም አትልበሱ የሚል ዝርዝር መመሪያ አላሰፈረም። ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች እስካልተጣሱ ድረስ ክርስቲያኖች የግላቸውን ምርጫ የማድረግ መብት እንዳላቸው ተገንዝቧል። በመሆኑም ሽማግሌዎች ምክር መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ከመወሰናቸው በፊት የግለሰቡ ምርጫ ልከኝነትና ማስተዋል የሚንጸባረቅበት መሆን አለመሆኑን ማጣራት ይኖርባቸዋል።
10. ከሌሎች የግል ምርጫ ጋር በተያያዘ ልናስታውሰው የሚገባን ነገር ምንድን ነው?
10 ሁለት የጎለመሱ ክርስቲያኖች ሁለት የተለያዩ ምርጫዎች ቢያደርጉም ሁለቱም ተቀባይነት ሊኖራቸው እንደሚችል ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። አንድ ነገር ትክክል ነው ወይም ስህተት ነው ብለን የራሳችንን መሥፈርት በእምነት ባልንጀሮቻችን ላይ መጫን የለብንም።—ሮም 14:10
ምክሩን መስጠት ያለበት ማን ነው?
11-12. ምክር መስጠት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ አንድ ሽማግሌ ራሱን ምን ብሎ ሊጠይቅ ይገባል? ለምንስ?
11 ምክር መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ከታመነበት ቀጣዩ ጥያቄ ደግሞ ‘ምክሩን ማን ይስጥ?’ የሚለው ነው። አንድ ሽማግሌ አንዲትን ያገባች እህት ወይም ለአካለ መጠን ያልደረሰን ልጅ ከመምከሩ በፊት የቤተሰቡን ራስ ማነጋገሩ የተሻለ ነው፤ ምናልባት የቤተሰቡ ራስ ጉዳዩን ራሱ ቢይዘው ይመርጥ ይሆናል። * ወይም ደግሞ ሽማግሌዎቹ እሱ ባለበት ምክሩን እንዲሰጡ ሊፈልግ ይችላል። አንዳንዴ ደግሞ አንቀጽ 3 ላይ እንደተጠቀሰው ወጣት እህቶችን በዕድሜ ከፍ ያሉ እህቶች ቢመክሯቸው የተሻለ ይሆናል።
12 ሌላም ግምት ውስጥ ሊገባ የሚገባ ነገር አለ። አንድ ሽማግሌ ራሱን እንዲህ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፦ ‘ይህ ምክር ከእኔ ቢመጣ ይሻላል? ወይስ ምክሩን ሌላ ሰው ቢሰጠው የበለጠ ተሰሚነት ይኖረው ይሆን?’ ለምሳሌ ያህል፣ አልረባም ከሚል ስሜት ጋር የሚታገል ሰው ተመሳሳይ ችግርን ካሸነፈ ሽማግሌ ምክር ቢሰጠው መቀበል የበለጠ ሊቀለው ይችላል። ይህን ችግር ያለፈበት ሽማግሌ የግለሰቡን ስሜት መረዳት ይቀለዋል፤ የሚሰጠው ምክርም ቢሆን ይበልጥ ተቀባይነት ይኖረዋል። ሆኖም ሁሉም ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን የማበረታታት እና የሚያስፈልጋቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስተካከያ እንዲያደርጉ የመምከር ኃላፊነት አለባቸው። ስለዚህ አንገብጋቢው ነገር አስፈላጊ በሚሆንበት ወቅት ምክሩ መሰጠቱ እንጂ ምክሩን ማን ይስጠው የሚለው ጉዳይ አይደለም።
ውጤታማ ምክር መስጠት የምንችለው እንዴት ነው?
13-14. አንድ ሽማግሌ ማዳመጥ ያለበት ለምንድን ነው?
13 አዳምጡ። አንድ ሽማግሌ ምክር ለመስጠት ሲዘጋጅ ራሱን እንዲህ ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል፦ ‘ወንድሜ ስላለበት ሁኔታ ምን የማውቀው ነገር አለ? በሕይወቱ ውስጥ ምን እያጋጠመው ነው? እኔ የማላውቃቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ገጥመውት ይሆን? በአሁኑ ወቅት በጣም የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው?’
