የጥናት ርዕስ 51
‘ይሖዋ ተስፋ የቆረጡትን ያድናል’
“ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ ተስፋ የቆረጡትንም ያድናል።”—መዝ. 34:18 ግርጌ
መዝሙር 30 አባቴ፣ አምላኬና ወዳጄ
ማስተዋወቂያ a
1-2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
ሕይወት “አጭርና በመከራ የተሞላ” መሆኑን ስናስብ እንጨነቅ ይሆናል። (ኢዮብ 14:1) ከዚህ አንጻር አንዳንድ ጊዜ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ቢሰማን የሚያስገርም አይደለም። በጥንት ዘመን የኖሩ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮችም እንደዚህ ተሰምቷቸው ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ ሞትን እስከ መመኘት ደርሰዋል። (1 ነገ. 19:2-4፤ ኢዮብ 3:1-3, 11፤ 7:15, 16) ሆኖም የሚታመኑበት አምላካቸው ይሖዋ በተደጋጋሚ አጽናንቷቸዋል እንዲሁም አጠንክሯቸዋል። የእነሱ ታሪክ የተመዘገበልን እኛን ለማጽናናት እና ለማስተማር ነው።—ሮም 15:4
2 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችን ስለተቋቋሙ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች እንመለከታለን፤ እነሱም የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ፣ መበለቷ ናኦሚና ምራቷ ሩት፣ መዝሙር 73ን የጻፈው ሌዋዊ እንዲሁም ሐዋርያው ጴጥሮስ ናቸው። ይሖዋ እነዚህን አገልጋዮቹን ያጠነከራቸው እንዴት ነው? ከእነሱ ምሳሌስ እያንዳንዳችን ምን ትምህርት እናገኛለን? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ” እንደሆነና ‘ተስፋ የቆረጡትን እንደሚያድን’ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።—መዝ. 34:18 ግርጌ
ዮሴፍ አስከፊ ግፍ ተፈጽሞበታል
3-4. ዮሴፍ ወጣት እያለ ምን አጋጠመው?
3 ዮሴፍ ከአምላክ የመጡ ሁለት ሕልሞችን ባየበት ወቅት ዕድሜው 17 ዓመት ገደማ ነበር። እነዚህ ሕልሞች ዮሴፍ ወደፊት በቤተሰቡ ውስጥ የተከበረ ሰው እንደሚሆን የሚጠቁሙ ነበሩ። (ዘፍ. 37:5-10) ሆኖም ዮሴፍ ሕልሞቹን ካለመ ብዙም ሳይቆይ ሕይወቱ በድንገት ተቀየረ። ወንድሞቹ ለእሱ አክብሮት ከማሳየት ይልቅ ለባርነት ሸጡት። በኋላም ዮሴፍ፣ ጶጢፋር የተባለን አንድ የግብፅ ባለሥልጣን ማገልገል ጀመረ። (ዘፍ. ) የዮሴፍ ሕይወት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተቀየረ፤ በአባቱ የተወደደ ልጅ የነበረው ዮሴፍ፣ ጣዖት አምላኪ የሆነ አንድ ግብፃዊ ባለሥልጣን ባሪያ ሆነ።— 37:21-28ዘፍ. 39:1
4 የዮሴፍ መከራ ግን በዚህ አላበቃም። የጶጢፋር ሚስት፣ ዮሴፍ ሊደፍራት እንደሞከረ በመግለጽ በሐሰት ወነጀለችው። ጶጢፋርም ጉዳዩን ሳያጣራ ዮሴፍን እስር ቤት አስገባው፤ እዚያም ዮሴፍ በብረት ታሰረ። (ዘፍ. 39:14-20፤ መዝ. 105:17, 18) ወጣቱ ዮሴፍ አስገድዶ በመድፈር ሙከራ በሐሰት ሲወነጀል ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስቡት። ይህ ውንጀላ በይሖዋ ስም ላይም ነቀፋ አስከትሎ ሊሆን ይችላል። በእርግጥም ዮሴፍን ያጋጠመው መከራ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነበር።
5. ዮሴፍ ያጋጠመውን ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ የተቋቋመው እንዴት ነው?
5 ዮሴፍ ባሪያ እያለም ሆነ እስረኛ በነበረበት ወቅት ሁኔታውን መቀየር የሚችልበት ምንም መንገድ አልነበረም። ታዲያ ዮሴፍ አዎንታዊ አመለካከት ይዞ መቀጠል የቻለው እንዴት ነው? ማድረግ በማይችለው ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ የተሰጠውን ሥራ በትጋት ይሠራ ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ ዮሴፍ ምንጊዜም ይሖዋን ለማስደሰት ጥረት ያደርግ ነበር። ይሖዋም ዮሴፍ የሠራውን ሥራ ሁሉ ባርኮለታል።—ዘፍ. 39:21-23
6. ዮሴፍ ቀደም ሲል ያያቸው ሕልሞች ያጽናኑት እንዴት ሊሆን ይችላል?
