ከሐሰት ሃይማኖት ነፃ ወጡ
“ሕዝቤ ሆይ፣ . . . ከእሷ ውጡ።”—ራእይ 18:4
1. የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ እንደሚወጡ ለመጠበቅ የሚያበቃ ምን መሠረት ነበራቸው? የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
ታማኝ ክርስቲያኖች በባቢሎን የተማረኩት እንዴት እንደሆነ ቀደም ባለው ርዕስ ላይ ተመልክተናል። ደስ የሚለው ነገር፣ ሁልጊዜ በዚህ ሁኔታ አይቀጥሉም። በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ ከምታመለክተው ከታላቂቱ ባቢሎን ተጽዕኖ ማንም ሰው መላቀቅ የማይችል ቢሆን ኖሮ “ሕዝቤ ሆይ፣ . . . ከእሷ ውጡ” የሚለው የአምላክ ትእዛዝ ትርጉም አይሰጥም ነበር። (ራእይ 18:4ን አንብብ።) የአምላክ ሕዝብ ከባቢሎን ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ ነፃ የወጣው መቼ እንደሆነ ለማወቅ እንጓጓለን! መጀመሪያ ግን ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለብን፦ ከ1914 በፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከታላቂቱ ባቢሎን ጋር በተያያዘ ምን አቋም ነበራቸው? በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወንድሞቻችን የስብከቱን ሥራ ምን ያህል በቅንዓት አከናውነዋል? በዚያ ወቅት እርማትና ተግሣጽ ያስፈለጋቸው መሆኑ በባቢሎን ከመማረካቸው ጋር ተያያዥነት አለው?
“የባቢሎን ውድቀት”
2. የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከሐሰት ሃይማኖት ጋር በተያያዘ ምን አቋም ነበራቸው?
2 ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት ቻርልስ ቴዝ ራስልና ተባባሪዎቹ፣ የሕዝበ ክርስትና ድርጅቶች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንደማያስተምሩ ተገንዝበው ነበር። በመሆኑም ከሐሰት ሃይማኖት ለመራቅ ወሰኑ። እነዚህ ወንድሞች የወሰዱትን ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋም በተመለከተ የኅዳር 1879 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ የሚከተለውን ግልጽ ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “የክርስቶስ ሚስት የሆነች ንጽሕት ድንግል መሆኗን የምትናገር ሆኖም ከዓለም (ከአውሬው) ጋር አንድነት ያላትና የዓለምን ድጋፍ የምታገኝ ማንኛዋም ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት አመንዝራ ቤተ ክርስቲያን [ታላቂቱ ባቢሎን] በመሆኗ ልናወግዛት ይገባል።”—ራእይ 17:1, 2ን አንብብ።
3. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከሐሰት ሃይማኖት መለየት እንዳለባቸው መረዳታቸውን የሚያሳይ ምን ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ወስደዋል? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
3 በወቅቱ የነበሩ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቁ ነበር። የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶችን እየደገፉ የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንደማይችሉ ተገንዝበዋል። በመሆኑም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የነበሩበትን ቤተ ክርስቲያን መልቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ አዘጋጁ። አንዳንዶቹ ቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ሕዝብ በተሰበሰበበት ደብዳቤያቸውን አንብበዋል። ደብዳቤያቸውን በሕዝብ ፊት እንዳያነቡ የተከለከሉት ደግሞ ደብዳቤውን ለእያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያኑ አባል ላኩት። ከዚያ በኋላ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዲኖራቸው አልፈለጉም! ቀደም ባሉት ዘመናት ቢሆን ኖሮ እንዲህ ያለ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ መውሰዳቸው ሕይወታቸውን ሊያሳጣቸው ይችል ነበር። ሆኖም በ1800ዎቹ መገባደጃ አካባቢ በብዙ አገሮች ውስጥ ቤተ ክርስቲያኗ ከመንግሥት የምታገኘውን ድጋፍ እያጣች ነበር። እንዲህ ባሉ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ቅጣት እንደሚደርስባቸው ሳይፈሩ በሃይማኖታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መወያየት እንዲሁም የአብያተ ክርስቲያናትን ትምህርት እንዳልተቀበሉ በይፋ መግለጽ ይችሉ ነበር።
4. በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአምላክ ሕዝቦች ለታላቂቱ ባቢሎን ምን አመለካከት እንደነበራቸው አብራራ።
