የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጽሐፍ ቅዱስ ምን ፈተናዎችን አልፏል?
መጽሐፍ ቅዱስ በስብሶ ከመጥፋት ተርፏል
ፈተናው፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችና ገልባጮች መልእክቱን በዋነኝነት የጻፉት በፓፒረስና በብራና ላይ ነበር። * (2 ጢሞቴዎስ 4:13) መጽሐፍ ቅዱስ በእነዚህ ነገሮች ላይ መጻፉ ምን አደጋ ነበረው?
ፓፒረስ በቀላሉ የሚቀደድ ከመሆኑም ሌላ ቶሎ ቀለሙ ይለቃል እንዲሁም ይበላሻል። “ከፓፒረስ የተዘጋጀ ወረቀት ውሎ አድሮ ስለሚበሰብስ የሚቀረው ቃጫና አቧራ ነው” በማለት ስለ ጥንታዊ ግብፅ የሚያጠኑት ሪቻርድ ፓርኪንሰንና ስቲቨን ክወርኪ ይናገራሉ። “ጥቅልሉ ተቀብሮ ከቆየ ሊሻግት ወይም በእርጥበት ሊበሰብስና በአይጦች ወይም በነፍሳት በተለይም በነጭ ምስጦች ሊበላ ይችላል።” አንዳንድ ፓፒረሶች ደግሞ ከተገኙ በኋላ ለኃይለኛ ብርሃን ወይም ለእርጥበት ስለተጋለጡ በፍጥነት ሊበላሹ ችለዋል።
ብራና ከፓፒረስ ለበለጠ ጊዜ የሚያገለግል ቢሆንም አላግባብ ከተያዘ ወይም ለከፍተኛ ሙቀት፣ እርጥበት፣ ወይም ብርሃን ከተጋለጠ እየተበላሸ ይሄዳል። * በነፍሳት ሊበላም ይችላል። በዚህም ምክንያት ኤቭሪዴይ ራይቲንግ ኢን ዘ ግሪኮ ሮማን ኢስት የተባለው መጽሐፍ እንደሚናገረው ጥንታዊ መዛግብት “ለረጅም ዘመን ሳይጠፉ መቆየታቸው እምብዛም የተለመደ አይደለም።” መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ሁኔታ ቢበሰብስ ኖሮ የያዘው መልእክትም ይጠፋ ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ፈተና ያለፈው እንዴት ነው? ለአይሁዳውያን የተሰጠው ሕግ እያንዳንዱ ንጉሥ የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት “ቅጂ ለራሱ በመጽሐፍ ላይ [መጻፍ]” እንዳለበት ያዛል። (ዘዳግም 17:18) ከዚህም በላይ በሙያቸው የሠለጠኑ ገልባጮች በእጅ የተገለበጡ በርካታ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎችን በማዘጋጀታቸው ቅዱሳን መጻሕፍት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. በመላው እስራኤል አልፎ ተርፎም ርቃ በምትገኘው መቄዶንያ ሊገኙ ችለው ነበር! (ሉቃስ 4:16, 17፤ የሐዋርያት ሥራ 17:11) በእጅ የተገለበጡ አንዳንድ ጥንታዊ ቅጂዎች እስከ ዘመናችን ሊቆዩ የቻሉት እንዴት ነው?
“አይሁዳውያን ቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፈባቸውን ጥቅልሎች ከብልሽትና ከመበስበስ ጠብቀው ለማቆየት ሲሉ ጽሑፎቹን በእንስራ ወይም በማሰሮ ውስጥ የማስቀመጥ ልማድ ነበራቸው” በማለት የአዲስ ኪዳን ምሁር የሆኑት ፊሊፕ ኮምፎርት ይናገራሉ። ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው ክርስቲያኖችም ይህንኑ ልማድ ተከትለዋል። በዚህም ምክንያት በእጅ የተገለበጡ አንዳንድ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በማሰሮዎች፣ በጨለማ ክፍሎችና በዋሻዎች ውስጥ እንዲሁም ደረቅ በሆኑ ቦታዎች ተገኝተዋል።
ውጤቱ፦ ከ2,000 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያላቸውን ጨምሮ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እስከ ዘመናችን ድረስ ሳይበሰብሱ መቆየት ችለዋል። የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በርካታ ጥንታዊ ቅጂዎች ያሉት ሌላ ጥንታዊ መጽሐፍ የለም።