6 በተጨማሪም ዮሴፍ ቀደም ሲል ባያቸው ትንቢታዊ ሕልሞች ላይ ማሰላሰሉ አበረታቶት ሊሆን ይችላል። ሕልሞቹ ከቤተሰቡ ጋር በድጋሚ እንደሚገናኝና ያለበት ሁኔታ እንደሚሻሻል የሚጠቁሙ ነበሩ። ደግሞም ይህ ሁኔታ ተፈጽሟል። ዮሴፍ 37 ዓመት ገደማ ሲሆነው፣ ትንቢታዊ ሕልሞቹ በአስደናቂ መንገድ መፈጸም ጀመሩ።—ዘፍ. 37:7, 9, 10፤ 42:6, 9
7. አንደኛ ጴጥሮስ 5:10 እንደሚናገረው ፈተናዎችን ለመቋቋም ምን ሊረዳን ይችላል?
7 ምን ትምህርት እናገኛለን? የዮሴፍ ታሪክ የምንኖርበት ዓለም ጨካኝ እንደሆነ እና ሰዎች ግፍ ሊያደርሱብን እንደሚችሉ ያስታውሰናል። የእምነት ባልንጀራችን እንኳ ሊጎዳን ይችላል። ሆኖም ይሖዋን እንደ ዓለታችን ወይም እንደ መጠጊያችን አድርገን ከተመለከትነው ተስፋ አንቆርጥም አሊያም እሱን ማገልገላችንን አናቆምም። (መዝ. 62:6, 7፤ 1 ጴጥሮስ 5:10ን አንብብ።) ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለዮሴፍ ልዩ ትኩረት በሰጠበት ወቅት ዮሴፍ ገና 17 ዓመቱ ገደማ እንደነበር ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ይሖዋ በወጣት አገልጋዮቹ እንደሚተማመን ከዚህ በግልጽ መመልከት እንችላለን። በዛሬው ጊዜም እንደ ዮሴፍ ያሉ በርካታ ወጣቶች አሉ። ልክ እንደ እሱ በይሖዋ ላይ እምነት አላቸው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት ለማላላት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ታስረዋል።—መዝ. 110:3
ከባድ ሐዘን የደረሰባቸው ሁለት ሴቶች
8. ናኦሚና ሩት ምን አጋጠማቸው?
8 ናኦሚና ቤተሰቧ በይሁዳ ከባድ ረሃብ በመከሰቱ የተነሳ አገራቸውን ለቀው ወደ ሞዓብ ተሰደዱ። በዚያም የናኦሚ ባል ኤሊሜሌክ ሞተ፤ ስለዚህ ናኦሚና ሁለት ወንዶች ልጆቿ ብቻቸውን ቀሩ። ከጊዜ በኋላ ልጆቿ፣ ሩት እና ዖርፋ የተባሉ ሞዓባውያን ሴቶችን አገቡ። ከአሥር ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ የናኦሚ ልጆች ዘር ሳይተኩ ሞቱ። (ሩት 1:1-5) ሦስቱ ሴቶች ምን ያህል በሐዘን ተውጠው እንደነበር መገመት አያዳግትም። እርግጥ ሩትና ዖርፋ እንደገና ማግባት ይችሉ ነበር። አረጋዊቷን ናኦሚን ግን ማን ይንከባከባታል? ናኦሚ በጭንቀት ከመዋጧ የተነሳ በአንድ ወቅት እንዲህ ብላ ነበር፦ “ናኦሚ ብላችሁ አትጥሩኝ። ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሕይወቴን መራራ አድርጎታልና ማራ ብላችሁ ጥሩኝ።” ልቧ በሐዘን የተሰበረው ናኦሚ ወደ ቤተልሔም ለመመለስ ወሰነች፤ ሩትም አብራት ሄደች።—ሩት 1:7, 18-20
9. ሩት 1:16, 17, 22 እንደሚናገረው ሩት ናኦሚን ያበረታታቻት እንዴት ነው?