4 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር በተያያዘ ስለወሰዱት አቋም፣ ለዘመዶቻቸውና ለቅርብ ወዳጆቻቸው እንዲሁም ለነበሩበት ቤተ ክርስቲያን አባላት ብቻ ማሳወቁ በቂ እንደሆነ አልተሰማቸውም። ታላቂቱ ባቢሎን ሃይማኖታዊ አመንዝራ መሆኗን መላው ዓለም ሊያውቅ ይገባል! በመሆኑም በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “የባቢሎን ውድቀት” የሚል ርዕሰ ጉዳይ የያዘና ሕዝበ ክርስትናን የሚያጋልጥ ትራክት 10,000,000 ቅጂዎች ከታኅሣሥ 1917 እስከ 1918 መጀመሪያ ባለው ጊዜ ውስጥ በቅንዓት አሰራጭተዋል። ይህ የሕዝበ ክርስትናን ቀሳውስት በእጅጉ ያስቆጣቸው መሆኑ ምንም አያስገርምም፤ ያም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ይህን አስፈላጊ ሥራ ከማከናወን ወደኋላ አላሉም። ‘ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያቸው አድርገው ለመታዘዝ’ ቆርጠው ነበር። (ሥራ 5:29) ይህ ምን ያስገነዝበናል? እነዚህ ክርስቲያኖች በጦርነቱ ወቅት በታላቂቱ ባቢሎን ከመማረክ ይልቅ ከተጽዕኖዋ እየተላቀቁና ሌሎች ይህን እንዲያደርጉ እየረዱ ነበር።
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በቅንዓት አገልግለዋል
5. በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ወንድሞች በቅንዓት ይሰብኩ እንደነበር እንዴት እናውቃለን?
5 ቀደም ባሉት ዓመታት፣ ይሖዋ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ሕዝቡ በቅንዓት ባለመስበካቸው እንዳዘነባቸው እናስብ ነበር። በዚህም የተነሳ ይሖዋ፣ ለተወሰነ ጊዜ በታላቂቱ ባቢሎን እንዲማረኩ እንደፈቀደ ይሰማን ነበር። ይሁን እንጂ ከ1914-1918 ባለው ጊዜ ውስጥ ይሖዋን በታማኝነት ያገለገሉ ወንድሞችና እህቶች ከጊዜ በኋላ እንደገለጹት፣ በጥቅሉ ሲታይ የጌታ ሕዝብ በዚያ ወቅት በስብከቱ ሥራ ለመቀጠል አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አድርገዋል። ይህን የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ አለ። ቲኦክራሲያዊ ታሪካችንን ይበልጥ በትክክል ማወቃችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡ አንዳንድ ክንውኖችን በግልጽ ለመረዳት አስችሎናል።
6, 7. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የትኞቹን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት አስፈልጓቸዋል? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ቅንዓት እንደነበራቸው የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ።
6 እንደ እውነቱ ከሆነ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት (1914-1918) የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በጊዜው ምሥራቹን በስፋት ሰብከዋል። ይህን ሥራ ማከናወን አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶች ነበሩ። እስቲ ሁለቱን እንመልከት። አንደኛ፣ በወቅቱ በዋነኝነት የሚያተኩሩት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማሰራጨት ላይ ነበር። የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ያለቀለት ሚስጥር (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ በ1918 መጀመሪያ አካባቢ ሲያግዱት ብዙ ወንድሞቻችን የስብከቱን ሥራ ማከናወን አስቸጋሪ ሆነባቸው። መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ተጠቅመው መስበክ አልለመዱም ነበር፤ እንደ አንደበት የሚሆንላቸው ይህ ጽሑፍ ነበር። ሁለተኛው ችግር ደግሞ በ1918 የኅዳር በሽታ ወረርሽኝ መነሳቱ ነው። ይህ አስከፊ ወረርሽኝ በስፋት መሰራጨቱ አስፋፊዎች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ከባድ እንዲሆንባቸው አደረገ። እነዚህና ሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም በጥቅሉ ሲታይ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ሥራውን ለማከናወን የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል።
7 ጥቂት ቁጥር ያላቸው እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1914 ብቻ “የፍጥረት ፎቶ ድራማን” ከ9,000,000 ለሚበልጡ ሰዎች አሳይተዋል። “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለው ፊልም ምስሎችን፣ የተቀዱ ድምፆችንና ስላይዶችን አንድ ላይ በማቀናጀት ከፍጥረት አንስቶ እስከ ሺህ ዓመቱ መጨረሻ ያለውን የሰው ዘር ሕይወት ያወሳል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በወቅቱ ይህን ማድረግ መቻላቸው በጣም አስገራሚ ነበር። እስቲ አስበው፦ በ1914 ይህን ፊልም ያዩት ሰዎች ቁጥር በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ካሉት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ይበልጣል! በተጨማሪም ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በ1916 በዩናይትድ ስቴትስ በድምሩ 809,393 ሰዎች በሕዝብ ስብሰባዎች ላይ የተገኙ ሲሆን በ1918 ደግሞ ይህ አኃዝ 949,444 ደርሷል። በእርግጥም እነዚያ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በቅንዓት ሰብከዋል!
8. በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ወንድሞች መንፈሳዊ ምግብ የሚያገኙት እንዴት ነበር?
8 በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ በየቦታው ተበታትነው ለነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መንፈሳዊ ምግብ በቀጣይነት ለማቅረብና ማበረታቻ ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ይህም ወንድሞች የስብከቱን ሥራ ማከናወናቸውን እንዲቀጥሉ ብርታት ሰጥቷቸዋል። በዚያ ወቅት ቀናተኛ ሰባኪ የነበረው ሪቻርድ ሃርቪ ባርበር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ጥቂት ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በሥራው ላይ እንዲቆዩና መጠበቂያ ግንብ መሰራጨቱን እንዲቀጥል ማድረግ እንዲሁም መጽሔቱን ታግዶ ወደነበረበት ወደ ካናዳ መላክ ችለን ነበር። ያለቀለት ሚስጥር (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፋቸው ለተወረሰባቸው አንዳንድ ወንድሞች፣ በኪስ የሚያዝ መጠን ያለውን የዚህ መጽሐፍ ቅጂ የመላክ መብት አግኝቼ ነበር። ወንድም ራዘርፎርድ በምዕራባዊ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች፣ ትላልቅ ስብሰባዎችን እንድናደራጅና በተቻለ መጠን ወንድሞችን ለማበረታታት ተናጋሪዎችን እንድንልክ ጠይቆን ነበር።”
የተወሰነ ማስተካከያ ያስፈልግ ነበር
9. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች ከ1914 እስከ 1919 ባለው ጊዜ ውስጥ እርማትና ተግሣጽ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? (ለ) ተግሣጽ ያስፈለጋቸው መሆኑ ምን አያሳይም?
9 ከ1914 እስከ 1919 ባሉት ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ከቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የማይጣጣሙ አንዳንድ ነገሮች ያደርጉ ነበር። ወንድሞች ቅን ልብ ቢኖራቸውም እንኳ ለሰብዓዊ መንግሥታት ስለ መገዛት ትክክለኛ አመለካከት ያልያዙበት ወቅት ነበር። (ሮም 13:1) በመሆኑም በቡድን ደረጃ ሲታይ ከጦርነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኞች ያልነበሩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ግንቦት 30, 1918 ስለ ሰላም የሚጸለይበት ቀን እንዲሆን ሲያውጁ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹም በዚህ ሥነ ሥርዓት እንዲካፈሉ የሚያበረታታ ሐሳብ መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቶ ነበር። አንዳንድ ወንድሞች ለጦርነቱ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ሲሉ ቦንዶችን የገዙ ሲሆን ጥቂቶች ደግሞ መሣሪያ ታጥቀው ወደ ጦርነቱ ዘምተዋል። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በታላቂቱ ባቢሎን የተማረኩት፣ እርማትና ተግሣጽ ስላስፈለጋቸው እንደሆነ መደምደም ስህተት ነው። እነዚህ ወንድሞች ከሐሰት ሃይማኖት መለየት እንዳለባቸው ተገንዝበው ነበር፤ እንዲያውም በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከባቢሎን ሙሉ በሙሉ ነፃ ለመውጣት ተቃርበው ነበር።—ሉቃስ 12:47, 48ን አንብብ።
10. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ሕይወትን እንደ ቅዱስ አድርጎ ከመመልከት ጋር በተያያዘ ምን ቁርጥ አቋም ወስደዋል?
