ኢያሱ 22:1-34
22 ከዚያም ኢያሱ ሮቤላውያንን፣ ጋዳውያንንና የምናሴን ነገድ እኩሌታ ጠርቶ
2 እንዲህ አላቸው፦ “የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ያዘዛችሁን ሁሉ ፈጽማችኋል፤+ እኔም ባዘዝኳችሁ ነገር ሁሉ ቃሌን ሰምታችኋል።+
3 በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፤+ አምላካችሁ ይሖዋ ከሰጣችሁ ትእዛዝ ጋር በተያያዘ ግዴታችሁን ተወጥታችኋል።+
4 እንግዲህ አሁን አምላካችሁ ይሖዋ ለወንድሞቻችሁ ቃል በገባላቸው መሠረት እረፍት ሰጥቷቸዋል።+ በመሆኑም የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ ከዮርዳኖስ ማዶ* ርስት አድርጎ በሰጣችሁ ምድር ወደሚገኙት ድንኳኖቻችሁ መመለስ ትችላላችሁ።+
5 ብቻ እናንተ አምላካችሁን ይሖዋን በመውደድ፣+ በመንገዶቹ ሁሉ በመሄድ፣+ ትእዛዛቱን በመጠበቅ፣+ ከእሱ ጋር በመጣበቅ+ እንዲሁም በሙሉ ልባችሁና በሙሉ ነፍሳችሁ*+ እሱን በማገልገል+ የይሖዋ አገልጋይ ሙሴ የሰጣችሁን ትእዛዝና ሕግ በጥንቃቄ ፈጽሙ።”+
6 ከዚያም ኢያሱ ባረካቸውና አሰናበታቸው፤ እነሱም ወደ ድንኳኖቻቸው ሄዱ።
7 ሙሴ ለምናሴ ነገድ እኩሌታ በባሳን ርስት ሰጥቶ ነበር፤+ ኢያሱ ደግሞ ለቀረው የነገዱ እኩሌታ ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ከወንድሞቻቸው ጋር መሬት ሰጣቸው።+ በተጨማሪም ኢያሱ ወደ ድንኳኖቻቸው እንዲሄዱ ባሰናበታቸው ጊዜ ባረካቸው፤
8 እንዲህም አላቸው፦ “ብዙ ሀብት፣ እጅግ ብዙ ከብት፣ ብር፣ ወርቅ፣ መዳብ፣ ብረትና እጅግ ብዙ ልብስ ይዛችሁ ወደየድንኳኖቻችሁ ተመለሱ።+ ከጠላቶቻችሁ ያገኛችሁትን ምርኮ ወስዳችሁ ከወንድሞቻችሁ ጋር ተካፈሉ።”+
9 ከዚህ በኋላ ሮቤላውያን፣ ጋዳውያንና የምናሴ ነገድ እኩሌታ በከነአን ምድር በምትገኘው በሴሎ ከነበሩት ከሌሎቹ እስራኤላውያን ተለይተው ወደ ጊልያድ ምድር+ ይኸውም ይሖዋ በሙሴ አማካኝነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ርስት አድርገው ወደሰፈሩባት ምድር ተመለሱ።+
10 ሮቤላውያን፣ ጋዳውያንና የምናሴ ነገድ እኩሌታ በከነአን ምድር ወዳለው የዮርዳኖስ ክልል ሲደርሱ በዮርዳኖስ አጠገብ ግዙፍ የሆነ አስደናቂ መሠዊያ ሠሩ።
11 በኋላም ሌሎቹ እስራኤላውያን “እነሆ፣ ሮቤላውያን፣ ጋዳውያንና የምናሴ ነገድ እኩሌታ የእስራኤላውያን ክልል በሆነው በከነአን ምድር ወሰን ላይ በሚገኘው የዮርዳኖስ ክልል መሠዊያ ሠርተዋል” የሚል ወሬ ሰሙ።+
12 እስራኤላውያንም ይህን በሰሙ ጊዜ መላው የእስራኤላውያን ማኅበረሰብ እነሱን ለመውጋት በሴሎ+ ተሰበሰበ።
13 ከዚያም እስራኤላውያን የካህኑን የአልዓዛርን ልጅ ፊንሃስን+ በጊልያድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤላውያን፣ ወደ ጋዳውያን እና ወደ ምናሴ ነገድ እኩሌታ ላኩት፤
