አንደኛ ሳሙኤል 15:1-35

  • ሳኦል አጋግን ባለመግደሉ የታዘዘውን ሳይፈጽም ቀረ (1-9)

  • ሳሙኤል ሳኦልን ገሠጸው (10-23)

    • ‘መታዘዝ ከመሥዋዕት ይበልጣል’ (22)

  • የሳኦል ንግሥና በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት አጣ (24-29)

  • ሳሙኤል አጋግን ገደለው (30-35)

15  ከዚያም ሳሙኤል ሳኦልን እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ በሕዝቡ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጌ እንድቀባህ የላከው እኔን ነበር፤+ እንግዲህ አሁን ይሖዋ ምን እንደሚል ስማ።+ 2  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ ጊዜ በመንገድ ላይ እነሱን በመቃወም ለፈጸሙት ድርጊት አማሌቃውያንን እቀጣቸዋለሁ።+ 3  በል አሁን ሂድ፤ አማሌቃውያንን+ ምታቸው፤ እነሱንም ካላቸው ነገር ሁሉ ጋር ፈጽመህ አጥፋቸው።+ አንዳቸውንም አታስቀር፤* ወንድም ሆነ ሴት፣ ልጅም ሆነ ሕፃን፣ በሬም ሆነ በግ፣ ግመልም ሆነ አህያ ሁሉንም ግደል።’”+ 4  ሳኦልም ሕዝቡን በጤላይም ሰብስቦ ቆጠረ፤ በዚያም 200,000 እግረኛ ወታደሮችና 10,000 የይሁዳ ሰዎች ነበሩ።+ 5  ከዚያም ሳኦል እስከ አማሌቃውያን ከተማ ድረስ በመጠጋት በሸለቆው* ውስጥ አደፈጠ። 6  ሳኦልም ቄናውያንን+ “ከአማሌቃውያን ጋር አብሬ እንዳላጠፋችሁ+ ሂዱ፣ ከእነሱ መካከል ውጡ። ምክንያቱም እናንተ እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡበት ጊዜ ለሕዝቡ በሙሉ ታማኝ ፍቅር አሳይታችኋል”+ አላቸው። በመሆኑም ቄናውያን ከአማሌቃውያን መካከል ወጡ። 7  ከዚያም ሳኦል አማሌቃውያንን+ ከሃዊላ+ አንስቶ በግብፅ አጠገብ እስከምትገኘው እስከ ሹር+ ድረስ መታቸው። 8  እሱም የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን+ ከነሕይወቱ ማረከው፤ የቀረውን ሕዝብ ሁሉ ግን በሰይፍ ፈጽሞ አጠፋ።+ 9  ሆኖም ሳኦልና ሕዝቡ አጋግን እንዲሁም ከመንጋው፣ ከከብቱ፣ ከደለቡት እንስሳትና ከአውራ በጎቹ መካከል ምርጥ የሆኑትንና ጥሩ ጥሩ የሆነውን ነገር ሁሉ ሳያጠፉ ተዉ።+ እነዚህን ሊያጠፏቸው አልፈለጉም። የማይረባውንና የማይፈለገውን ነገር ሁሉ ግን ፈጽመው አጠፉ። 10  ከዚያም የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ወደ ሳሙኤል መጣ፦ 11  “ሳኦልን ንጉሥ በማድረጌ ተጸጽቻለሁ፤* ምክንያቱም እሱ እኔን ከመከተል ዞር ብሏል፤ ቃሌንም አልፈጸመም።”+ ሳሙኤልም በጣም ስለተረበሸ ሌሊቱን ሙሉ ወደ ይሖዋ ሲጮኽ አደረ።+ 12  ሳሙኤል ሳኦልን ለማግኘት በማለዳ ተነስቶ ሲሄድ “ሳኦል ወደ ቀርሜሎስ+ ሄዶ በዚያ ለራሱ የመታሰቢያ ሐውልት አቁሟል።+ ከዚያም ተመልሶ ወደ ጊልጋል ወርዷል” ተብሎ ተነገረው። 13  በመጨረሻም ሳሙኤል ወደ ሳኦል ሲመጣ ሳኦል “ይሖዋ ይባርክህ። የይሖዋን ቃል ፈጽሜአለሁ” አለው። 14  ሳሙኤል ግን “ታዲያ ይህ በጆሮዬ የምሰማው የበጎችና የከብቶች ድምፅ ምንድን ነው?” አለው።+ 15  በዚህ ጊዜ ሳኦል “ሕዝቡ ከአማሌቃውያን ላይ ወስዶ ያመጣቸው ናቸው፤ ከመንጋውና ከከብቶቹ መካከል ምርጥ የሆኑትን ለአምላክህ ለይሖዋ መሥዋዕት እንዲሆኑ ሳያጠፉ ተዉአቸው፤* የቀረውን ግን ሙሉ በሙሉ አጥፍተናል” አለው። 16  ሳሙኤልም ሳኦልን “ተው በቃ! ትናንት ማታ ይሖዋ ምን እንዳለኝ ልንገርህ” አለው።+ እሱም “እሺ ንገረኝ!” አለው። 17  ሳሙኤልም እንዲህ አለው፦ “በእስራኤል ነገዶች ላይ መሪ ሆነህ በተሾምክበትና ይሖዋ በእስራኤል ላይ ንጉሥ አድርጎ በቀባህ+ ጊዜ አንተ ራስህ እዚህ ግባ የማትባል ሰው እንደሆንክ ተሰምቶህ አልነበረም?