10 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ከክርስቲያናዊ ገለልተኝነት ጋር በተያያዘ ዛሬ ያለን ዓይነት ግልጽ ግንዛቤ ባይኖራቸውም እንኳ ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች ነበሩ፦ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ሕይወት ማጥፋትን ይከለክላል። በመሆኑም በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት መሣሪያ ታጥቀው የዘመቱት ጥቂት ወንድሞችም እንኳ የሰው ሕይወት ለማጥፋት ፈጽሞ ፈቃደኞች አልነበሩም። ሌሎችን ለመግደል ፈቃደኛ ያልነበሩ አንዳንድ ወንድሞች በጦርነቱ እንዲገደሉ ሲባል ውጊያ ወደተፋፋመበት ቦታ ተልከዋል።
11. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ መሣሪያ ታጥቆ ከመዋጋት ጋር በተያያዘ የወሰዱትን እርምጃ በተመለከተ የመንግሥት ባለሥልጣናት ምን ተሰማቸው?
11 እነዚህ ወንድሞች የያዙት አቋም ሙሉ በሙሉ ትክክል ባይሆንም እንኳ ዲያብሎስ በአቋማቸው በጣም ተቆጥቶ ነበር። በመሆኑም “በሕግ ስም ችግር ለመፍጠር” አሴረ። (መዝ. 94:20) የዩናይትድ ስቴትስ ሠራዊት አባል የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ጄምስ ፍራንክሊን ቤል፣ ከወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድና ከወንድም ቫን አምበርግ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ እንደተናገሩት የዩናይትድ ስቴትስ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ በጦርነቱ ላይ መሣሪያ ታጥቀው ለመዋጋት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች በሞት እንዲቀጡ ለማድረግ የሚያስችል የሕግ ረቂቅ ለምክር ቤቱ አቅርቦ ነበር። ጄኔራሉ ይህን የተናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን በማስመልከት ነው። በውይይቱ መሃል ጄኔራል ቤል ወንድም ራዘርፎርድን በብስጭት እንዲህ አሉት፦ “ረቂቁ ያልጸደቀው [የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የሆነው] ዊልሰን ስላልተስማማበት ነው፤ ያም ቢሆን እንዴት አድርገን እንደምናጠቃችሁ እናውቃለን፤ ደግሞም አንለቃችሁም!”
12, 13. (ሀ) ኃላፊነት ያላቸው ስምንት ወንድሞች የረጅም ዓመት እስራት የተበየነባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ወንድሞች ወኅኒ መውረዳቸው ይሖዋን ለመታዘዝ ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያላሉ አድርጓቸዋል? አብራራ።
12 ባለሥልጣናቱ ልክ እንደዛቱት አድርገዋል። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ተወካዮች የነበሩት ጆሴፍ ራዘርፎርድ፣ ቫን አምበርግ እና ሌሎች ስድስት ወንድሞች ተያዙ። ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ብይኑን ሲያስተላልፉ እንዲህ ብለዋል፦ “እነዚህ ሰዎች የሚያስፋፉት ሃይማኖታዊ ፕሮፖጋንዳ ከአንድ የጀርመን ክፍለ ጦር . . . ይበልጥ አደገኛ ነው። እነዚህ ሰዎች በመንግሥት የሕግ አካላት እንዲሁም በሠራዊቱ የደህንነት ቢሮ ላይ ጥርጣሬ ከመፍጠራቸውም ሌላ የሁሉንም አብያተ ክርስቲያናት አገልጋዮች አውግዘዋል። በመሆኑም ከባድ ቅጣት ይገባቸዋል።” (ፌዝ ኦን ዘ ማርች በአሌክሳንደር ሂዩ ማክሚላን፣ ገጽ 99) ዳኛው እንዳሉትም ፍርዱ ከባድ ነበር። ስምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በአትላንታ፣ ጆርጂያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የፌዴራል ማረሚያ ቤት የረጅም ዓመታት እስር ተበየነባቸው። ጦርነቱ ሲያበቃ ግን ከእስር የተለቀቁ ሲሆን የተመሠረተባቸው ክስም ተነሳላቸው።
13 ስምንቱ ወንድሞች እስር ቤት እያሉም እንኳ ቅዱሳን መጻሕፍትን በተረዱት መጠን በጥብቅ ለመከተል ጥረት አድርገዋል። ምሕረት እንዲደረግላቸው ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባቀረቡት ጥያቄ ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚያሳዩት የጌታ ፈቃድ ‘አትግደል’ የሚል ነው፤ በመሆኑም ራሱን ለጌታ የወሰነ ማንኛውም [የዓለም አቀፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር] አባል፣ ከዚህ ቃል ኪዳኑ ጋር የሚጋጭ ነገር በፈቃዱ ከፈጸመ የአምላክን ሞገስ ሊያጣ አልፎ ተርፎም ለጥፋት ሊዳረግ ይችላል። ስለዚህ የዚህ ማኅበር አባላት የሰውን ሕይወት ሆን ብለው ለማጥፋት ሕሊናቸው አይፈቅድላቸውም።” ይህ እንዴት ያለ ድፍረት የተሞላበት ንግግር ነው! ወንድሞች አቋማቸውን ለማላላት ሐሳቡ እንኳ እንዳልነበራቸው ግልጽ ነበር!
