የዮሐንስ ወንጌል 12:1-50

  • ማርያም በኢየሱስ እግር ላይ ዘይት አፈሰሰች (1-11)

  • ኢየሱስ እንደ ድል አድራጊ ሆኖ ገባ(12-19)

  • ኢየሱስ እንደሚሞት ተናገረ (20-37)

  • አይሁዳውያን እንደማያምኑ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ (38-43)

  • ኢየሱስ ዓለምን ለማዳን መጣ (44-50)

12  የፋሲካ በዓል ከመድረሱ ከስድስት ቀን በፊት ኢየሱስ፣ ከሞት ያስነሳው አልዓዛር+ ወደሚኖርባት ወደ ቢታንያ መጣ። 2  በዚያም የራት ግብዣ አዘጋጁለት፤ ማርታ ታገለግላቸው የነበረ+ ሲሆን አልዓዛር ግን ከእሱ ጋር ከሚበሉት አንዱ ነበር። 3  ከዚያም ማርያም ግማሽ ሊትር ገደማ* የሚሆን እጅግ ውድ የሆነና ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ይኸውም ንጹሕ ናርዶስ አምጥታ በኢየሱስ እግር ላይ አፈሰሰች፤ እግሩንም በፀጉሯ አብሳ አደረቀች። ቤቱም በዘይቱ መዓዛ ታወደ።+ 4  ሆኖም ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የሆነውና አሳልፎ የሚሰጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ+ እንዲህ አለ፦ 5  “ይህ ዘይት በ300 ዲናር* ተሸጦ ገንዘቡ ለድሆች ያልተሰጠው ለምንድን ነው?” 6  እንዲህ ያለው ግን ለድሆች አስቦ ሳይሆን ሌባ ስለነበረ ነው፤ የገንዘብ ሣጥኑን ይይዝ የነበረው እሱ በመሆኑ ወደ ሣጥኑ ከሚገባው ገንዘብ የመስረቅ ልማድ ነበረው። 7  በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ለቀብሬ ቀን ለማዘጋጀት+ ብላ ያደረገችው ስለሆነ ይህን ልማድ እንዳትፈጽም አትከልክሏት። 8  ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ናቸው፤+ እኔን ግን ሁልጊዜ አታገኙኝም።”+ 9  በዚህ ጊዜ ብዙ አይሁዳውያን ኢየሱስ እዚያ መኖሩን አውቀው መጡ፤ የመጡትም ኢየሱስን ለማየት ብቻ ሳይሆን እሱ ከሞት ያስነሳውን አልዓዛርንም ለማየት ነበር።+ 10  በመሆኑም የካህናት አለቆቹ አልዓዛርንም ለመግደል አሴሩ፤ 11  ምክንያቱም በእሱ የተነሳ ብዙ አይሁዳውያን ወደዚያ እየሄዱ በኢየሱስ ያምኑ ነበር።+ 12  በማግስቱም ወደ በዓሉ የመጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየመጣ መሆኑን ሰሙ። 13  በመሆኑም የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ሊቀበሉት ወጡ። እንዲህ እያሉም ይጮኹ ጀመር፦ “እንድታድነው እንለምንሃለን!* በይሖዋ* ስም የሚመጣው የእስራኤል ንጉሥ+ የተባረከ ነው!”+ 14  ኢየሱስ የአህያ ውርንጭላ አግኝቶ ተቀመጠበት፤+ ይህም የሆነው እንዲህ ተብሎ በተጻፈው መሠረት ነው፦ 15  “የጽዮን ልጅ ሆይ፣ አትፍሪ። እነሆ ንጉሥሽ በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ይመጣል።”+ 16  ደቀ መዛሙርቱ በመጀመሪያ እነዚህን ነገሮች አላስተዋሉም ነበር፤ ኢየሱስ ክብር በተጎናጸፈ ጊዜ+ ግን እነዚህ ነገሮች የተጻፉት ስለ እሱ እንደሆነና እነዚህን ነገሮች ለእሱ እንዳደረጉለት ትዝ አላቸው።+ 17  ኢየሱስ አልዓዛርን ከመቃብር ጠርቶ+ ከሞት ባስነሳበት ጊዜ አብረውት የነበሩት ሰዎች ስላዩት ነገር ይመሠክሩ ነበር።+ 18  ከዚህም የተነሳ ይህን ተአምራዊ ምልክት መፈጸሙን የሰማው ሕዝብ ሊቀበለው ወጣ። 19  ስለዚህ ፈሪሳውያን እርስ በርሳቸው “ምንም ማድረግ እንዳልቻልን አያችሁ! ተመልከቱ፣ ዓለሙ ሁሉ ግልብጥ ብሎ ተከትሎታል” ተባባሉ።+ 20  ለአምልኮ ወደ በዓሉ ከመጡት ሰዎች መካከል አንዳንድ ግሪካውያን ነበሩ። 21  እነሱም በገሊላ የምትገኘው የቤተሳይዳ ሰው ወደሆነው ወደ ፊልጶስ+ ቀርበው “ጌታ ሆይ፣ ኢየሱስን ማየት እንፈልጋለን” ብለው ጠየቁት። 22  ፊልጶስ መጥቶ ለእንድርያስ ነገረው። ከዚያም እንድርያስና ፊልጶስ መጥተው ለኢየሱስ ነገሩት። 23  ኢየሱስ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “የሰው ልጅ ክብር የሚያገኝበት ሰዓት ደርሷል።+ 24  እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አንዲት የስንዴ ዘር መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች አንድ ዘር ብቻ ሆና ትቀራለች፤ ከሞተች ግን+ ብዙ ፍሬ ታፈራለች። 25  ሕይወቱን የሚወድ ሁሉ* ያጠፋታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን* የሚጠላ+ ሁሉ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል።+ 26  እኔን ሊያገለግል የሚፈልግ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔ ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል።