ለፌቭር ዴታፕለ—ተራው ሕዝብ የአምላክን ቃል እንዲያውቅ ይፈልግ ነበር
ጊዜው የ1520ዎቹ መባቻ ሲሆን ዕለቱ እሁድ ጠዋት ነው፤ በፓሪስ አቅራቢያ በምትገኘው ሞ የተባለች ትንሽ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን የተሰበሰቡት ሰዎች በዚያ የሰሙትን ነገር ማመን ከብዷቸዋል። የወንጌል መጻሕፍት በላቲን ሳይሆን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በፈረንሳይኛ ሲነበብ ሰሙ!
ይህ ነገር እንዲሳካ ትልቅ ሚና የተጫወተው የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የሆነው ዣክ ለፌቭር ዴታፕለ (በላቲን ጀኮብስ ፈበር ስታፕዩሌንሰስ ይባላል) ከጊዜ በኋላ ለአንድ የቅርብ ወዳጁ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ተራ [የሆኑ ሰዎችም] ቃሉን እንዲረዱ ምን ያህል እንደሚያነሳሳ ስትመለከት ትገረማለህ።”
በወቅቱ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና በፓሪስ የሚገኙት የሃይማኖት ምሁራን ተራው ሕዝብ በሚግባባበት ቋንቋ የተተረጎሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን መጠቀምን ይቃወሙ ነበር። ታዲያ ለፌቭር መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ፈረንሳይኛ እንዲተረጉም ያነሳሳው ምንድን ነው? ተራው ሕዝብ የአምላክን ቃል መረዳት የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት የቻለው እንዴት ነው?
የቅዱሳን መጻሕፍትን ትክክለኛ ትርጉም መረዳት
ለፌቭር የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ ከመሆኑ በፊት፣ ጥንታዊ የፍልስፍና እና የሃይማኖት መጻሕፍት በትክክለኛ መንገድ መተርጎማቸውን በማጣራቱና በማስተካከሉ ሥራ ተጠምዶ ነበር። ጥንታዊ ጽሑፎች በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት በዘለቁ የአተረጓጎምና የአጻጻፍ ስህተቶች እንደተበረዙ አስተዋለ። የጥንታዊ ጽሑፎችን ትክክለኛ ትርጉም ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትጠቀምበት የነበረውን ላቲን ቩልጌት የተባለ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማጥናት ጀመረ።
ለፌቭር ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት ማጥናቱ “ከሁሉ የላቀ ደስታ ማግኘት የሚቻለው መለኮታዊውን እውነት በማጥናት ነው” የሚል መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ አስችሎታል። በመሆኑም ስለ ፍልስፍና ማጥናቱን ትቶ ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎም ሥራ ላይ አደረገ።
ለፌቭር በ1509 በቩልጌት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ያደረገውን ማስተካከያ ጨምሮ በላቲን የተዘጋጁ አምስት የተለያዩ የመዝሙር መጽሐፍ ትርጉሞችን a እያወዳደረ የሚያቀርብ አንድ ጽሑፍ አዘጋጀ። በወቅቱ ከነበሩት የሃይማኖት ምሁራን በተለየ መልኩ እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሚያስተላልፈውን “ትክክለኛ ስሜት” ለማግኘት ይሞክር ነበር። እሱ የተጠቀመበት ቅዱሳን መጻሕፍትን የመተርጎም ዘዴ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራንና የተሃድሶ አራማጆች ላይም ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል።—“ ለፌቭር በማርቲን ሉተር ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
ከልጅነቱ ጀምሮ ካቶሊክ የነበረው ለፌቭር በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ተሃድሶ ሊኖር የሚችለው ቅዱሳን መጻሕፍትን ለተራው ሕዝብ በሚገባ በማስተማር ብቻ እንደሆነ ያምን ነበር። ታዲያ ቅዱሳን መጻሕፍት በአብዛኛው በላቲን ቋንቋ በሚገኙበት በዚያ ዘመን ተራው ሕዝብ ከቅዱሳን መጻሕፍት ጥቅም ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው?