በመጨረሻ ነፃ ወጡ!
14. ከ1914 እስከ 1919 ባሉት ዓመታት ምን እንደተከናወነ ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅመህ ግለጽ።
14 ሚልክያስ 3:1-3 የተቀቡት ‘የሌዊ ልጆች ስለሚነጹበት’ ጊዜ (ከ1914 እስከ 1919 መጀመሪያ አካባቢ) ይናገራል። (ጥቅሱን አንብብ።) በዚህ ጊዜ፣ “እውነተኛው ጌታ” ይኸውም ይሖዋ አምላክና “የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ” ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉትን ለመመርመር መጡ። የይሖዋ ሕዝቦች አስፈላጊው እርማት ከተሰጣቸው በኋላ ስለነጹ ተጨማሪ የአገልግሎት ኃላፊነት ለመቀበል ዝግጁ ሆኑ። በ1919 ለእምነት ቤተሰቡ መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ተሾመ። (ማቴ. 24:45) አሁን የአምላክ ሕዝቦች ከታላቂቱ ባቢሎን ተጽዕኖ ነፃ ወጡ። ለይሖዋ ጸጋ ምስጋና ይግባውና፣ ሕዝቡ ስለ አምላክ ፈቃድ ያላቸው እውቀትና በሰማይ ለሚኖረው አባታቸው ያላቸው ፍቅር ከዚያ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ መጥቷል። ለዚህ በረከት ምንኛ አመስጋኞች ነን! [1]
15. ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ መውጣታችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?
15 ከታላቂቱ ባቢሎን ምርኮ ነፃ መውጣት ምንኛ የሚያስደስት ነገር ነው! ሰይጣን እውነተኛ ክርስትናን ከምድር ገጽ ለማጥፋት ያደረገው ሙከራ ሙሉ በሙሉ ከሽፏል። ይሁንና ይሖዋ ይህን ነፃነት እንድናገኝ ያደረገበትን ዓላማ እንዳንስት መጠንቀቅ ይኖርብናል። (2 ቆሮ. 6:1) አሁንም በጣም ብዙ ሰዎች በሐሰት ሃይማኖት ቀንበር ሥር ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከባቢሎን እንዴት ነፃ መውጣት እንደሚችሉ ልናሳያቸው ይገባል። መንገዱን ልንጠቁማቸው እንችላለን። እንግዲያው ባለፈው መቶ ዘመን የኖሩ ወንድሞቻችን የተዉትን ምሳሌ በመከተል፣ እነዚህ ሰዎች ነፃ እንዲወጡ ለመርዳት የቻልነውን ሁሉ እናድርግ!
^ [1] (አንቀጽ 14) አይሁዳውያን ለ70 ዓመታት በባቢሎን ተማርከው መቆየታቸው፣ ክህደት ከተነሳ በኋላ ክርስቲያኖች ካጋጠማቸው ነገር ጋር በብዙ መንገዶች ይመሳሰላል። ይሁንና አይሁዳውያን በምርኮ መወሰዳቸው ክርስቲያኖች ላጋጠማቸው ነገር ትንቢታዊ ጥላ የሚሆን አይመስልም። ይህን የምንልበት አንደኛው ምክንያት፣ የአምላክ ሕዝብ በምርኮ የቆዩበት ጊዜ ርዝመት የሚለያይ መሆኑ ነው። በመሆኑም አይሁዳውያን በምርኮ ከመወሰዳቸው ጋር የሚያያዙት ሁኔታዎች በሙሉ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እስከ 1919 ባሉት ዓመታት ላጋጠሟቸው ነገሮች ትንቢታዊ ጥላ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰብ አይኖርብንም።