በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ችግሮችን ለመቋቋም የሚረዳ ምክር

ችግሮችን ለመቋቋም የሚረዳ ምክር

በአሁኑ ጊዜ ሊወገዱ አሊያም መፍትሔ ሊገኝላቸው የማይችሉ ችግሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የምትወደውን ሰው በሞት አጥተህ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ሥር የሰደደ ሕመም ሊኖርብህ ይችላል፤ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ ሥቃይህን ለመቋቋም የሚረዱህ መንገዶች ከመፈለግ ውጭ ሌላ ምርጫ ላይኖርህ ይችላል። ታዲያ እንዲህ ባሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳህ ይችላል?

ሥር የሰደደ ሕመም

ሮዝ “በዘር የሚተላለፍ ሕመም አለብኝ፤ ሕመሙ ከባድና ፋታ የማይሰጥ ሥቃይ ስለሚያስከትል ሕይወቴን ምስቅልቅል አድርጎብኛል” ብላለች። ሮዝ በጣም ከሚረብሿት ነገሮች አንዱ፣ መጽሐፍ ቅዱስንና መንፈሳዊ ነገሮችን ስታጠና አንዳንድ ጊዜ ትኩረቷን መሰብሰብ አለመቻሏ ነው። በማቴዎስ 19:26 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ በእጅጉ ረድቷታል፤ ጥቅሱ “በአምላክ ዘንድ . . . ሁሉ ነገር ይቻላል” ይላል። ሮዝ ማጥናት የሚቻልባቸው የተለያዩ መንገዶች እንዳሉ ተገንዝባለች። ከሥቃይዋ የተነሳ ማንበብ አዳጋች ሲሆንባት በድምፅ ተቀርጾ የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስና የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ንባብ ማዳመጥ ጀመረች። a ሮዝ “እንዲህ ዓይነት አማራጭ ባይኖረኝ ኖሮ መንፈሳዊነቴን እንዴት መጠበቅ እንደምችል አላውቅም” ብላለች።

ሮዝ በአንድ ወቅት ታከናውናቸው የነበሩ ነገሮችን ማከናወን ባለመቻሏ በምታዝንበት ጊዜ በ2 ቆሮንቶስ 8:12 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ያጽናናታል፤ ጥቅሱ “ለመስጠት ፈቃደኝነቱ ካለ ስጦታው ይበልጥ ተቀባይነት የሚኖረው አንድ ሰው ባለው መጠን ሲሰጥ እንጂ በሌለው መጠን ሲሰጥ አይደለም” ይላል። ይህ ጥቅስ አምላክ በምታደርገው ነገር እንደሚደሰት እንድታስታውስ ይረዳታል፤ ምክንያቱም ሮዝ አቅሟ የፈቀደውን ነገር ሁሉ እያደረገች ነው።

ሐዘን

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ዴልፊን የ18 ዓመት ወጣት የነበረችውን ልጇን በሞት ባጣችበት ወቅት የተሰማትን ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ልጄ ስትሞት ሐዘኑ በጣም ስለከበደኝ በሕይወት መቀጠል የምችል አልመሰለኝም ነበር። ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር እንደ ድሮው ሊሆንልኝ አልቻለም።” ይሁንና ዴልፊን በመዝሙር 94:19 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በጣም አጽናንቷታል፤ መዝሙራዊው፣ አምላክ ያደረገለትን እርዳታ አስመልክቶ ሲናገር “በጭንቀት በተዋጥኩ ጊዜ፣ አጽናናኸኝ፤ ደግሞም አረጋጋኸኝ” ብሎ ነበር። ዴልፊን “ሥቃዬን ለማስታገሥ በሚረዱኝ ነገሮች መጠመድ እንድችል ወደ ይሖዋ ጸለይኩ” ብላለች።

ከዚያም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመካፈል ራሷን በሥራ አስጠመደች። ዴልፊን ራሷን የምትመለከተው፣ ልጆች ሥዕሎችን ቀለም ለመቀባት እንደሚጠቀሙባቸው እርሳሶች አድርጋ እንደሆነ ትናገራለች፤ የተሰበሩት እርሳሶችም ቢሆኑ ሥዕሎችን ለማቅለም ያገለግላሉ። በተመሳሳይ እሷም እንደተሰበረች ቢሰማትም እንኳ ሌሎችን መርዳት እንደምትችል ተገነዘበች። እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “የአምላክን ቃል የማስጠናቸውን ሰዎች ለማጽናናት የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎችና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ሐሳቦችን ስጠቀም እኔም እበረታታለሁ፤ ይሖዋ እኔን የሚያጽናናኝና የሚያረጋጋኝ በዚህ መንገድ እንደሆነ ማስተዋል ችያለሁ።” በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹ ከባድ ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎችን ስም ዝርዝር ጻፈች። ዴልፊን “ሁሉም የጸሎት ሰዎች ነበሩ” ብላለች። አክላም “መጽሐፍ ቅዱስን ካላነበብን ከሐዘናችን መጽናናት እንደማንችል” መገንዘቧን ገልጻለች።

ዴልፊን መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቷ ያስገኘላት ሌላም ጥቅም አለ፤ ያለፈውን እያሰበች ከመቆዘም ይልቅ በወደፊቱ ጊዜ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባት ተገንዝባለች። በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ የሰፈረው “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ” የሚገልጸው ተስፋ አጽናንቷታል። ዴልፊን፣ ይሖዋ ልጇን ከሞት እንደሚያስነሳላት ምን ያህል ትተማመናለች? እንዲህ ብላለች፦ “ወደፊት ልጄ ከሞት ተነስታ አብረን ስንሆን ይታየኛል። ከልጄ ጋር የምንገናኝበት ቀን ተቀጥሯል፤ ቀጠሯችን በይሖዋ የቀን መቁጠሪያ ላይ የሰፈረ ያህል ነው። ልጄ በተወለደችበት ቀን የነበረው ሁኔታ ከአእምሮዬ እንደማይጠፋ ሁሉ ወደፊት ከእሷ ጋር በአትክልት ቦታችን ውስጥ የምናሳልፈው ጊዜም ቁልጭ ብሎ ይታየኛል።”

a እንደዚህ ያሉ በድምፅ የተቀረጹ ነገሮች jw.org በተባለው ድረ ገጽ ላይ ይገኛሉ።

በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያትም ጭምር መጽሐፍ ቅዱስ ሊያጽናናህ ይችላል