ዘኁልቁ 4:1-49

  • ቀአታውያን የሚያከናውኑት አገልግሎት (1-20)

  • ጌድሶናውያን የሚያከናውኑት አገልግሎት (21-28)

  • ሜራራውያን የሚያከናውኑት አገልግሎት (29-33)

  • የቆጠራው ውጤት (34-49)

4  ይሖዋም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 2  “ከሌዊ ልጆች መካከል የቀአትን ወንዶች ልጆች+ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች መሠረት ቁጠሩ፤ 3  በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ እንዲሠራ በተመደበው ቡድን ውስጥ ያሉትን ዕድሜያቸው ከ30+ እስከ 50 ዓመት+ የሆኑትን ሁሉ ቁጠሩ።+ 4  “የቀአት ወንዶች ልጆች በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ የሚያከናውኑት አገልግሎት ይህ ነው።+ ይህ እጅግ ቅዱስ የሆነ ነገር ነው፦ 5  ሰፈሩ በሚነሳበት ጊዜ አሮንና ወንዶች ልጆቹ መጥተው ታቦቱን+ የሚከልለውን መጋረጃ+ ያወርዱታል፤ የምሥክሩንም ታቦት በእሱ ይሸፍኑታል። 6  በላዩም ላይ ከአቆስጣ ቆዳ የተሠራ መሸፈኛ ይደርቡበታል፤ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ሰማያዊ የሆነ ጨርቅ ያለብሱታል፤ ለመሸከሚያ የሚያገለግሉትንም መሎጊያዎች+ በቦታቸው ላይ ያደርጓቸዋል። 7  “ገጸ ኅብስቱ የሚቀመጥበትንም ጠረጴዛ+ ሰማያዊ ጨርቅ ያለብሱታል፤ በላዩም ላይ ሳህኖቹን፣ ጽዋዎቹን፣ ጎድጓዳ ሳህኖቹንና ለመጠጥ መባ የሚሆኑትን ማንቆርቆሪያዎች ያስቀምጣሉ፤+ የዘወትሩም የቂጣ መባ+ ከላዩ ላይ አይነሳ። 8  ደማቅ ቀይ ጨርቅ ያለብሷቸዋል፤ ከአቆስጣ ቆዳ የተሠራ መሸፈኛም ይደርቡበታል፤ እንዲሁም ለመሸከሚያ የሚያገለግሉትን መሎጊያዎች+ በቦታቸው ላይ ያደርጓቸዋል። 9  ከዚያም ሰማያዊ ጨርቅ ወስደው የመብራቱን መቅረዝ+ ከመብራቶቹ፣+ ከመቆንጠጫዎቹና ከመኮስተሪያዎቹ+ እንዲሁም ዘወትር ዘይት እንዲኖር ለማድረግ ከሚያገለግሉት ዘይት የሚቀመጥባቸው ዕቃዎች ሁሉ ጋር ይሸፍኑታል። 10  መቅረዙን ከዕቃዎቹ ሁሉ ጋር ከአቆስጣ ቆዳ በተሠራ መሸፈኛ ይጠቀልሉታል፤ በመሸከሚያ ሳንቃ ላይም ያስቀምጡታል። 11  የወርቁን መሠዊያም+ ሰማያዊ ጨርቅ ያለብሱታል፤ ከአቆስጣ ቆዳ የተሠራ መሸፈኛም ይደርቡበታል፤ ለመሸከሚያ የሚያገለግሉትንም መሎጊያዎች+ በቦታቸው ላይ ያደርጓቸዋል። 12  ከዚያም በቅዱሱ ስፍራ ዘወትር የሚጠቀሙባቸውን መገልገያ ዕቃዎች በሙሉ+ ወስደው በሰማያዊ ጨርቅ ይጠቀልሏቸዋል፤ ከአቆስጣ ቆዳ የተሠራ መሸፈኛም ይደርቡባቸዋል፤ በመሸከሚያ ሳንቃ ላይም ያስቀምጧቸዋል። 13  “አመዱን* ከመሠዊያው ላይ ያስወግዱ፤+ መሠዊያውንም ሐምራዊ የሱፍ ጨርቅ ያልብሱት። 14  እንዲሁም በመሠዊያው ላይ ለማገልገል የሚጠቀሙባቸውን ዕቃዎች በሙሉ ይኸውም መኮስተሪያዎቹን፣ ሹካዎቹን፣ አካፋዎቹን፣ ጎድጓዳ ሳህኖቹንና የመሠዊያውን ዕቃዎች በሙሉ በላዩ ላይ ያደርጉበታል፤+ ከአቆስጣ ቆዳ የተሠራ መሸፈኛም ይደርቡበታል፤ ለመሸከሚያ የሚያገለግሉትንም መሎጊያዎች+ በቦታቸው ላይ ያደርጓቸዋል። 15  “አሮንና ወንዶች ልጆቹ ሰፈሩ ከመነሳቱ በፊት በቅዱሱ ስፍራ ያሉትን ነገሮችና የቅዱሱን ስፍራ ዕቃዎች በሙሉ ሸፍነው መጨረስ አለባቸው።+ ከዚያም የቀአት ወንዶች ልጆች ለመሸከም ይመጣሉ፤+ ሆኖም በቅዱሱ ስፍራ ያሉትን ነገሮች መንካት የለባቸውም፤ ከነኩ ግን ይሞታሉ።