9 ታዲያ ናኦሚን የረዳት ምንድን ነው? ታማኝ ፍቅር ነው። ሩት ከናኦሚ ባለመለየት ታማኝ ፍቅር አሳይታታለች። (ሩት 1:16, 17, 22ን አንብብ።) በቤተልሔምም ሩት በትጋት ገብስ በመቃረም ለራሷና ለናኦሚ የሚያስፈልገውን ነገር ታቀርብ ነበር። በዚህም የተነሳ ብዙም ሳይቆይ ይህች ወጣት ጥሩ ስም አተረፈች።—ሩት 3:11፤ 4:15
10. ይሖዋ እንደ ናኦሚና እንደ ሩት ላሉ ድሆች ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው?
10 ይሖዋ እንደ ናኦሚና እንደ ሩት ያሉ ድሆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያገኙ ሲል ለእስራኤላውያን ርኅራኄ የተንጸባረቀበት ሕግ ሰጥቷቸው ነበር። ይሖዋ፣ ሕዝቡ አዝመራ በሚሰበስቡበት ወቅት፣ ዳር ዳር ያለውን ለድሆች እንዲተዉላቸው አዟቸው ነበር። (ዘሌ. 19:9, 10) ስለዚህ ናኦሚና ሩት ምግብ ለማግኘት መለመን አላስፈለጋቸውም። ቃርሚያ በመሰብሰብ፣ ክብራቸው ሳይነካ ምግብ ማግኘት ይችሉ ነበር።
11-12. ናኦሚና ሩት ደስተኛ እንዲሆኑ ቦዔዝ የረዳቸው እንዴት ነው?
11 ሩት የምትቃርምበት እርሻ ባለቤት፣ ቦዔዝ የተባለ ባለጸጋ ሰው ነበር። ቦዔዝ፣ ሩት ለናኦሚ ባሳየችው ታማኝነትና ፍቅር ልቡ ስለተነካ የቤተሰባቸውን ርስት የተቤዠ ከመሆኑም ሌላ ሩትን ሚስቱ አድርጎ ወሰዳት። (ሩት 4:9-13) ቦዔዝና ሩት ኢዮቤድ የተባለ ልጅ ወለዱ፤ ኢዮቤድ የንጉሥ ዳዊት አያት ነው።—ሩት 4:17
12 ናኦሚ ሕፃኑን ኢዮቤድን አቅፋ በደስታ ይሖዋን ስታመሰግን ይታያችሁ! ሆኖም ናኦሚና ሩት ከዚያም የላቀ በረከት ይጠብቃቸዋል። ከሞት ሲነሱ ኢዮቤድ፣ የመሲሑ ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት እንደነበር ይገነዘባሉ።
13. ከናኦሚና ከሩት ታሪክ ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?
13 ምን ትምህርት እናገኛለን? መከራ ሲደርስብን ተስፋ እንቆርጥ ወይም ቅስማችን ይሰበር ይሆናል። ምናልባትም የደረሰብን ችግር ምንም መፍትሔ እንደሌለው ሊሰማን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን፣ በሰማይ ባለው አባታችን ሙሉ በሙሉ መተማመን እንዲሁም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ይበልጥ መቀራረብ ይኖርብናል። እርግጥ ይሖዋ መከራውን ላያስወግድልን ይችላል። ለናኦሚም ቢሆን ባለቤቷንና ልጆቿን ከሞት አላስነሳላትም። ሆኖም ይሖዋ የደረሰብንን መከራ ለመቋቋም ይረዳናል። ይህን የሚያደርገው ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በሚያሳዩን ታማኝ ፍቅር አማካኝነት ሊሆን ይችላል።—ምሳሌ 17:17
ሊሰናከል ተቃርቦ የነበረ ሌዋዊ
14. አንድ ሌዋዊ ተስፋ የቆረጠው ለምንድን ነው?
14 የመዝሙር 73 ጸሐፊ ሌዋዊ ነበር። በመሆኑም በይሖዋ የአምልኮ ቦታ የማገልገል ልዩ መብት ነበረው። ያም ቢሆን እሱም እንኳ ተስፋ የቆረጠበት ጊዜ ነበር። ለምን? በክፉዎችና በእብሪተኞች መቅናት ጀምሮ ነበር፤ የቀናው በክፋታቸው ሳይሆን የተሻለ ሕይወት ያላቸው ስለመሰለው ነው። (መዝ. 73:2-9, 11-14) ሀብትና ጥሩ ሕይወት ያላቸው እንዲሁም ምንም ጭንቀት የሌለባቸው፣ በአጭር አነጋገር ሁሉ ነገር የተሳካላቸው ይመስላሉ። መዝሙራዊው ይህን ሲያይ ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ “በእርግጥም ልቤን ያነጻሁት፣ ንጹሕ መሆኔንም ለማሳየት እጄን የታጠብኩት በከንቱ ነው” ብሏል። ይህ ሌዋዊ፣ ከባድ መንፈሳዊ አደጋ ተጋርጦበት እንደነበር በግልጽ ማየት ይቻላል።
15. መዝሙር 73:16-19, 22-25 እንደሚያሳየው ይህን መዝሙር የጻፈው መዝሙራዊ የተስፋ መቁረጥ ስሜቱን እንዲያሸንፍ የረዳው ምንድን ነው?
