ዘዳግም 17:1-20
17 “እንከን ወይም ማንኛውም ዓይነት ጉድለት ያለበትን በሬ ወይም በግ ለአምላክህ ለይሖዋ አትሠዋ፤ ምክንያቱም ይህ ለአምላክህ ለይሖዋ አስጸያፊ ነው።+
2 “አምላክህ ይሖዋ ከሚሰጥህ ከተሞች በአንዱ ውስጥ በአምላክህ በይሖዋ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር የሚፈጽምና ቃል ኪዳኑን የሚያፈርስ ወንድ ወይም ሴት ቢገኝ+
3 እሱም ሄዶ ሌሎች አማልክትን በማምለክ እንዲሁም ለእነሱ ወይም ለፀሐይ አሊያም ለጨረቃ ወይም ደግሞ ለሰማይ ሠራዊት በሙሉ በመስገድ+ እኔ ያላዘዝኩትን ነገር ቢያደርግ+
4 አንተም ይህ ነገር ቢነገርህ ወይም ሁኔታውን ብትሰማ ጉዳዩን በጥንቃቄ አጣራ። ይህ አስጸያፊ ነገር በእስራኤል ውስጥ መፈጸሙ እውነት እንደሆነ ቢረጋገጥ+
5 እንዲህ ያለ መጥፎ ድርጊት የፈጸመውን ያንን ሰው ወይም ያቺን ሴት ወደ ከተማዋ በር አውጣቸው፤ ከዚያም ሰውየው ወይም ሴትየዋ እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ይወገሩ።+
6 ሞት የሚገባው ሰው ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች በሚሰጡት ምሥክርነት*+ ይገደል። አንድ ምሥክር በሚሰጠው ቃል ብቻ መገደል የለበትም።+
7 እሱን ለመግደል መጀመሪያ እጃቸውን የሚያነሱት ምሥክሮቹ መሆን ይኖርባቸዋል፤ ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ እጁን ያንሳበት። ክፉ የሆነውን ከመካከልህ አስወግድ።+
8 “ከከተሞችህ በአንዱ ውስጥ ለመዳኘት አስቸጋሪ የሆነ ክርክር ቢነሳ ለምሳሌ፣ ጉዳዩ ደም ማፍሰስን+ የሚመለከትም ይሁን ለሕግ አቤቱታ ማቅረብን ወይም የዓመፅ ድርጊትን አሊያም ሌሎች አለመግባባቶችን የሚመለከት ቢሆን ተነስተህ አምላክህ ይሖዋ ወደሚመርጠው ስፍራ ውጣ።+
9 ወደ ሌዋውያን ካህናትና በዚያን ጊዜ ዳኛ ሆኖ ወደሚያገለግለው ሰው+ ሄደህ ጠይቅ፤ እነሱም ውሳኔውን ይነግሩሃል።+
10 አንተም እነዚህ ሰዎች ይሖዋ በሚመርጠው ስፍራ ሆነው በነገሩህ ውሳኔ መሠረት እርምጃ ውሰድ። የሰጡህንም መመሪያ በሙሉ በጥንቃቄ ፈጽም።
11 በሚሰጡህ ሕግና በሚነግሩህ ውሳኔ መሠረት እርምጃ ውሰድ።+ እነሱ ካሳለፉት ውሳኔ ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አትበል።+
12 አምላክህን ይሖዋን የሚያገለግለውን ካህን ወይም ዳኛውን ባለመስማት እብሪተኛ የሚሆን ሰው ካለ ይገደል።+ ክፉ የሆነውን ከእስራኤል መካከል አስወግድ።+
13 ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲሰማ ይፈራል፤ ከእንግዲህም የእብሪት ድርጊት አይፈጽምም።+
14 “አምላክህ ይሖዋ የሚሰጥህን ምድር ገብተህ ከወረስካት በኋላ በዚያ መኖር ስትጀምር ‘በዙሪያዬ እንዳሉት ብሔራት ሁሉ እኔም በላዬ ላይ ንጉሥ ላንግሥ’ ብትል+
15 አምላክህ ይሖዋ የሚመርጠውን ንጉሥ ታነግሣለህ። የምታነግሠውም ንጉሥ ከወንድሞችህ መካከል መሆን ይኖርበታል።+ ወንድምህ ያልሆነን ባዕድ ሰው በላይህ ላይ ማንገሥ አይገባህም።
16 ይሁን እንጂ ንጉሡ ለራሱ ፈረሶች ማብዛት+ ወይም የፈረሶቹን ቁጥር ለመጨመር ሲል ሕዝቡ ወደ ግብፅ እንዲመለስ ማድረግ የለበትም፤+ ምክንያቱም ይሖዋ ‘በዚህ መንገድ ፈጽሞ ዳግመኛ እንዳትመለሱ’ ብሏችኋል።
17 ልቡ ከትክክለኛው መንገድ ዞር እንዳይል ለራሱ ሚስቶች አያብዛ፤+ ለራሱም ብርና ወርቅ አያከማች።+
18 በመንግሥቱ ዙፋን ላይ በሚቀመጥበትም ጊዜ በሌዋውያን ካህናት እጅ ካለው ላይ ወስዶ የዚህን ሕግ ቅጂ ለራሱ በመጽሐፍ* ላይ ይጻፍ።+
19 “አምላኩን ይሖዋን መፍራትን እንዲማር እንዲሁም በዚህ ሕግና በእነዚህ ሥርዓቶች ላይ የሰፈሩትን ቃላት በሙሉ በመፈጸም እንዲጠብቃቸው ይህ መጽሐፍ ከእሱ ጋር ይሁን፤+ በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ያንብበው።+
20 ይህን ካደረገ ልቡ በወንድሞቹ ላይ አይታበይም፤ ከትእዛዛቱም ወደ ቀኝም ሆነ ወደ ግራ ዞር አይልም፤ ይህም እሱም ሆነ ልጆቹ በእስራኤል መካከል በመንግሥቱ ላይ ረጅም ዘመን እንዲቆዩ ያስችላቸዋል።