ኢሳይያስ 59:1-21
59 እነሆ፣ የይሖዋ እጅ ማዳን ይሳናት ዘንድ አላጠረችም፤+ጆሮውም መስማት ይሳናት ዘንድ አልደነዘዘችም።*+
2 ከዚህ ይልቅ ከአምላካችሁ ያለያያችሁ የገዛ በደላችሁ ነው።+
የፈጸማችሁት ኃጢአት ፊቱን እንዲሰውርባችሁ አድርጎታል፤እናንተን ለመስማትም ፈቃደኛ አይደለም።+
3 እጆቻችሁ በደም፣ጣቶቻችሁም በበደል ተበክለዋልና።+
ከንፈሮቻችሁ ውሸት ይናገራሉ፤+ አንደበታችሁም ክፋትን ያጉተመትማል።
4 ጽድቅን የሚጣራ ማንም የለም፤+እውነትን ይዞ ፍርድ ቤት የሚቀርብ የለም።
በማይጨበጥ* ነገር ይታመናሉ፤+ ፍሬ ቢስ ነገሮችን ይናገራሉ።
ችግርን ይፀንሳሉ፤ የሚጎዳ ነገርም ይወልዳሉ።+
5 የመርዘኛ እባብን እንቁላሎች ይቀፈቅፋሉ፤የሸረሪት ድርም ያደራሉ።+
እንቁላሎቻቸውንም የሚበላ ሁሉ ይሞታል፤እንቁላሉም ሲሰበር እፉኝት ይወጣል።
6 የሸረሪት ድራቸው ልብስ ሆኖ አያገለግልም፤በሚሠሩትም ነገር ራሳቸውን መሸፈን አይችሉም።+
ሥራቸው ጉዳት የሚያስከትል ነው፤በእጃቸውም የዓመፅ ሥራ አለ።+
7 እግሮቻቸው ክፋት ለመፈጸም ይሮጣሉ፤ንጹሕ ደም ለማፍሰስም ይጣደፋሉ።+
የሚያስቡት ጎጂ ሐሳብ ነው፤በመንገዳቸው ላይ ጥፋትና መከራ አለ።+
8 የሰላምን መንገድ አያውቁም፤በጎዳናቸውም ፍትሕ የለም።+
መንገዳቸውን ጠማማ ያደርጋሉ፤በዚያም የሚሄድ ሁሉ ሰላምን አያውቅም።+
9 ከዚህ የተነሳ ፍትሕ ከእኛ ራቀ፤ጽድቅም ወደ እኛ አይደርስም።
ብርሃን ይሆናል ብለን በተስፋ ተጠባበቅን፤ ሆኖም ጨለማ ሆነ፤ጸዳልን ተጠባበቅን፤ ሆኖም በጨለማ እንመላለሳለን።+
10 ልክ እንደ ዓይነ ስውራን ቅጥሩን እየዳበስን እንሄዳለን፤ዓይን እንደሌላቸው ሰዎች እንደናበራለን።+
በምሽት ጨለማ እንደሚሆነው በቀትር ብርሃን እንሰናከላለን፤በብርቱ ሰዎች መካከል እንደ ሙታን ነን።
11 ሁላችንም እንደ ድቦች እናጉረመርማለን፤እንደ ርግቦችም በሐዘን እናልጎመጉማለን።
ፍትሕን በተስፋ ተጠባበቅን፤ ነገር ግን አላገኘንም፤መዳንን ተጠባበቅን፤ ነገር ግን ከእኛ ርቋል።
12 ዓመፃችን በፊትህ በዝቷልና፤+የሠራነው ኃጢአት ሁሉ ይመሠክርብናል።+
ዓመፃችን ከእኛ ጋር ነውና፤በደላችንን በሚገባ እናውቃለን።+
13 ሕግ ተላልፈናል፤ ይሖዋንም ክደናል፤ለአምላካችን ጀርባችንን ሰጥተናል።
ግፍንና ዓመፅን ተናግረናል፤+በልባችን ውሸትን ፀንሰናል፤ እንዲሁም የሐሰት ቃላትን አጉተምትመናል።+
14 ፍትሕ ወደ ኋላ ተመልሷል፤+ጽድቅም በሩቅ ቆሟል፤+እውነት* በአደባባይ ተሰናክሏልና፤ቀና የሆነውም ነገር ወደዚያ መግባት አልቻለም።
15 እውነት* ጠፍቷል፤+ከክፋት የራቀ ሁሉ ለጥፋት ተዳርጓል።
ይሖዋ ይህን አየ፤ ደስም አልተሰኘም፤*ፍትሕ አልነበረምና።+
16 እርዳታ የሚሰጥ ሰው እንደሌለ አየ፤ጣልቃ የሚገባ ባለመኖሩም ተገረመ፤በመሆኑም የገዛ ክንዱ መዳን አስገኘ፤*የገዛ ጽድቁም ድጋፍ ሆነለት።
17 ከዚያም ጽድቅን እንደ ጥሩር ለበሰ፤በራሱም ላይ የመዳንን* ቁር አደረገ።+
የበቀልንም ልብስ ለበሰ፤+ቅንዓትንም እንደ ካባ* ተጎናጸፈ።
18 ላደረጉት ነገር ብድራት ይከፍላቸዋል፦+
ቁጣን ለባላጋራዎቹ፣ በቀልን ለጠላቶቹ ይከፍላል።+
ለደሴቶችም የሚገባቸውን ዋጋ ይከፍላቸዋል።
19 በፀሐይ መግቢያ ያሉ የይሖዋን ስም ይፈራሉ፤በፀሐይ መውጫም ያሉ ክብሩን ይፈራሉ፤እሱ የይሖዋ መንፈስ እንደሚነዳውኃይለኛ ወንዝ ሆኖ ይመጣልና።
20 “ጽዮንን፣ በደል መፈጸም ያቆሙትንምየያዕቆብ ቤት ሰዎች የሚቤዥ+ ይመጣል”+ ይላል ይሖዋ።+
21 “በእኔ በኩል ከእነሱ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳን ይህ ነው”+ ይላል ይሖዋ። “በአንተ ላይ ያለው መንፈሴና በአፍህ ያኖርኩት ቃሌ፣ ከአንተ አፍ ወይም ከልጆችህ* አፍ ወይም ከልጅ ልጆችህ* አፍ ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም አይወሰዱም” ይላል ይሖዋ።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ቃል በቃል “አልከበደችም።”
^ ወይም “ባዶ በሆነ።”
^ ወይም “ሐቀኝነት።”
^ ወይም “ሐቀኝነት።”
^ ቃል በቃል “ይህም በዓይኖቹ ፊት መጥፎ ነበር።”
^ ወይም “ድል አስገኘለት።”
^ ወይም “እጅጌ እንደሌለው ቀሚስ።”
^ ወይም “የድልን።”
^ ቃል በቃል “ከዘርህ።”
^ ቃል በቃል “ከዘርህ ዘር።”