ኤርምያስ 16:1-21

  • ኤርምያስ እንዳያገባ፣ እንዳያለቅስና ወደ ግብዣ እንዳይሄድ ተነገረው (1-9)

  • ከተቀጡ በኋላ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ይመለሳሉ (10-21)

16  የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፦ 2  “በዚህ ስፍራ ሚስት አታግባ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም አትውለድ። 3  ይሖዋ በዚህ ስለሚወለዱ ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንዲሁም በዚህች ምድር ስለሚወልዷቸው እናቶችና አባቶች እንዲህ ይላልና፦ 4  ‘በገዳይ በሽታዎች ይሞታሉ፤+ ይሁንና ማንም አያለቅስላቸውም ወይም አይቀብራቸውም፤ በምድር ላይ እንደ ፍግ ይሆናሉ።+ በሰይፍና በረሃብ ይጠፋሉ፤+ አስከሬናቸውም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል።’  5  ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦‘ለለቀስተኞች ድግስ ወደተዘጋጀበት ቤት አትግባ፤እዚያም ሄደህ አታልቅስ ወይም አታስተዛዝን።’+ ‘ሰላሜን ከዚህ ሕዝብ ወስጄአለሁና’ ይላል ይሖዋ፤‘ታማኝ ፍቅሬና ምሕረቴ ከእነሱ እንዲርቅ አድርጌአለሁ።+  6  ታላላቆችም ሆኑ ታናናሾች በዚህች ምድር ላይ ይሞታሉ። ደግሞም አይቀበሩም፤ማንም ሰው አያዝንላቸውም፤ለእነሱ ሲል ሰውነቱን የሚተለትልም ሆነ ራሱን የሚላጭ አይኖርም።*  7  ሰው የሞተባቸውንም ለማጽናናትየእዝን እንጀራ የሚወስድላቸው አይኖርም፤አባት ወይም እናት ለሞተባቸውምየመጽናኛ ጽዋ እንዲጠጡ የሚሰጣቸው አይኖርም።  8  ከእነሱ ጋር ተቀምጠህ ለመብላትና ለመጠጣትግብዣ ወደተዘጋጀበት ቤት አትግባ።’ 9  “የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላልና፦ ‘በዚህ ስፍራ፣ በእናንተ ዘመን ዓይናችሁ እያየ የሐሴትንና የደስታን ድምፅ እንዲሁም የሙሽራንና የሙሽሪትን ድምፅ አስወግዳለሁ።’+ 10  “ይህን ሁሉ ቃል ለዚህ ሕዝብ በምትነግርበት ጊዜ እንዲህ ብለው ይጠይቁሃል፦ ‘ይሖዋ ይህን ሁሉ ታላቅ ጥፋት በእኛ ላይ የተናገረው ለምንድን ነው? በአምላካችን በይሖዋ ላይ የፈጸምነው በደልና ኃጢአት ምንድን ነው?’+ 11  አንተም እንዲህ ብለህ ትመልስላቸዋለህ፦ ‘“አባቶቻችሁ እኔን ስለተዉ ነው”+ ይላል ይሖዋ፤ “ደግሞም ሌሎች አማልክትን ስለተከተሉና ስላገለገሉ እንዲሁም ስለሰገዱላቸው ነው።+ እኔን ግን ትተውኛል፤ ሕጌንም አልጠበቁም።+ 12  እናንተ ደግሞ አባቶቻችሁ ከፈጸሙት የባሰ ነገር አድርጋችኋል፤+ እያንዳንዳችሁም እኔን ከመታዘዝ ይልቅ ግትር የሆነውን ክፉ ልባችሁን ተከተላችሁ።+ 13  ስለዚህ ከዚህች ምድር አስወጥቼ እናንተም ሆነ አባቶቻችሁ ወደማታውቁት ምድር እጥላችኋለሁ፤+ በዚያም ሌሎች አማልክትን ቀን ከሌት ታገለግላላችሁ፤+ ምክንያቱም እኔ ምንም ምሕረት አላሳያችሁም።”’ 14  “‘ይሁን እንጂ ከዚህ በኋላ “የእስራኤልን ሕዝብ ከግብፅ ምድር ባወጣው ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ” የማይሉበት ጊዜ ይመጣል’ ይላል ይሖዋ፤+ 15  ‘ከዚህ ይልቅ “እስራኤላውያንን ከሰሜን ምድርና እነሱን ከበተነባቸው አገሮች ሁሉ ሰብስቦ ባመጣቸው ሕያው በሆነው በይሖዋ እምላለሁ” ይባላል፤ እኔም ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት፣ ወደ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ።’+ 16  ‘እነሆ፣ እኔ ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እሰዳለሁ’ ይላል ይሖዋ፤‘እነሱንም ያጠምዷቸዋል። ከዚያም በኋላ ብዙ አዳኞችን እሰዳለሁ፤እነሱም ከየተራራው፣ ከየኮረብታውናከየቋጥኙ ስንጣቂ አድነው ይይዟቸዋል። 17  ዓይኖቼ በሚያደርጉት ነገር ሁሉ* ላይ ነውና። ከፊቴ አልተሸሸጉም፤በደላቸውም ከዓይኔ አልተሰወረም። 18  በመጀመሪያ፣ ለሠሩት በደልና ኃጢአት የሚገባቸውን ሙሉ ዋጋ እከፍላቸዋለሁ፤+ምድሬን አስጸያፊ በሆኑ ጣዖቶቻቸው በድን ምስሎች* አርክሰዋልና፤ርስቴንም አስነዋሪ በሆኑ ነገሮች ሞልተዋል።’”+ 19  ብርታቴና መጠጊያዬ፣በጭንቀት ጊዜ መሸሸጊያዬ የሆንከው ይሖዋ ሆይ፣+ብሔራት ከምድር ዳርቻዎች ወደ አንተ ይመጣሉ፤እንዲህም ይላሉ፦ “አባቶቻችን ፍጹም ውሸትን፣ከንቱ የሆኑና ምንም ጥቅም የሌላቸውን የማይረቡ ነገሮች ወርሰዋል።”+ 20  ሰው ለራሱ አማልክት ሊሠራ ይችላል?የሚሠራቸው አማልክት እውነተኛ አማልክት አይደሉም።+ 21  “ስለዚህ አስተምራቸዋለሁ፤በዚህ ጊዜ ኃይሌንና ብርታቴን እንዲያውቁ አደርጋለሁ፤እነሱም ስሜ ይሖዋ መሆኑን ያውቃሉ።”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ይህ የአረማውያን የለቅሶ ልማድ ሲሆን ከሃዲዋ እስራኤልም ይህን ልማድ ሳትከተል አትቀርም።
ቃል በቃል “በመንገዶቻቸው ሁሉ።”
ቃል በቃል “አስከሬኖች።”