+ ከመገናኛ ድንኳኑ ጋር በተያያዘ እነዚህን ነገሮች የማከናወኑ ኃላፊነት* የተጣለው በቀአት ወንዶች ልጆች ላይ ነው። 16  “የመብራቱን ዘይት፣+ ጥሩ መዓዛ ያለውን ዕጣን፣+ ዘወትር የሚቀርበውን የእህል መባና የቅብዓት ዘይቱን+ የመቆጣጠሩ ኃላፊነት የካህኑ የአሮን ልጅ የአልዓዛር+ ነው። ቅዱሱን ስፍራና ዕቃዎቹን ጨምሮ የማደሪያ ድንኳኑን ሁሉና በውስጡ ያለውን ነገር በሙሉ የመቆጣጠሩ ኃላፊነት የእሱ ነው።” 17  በተጨማሪም ይሖዋ ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 18  “የቀአታውያን+ ቤተሰቦች ነገድ ከሌዋውያን መካከል ተለይቶ እንዲጠፋ አታድርጉ። 19  እጅግ ቅዱስ ወደሆኑት ነገሮች+ በመቅረባቸው የተነሳ እንዳይሞቱ፣ ከዚህ ይልቅ በሕይወት እንዲኖሩ ይህን አድርጉላቸው። አሮንና ወንዶች ልጆቹ ገብተው ለእያንዳንዳቸው ሥራቸውንና የሚሸከሙትን ነገር ይመድቡላቸው። 20  ቅዱስ የሆኑትን ነገሮች ለአፍታ እንኳ ገብተው ማየት የለባቸውም፤ ካዩ ግን ይሞታሉ።”+ 21  ከዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ 22  “የጌድሶንን ወንዶች ልጆች+ በየአባቶቻቸው ቤቶችና በየቤተሰባቸው ቁጠር። 23  በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ እንዲያገለግል በተመደበው ቡድን ውስጥ ያሉትን ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 50 ዓመት የሆኑትን ሁሉ መዝግብ። 24  የጌድሶናውያን ቤተሰቦች እንዲንከባከቡና እንዲሸከሙ+ የተመደቡት እነዚህን ነገሮች ነው፦ 25  እነሱም የማደሪያ ድንኳኑን የድንኳን ጨርቆች፣+ የመገናኛ ድንኳኑን ጨርቆች፣ መደረቢያውንና ከእሱ በላይ ያለውን ከአቆስጣ ቆዳ የተሠራ መደረቢያ+ እንዲሁም የመገናኛ ድንኳኑን መግቢያ መከለያ*+ ይሸከማሉ፤ 26  በተጨማሪም የግቢውን መጋረጃዎች፣+ በማደሪያ ድንኳኑና በመሠዊያው ዙሪያ ባለው ግቢ መግቢያ ላይ የሚገኘውን መከለያ፣*+ የድንኳን ገመዶቻቸውንና ዕቃዎቻቸውን በሙሉ እንዲሁም ለአገልግሎቱ የሚውሉትን ነገሮች ሁሉ ይሸከማሉ። የሥራ ምድባቸው ይህ ነው። 27  ጌድሶናውያን+ የሚያከናውኑትን አገልግሎትና የሚሸከሟቸውን ነገሮች ሁሉ የሚቆጣጠሩት አሮንና ወንዶች ልጆቹ ናቸው፤ እነዚህን ነገሮች ሁሉ የመሸከሙን ኃላፊነት ለእነሱ ትሰጣቸዋለህ። 28  የጌድሶናውያን ቤተሰቦች በመገናኛ ድንኳኑ ውስጥ የሚያከናውኑት አገልግሎት ይህ ነው፤+ ኃላፊነታቸውንም የሚወጡት በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር+ አመራር ሥር ሆነው ነው። 29  “የሜራሪን ወንዶች ልጆችም+ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት ትመዘግባቸዋለህ። 30  በመገናኛ ድንኳኑ እንዲያገለግል በተመደበው ቡድን ውስጥ ያሉትን ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 50 ዓመት የሆኑትን ሁሉ ትመዘግባለህ። 31  በመገናኛ ድንኳኑ ከሚያከናውኑት አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ነገሮች የመሸከም ኃላፊነት+ ተጥሎባቸዋል፦ የማደሪያ ድንኳኑን ቋሚዎች፣+ አግዳሚ እንጨቶቹን፣+ ዓምዶቹን፣+ መሰኪያዎቹን፣+ 32  በግቢው ዙሪያ ያሉትን ቋሚዎች፣+ መሰኪያዎቻቸውን፣+ የድንኳን ካስማዎቻቸውን፣+ የድንኳን ገመዶቻቸውን እንዲሁም ቁሳቁሶቻቸውንና ከዚህ አገልግሎት ጋር የተያያዙትን ነገሮች ሁሉ ይሸከማሉ። በኃላፊነት የሚሸከሙትንም ዕቃ በስም ጠቅሰህ ትመድብላቸዋለህ። 