14 ከእሱም ጋር አሥር አለቆችን ይኸውም ከሁሉም የእስራኤል ነገዶች ከእያንዳንዱ የአባቶች ቤት አንድ አንድ አለቃ አብረው ላኩ፤ እነዚህም እያንዳንዳቸው ከእስራኤል የሺህ አለቆች* መካከል የሆኑ የአባቶች ቤት መሪዎች ነበሩ።+
15 እነሱም በጊልያድ ምድር ወዳሉት ወደ ሮቤላውያን፣ ወደ ጋዳውያንና ወደ ምናሴ ነገድ እኩሌታ መጥተው እንዲህ አሏቸው፦
16 “መላው የይሖዋ ጉባኤ እንዲህ ይላል፦ ‘በእስራኤል አምላክ ላይ እንዲህ ያለ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት የፈጸማችሁት ለምንድን ነው?+ ለራሳችሁ መሠዊያ በመሥራትና በይሖዋ ላይ በማመፅ ይኸው ዛሬ ይሖዋን ከመከተል ዞር ብላችኋል።+
17 በፌጎር የሠራነው ስህተት አንሶ ነው? ምንም እንኳ ያኔ በይሖዋ ጉባኤ ላይ መቅሰፍት ቢወርድም ይኸው እስከ ዛሬ ድረስ ከዚህ ነገር ራሳችንን አላነጻንም።+
18 እናንተ ደግሞ ዛሬ ይሖዋን ከመከተል ዞር ትላላችሁ! ዛሬ እናንተ በይሖዋ ላይ ብታምፁ ነገ ደግሞ እሱ በመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ላይ ይቆጣል።+
19 የወረሳችኋት ምድር ረክሳ ከሆነ የይሖዋ የማደሪያ ድንኳን ወደሚገኝበት+ የይሖዋ ርስት ወደሆነው ምድር ተሻግራችሁ+ በመካከላችን ኑሩ፤ ሆኖም ከአምላካችን ከይሖዋ መሠዊያ ሌላ ለራሳችሁ መሠዊያ በመሥራት በይሖዋ ላይ አታምፁ፣ እኛንም ዓመፀኞች አታድርጉን።+
20 የዛራ ልጅ አካን+ ለጥፋት ከተለየው ነገር ጋር በተያያዘ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት በፈጸመ ጊዜ በመላው የእስራኤል ማኅበረሰብ ላይ ቁጣ አልወረደም?+ በሠራው ስህተት የሞተው እሱ ብቻ አልነበረም።’”+
21 በዚህ ጊዜ ሮቤላውያን፣ ጋዳውያንና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ለእስራኤል የሺህ* አለቆች እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፦+
22 “የአማልክት አምላክ፣ ይሖዋ!* የአማልክት አምላክ፣ ይሖዋ!+ እሱ ያውቃል፤ እስራኤልም ቢሆን ያውቃል። በይሖዋ ላይ ዓምፀንና ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ፈጽመን ከሆነ ዛሬ አይታደገን።
23 ለራሳችን መሠዊያ የሠራነው ይሖዋን ከመከተል ዞር ለማለት ወይም በላዩ ላይ የሚቃጠሉ መባዎችንና የእህል መባዎችን ለማቅረብ አሊያም የኅብረት መሥዋዕቶችን ለመሠዋት ብለን ከሆነ ይሖዋ ይቅጣን።+
24 እኛ ግን ይህን ያደረግነው ወደፊት ልጆቻችሁ ልጆቻችንን እንዲህ ማለታቸው አይቀርም ብለን ስለሰጋን ነው፦ ‘ከእስራኤል አምላክ ከይሖዋ ጋር ምን ግንኙነት አላችሁ?
