ኢዮብ 28:1-28

  • ኢዮብ የምድርን ውድ ሀብት ከጥበብ ጋር አነጻጸረ (1-28)

    • ሰው ማዕድን ለማግኘት የሚያደርገው ጥረት (1-11)

    • ጥበብ ከዕንቁ ትበልጣለች (18)

    • ይሖዋን መፍራት እውነተኛ ጥበብ ነው (28)

28  “ብር የሚወጣበት ቦታ፣ወርቅም የሚነጠርበት ስፍራ አለ፤+  2  ብረት ከመሬት ውስጥ ይገኛል፤መዳብም ከዓለት ቀልጦ ይወጣል።*+  3  ሰው ጨለማን ያሸንፋል፤ማዕድን* ለማግኘትበጨለማና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እስከ ወሰኑ ድረስ ፍለጋ ያካሂዳል።  4  ሰዎች ከሚኖሩበት ክልል ርቆ በሚገኝ ስፍራ፣ሰዎች ከሚመላለሱበት አካባቢ ርቀው በሚገኙ የተረሱ ቦታዎች ጥልቅ ጉድጓድ ይቆፍራል፤አንዳንድ ሰዎች በገመድ ወደዚያ ይወርዳሉ፤ ተንጠልጥለውም ይሠራሉ።  5  በምድር ላይ እህል ይበቅላል፤ከታች ግን ምድር በእሳት የሆነ ያህል ትታመሳለች።*  6  በዚያ በድንጋዮቹ ውስጥ ሰንፔር ይገኛል፤በአፈሩም ውስጥ ወርቅ አለ።  7  ወደዚያ የሚወስደውን መንገድ የትኛውም አዳኝ አሞራ አያውቀውም፤የጥቁር ጭልፊትም ዓይን አላየውም።  8  ግርማ የተላበሱ አራዊት አልረገጡትም፤ብርቱ አንበሳም በዚያ አላደባም።  9  ሰው የባልጩት ድንጋይ በእጁ ይመታል፤ተራሮችንም ከሥር መሠረታቸው ይገለብጣል። 10  በዓለት ውስጥ የውኃ ቦዮች ይሠራል፤+ዓይኑም ውድ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ያያል። 11  ወንዞች የሚፈልቁባቸውን ቦታዎች ይገድባል፤የተሰወረውንም ነገር ወደ ብርሃን ያወጣል። 12  ይሁንና ጥበብ የት ልትገኝ ትችላለች?+ማስተዋል የሚገኘውስ ከየት ነው?+ 13  ማንም ሰው ዋጋዋን አይገነዘብም፤+በሕያዋንም ምድር ልትገኝ አትችልም። 14  ጥልቁ ውኃ ‘እኔ ውስጥ የለችም!’ ይላል፤ ባሕሩም ‘በእኔ ዘንድ አይደለችም!’ ይላል።+ 15  እሷን በንጹሕ ወርቅ መግዛት አይቻልም፤በብርም ልትለወጥ አትችልም።+ 16  በኦፊር ወርቅም+ ሆነብርቅ በሆነው ኦኒክስና በሰንፔር ልትገዛ አትችልም። 17  ወርቅና መስተዋት* ከእሷ ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም፤ምርጥ ከሆነ* ወርቅ በተሠራ ዕቃም እሷን መለወጥ አይቻልም።+ 18  ዛጎልና ክሪስታል ጨርሶ አይወዳደሯትም፤+ጥበብ በከረጢት ሙሉ ካለ ዕንቁ ትበልጣለችና። 19  የኢትዮጵያ* ቶጳዝዮን+ ከእሷ ጋር ሊወዳደር አይችልም፤በንጹሕ ወርቅ እንኳ እሷን መግዛት አይቻልም። 20  ታዲያ ጥበብ ከየት ትመጣለች?ማስተዋል የሚገኘውስ ከየት ነው?+ 21  ከሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ዓይን ተሰውራለች፤+በሰማያት ከሚበርሩ ወፎችም ተሸሽጋለች። 22  ጥፋትና ሞት፣‘ወሬዋን ብቻ በጆሯችን ሰምተናል’ ይላሉ። 23  ወደ እሷ የሚወስደውን መንገድ የሚረዳው አምላክ ነው፤መኖሪያዋን የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው፤+ 24  እሱ እስከ ምድር ዳርቻ ይመለከታልና፤ከሰማያትም በታች ያለውን ሁሉ ያያል።+ 25  የነፋስን ኃይል* በወሰነ ጊዜ፣+ውኃዎችንም በለካ ጊዜ፣+ 26  ለዝናብ ሥርዓትን ባወጣ ጊዜ፣+ነጎድጓድ ለቀላቀለ ጥቁር ደመና መንገድን ባዘጋጀ ጊዜ፣+ 27  ያኔ ጥበብን አያት፤ ደግሞም ገለጻት፤መሠረታት፤ እንዲሁም መረመራት። 28  ሰውንም እንዲህ አለው፦ ‘እነሆ፣ ይሖዋን መፍራት ጥበብ ነው፤+ከክፉም መራቅ ማስተዋል ነው።’”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “(ከዓለት) ይፈስሳል።”
ቃል በቃል “ድንጋይ።”
ማዕድን የማውጣት ሥራን የሚያመለክት ይመስላል።
ወይም “ከጠራ።”
ይህ ቃል የገባው ማዕድኑን ለማመልከት ነው።
ወይም “የኩሽ።”
ቃል በቃል “ክብደት።”