14 በያዕቆብ 1:19 ላይ የሚገኘው መመሪያ ምክር ለሚሰጡም እንደሚሠራ የታወቀ ነው። ያዕቆብ እንዲህ ብሏል፦ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት።” አንድ ሽማግሌ ስለ ወንድም ሁሉንም ነገር እንደሚያውቅ ይሰማው ይሆናል፤ ግን በእርግጥ ያውቃል? ምሳሌ 18:13 እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ይሰጠናል፦ “እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ የሚሰጥ ሰው፣ ሞኝነት ይሆንበታል፤ ውርደትም ይከናነባል።” እንግዲያው ግለሰቡ ራሱ ስላለበት ሁኔታ እንዲናገር ማድረግ ከሁሉ የተሻለ ነው። በመሆኑም አንድ ሽማግሌ ከመናገሩ በፊት ማዳመጥ ይኖርበታል። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ሽማግሌ ያገኘውን ትምህርት አስታውሱ። ለእህት እረኝነት ባደረጉላት ወቅት የተዘጋጀበትን ነገር በመናገር ከመጀመር ይልቅ “እንዴት ነሽ?” “ልንረዳሽ የምንችለው ነገር አለ?” ብሎ ቢጠይቃት የተሻለ እንደነበር ተገንዝቧል። ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ስላሉበት ሁኔታ ለማወቅ ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ እነሱን በተሻለ መንገድ መርዳትና ማበረታታት ይችላሉ።
15. ሽማግሌዎች በምሳሌ 27:23 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
15 መንጋውን በደንብ እወቁ። መግቢያችን ላይ እንዳየነው ውጤታማ ምክር መስጠት፣ እንዲሁ የተወሰኑ ጥቅሶችን ማንበብ ወይም አንዳንድ ሐሳቦችን ማካፈል ብቻ አይደለም። ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንደምናስብላቸው፣ ስሜታቸውን እንደምንረዳና ልንረዳቸው እንደምንፈልግ ሊሰማቸው ይገባል። (ምሳሌ 27:23ን አንብብ።) ሽማግሌዎች ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ጋር ለመቀራረብ የቻሉትን ሁሉ ጥረት ማድረግ አለባቸው።
16. ሽማግሌዎች ውጤታማ ምክር ለመስጠት ምን ይረዳቸዋል?
16 ሽማግሌዎች ወንድሞችን የሚያነጋግሩት፣ ምክር ሲያስፈልጋቸው ወይም የተሳሳተ ነገር ሲያደርጉ ብቻ እንደሆነ የሚያስመስል ነገር ማድረግ የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ ዘወትር ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ጋር መጨዋወት እንዲሁም ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ሊረዷቸው እንደሚፈልጉ ማሳየት ይኖርባቸዋል። አንድ ተሞክሮ ያለው ሽማግሌ “እንዲህ የምታደርጉ ከሆነ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ጥሩ ወዳጅነት ይኖራችኋል” ብሏል። “ይህም ምክር መስጠት አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁኔታውን ይበልጥ ምቹ ያደርገዋል።” ምክር የሚሰጠው ሰውም ቢሆን ምክሩን መቀበል ቀላል ይሆንለታል።
17. አንድ ሽማግሌ ታጋሽና ደግ መሆን ይበልጥ የሚያስፈልገው መቼ ነው?