25 ይሖዋ ሮቤላውያንና ጋዳውያን በሆናችሁት በእናንተና በእኛ መካከል ዮርዳኖስን ድንበር አድርጓል። እናንተ በይሖዋ ዘንድ ምንም ድርሻ የላችሁም።’ ልጆቻችሁም ልጆቻችን ይሖዋን እንዳያመልኩ* እንቅፋት ይሆኑባቸዋል።”
26 “በመሆኑም እንዲህ አልን፦ ‘እንግዲህ አንድ እርምጃ መውሰድ አለብን፤ መሠዊያ እንሥራ፤ ይህም የሚቃጠል መባ ወይም መሥዋዕት የሚቀርብበት አይደለም፤
27 ከዚህ ይልቅ የሚቃጠሉ መባዎቻችንን፣ መሥዋዕቶቻችንንና የኅብረት መሥዋዕቶቻችንን+ ይዘን በመምጣት በይሖዋ ፊት አገልግሎት እንደምናቀርብ ለማሳየት በእኛና በእናንተ እንዲሁም ከእኛ በኋላ በሚመጡት ዘሮቻችን* መካከል ምሥክር የሚሆን ነው፤+ ስለዚህ ወደፊት ልጆቻችሁ ልጆቻችንን “እናንተ በይሖዋ ዘንድ ምንም ድርሻ የላችሁም” አይሏቸውም።’
28 ስለዚህ እኛ እንዲህ አልን፦ ‘ወደፊት እኛንም ሆነ ዘሮቻችንን* እንዲህ ቢሉ እኛ ደግሞ “የሚቃጠል መባ ወይም መሥዋዕት የሚቀርብበት ሳይሆን በእኛና በእናንተ መካከል ምሥክር እንዲሆን አባቶቻችን የይሖዋን መሠዊያ አስመስለው የሠሩት መሠዊያ ይኸውና” እንላቸዋለን።’
29 በማደሪያ ድንኳኑ ፊት ካለው ከአምላካችን ከይሖዋ መሠዊያ ሌላ የሚቃጠል መባ፣ የእህል መባና መሥዋዕት የሚቀርብበት መሠዊያ በመሥራት+ ዛሬ በይሖዋ ላይ ማመፅና ይሖዋን ከመከተል ወደኋላ ማለት+ በእኛ በኩል ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው!”
30 ካህኑ ፊንሃስና ከእሱ ጋር የነበሩት የማኅበረሰቡ አለቆች ይኸውም የእስራኤል የሺህ* አለቆች የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ዘሮች የተናገሩትን በሰሙ ጊዜ ነገሩን አሳማኝ ሆኖ አገኙት።+
31 በመሆኑም የካህኑ የአልዓዛር ልጅ ፊንሃስ የሮቤልን፣ የጋድንና የምናሴን ዘሮች እንዲህ አላቸው፦ “በይሖዋ ላይ እንዲህ ያለ ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ስላልፈጸማችሁ ይሖዋ በመካከላችን እንዳለ ዛሬ አውቀናል። እነሆ እስራኤላውያንን ከይሖዋ እጅ ታድጋችኋል።”
32 ከዚያም የካህኑ የአልዓዛር ልጅ ፊንሃስና አለቆቹ በጊልያድ ምድር ከሰፈሩት ከሮቤላውያንና ከጋዳውያን ዘንድ ተመልሰው በከነአን ምድር ወደሚገኙት ወደ ሌሎቹ እስራኤላውያን በመምጣት ስለ ሁኔታው ነገሯቸው።
33 እስራኤላውያንም ነገሩን አሳማኝ ሆኖ አገኙት። ከዚያም እስራኤላውያን አምላክን ባረኩ፤ ከዚያ በኋላም በሮቤላውያንና በጋዳውያን ላይ ስለመዝመትም ሆነ የሚኖሩባትን ምድር ስለማጥፋት አንስተው አያውቁም።
34 ስለሆነም ሮቤላውያንና ጋዳውያን “ይህ መሠዊያ ይሖዋ እውነተኛ አምላክ ስለመሆኑ በመካከላችን ያለ ምሥክር ነው” በማለት ለመሠዊያው ስም* አወጡለት።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ በስተ ምሥራቅ ያለውን ያመለክታል።
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ጎሳዎች።”
^ ወይም “የጎሳ።”
^ ወይም “መለኮታዊው አምላክ፣ ይሖዋ።”
^ ቃል በቃል “እንዳይፈሩ።”
^ ቃል በቃል “ትውልዶቻችን።”
^ ቃል በቃል “ትውልዶቻችንን።”
^ ወይም “የጎሳ።”
^ ከተሰጠው ማብራሪያ መረዳት እንደሚቻለው የመሠዊያው ስም ‘ምሥክር’ ሳይሆን አይቀርም።