በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቅርቡ አምላክ መከራን ሁሉ ያስወግዳል

በቅርቡ አምላክ መከራን ሁሉ ያስወግዳል

“ይሖዋ ሆይ፣ እርዳታ ለማግኘት ስጮኽ የማትሰማው እስከ መቼ ነው? ከግፍ እንድታስጥለኝ ስለምን ጣልቃ የማትገባው እስከ መቼ ነው?” (ዕንባቆም 1:2, 3) እንዲህ ብሎ የተናገረው በአምላክ ፊት ሞገስ ያገኘውና ጥሩ ሰው የነበረው ዕንባቆም ነው። እንዲህ ብሎ መጸለዩ እምነት እንደጎደለው የሚያመለክት ነው? በጭራሽ! አምላክ መከራን ለማስወገድ አስቀድሞ የወሰነው ጊዜ እንዳለ በመንገር ዕንባቆምን አጽናንቶታል።—ዕንባቆም 2:2, 3

በአንተ ወይም በምትወደው ሰው ላይ መከራ በሚደርስበት ጊዜ አምላክ እርምጃ ለመውሰድ የዘገየውና ቶሎ ጣልቃ ያልገባው ለምን እንደሆነ ግራ ሊገባህ ይችላል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል፦ “አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ይሖዋ የገባውን ቃል ለመፈጸም አይዘገይም፤ ከዚህ ይልቅ እናንተን የታገሠው፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው።”—2 ጴጥሮስ 3:9

አምላክ እርምጃ የሚወስደው መቼ ነው?

በቅርቡ እርምጃ ይወስዳል! ኢየሱስ የተለያዩ ገጽታዎች ያሉትን ‘የዚህን ሥርዓት’ የመጨረሻ ቀናት ለይቶ የሚያሳውቀውን ምልክት የሚያይ አንድ ትውልድ እንደሚኖር ገልጾ ነበር። (ማቴዎስ 24:3-42) ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት በእኛ ዘመን እየተፈጸመ መሆኑ አምላክ በሰው ልጆች ጉዳይ ጣልቃ የሚገባበት ጊዜ በጣም ቅርብ እንደሆነ ያመለክታል። *

ይሁንና አምላክ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ ሙሉ በሙሉ የሚያስወግደው እንዴት ነው? ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ያደረጋቸው ነገሮች አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን መከራ ለማስወገድ የሚያስችል ኃይል እንዳለው ያሳያሉ። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት።

የተፈጥሮ አደጋዎች፦ ኢየሱስና ሐዋርያቱ በገሊላ ባሕር ላይ በጀልባ እየተጓዙ ሳሉ ኃይለኛ ማዕበል ጀልባዋን ሊገለብጣት ደርሶ ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ እሱም ሆነ አባቱ የተፈጥሮ ኃይሎችን መቆጣጠር እንደሚችሉ አሳየ። (ቆላስይስ 1:15, 16) ኢየሱስ ማዕበሉን “ጸጥ በል! ረጭ በል!” አለው። ከዚያም “ነፋሱ ቆመ፤ ታላቅ ጸጥታም ሰፈነ።”—ማርቆስ 4:35-39

በሽታ፦ ኢየሱስ ዓይነ ስውራንንና አንካሶችን እንዲሁም በሚጥል በሽታ፣ በሥጋ ደዌ ወይም በሌላ ዓይነት በሽታ የሚሠቃዩ ሰዎችን በመፈወስ ችሎታው በሰፊው ይታወቅ ነበር። “እየተሠቃዩ የነበሩትንም ሁሉ [ፈውሷል]።”—ማቴዎስ 4:23, 24፤ 8:16፤ 11:2-5

የምግብ እጥረት፦ ኢየሱስ አባቱ የሰጠውን ኃይል ተጠቅሞ በጣም ጥቂት የነበረው ምግብ ብዙ እንዲሆን አድርጓል። ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ከአንዴም ሁለት ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደመገበ ተመዝግቧል።—ማቴዎስ 14:14-21፤ 15:32-38

ሞት፦ ኢየሱስ የሞቱ ሰዎችን በሦስት የተለያዩ አጋጣሚዎች ከሞት እንዳስነሳ የሚገልጹት ዘገባዎች ይሖዋ በሞት ላይ ሥልጣን እንዳለው ያሳያሉ። ኢየሱስ ከሞት ካስነሳቸው ሰዎች መካከል አንዱ ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ነበር።—ማርቆስ 5:35-42፤ ሉቃስ 7:11-16፤ ዮሐንስ 11:3-44

^ አን.5 የመጨረሻዎቹን ቀናት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 32 ተመልከት። መጽሐፉን ከ​www.jw.org/am ላይ በነፃ ማውረድ ይቻላል።