+ የሚያገለግለኝንም ሁሉ አብ ያከብረዋል። 27  አሁን ተጨንቄአለሁ፤*+ እንግዲህ ምን ማለት እችላለሁ? አባት ሆይ፣ ከዚህ ሰዓት አድነኝ።+ ይሁንና የመጣሁት ለዚህ ሰዓት ነው። 28  አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው።” በዚህ ጊዜ “ስሜን አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ”+ የሚል ድምፅ+ ከሰማይ መጣ። 29  በዚያ ቆመው የነበሩት ብዙ ሰዎች ድምፁን በሰሙ ጊዜ ‘ነጎድጓድ ነው’ አሉ። ሌሎች ደግሞ “መልአክ አናገረው” አሉ። 30  ኢየሱስ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ይህ ድምፅ የተሰማው ለእኔ ሳይሆን ለእናንተ ሲባል ነው። 31  ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህ ዓለም ገዢ+ አሁን ይባረራል።+ 32  እኔ ግን ከምድር ወደ ላይ ከፍ ከተደረግኩ+ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ወደ ራሴ እስባለሁ።” 33  ይህን የተናገረው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምን ዓይነት አሟሟት እንደሚሞት ለማመልከት ነው።+ 34  በዚህ ጊዜ ሕዝቡ “ክርስቶስ ለዘላለም እንደሚኖር ከሕጉ ሰምተናል።+ ታዲያ አንተ የሰው ልጅ ከፍ ማለት አለበት እንዴት ትላለህ?+ ይህ የሰው ልጅ ማን ነው?” ብለው መለሱለት። 35  ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “ብርሃኑ ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ይቆያል። ጨለማ እንዳይውጣችሁ ብርሃኑ እያለላችሁ በብርሃን ሂዱ፤ በጨለማ የሚሄድ ሁሉ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም።+ 36  የብርሃን ልጆች+ እንድትሆኑ ብርሃኑ እያለላችሁ በብርሃኑ እመኑ።” ኢየሱስ ይህን ተናግሮ እንደጨረሰ ሄደ፤ ከእነሱም ተሰወረ። 37  በፊታቸው ብዙ ተአምራዊ ምልክቶች ቢፈጽምም በእሱ አላመኑም፤ 38  ይህም ነቢዩ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል የተናገረው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው፦ “ይሖዋ* ሆይ፣ ከእኛ የሰማውን* ነገር ያመነ ማን ነው?+ የይሖዋስ* ክንድ ለማን ተገለጠ?”+ 39  ደግሞም ኢሳይያስ ሊያምኑ ያልቻሉበትን ምክንያት እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ 40  “በዓይናቸው አይተውና በልባቸው አስተውለው እንዳይመለሱና እንዳይፈውሳቸው ዓይናቸውን አሳውሯል፤ ልባቸውንም አደንድኗል።”+ 41  ኢሳይያስ ይህን የተናገረው ክብሩን ስላየ ነው፤ ስለ እሱም ተናገረ።+ 42  ያም ሆኖ ከገዢዎችም እንኳ ሳይቀር ብዙዎች በእሱ አመኑ፤+ ይሁንና ፈሪሳውያን ከምኩራብ እንዳያባርሯቸው ስለፈሩ በእሱ ማመናቸውን በግልጽ አይናገሩም ነበር፤+ 43  ይህም የሆነው ከሰው የሚገኘውን ክብር ከአምላክ ከሚገኘው ክብር አስበልጠው ስለወደዱ ነው።+ 44  ይሁን እንጂ ኢየሱስ ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ “በእኔ የሚያምን ሁሉ በእኔ ብቻ ሳይሆን በላከኝም ጭምር ያምናል፤+ 45  እኔን የሚያይ ሁሉ የላከኝንም ያያል።+ 46  በእኔ የሚያምን ሁሉ በጨለማ እንዳይኖር+ ብርሃን ሆኜ ወደ ዓለም መጥቻለሁ።+ 47  ይሁንና ማንም ቃሌን ሰምቶ የማይጠብቅ ከሆነ የምፈርድበት እኔ አይደለሁም፤ እኔ የመጣሁት ዓለምን ለማዳን እንጂ በዓለም ላይ ለመፍረድ አይደለምና።+ 48  እኔን የሚንቀውንና ቃሌን የማይቀበለውን ሁሉ የሚፈርድበት አለ። በመጨረሻው ቀን የሚፈርድበት የተናገርኩት ቃል ነው። 49  እኔ የተናገርኩት በራሴ ተነሳስቼ አይደለምና፤ ከዚህ ይልቅ ምን እንደምልና ምን እንደምናገር ያዘዘኝ የላከኝ አብ ራሱ ነው።+ 50  ደግሞም የእሱ ትእዛዝ የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝ አውቃለሁ።+ ስለዚህ ምንጊዜም የምናገረው ልክ አባቴ በነገረኝ መሠረት ነው።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ክብደቱ አንድ የሮማውያን ፓውንድ ሲሆን 327 ግራም ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ግሪክኛ፣ ሆሳዕና።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ነፍሱን የሚወድ ሁሉ።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ነፍሴ ተጨንቃለች።”
ወይም “እኛ የተናገርነውን።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።