15 መዝሙር 73:16-19, 22-25ን አንብብ። ሌዋዊው “ወደ ታላቁ የአምላክ መቅደስ [ገባ]።” ከሌሎች የእምነት ባልንጀሮቹ ጋር መገናኘት በሚችልበት በአምላክ መቅደስ ውስጥ በእርጋታ ማሰብ፣ ሁኔታውን አጥርቶ ማየትና ስለ ጉዳዩ መጸለይ ችሏል። በዚህም የተነሳ፣ ማስተዋል እንደጎደለውና ከይሖዋ ሊያርቀው በሚችል አደገኛ ጎዳና ላይ እየተጓዘ እንዳለ ተገነዘበ። በተጨማሪም ክፉዎች “በሚያዳልጥ መሬት ላይ” እንዳሉና ቅጽበታዊ “ጥፋት” እንደሚደርስባቸው አስተዋለ። መዝሙራዊው ያደረበትን ቅናትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለማስወገድ ጉዳዩን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ማየት ነበረበት። እንዲህ ሲያደርግ ውስጣዊ ሰላሙንና ደስታውን መልሶ ማግኘት ችሏል። ‘በምድር ላይ ከይሖዋ ሌላ የምሻው የለም’ በማለት ተናግሯል።
16. ከአንድ ሌዋዊ ምን ትምህርት እናገኛለን?
16 ምን ትምህርት እናገኛለን? የተሳካላቸው በሚመስሉ ክፉ ሰዎች ፈጽሞ መቅናት አይኖርብንም። ደስታቸው ዘላቂና እውነተኛ አይደለም፤ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት አያገኙም። (መክ. 8:12, 13) በእነሱ መቅናት፣ ተስፋ እንድንቆርጥና ለመንፈሳዊ አደጋ እንድንዳረግ ያደርገናል። በመሆኑም ክፉዎች ስኬታማ በመምሰላቸው ምክንያት መቅናት ከጀመርን ሌዋዊው የወሰደውን ዓይነት እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ፍቅር የሚንጸባረቅበትን የአምላክን ምክር መታዘዝና የይሖዋን ፈቃድ ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር መቀራረብ አለብን። ከምንም ነገር በላይ ይሖዋን የምንወደው ከሆነ እውነተኛ ደስታ እናገኛለን። እንዲሁም “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” በሚያስገኝልን ጎዳና ላይ መጓዛችንን እንቀጥላለን።—1 ጢሞ. 6:19
ጴጥሮስ በድክመቶቹ የተነሳ ተስፋ ቆርጦ ነበር
17. ጴጥሮስ የትኞቹ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች አጋጥመውታል?
17 ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ ቀናተኛ ክርስቲያን ቢሆንም ችኩልና ስሜታዊ ሰው ነበር። በመሆኑም የኋላ ኋላ የተቆጨባቸውን ነገሮች የተናገረበት ወይም ያደረገበት ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ኢየሱስ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል ለሐዋርያቱ በነገራቸው ጊዜ ጴጥሮስ “በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም” በማለት ኢየሱስን ገሥጾታል። (ማቴ. 16:21-23) በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ለጴጥሮስ እርማት ሰጠው። ብዙ ሰዎች ኢየሱስን ሊያስሩት በመጡበት ወቅት፣ ጴጥሮስ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን በመቁረጥ የችኮላ እርምጃ ወሰደ። (ዮሐ. 18:10, 11) በዚህ ወቅትም ኢየሱስ ለሐዋርያው እርማት ሰጥቶታል። በተጨማሪም ጴጥሮስ ሌሎቹ ሐዋርያት ሁሉ በኢየሱስ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እሱ ፈጽሞ እንደማይሰናከል በመግለጽ ጉራውን ነዝቷል! (ማቴ. 26:33) ጴጥሮስ ከልክ በላይ በራሱ ተማምኖ ነበር፤ ሆኖም ለሰው ፍርሃት እጅ በመስጠት ጌታውን ሦስት ጊዜ ካደው። ጴጥሮስ በዚህ ቅስሙ ስለተሰበረ “ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።” (ማቴ. 26:69-75) ምናልባትም ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ጨርሶ ይቅር እንደማይለው ተሰምቶት ሊሆን ይችላል።
18. ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ የተስፋ መቁረጥ ስሜቱን እንዲያሸንፍ የረዳው እንዴት ነው?