ሁሉም ሰው ሊያገኘው የሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም
ለፌቭር ለአምላክ ቃል የነበረው ጥልቅ ፍቅር በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች የአምላክን ቃል ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ
አነሳስቶታል። ይህን ግቡን ለማሳካት፣ በሰኔ 1523 የወንጌል መጻሕፍትን በፈረንሳይኛ ቋንቋ በኪስ ሊያዝ የሚችል መጠን ባላቸው ሁለት ጥራዞች አሳተመ። ይህ እትም መጠኑ ትንሽ በመሆኑ ዋጋው ከመደበኛው እትም በግማሽ የሚያንስ ሲሆን ይህም ድሆች እንኳ የራሳቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲኖራቸው አስችሏል።ተራው ሕዝብ ለዚህ ሥራ ያለውን አድናቆት ለመግለጽ ጊዜ አልፈጀበትም። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ኢየሱስ የተናገራቸውን ቃላት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ለማንበብ በጣም ጓጉተው ስለነበር መጀመሪያ ላይ የታተሙት 1,200 ቅጂዎች በጥቂት ወራት ውስጥ ተሸጠው አለቁ።
ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥብቅና መቆም
ለፌቭር በወንጌል መጻሕፍቱ መግቢያ ላይ እነዚህን መጻሕፍት ወደ ፈረንሳይኛ የተረጎመው ‘ተራው የቤተ ክርስቲያን አባል የወንጌልን እውነት በላቲን ከሚያነቡት ሰዎች እኩል እንዲረዳ’ ለማስቻል መሆኑን ገልጿል። ሆኖም ለፌቭር ተራው ሕዝብ የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት መርዳት የሚችልበትን መንገድ ለማመቻቸት ይህን ያህል ፍላጎት ያደረበት ለምንድን ነው?
ለፌቭር የሰዎች ወግና ፍልስፍና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ምን ያህል እንደበረዘ በሚገባ ተገንዝቦ ነበር። (ማርቆስ 7:7፤ ቆላስይስ 2:8) ሕዝቡ “በሰዎች እንግዳ መሠረተ ትምህርቶች እንዳይታለሉ ሲባል ወንጌሎች በትክክል በመላው ዓለም የሚታወጁበት” ጊዜ እንደደረሰ ተሰምቶት ነበር።
ለፌቭር መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ፈረንሳይኛ ለመተርጎም ያደረገውን ጥረት የሚቃወሙ ሰዎች የሚያቀርቡትን የተሳሳተ ሮም 10:14
ምክንያት ለማጋለጥም ሞክሯል። እንዲህ በማለት ግብዝነታቸውን አውግዟል፦ “ተራው ሕዝብ በራሱ ቋንቋ የአምላክን ወንጌል እንዲያይና እንዲያነብ ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆኑ [ሰዎች] ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጣቸውን ትእዛዛት ሁሉ እንዲጠብቁ እንዴት ማስተማር ይችላሉ?”—በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ በሶርቦን የሚገኙት የሃይማኖት ምሁራን ወዲያውኑ የለፌቭርን አፍ ለማዘጋት ጥረት ማድረግ ጀመሩ። ነሐሴ 1523፣ ምሁራኑ ወደ ፈረንሳይኛ የተተረጎሙት መጽሐፍ ቅዱሶችና የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎች “ለቤተ ክርስቲያኒቱ ጎጂ” እንደሆኑ በመናገር ተቃውሟቸውን ገለጹ። የፈረንሳዩ ንጉሥ ቀዳማዊ ፍራንሲስ ጣልቃ ባይገባ ኖሮ ለፌቭር መናፍቅ ተብሎ ይወገዝ ነበር።
ተርጓሚው “ድምፁን አጥፍቶ” ሥራውን ቀጠለ
