ሁለተኛ ዜና መዋዕል 36:1-23
36 ከዚያም የምድሪቱ ሕዝብ የኢዮስያስን ልጅ ኢዮዓካዝን+ በአባቱ ምትክ በኢየሩሳሌም አነገሡት።+
2 ኢዮዓካዝ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 23 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሦስት ወር ገዛ።
3 ይሁን እንጂ የግብፅ ንጉሥ በኢየሩሳሌም ካለው ዙፋኑ አወረደው፤ በምድሪቱም ላይ 100 የብር ታላንትና* አንድ የወርቅ ታላንት ቅጣት ጣለ።+
4 በተጨማሪም የግብፁ ንጉሥ ኒካዑ+ የኢዮዓካዝን ወንድም ኤልያቄምን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው፤ ስሙንም ቀይሮ ኢዮዓቄም አለው፤ ወንድሙን ኢዮዓካዝን ግን ወደ ግብፅ ወሰደው።+
5 ኢዮዓቄም+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 25 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ። እሱም በአምላኩ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+
6 የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር+ ከመዳብ በተሠሩ ሁለት የእግር ብረቶች አስሮ ወደ ባቢሎን ለመውሰድ በእሱ ላይ ዘመተ።+
7 ናቡከደነጾርም በይሖዋ ቤት ያሉ የተወሰኑ ዕቃዎችን ወደ ባቢሎን ወስዶ በባቢሎን በሚገኘው ቤተ መንግሥቱ አስቀመጣቸው።+
8 የቀረው የኢዮአቄም ታሪክ፣ የፈጸማቸው አስጸያፊ ነገሮችና በእሱ ላይ የተገኘበት መጥፎ ነገር በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል፤ በእሱም ምትክ ልጁ ዮአኪን ነገሠ።+
9 ዮአኪን+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 18 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለሦስት ወር ከአሥር ቀን ገዛ፤ እሱም በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ።+
10 በዓመቱ መጀመሪያ* ላይ ንጉሥ ናቡከደነጾር አገልጋዮቹን ልኮ በይሖዋ ቤት ካሉት ውድ ዕቃዎች+ ጋር ወደ ባቢሎን አመጣው።+ የአባቱን ወንድም ሴዴቅያስንም በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነገሠው።+
11 ሴዴቅያስ+ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው 21 ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌምም ሆኖ ለ11 ዓመት ገዛ።+
12 በአምላኩ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አደረገ። በይሖዋ ትእዛዝ በተናገረው በነቢዩ ኤርምያስ ፊት ራሱን ዝቅ አላደረገም።+
13 ደግሞም በአምላክ ስም ባስማለው በንጉሥ ናቡከደነጾር ላይ ዓመፀ፤+ ግትር ሆነ፤* ልቡንም አጠነከረ፤ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ ይሖዋ ለመመለስ አሻፈረኝ አለ።
14 ዋነኞቹ ካህናት ሁሉና ሕዝቡ፣ ብሔራት የሚፈጽሟቸውን አስጸያፊ ነገሮች በማድረግ እጅግ ከፍተኛ ክህደት ፈጸሙ፤ ይሖዋ በኢየሩሳሌም የቀደሰውንም ቤት አረከሱ።+
15 የአባቶቻቸው አምላክ ይሖዋ ለሕዝቡና ለማደሪያው ስፍራ ስለራራ መልእክተኞቹን እየላከ በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃቸው ነበር።
16 እነሱ ግን የይሖዋ ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪነድና+ ፈውስ እስከማይገኝላቸው ድረስ በእውነተኛው አምላክ መልእክተኞች ላይ ያላግጡ፣+ ቃሉን ይንቁና+ በነቢያቱ ላይ ያፌዙ+ ነበር።
17 ስለዚህ የከለዳውያንን+ ንጉሥ አመጣባቸው፤ እሱም ወጣቶቻቸውን በቤተ መቅደሳቸው+ ውስጥ በሰይፍ ገደለ፤+ ለወጣቱም ሆነ ለድንግሊቱ፣ ለሽማግሌውም ሆነ ለአቅመ ደካማው አልራራም።+ አምላክ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው።+
18 በእውነተኛው አምላክ ቤት የነበሩትን ትላልቅም ሆኑ ትናንሽ ዕቃዎች በሙሉ፣ የይሖዋን ቤት ውድ ሀብት እንዲሁም የንጉሡንና የመኳንንቱን ውድ ሀብት ሁሉ ወደ ባቢሎን አጋዘ።+
19 የእውነተኛውን አምላክ ቤት አቃጠለ፤+ የኢየሩሳሌምን ቅጥር አፈረሰ፤+ የማይደፈሩ ማማዎቿን ሁሉ በእሳት አቃጠለ፤ እንዲሁም ውድ የሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ አወደመ።+
20 ከሰይፍ የተረፉትንም ሁሉ ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤+ እነሱም የፋርስ መንግሥት* መግዛት እስከጀመረበት ጊዜ ድረስ+ የእሱና የወንዶች ልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ፤+
21 ይህም የሆነው ይሖዋ በኤርምያስ በኩል የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ፣+ ምድሪቱ የሰንበት ዕዳዋን እስክትከፍል ድረስ ነው።+ ፈራርሳ በቆየችባቸው ጊዜያት ሁሉ፣ 70 ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ሰንበትን አከበረች።+
22 በኤርምያስ በኩል የተነገረው የይሖዋ ቃል ይፈጸም ዘንድ+ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ+ በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት የሚከተለውን አዋጅ በመላ ግዛቱ እንዲያውጅ ይሖዋ የፋርሱን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሳሳ፤ እሱም ይህ በጽሑፍ እንዲሰፍር አደረገ፦+
23 “የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ ‘የሰማይ አምላክ ይሖዋ የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፤+ በይሁዳ በምትገኘው በኢየሩሳሌምም ቤት እንድሠራለት አዞኛል።+ ከእሱ ሕዝብ መካከል የሆነ አብሯችሁ የሚኖር ማንኛውም ሰው አምላኩ ይሖዋ ከእሱ ጋር ይሁን፤ እሱም ወደዚያ ይውጣ።’”+