+ 18  በኋላም ይሖዋ ‘ሄደህ ኃጢአተኞቹን አማሌቃውያንን ፈጽመህ አጥፋቸው።+ ጨርሰህ እስክታጠፋቸውም ድረስ ከእነሱ ጋር ተዋጋ’ በማለት ላከህ።+ 19  ታዲያ የይሖዋን ቃል ያልታዘዝከው ለምንድን ነው? ከዚህ ይልቅ ለምርኮው በመስገብገብ+ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር አድርገሃል!” 20  ሳኦል ግን ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “እኔ እኮ የይሖዋን ቃል ታዝዣለሁ! ይሖዋ የሰጠኝን ተልእኮ ለመፈጸም ሄጃለሁ፤ የአማሌቃውያንን ንጉሥ አጋግን ይዤ አምጥቻለሁ፤ አማሌቃውያንንም ፈጽሜ አጥፍቻለሁ።+ 21  ሕዝቡ ግን በጊልጋል ለአምላክህ ለይሖዋ ለመሠዋት ከምርኮው ላይ በጎችንና ከብቶችን ይኸውም ለጥፋት ከተለየው ነገር ላይ ምርጥ የሆነውን ወሰደ።”+ 22  ከዚያም ሳሙኤል እንዲህ አለ፦ “ይሖዋን ይበልጥ የሚያስደስተው የትኛው ነው? የሚቃጠሉ መባዎችንና መሥዋዕቶችን+ ማቅረብ ወይስ የይሖዋን ቃል መታዘዝ? እነሆ፣ መታዘዝ ከመሥዋዕት፣+ መስማትም ከአውራ በግ ስብ+ ይበልጣል፤ 23  ምክንያቱም ዓመፀኝነት+ ሟርት+ ከመፈጸም አይተናነስም፤ እብሪተኝነትም ቢሆን ከጥንቆላና ከጣዖት አምልኮ* ተለይቶ አይታይም። አንተ የይሖዋን ቃል ስላልተቀበልክ+ እሱም የአንተን ንግሥና አልተቀበለውም።”+ 24  ከዚያም ሳኦል ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ “ኃጢአት ሠርቻለሁ፤ ሕዝቡን በመፍራትና ቃላቸውን በመስማት የይሖዋን ትእዛዝም ሆነ የአንተን ቃል ጥሻለሁ። 25  አሁንም እባክህ ኃጢአቴን ይቅር በል፤ ለይሖዋም እንድሰግድ አብረኸኝ ተመለስ።”+ 26  ሳሙኤል ግን ሳኦልን “አንተ የይሖዋን ቃል ስላልተቀበልክና ይሖዋም በእስራኤል ላይ ንጉሥ ሆነህ እንድትቀጥል ስላልፈቀደ ከአንተ ጋር አልመለስም” አለው።+ 27  ሳሙኤል ለመሄድ ዞር ሲል ሳኦል የሳሙኤልን ልብስ ጫፍ አፈፍ አድርጎ ያዘ፤ ልብሱም ተቀደደ። 28  በዚህ ጊዜ ሳሙኤል እንዲህ አለው፦ “ይሖዋ የእስራኤልን ንጉሣዊ አገዛዝ በዛሬው ዕለት ከአንተ ቀዶታል፤ ከአንተ ለሚሻል ባልንጀራህም አሳልፎ ይሰጠዋል።+ 29  ደግሞም የእስራኤል ክቡር+ አይዋሽም+ ወይም ሐሳቡን አይቀይርም፤* ምክንያቱም እሱ ሐሳቡን ይቀይር* ዘንድ+ የሰው ልጅ አይደለም።” 30  እሱም “ኃጢአት ሠርቻለሁ። ሆኖም እባክህ በሕዝቤ ሽማግሌዎችና በእስራኤል ፊት አክብረኝ። አብረኸኝ ተመለስ፤ እኔም ለአምላክህ ለይሖዋ እሰግዳለሁ”+ አለው። 31  በመሆኑም ሳሙኤል ሳኦልን ተከትሎት ተመለሰ፤ ሳኦልም በይሖዋ ፊት ሰገደ። 32  ሳሙኤልም “የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን አምጡልኝ” አለ። አጋግም “መቼም የሞትን መራራ ጽዋ የምቀምስበት ጊዜ አልፏል” ብሎ ስላሰበ ፈራ ተባ እያለ* ወደ እሱ ሄደ። 33  ሆኖም ሳሙኤል “በአንተ ሰይፍ የተነሳ ልጆቻቸውን ያጡ ሴቶች እንዳዘኑ ሁሉ የአንተም እናት ከሴቶች ሁሉ ይበልጥ ታዝናለች” አለው። ከዚያም ሳሙኤል በጊልጋል በይሖዋ ፊት አጋግን ቆራረጠው።+ 34  ሳሙኤል ወደ ራማ ሄደ፤ ሳኦልም በጊብዓ ወደሚገኘው ቤቱ አቀና። 35  ሳሙኤልም ለሳኦል እጅግ አዘነ፤+ እስከ ዕለተ ሞቱም ድረስ ሳኦልን ዳግመኛ አላየውም። ይሖዋም ሳኦልን በእስራኤል ላይ ንጉሥ በማድረጉ ተጸጸተ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “አትራራላቸው።”
ወይም “በደረቁ ወንዝ።”
ወይም “አዝኛለሁ።”
ወይም “ራሩላቸው።”
ቃል በቃል “ከተራፊም ሐውልቶች።” የቤት ውስጥ አማልክትን ወይም ጣዖታትን ያመለክታሉ።
ወይም “አይጸጸትም።”
ወይም “ይጸጸት።”
“እየተጀነነ” ማለትም ሊሆን ይችላል።