ለፌቭር በእሱ ሥራ ላይ የተነሱትን ውዝግቦች ችላ ብሎ መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎሙን ቀጠለ። በ1524 የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን (በተለምዶ አዲስ ኪዳን ይባላል) ተርጎሞ ካጠናቀቀ በኋላ ምዕመናን “በጠለቀ ፍቅርና ስሜት” ወደ አምላክ መጸለይ እንዲችሉ ለመርዳት መዝሙር መጽሐፍን በፈረንሳይኛ ቋንቋ አዘጋጀ።
በሶርቦን የሚገኙት የሃይማኖት ምሁራን ወዲያውኑ የለፌቭርን ትርጉሞች በጥንቃቄ መመርመር ጀመሩ። ብዙም ሳይቆይ የለፌቭር የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በሕዝብ ፊት እንዲቃጠል አዘዙ፤ አንዳንድ ጽሑፎቹን ደግሞ “የሉተርን ኑፋቄ የሚደግፉ ናቸው” በማለት አወገዟቸው። የሃይማኖት ምሁራኑ፣ ለፌቭር ለተሰነዘረበት ክስ ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ሲጠይቁት “ድምፁን አጥፍቶ” ወደ ስትራዝቡርግ ሸሸ። በዚያም በድብቅ መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎሙን ቀጠለ። አንዳንዶች መሸሹ ድፍረት እንደሌለው የሚያሳይ እንደሆነ አድርገው ቢወስዱትም እሱ ግን ውድ “ዕንቁዎች” ለሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ምንም አድናቆት ለሌላቸው ሰዎች ትክክለኛው ምላሽ ይህ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር።—ማቴዎስ 7:6
ለፌቭር ከፈረንሳይ ከሸሸ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ንጉሥ ቀዳማዊ ፍራንሲስ ለፌቭርን ቻርልስ ለተባለው የአራት ዓመት ልጁ አስተማሪ አደረገው። ይህ ሥራ ለለፌቭር የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራውን እንዲያጠናቅቅ ሰፊ ጊዜ ሰጥቶታል። በ1530 ሙሉው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሙ በንጉሠ ነገሥት ቻርልስ አምስተኛ ፈቃድ ከፈረንሳይ ውጪ በአንትወርፕ ታተመ። b
ሳይሳካ የቀረ ምኞት
ለፌቭር በሕይወት ዘመኑ በሙሉ ቤተ ክርስቲያኒቷ የሰው ወጎችን ትታ ወደጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ትመለሳለች የሚል ተስፋ ነበረው። “እያንዳንዱ ክርስቲያን በግሉ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ መብት፣ እንዲያውም ግዴታ” እንዳለበት ያምን ነበር። ሁሉም ሰው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያገኝ ሲል በትጋት የሠራው በዚህ ምክንያት ነው። ለፌቭር ቤተ ክርስቲያኒቱ ተሃድሶ አድርጋ የማየት ምኞቱ ባይሳካም ተራው ሕዝብ የአምላክን ቃል እንዲያውቅ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱ የማይታበል ሐቅ ነው።
a ፋይቭፎልድ ሳልተር የተባለው ይህ ጽሑፍ አምስቱን የመዝሙር መጽሐፍ ትርጉሞች በተለያዩ ረድፎች ያስቀመጠ ሲሆን ቴትራግራማተንን ማለትም የአምላክን ስም የሚያመለክቱትን አራት የዕብራይስጥ ፊደላት ጨምሮ ለአምላክ የተሰጡትን የማዕረግ ስሞች የያዘ ሰንጠረዥ አካትቷል።
b ከአምስት ዓመት በኋላ ማለትም በ1535 ፈረንሳዊው ተርጓሚ ኦሊቬታ መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ የተጻፈባቸው ቋንቋዎችን መሠረት በማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አዘጋጀ። ኦሊቬታ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ሲተረጉም በዋነኝነት የለፌቭርን ሥራዎች ተጠቅሟል።