18 ያም ቢሆን ጴጥሮስ ተስፋ ቆርጦ ይሖዋን ማገልገሉን አላቆመም። ተደናቅፎ የነበረ ቢሆንም ከሌሎቹ ሐዋርያት ጋር ሆኖ ይሖዋን ማገልገሉን ቀጥሏል። (ዮሐ. 21:1-3፤ ሥራ 1:15, 16) ጴጥሮስ እንዲህ እንዲያደርግ የረዳው ምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ቀደም ሲል ኢየሱስ የጴጥሮስ እምነት እንዳይጠፋ ጸልዮ ነበር፤ በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ተመልሶ ወንድሞቹን እንዲያበረታ አሳስቦት ነበር። ይሖዋ የኢየሱስን ልባዊ ጸሎት መልሶለታል። በኋላም ኢየሱስ ለጴጥሮስ ብቻውን ተገልጦለታል፤ ይህን ያደረገው እሱን ለማበረታታት መሆን አለበት። (ሉቃስ 22:32፤ 24:33, 34፤ 1 ቆሮ. 15:5) ከዚህም ሌላ ሐዋርያቱ ሌሊቱን ሙሉ ዓሣ ለማጥመድ ሲሞክሩ አድረው ምንም ዓሣ ባልያዙበት ወቅት ኢየሱስ ተገልጦላቸው ነበር። በዚህ ወቅት ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ለእሱ ያለውን ፍቅር የሚገልጽበት አጋጣሚ ሰጥቶታል። ኢየሱስ የቅርብ ወዳጁን ይቅር ብሎት ነበር፤ እንዲሁም ተጨማሪ ሥራ በአደራ ሰጥቶታል።—ዮሐ. 21:15-17
19. መዝሙር 103:13, 14 ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ ስለ ራሳችን የይሖዋ ዓይነት አመለካከት እንድንይዝ የሚረዳን እንዴት ነው?
19 ምን ትምህርት እናገኛለን? ኢየሱስ ጴጥሮስን የያዘበት መንገድ የኢየሱስን ምሕረት ያሳያል፤ ኢየሱስ ደግሞ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ ነው። በመሆኑም ስህተት በምንሠራበት ወቅት፣ ይሖዋ መቼም ይቅር እንደማይለን ሊሰማን አይገባም። ሰይጣን እንዲህ ያለ ስሜት እንዲያድርብን እንደሚፈልግ መዘንጋት አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ራሳችንንም ሆነ የበደሉንን ሰዎች በተመለከተ፣ ሩኅሩኅና አፍቃሪ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን ዓይነት አመለካከት ለመያዝ ጥረት እናድርግ።—መዝሙር 103:13, 14ን አንብብ።
20. በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
20 የዮሴፍ፣ የናኦሚና የሩት፣ የሌዋዊው እንዲሁም የጴጥሮስ ምሳሌ “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ [መሆኑን]” ያረጋግጥልናል። (መዝ. 34:18) እርግጥ ይሖዋ መከራ እንዳይደርስብን እና የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዳያድርብን ይከላከልልናል ማለት አይደለም። ያም ቢሆን መከራዎቹን በይሖዋ እርዳታ በጽናት ስንወጣ እምነታችን ይጠናከራል። (1 ጴጥ. 1:6, 7) በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ በአለፍጽምናቸው ወይም ባጋጠማቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ምክንያት ተስፋ የቆረጡ ታማኝ አገልጋዮቹን ይሖዋ የሚደግፍባቸውን ተጨማሪ መንገዶች እንመለከታለን።
መዝሙር 7 ይሖዋ ኃይላችን
a ዮሴፍ፣ ናኦሚና ሩት፣ አንድ ሌዋዊ እንዲሁም ሐዋርያው ጴጥሮስ ተስፋ አስቆራጭ መከራዎች አጋጥመዋቸው ነበር። ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ያጽናናቸውና ያጠነከራቸው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም እነሱ ከተዉት ምሳሌ እና አምላክ እነሱን በርኅራኄ ከያዘበት መንገድ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመረምራለን።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ ናኦሚ፣ ሩት እና ዖርፋ የትዳር ጓደኞቻቸውን በሞት በማጣታቸው አዝነውና ተስፋ ቆርጠው ነበር። በኋላ ግን ኢዮቤድ ሲወለድ ሩትና ናኦሚ ከቦዔዝ ጋር ተደስተዋል።