የዮሐንስ ወንጌል 21:1-25

  • ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠ (1-14)

  • ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደሚወደው አረጋገጠለት (15-19)

    • “ግልገሎቼን መግብ” (17)

  • ኢየሱስ የሚወደው ደቀ መዝሙር ወደፊት የሚያጋጥመው ሁኔታ (20-23)

  • መደምደሚያ (24, 25)

21  ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ* ባሕር እንደገና ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠ።* የተገለጠውም በዚህ መንገድ ነበር፤ 2  ስምዖን ጴጥሮስ፣ ዲዲሞስ* የሚባለው ቶማስ፣+ የገሊላ ቃና ሰው የሆነው ናትናኤል፣+ የዘብዴዎስ ልጆችና+ ሌሎች ሁለት ደቀ መዛሙርቱ አብረው ነበሩ። 3  ስምዖን ጴጥሮስ “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” አላቸው። እነሱም “እኛም አብረንህ እንሄዳለን” አሉት። ወጥተው ሄዱና ጀልባ ላይ ተሳፈሩ፤ በዚያ ሌሊት ግን አንድም ዓሣ አልያዙም።+ 4  ይሁን እንጂ ጎህ ሲቀድ ኢየሱስ መጥቶ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር።+ 5  ከዚያም ኢየሱስ “ልጆቼ፣ የሚበላ ነገር* አላችሁ?” አላቸው። እነሱም “የለንም!” ብለው መለሱለት። 6  እሱም “መረቡን ከጀልባዋ በስተ ቀኝ ጣሉት፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነሱም መረቡን ጣሉ፤ ከዓሣውም ብዛት የተነሳ መረቡን መጎተት አቃታቸው።+ 7  በዚህ ጊዜ፣ ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር+ ጴጥሮስን “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም ጌታ መሆኑን ሲሰማ ከወገቡ በላይ ራቁቱን* ስለነበር መደረቢያውን ለበሰና* ዘሎ ባሕሩ ውስጥ ገባ። 8  ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ ብዙም ሳይርቁ 90 ሜትር ገደማ* ርቀት ላይ ስለነበሩ በዓሣዎች የተሞላውን መረብ እየጎተቱ በትንሿ ጀልባ መጡ። 9  ወደ ባሕሩ ዳርቻ በደረሱ ጊዜ በከሰል ፍም ላይ የተቀመጠ ዓሣ እንዲሁም ዳቦ አዩ። 10  ኢየሱስ “አሁን ከያዛችሁት ዓሣ የተወሰነ አምጡ” አላቸው። 11  ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጀልባዋ ላይ ወጥቶ በትላልቅ ዓሣዎች የተሞላውን መረብ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ጎተተው፤ የዓሣዎቹም ብዛት 153 ነበር። መረቡ ይህን ያህል ብዙ ዓሣ ቢይዝም አልተቀደደም። 12  ኢየሱስ “ኑ፣ ቁርሳችሁን ብሉ” አላቸው። ጌታ መሆኑን አውቀው ስለነበር ከደቀ መዛሙርቱ መካከል “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው የደፈረ አልነበረም። 13  ኢየሱስም መጥቶ ዳቦውን አነሳና ሰጣቸው፤ ዓሣውንም አንስቶ እንዲሁ አደረገ። 14  ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ነበር።+ 15  ቁርስ በልተው ከጨረሱም በኋላ ኢየሱስ፣ ስምዖን ጴጥሮስን “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ ከእነዚህ አስበልጠህ ትወደኛለህ?” አለው። እሱም “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም “ጠቦቶቼን መግብ” አለው።+ 16  ደግሞም ለሁለተኛ ጊዜ “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ ትወደኛለህ?” አለው። እሱም “አዎ፣ ጌታ ሆይ፣ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” ሲል መለሰለት። ኢየሱስም “ግልገሎቼን ጠብቅ” አለው።+ 17  ለሦስተኛ ጊዜም “የዮሐንስ ልጅ ስምዖን፣ በጣም ትወደኛለህ?” አለው። ጴጥሮስ ለሦስተኛ ጊዜ “በጣም ትወደኛለህ?” ብሎ ስለጠየቀው አዘነ። በመሆኑም “ጌታ ሆይ፣ አንተ ሁሉን ታውቃለህ፤ በጣም እንደምወድህ ታውቃለህ” አለው። ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ “ግልገሎቼን መግብ።+ 18  እውነት እውነት እልሃለሁ፣ ወጣት ሳለህ ራስህ ለብሰህ ወደፈለግክበት ቦታ ትሄድ ነበር። ስታረጅ ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላ ሰውም ያለብስሃል፤ ወደማትፈልግበትም ቦታ ይወስድሃል።” 19  ይህን የተናገረው፣ ጴጥሮስ በምን ዓይነት አሟሟት አምላክን እንደሚያከብር ለማመልከት ነበር። ይህን ካለ በኋላ “እኔን መከተልህን ቀጥል” አለው።+ 20  ጴጥሮስ ዞር ሲል ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር+ ሲከተላቸው አየ፤ ይህ ደቀ መዝሙር ራት በበሉ ጊዜ ወደ ኢየሱስ ደረት ተጠግቶ “ጌታ ሆይ፣ አሳልፎ የሚሰጥህ ማን ነው?” ብሎ የጠየቀው ነው። 21  ጴጥሮስም ባየው ጊዜ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ፣ ይህስ ሰው ምን ይሆናል?” አለው። 22  ኢየሱስም “እኔ እስክመጣ ድረስ እንዲቆይ ብፈቅድ አንተ ምን ቸገረህ? አንተ እኔን መከተልህን ቀጥል” አለው። 23  በመሆኑም ይህ ደቀ መዝሙር አይሞትም የሚል ወሬ በወንድሞች መካከል ተሰራጨ። ይሁንና ኢየሱስ “እኔ እስክመጣ ድረስ እንዲቆይ ብፈቅድ አንተ ምን ቸገረህ?” አለው እንጂ አይሞትም አላለውም። 24  ስለ እነዚህ ነገሮች የሚመሠክረውና እነዚህን ነገሮች የጻፈው ይህ ደቀ መዝሙር ነው፤+ እሱ የሚሰጠው ምሥክርነትም እውነት እንደሆነ እናውቃለን። 25  እርግጥ ኢየሱስ ያደረጋቸው ሌሎች ብዙ ነገሮችም አሉ፤ እነዚህ ሁሉ በዝርዝር ቢጻፉ ዓለም ራሱ የተጻፉትን ጥቅልሎች ለማስቀመጥ የሚበቃ ቦታ የሚኖረው አይመስለኝም።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ማቴ 4:18 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ወይም “ታየ።”
ወይም “መንትያ።”
ወይም “ዓሣ።”
ወይም “ታጠቀና።”
ወይም “ከውስጥ በለበሳት ልብስ ብቻ።”
ቃል በቃል “200 ክንድ ገደማ።” ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።