ዘሌዋውያን 21:1-24
21 ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለካህናቱ ማለትም ለአሮን ወንዶች ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ማንም ሰው ከሕዝቦቹ መካከል ለሞተ ሰው* ራሱን አያርክስ።*+
2 ይሁንና ለቅርብ የሥጋ ዘመዱ ይኸውም ለእናቱ፣ ለአባቱ፣ ለወንድ ልጁ፣ ለሴት ልጁ፣ ለወንድሙ እንዲህ ማድረግ ይችላል፤
3 እንዲሁም ድንግል ለሆነች፣ ለምትቀርበውና ላላገባች እህቱ ሲል ራሱን ማርከስ ይችላል።
4 ከሕዝቡ መካከል ባል ላገባች ሴት ሲል ራሱን ማርከስና ማዋረድ የለበትም።
5 ራሳቸውን መላጨት+ ወይም የጢማቸውን ዳር ዳር መላጨት አሊያም ሰውነታቸውን መተልተል የለባቸውም።+
6 የአምላካቸው ምግብ* የሆኑትን ለይሖዋ በእሳት የሚቀርቡትን መባዎች የሚያቀርቡት እነሱ ስለሆኑ ለአምላካቸው ቅዱሳን መሆንና+ የአምላካቸውን ስም ከማርከስ መራቅ አለባቸው፤+ ቅዱሳን መሆን ይኖርባቸዋል።+
7 ዝሙት አዳሪ የሆነችን ይኸውም የረከሰችን ሴት ወይም ከባሏ የተፋታችን ሴት አያግቡ፤+ ምክንያቱም ካህኑ ለአምላኩ ቅዱስ ነው።
8 የአምላክህን ምግብ የሚያቀርበው እሱ ስለሆነ ቀድሰው።+ እናንተን የምቀድሳችሁ እኔ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እሱም በአንተ ፊት ቅዱስ ሆኖ መገኘት አለበት።+
9 “‘የአንድ ካህን ሴት ልጅ ዝሙት አዳሪ በመሆን ራሷን ብታረክስ አባቷን ታረክሳለች። ስለዚህ በእሳት መቃጠል አለባት።+
10 “‘ከወንድሞቹ መካከል ሊቀ ካህናት በመሆን በራሱ ላይ የቅብዓት ዘይት የሚፈስበትና+ የክህነት ልብሶቹን እንዲለብስ+ የተሾመው* ካህን ፀጉሩን ማንጨብረር ወይም ልብሶቹን መቅደድ የለበትም።+
11 ወደ ሞተ ሰው* አይጠጋ።+ ሌላው ቀርቶ ለአባቱ ወይም ለእናቱ ሲል ራሱን አያርክስ።
12 ለአምላክ የተወሰኑ መሆንን የሚያሳየው ምልክት ይኸውም የአምላኩ የቅብዓት ዘይት+ በላዩ ላይ ስላለ ከመቅደሱ መውጣትም ሆነ የአምላኩን መቅደስ ማርከስ የለበትም።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።
13 “‘የሚያገባው ድንግል የሆነችን ሴት መሆን ይኖርበታል።+
14 ባል የሞተባትን፣ ከባሏ የተፋታችን፣ የረከሰችን ወይም ዝሙት አዳሪ የሆነችን ሴት አያግባ፤ ሆኖም ከሕዝቡ መካከል ድንግል የሆነችውን ያግባ።
15 እሱን የምቀድሰው እኔ ይሖዋ ስለሆንኩ በሕዝቡ መካከል ዘሩን ማርከስ የለበትም።’”+
16 ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦
17 “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘ከዘርህ መካከል በትውልዶቹ ሁሉ በሰውነቱ ላይ እንከን ያለበት ማንም ሰው የአምላኩን ምግብ ለማቅረብ አይምጣ።
18 እንደሚከተሉት ያሉ እንከኖች ያሉበት ማንም ሰው መቅረብ የለበትም፦ ዓይነ ስውር ወይም አንካሳ አሊያም የፊቱ ገጽታ የተበላሸ* ወይም አንዱ እግሩ ወይም አንዱ እጁ የረዘመ
19 አሊያም እግሩ የተሰበረ ወይም እጁ የተሰበረ ሰው
20 አሊያም ጀርባው ላይ ጉብር ያለበት ወይም ድንክ የሆነ* አሊያም የዓይን ችግር ያለበት ወይም ችፌ የያዘው አሊያም ጭርት ያለበት ወይም የዘር ፍሬው የተጎዳ አይቅረብ።+
21 ከካህኑ ከአሮን ዘር እንከን ያለበት ማንኛውም ሰው በእሳት የሚቀርቡትን የይሖዋን መባዎች ለማቅረብ አይምጣ። ይህ ሰው እንከን ስላለበት የአምላኩን ምግብ ለማቅረብ መምጣት አይችልም።
22 እጅግ ቅዱስ ከሆኑት ነገሮችና+ ቅዱስ ከሆኑት ነገሮች+ የአምላኩን ምግብ መብላት ይችላል።
23 ሆኖም እንከን ስላለበት ወደ መጋረጃው+ አይቅረብ፤ ወደ መሠዊያውም+ አይጠጋ፤ የምቀድሳቸው+ እኔ ይሖዋ ስለሆንኩ መቅደሴን+ አያርክስ።’”
24 ስለዚህ ሙሴ ይህን ለአሮን፣ ለወንዶች ልጆቹና ለእስራኤላውያን በሙሉ ነገራቸው።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ነፍስ።”
^ ካህናት ሬሳ ከነኩ ወይም በሞተው ሰው የሐዘን ሥርዓት ላይ ከተካፈሉ ራሳቸውን ያረክሳሉ።
^ መሥዋዕቶችን ያመለክታል።
^ ቃል በቃል “እጁ የተሞላው።”
^ ወይም “ወደ ሞተ ነፍስ።” እዚህ ቦታ ላይ የገባው ነፈሽ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ሙት” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ጋር ተያያዥነት አለው።
^ ቃል በቃል “አፍንጫው የተሰነጠቀ።”
^ “የመነመነ” ማለትም ሊሆን ይችላል።