33  የሜራሪ ወንዶች ልጆች ቤተሰቦች+ በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታምር አመራር ሥር ሆነው በመገናኛ ድንኳኑ የሚያገለግሉት በዚህ መሠረት ነው።”+ 34  ከዚያም ሙሴ፣ አሮንና የማኅበረሰቡ አለቆች+ የቀአታውያንን ወንዶች ልጆች+ በየቤተሰቦቻቸውና በየአባቶቻቸው ቤት መዘገቡ፤ 35  በመገናኛ ድንኳኑ እንዲያገለግል በተመደበው ቡድን ውስጥ ያሉትን ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 50 ዓመት የሆኑትን ሁሉ መዘገቡ።+ 36  በየቤተሰባቸው የተመዘገቡትም በአጠቃላይ 2,750 ነበሩ።+ 37  ከቀአታውያን ቤተሰቦች መካከል የተመዘገቡትና በመገናኛ ድንኳኑ የሚያገለግሉት በአጠቃላይ እነዚህ ነበሩ። ሙሴና አሮንም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት መዘገቧቸው።+ 38  የጌድሶን ወንዶች ልጆችም+ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት ተመዘገቡ፤ 39  በመገናኛ ድንኳኑ እንዲያገለግል በተመደበው ቡድን ውስጥ ያሉት ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 50 ዓመት የሆኑት ሁሉ ተመዘገቡ። 40  በየቤተሰቦቻቸውና በየአባቶቻቸው ቤት የተመዘገቡት በአጠቃላይ 2,630 ነበሩ።+ 41  በመገናኛ ድንኳኑ እንዲያገለግሉ የተመዘገቡት የጌድሶን ወንዶች ልጆች ቤተሰቦች በአጠቃላይ እነዚህ ነበሩ። ሙሴና አሮንም ይሖዋ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት መዘገቧቸው።+ 42  የሜራሪ ወንዶች ልጆች በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤት ተመዘገቡ፤ 43  በመገናኛ ድንኳኑ እንዲያገለግል በተመደበው ቡድን ውስጥ ያሉት ዕድሜያቸው ከ30 እስከ 50 ዓመት የሆኑት ሁሉ ተመዘገቡ።+ 44  ከእነሱ መካከል በየቤተሰባቸው የተመዘገቡት በአጠቃላይ 3,200 ነበሩ።+ 45  ሙሴና አሮን ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት የመዘገቧቸው የሜራሪ ወንዶች ልጆች ቤተሰቦች እነዚህ ነበሩ።+ 46  ሙሴ፣ አሮንና የእስራኤል አለቆች እነዚህን ሌዋውያን ሁሉ በየቤተሰባቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች መዘገቧቸው፤ 47  እነሱም ከ30 እስከ 50 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ሁሉም ከመገናኛ ድንኳኑ ጋር በተያያዘ እንዲያገለግሉና ሸክም እንዲሸከሙ ተመድበው ነበር።+ 48  የተመዘገቡትም በአጠቃላይ 8,580 ነበሩ።+ 49  እነሱም ይሖዋ በሙሴ በኩል ባስተላለፈው ትእዛዝ መሠረት ተመዝግበው ነበር፤ የተመዘገቡትም እያንዳንዳቸው በሚያከናውኑት አገልግሎትና በሚሸከሙት ሸክም መሠረት ነበር፤ እነሱም ልክ ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ተመዘገቡ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በስብ የራሰውን አመድ።” መሥዋዕት ሆነው በሚቀርቡት እንስሳት ስብ የራሰውን አመድ ያመለክታል።
ቃል በቃል “ሸክም።”
ወይም “መጋረጃ።”
ወይም “መጋረጃ።”