የያዕቆብ ደብዳቤ 4:1-17

  • የዓለም ወዳጅ አትሁኑ (1-12)

    • ‘ዲያብሎስን ተቃወሙት’ (7)

    • “ወደ አምላክ ቅረቡ” (8)

  • ጉራ በመንዛት አትኩራሩ (13-17)

    • “ይሖዋ ከፈቀደ” (15)

4  በእናንተ መካከል ያለው ጦርነትና ጠብ ከየት የመጣ ነው? በውስጣችሁ* ከሚዋጉት ሥጋዊ ፍላጎቶቻችሁ የመነጨ አይደለም?+ 2  ትመኛላችሁ ሆኖም አታገኙም። ትገድላላችሁ እንዲሁም ትጎመጃላችሁ፤* ይሁንና ማግኘት አትችሉም። ትጣላላችሁ እንዲሁም ትዋጋላችሁ።+ ስለማትጠይቁም አታገኙም። 3  በምትጠይቁበት ጊዜም አታገኙም፤ ምክንያቱም የምትጠይቁት ለተሳሳተ ዓላማ ይኸውም ሥጋዊ ፍላጎታችሁን ለማርካት ነው። 4  አመንዝሮች ሆይ፣* ከዓለም ጋር መወዳጀት ከአምላክ ጋር ጠላትነት መፍጠር እንደሆነ አታውቁም? ስለዚህ የዓለም ወዳጅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ራሱን የአምላክ ጠላት ያደርጋል።+ 5  ወይስ ቅዱስ መጽሐፉ “በውስጣችን ያደረው መንፈስ በቅናት ሁልጊዜ ይመኛል” ያለው ያለምክንያት ይመስላችኋል?+ 6  ይሁን እንጂ አምላክ የሚሰጠው ጸጋ እንዲህ ካለው መንፈስ የላቀ ነው። በመሆኑም ቅዱስ መጽሐፉ “አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤+ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል።+ 7  ስለዚህ ራሳችሁን ለአምላክ አስገዙ፤+ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤+ እሱም ከእናንተ ይሸሻል።+ 8  ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።+ እናንተ ኃጢአተኞች እጆቻችሁን አንጹ፤+ እናንተ ወላዋዮች ልባችሁን አጥሩ።+ 9  ተጨነቁ፣ እዘኑ፣ አልቅሱ።+ ሳቃችሁ ወደ ሐዘን፣ ደስታችሁም ወደ ተስፋ መቁረጥ ይለወጥ። 10  በይሖዋ* ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤+ እሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል።+ 11  ወንድሞች፣ አንዳችሁ ሌላውን መንቀፋችሁን ተዉ።+ ወንድሙን የሚነቅፍ ወይም በወንድሙ ላይ የሚፈርድ ሁሉ ሕግን ይነቅፋል እንዲሁም በሕግ ላይ ይፈርዳል። በሕግ ላይ የምትፈርድ ከሆነ ደግሞ ፈራጅ ነህ እንጂ ሕግን ፈጻሚ አይደለህም። 12  ሕግ የሚሰጥና የሚፈርድ አንድ ብቻ ነው፤+ እሱ ማዳንም ሆነ ማጥፋት ይችላል።+ ታዲያ በባልንጀራህ* ላይ የምትፈርድ አንተ ማን ነህ?+ 13  እንግዲህ እናንተ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ከተማ እንሄዳለን፤ እዚያም ዓመት እንቆያለን፤ እንነግዳለን እንዲሁም እናተርፋለን” የምትሉ ስሙ፤+ 14  ሕይወታችሁ ነገ ምን እንደሚሆን እንኳ አታውቁም።+ ለጥቂት ጊዜ ታይቶ እንደሚጠፋ እንፋሎት ናችሁና።+ 15  ከዚህ ይልቅ “ይሖዋ* ከፈቀደ+ በሕይወት እንኖራለን፤ ደግሞም ይህን ወይም ያን እናደርጋለን” ማለት ይገባችኋል። 16  አሁን ግን እናንተ ከልክ በላይ ጉራ በመንዛት ትኩራራላችሁ። እንዲህ ያለው ጉራ ሁሉ ክፉ ነው። 17  ስለዚህ አንድ ሰው ትክክል የሆነውን ነገር እንዴት ማድረግ እንዳለበት እያወቀ ሳያደርገው ቢቀር ኃጢአት ይሆንበታል።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ።”
ወይም “ትቀናላችሁ።”
ወይም “እናንተ ከዳተኞች።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።