ዘካርያስ 10:1-12

  • ዝናብ ለማግኘት የሐሰት አማልክትን ሳይሆን ይሖዋን ጠይቁ (1, 2)

  • ይሖዋ ሕዝቡን አንድ ያደርጋል (3-12)

    • ከይሁዳ ቤት ቁልፍ የሆነ ሰው ይወጣል (3, 4)

10  “በበልግ ዝናብ ወቅት ይሖዋ ዝናብ እንዲያዘንብላችሁ ጠይቁ። ነጎድጓድ የቀላቀለ ደመና የሚያመጣው፣ለሰዎች ዝናብ የሚያዘንበው፣+ለእያንዳንዱም በሜዳ ላይ የሚበቅለውን ተክል የሚሰጠው ይሖዋ ነው።  2  የተራፊም ምስሎች* አታላይ ነገር* ተናግረዋልና፤ሟርተኞችም የሐሰት ራእይ አይተዋል። ከንቱ ስለሆኑ ሕልሞች ይናገራሉ፤በከንቱም ሊያጽናኑ ይሞክራሉ። ከዚህም የተነሳ ሕዝቡ እንደ በግ ይቅበዘበዛል። እረኛ ስለሌለ ይሠቃያል።  3  በእረኞቹ ላይ ቁጣዬ ይነዳል፤ጨቋኞቹንም መሪዎች* ተጠያቂ አደርጋቸዋለሁ፤የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ትኩረቱን ወደ መንጋው፣ ወደ ይሁዳ ቤት አዙሯልና፤+ግርማ ሞገስ እንደተላበሰው የጦር ፈረሱ እነሱንም ግርማ ሞገስ አላብሷቸዋል።  4  ከእሱ ቁልፍ የሆነ ሰው፣*ድጋፍ የሚሰጥ ገዢና*የጦርነት ቀስት ይወጣል፤ተቆጣጣሪዎች* ሁሉ፣ እያንዳንዳቸው ከእሱ ይወጣሉ።  5  እነሱም በጦርነት ጊዜ፣በመንገድ ላይ ያለን ጭቃ እንደሚረግጡ ተዋጊዎች ይሆናሉ። ይሖዋ ከእነሱ ጋር ስለሆነ ይዋጋሉ፤+የጠላት ፈረሰኞችም ኀፍረት ይከናነባሉ።+  6  የይሁዳን ቤት ከሁሉ የላቀ አደርጋለሁ፤የዮሴፍንም ቤት አድናለሁ።+ ምሕረት ስለማሳያቸው+ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ እመልሳቸዋለሁ፤እነሱም ፈጽሞ እንዳልጣልኳቸው ሰዎች ይሆናሉ፤+እኔ ይሖዋ አምላካቸው ነኝና፤ ደግሞም እመልስላቸዋለሁ።  7  የኤፍሬም ሰዎች እንደ ኃያል ተዋጊ ይሆናሉ፤ልባቸውም የወይን ጠጅ እንደጠጣ ሰው ሐሴት ያደርጋል።+ ልጆቻቸው ይህን አይተው ሐሴት ያደርጋሉ፤ልባቸውም በይሖዋ ደስ ይለዋል።+  8  ‘አፏጭቼ አንድ ላይ እሰበስባቸዋለሁ፤እዋጃቸዋለሁና፣+ ብዙ ይሆናሉ፤መባዛታቸውንም ይቀጥላሉ።  9  በሕዝቦች መካከል እንደ ዘር ብበትናቸውም፣በሩቅ ስፍራዎች ሆነው ያስታውሱኛል፤ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ያንሰራራሉ፤ ደግሞም ይመለሳሉ። 10  ከግብፅ ምድር መልሼ አመጣቸዋለሁ፤ከአሦርም አንድ ላይ እሰበስባቸዋለሁ፤+ወደ ጊልያድ+ ምድርና ወደ ሊባኖስ አመጣቸዋለሁ፤በቂ ስፍራም አይገኝላቸውም።+ 11  እሱም ባሕሩን አስጨንቆ ያልፋል፤በባሕሩም ውስጥ ሞገዱን ይመታል፤+የአባይ ጥልቆች በሙሉ ይደርቃሉ። የአሦር ኩራት ይዋረዳል፤የግብፅም በትረ መንግሥት ይወገዳል።+ 12  በይሖዋ ብርቱ አደርጋቸዋለሁ፤+በስሙም ይሄዳሉ’+ ይላል ይሖዋ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የቤት ውስጥ አማልክት፤ ጣዖታት።”
ወይም “ምትሃታዊ ነገር፤ አስማታዊ ነገር።”
ቃል በቃል “አውራ ፍየሎች።”
ቃል በቃል “የማዕዘን ማማ።” ወሳኝ የሆነን ወይም ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ሰው ያመለክታል፤ አለቃ።
ቃል በቃል “ማንጠልጠያና።” ድጋፍ የሚሰጥን ሰው ያመለክታል፤ ገዢ።
ወይም “አሠሪዎች።”