17 ታጋሽ እና ደግ ሁኑ። በተለይ ግለሰቡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተሰጠውን ምክር ለመቀበል ሲያንገራግር ትዕግሥትና ደግነት ማሳየት አስፈላጊ ነው። አንድ ሽማግሌ የሰጠው ምክር ወዲያውኑ ተቀባይነት ካላገኘ ወይም ተግባር ላይ ካልዋለ እንዳይበሳጭ መጠንቀቅ አለበት። ኢየሱስን በተመለከተ “የተቀጠቀጠን ሸምበቆ አይሰብርም፤ የሚጨስንም የጧፍ ክር አያጠፋም” የሚል ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ማቴ. 12:20) ሽማግሌው በግሉ በሚያቀርበው ጸሎት ላይ ይሖዋ ምክር የተሰጠውን ግለሰብ እንዲባርከው እንዲሁም ምክሩ ያስፈለገበትን ምክንያት እንዲረዳና ተግባራዊ እንዲያደርግ እንዲረዳው መለመኑ የተሻለ ነው። ምክር የተሰጠው ግለሰብ ስለ ምክሩ ለማሰብ ጊዜ ያስፈልገው ይሆናል። ሽማግሌው ታጋሽና ደግ ከሆነ የሚመከረው ሰው ምክሩ በተሰጠበት መንገድ ላይ አያተኩርም፤ ከዚህ ይልቅ ምክሩ በያዘው መልእክት ላይ ማተኮር ይችላል። እርግጥ ነው፣ ምክሩ ምንጊዜም በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት።
18. (ሀ) ምክር ከመስጠት ጋር በተያያዘ ምን ማስታወስ ይኖርብናል? (ለ) ሣጥኑ ላይ ያለው ምስል እንደሚያሳየው ወላጆች የትኞቹን ጉዳዮች ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል?
18 ከስህተታችሁ ተማሩ። ፍጹም ባለመሆናችን በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሱትን ሐሳቦች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አንችልም። (ያዕ. 3:2) ስህተት መሥራታችን አይቀርም፤ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ግን ከስህተታችን ልንማር ይገባል። ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እንደምንወዳቸው የሚሰማቸው ከሆነ በንግግራችን ወይም በድርጊታችን ቅር በምናሰኛቸው ወቅት እኛን ይቅር ማለት አይከብዳቸውም።—“ ጠቃሚ ማስታወሻ ለወላጆች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።
ምን ትምህርት አግኝተናል?
19. የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን ልብ ደስ ማሰኘት የምንችለው እንዴት ነው?
19 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ውጤታማ ምክር መስጠት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ፍጹማን አይደለንም፤ የምንመክራቸው ሰዎችም ቢሆኑ ፍጹማን አይደሉም። በዚህ ርዕስ ላይ የተመለከትናቸውን ነጥቦች ምንጊዜም አስታውሱ። ምክር ለመስጠት ያነሳሳችሁ ምክንያት ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጡ። በተጨማሪም ‘ምክሩ በእርግጥ አስፈላጊ ነው?’ እንዲሁም ‘ይህ ምክር ከእኔ ቢመጣ የተሻለ ነው?’ የሚለውን ጉዳይ አስቡበት። ምክር ከመስጠታችሁ በፊት ግለሰቡ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ጥያቄ ጠይቁት፤ እንዲሁም በጥሞና አዳምጡት። ጉዳዩን በእሱ ቦታ ሆናችሁ ለማየት ጥረት አድርጉ። አሳቢነት በማሳየት ከወንድሞቻችሁና ከእህቶቻችሁ ጋር የቀረበ ወዳጅነት መሥርቱ። ምንጊዜም ግባችን ውጤታማ ብቻ ሳይሆን ‘ልብን ደስ የሚያሰኝ’ ምክር መስጠት እንደሆነ አትርሱ።—ምሳሌ 27:9
መዝሙር 103 እረኞች—ስጦታ የሆኑ ወንዶች
^ አን.5 ምክር መስጠት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ታዲያ ምክር መስጠት የሚያስገድድ ሁኔታ ሲያጋጥመን ጠቃሚ በሆነና መንፈስን በሚያድስ መንገድ መምከር የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ርዕስ በተለይ ሽማግሌዎች፣ የሚመክሯቸውን ሰዎች ልብ በሚያስደስት መንገድ መምከር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ያብራራል።
^ አን.11 በየካቲት 2021 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “በጉባኤው ውስጥ ስላለው የራስነት ሥርዓት ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።