ዘካርያስ 7:1-14

  • ይሖዋ ልባዊ ያልሆነን ጾም ያወግዛል (1-14)

    • “ትጾሙ የነበረው በእርግጥ ለእኔ ነበር?” (5)

    • ‘አንዳችሁ ለሌላው ፍትሕ፣ ታማኝ ፍቅርና ምሕረት አሳዩ’ (9)

7  ንጉሥ ዳርዮስ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ኪስሌው* በተባለው በዘጠነኛው ወር፣ ከወሩም በአራተኛው ቀን የይሖዋ ቃል ወደ ዘካርያስ መጣ።+ 2  የቤቴል ሰዎች ይሖዋ ሞገስ እንዲያሳያቸው ለመለመን ሳሬጸርንና ረጌምሜሌክን ከሰዎቹ ጋር ላኩ፤   3  እነሱም የሠራዊት ጌታን የይሖዋን ቤት* ካህናትና ነቢያቱን “ለብዙ ዓመታት እንዳደረግኩት በአምስተኛው ወር ማልቀስና+ መጾም ይኖርብኛል?” ብለው ጠየቁ። 4  የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ እኔ መጣ፦ 5  “ለምድሪቱ ነዋሪዎች ሁሉና ለካህናቱ እንዲህ በላቸው፦ ‘ለ70 ዓመታት+ በአምስተኛውና በሰባተኛው ወር ስትጾሙና ዋይ ዋይ ስትሉ፣+ ትጾሙ የነበረው በእርግጥ ለእኔ ነበር? 6  ትበሉና ትጠጡ በነበረበት ጊዜስ ትበሉና ትጠጡ የነበረው ለራሳችሁ አልነበረም? 7  ኢየሩሳሌምና በዙሪያዋ ያሉት ከተሞቿ በሰዎች ተሞልተውና ሰላም ሰፍኖባቸው በነበረበት ጊዜ እንዲሁም ሰዎች በኔጌብና በሸፌላ ይኖሩ በነበረበት ወቅት ይሖዋ በቀድሞዎቹ ነቢያት አማካኝነት ያወጀውን ቃል መታዘዝ አልነበረባችሁም?’”+ 8  የይሖዋ ቃል እንዲህ ሲል ዳግመኛ ወደ ዘካርያስ መጣ፦ 9  “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘በእውነተኛ ፍትሕ ላይ ተመሥርታችሁ ፍረዱ፤+ አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ፍቅርና+ ምሕረት አሳዩ። 10  መበለቲቱንም ሆነ አባት የሌለውን ልጅ፣*+ ከባዕድ አገር የመጣውን ሰውም+ ሆነ ድሃውን አታታሉ፤+ ደግሞም አንዳችሁ በሌላው ላይ ክፉ ለማድረግ በልባችሁ አታሲሩ።’+ 11  እነሱ ግን ለመስማት ፈቃደኛ አልሆኑም፤+ በግትርነትም ጀርባቸውን ሰጡ፤+ ላለመስማትም ሲሉ ጆሯቸውን ደፈኑ።+ 12  ልባቸውን እንደ አልማዝ* አጠነከሩ፤+ እንዲሁም የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት፣ በቀድሞዎቹ ነቢያት በኩል የላከውን ሕግና* ቃል አልታዘዙም።+ ከዚህም የተነሳ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እጅግ ተቆጣ።”+ 13  “‘እኔ ስጠራቸው እንዳልሰሙኝ ሁሉ+ እነሱ ሲጣሩም አልሰማቸውም’+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። 14  ‘ደግሞም ወደማያውቋቸው ብሔራት ሁሉ በአውሎ ነፋስ በተንኳቸው፤+ ምድሪቱም ትተዋት ከሄዱ በኋላ ባድማ ሆነች፤ በእሷ የሚያልፍ ወይም ወደ እሷ የሚመለስ ማንም የለም፤+ የተወደደችውን ምድር አስፈሪ ቦታ አድርገዋታልና።’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
ወይም “ወላጅ አልባ የሆነውን ልጅ።”
“እንደ ጠንካራ ድንጋይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “መመሪያና፤ ትምህርትና።”