ኢሳይያስ 46:1-13

  • በባቢሎን ጣዖታትና በእስራኤል አምላክ መካከል ያለው ልዩነት (1-13)

    • ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስቀድሞ ይናገራል (10)

    • ከፀሐይ መውጫ የሚመጣ አዳኝ አሞራ (11)

46  ቤል ያጎነብሳል፤+ ነቦ አንገቱን ይደፋል። ጣዖቶቻቸው በደከሙ እንስሳት ላይ እንደሚጫን ከባድ ጭነትበእንስሳት ይኸውም በጋማ ከብቶች ላይ ተጭነዋል።+  2  አንገታቸውን ይደፋሉ፤ በአንድነት ያጎነብሳሉ፤ጭነቱን* ማዳን አይችሉም፤እነሱ ራሳቸውም ተማርከው ይወሰዳሉ።*  3  “የያዕቆብ ቤት ሆይ፣ ከእስራኤልም ቤት የቀራችሁት ሁሉ፣+ከተወለዳችሁበት ጊዜ አንስቶ የረዳኋችሁ፣ በማህፀን ከነበራችሁበት ጊዜም አንስቶ የተሸከምኳችሁ+ ስሙኝ።  4  እስከ እርጅናችሁ ዘመን ድረስ እኔ ያው ነኝ፤+ፀጉራችሁ እስኪሸብትም ድረስ እሸከማችኋለሁ። ከዚህ ቀደም እንዳደረግኩት እሸከማችኋለሁ፣ እደግፋችኋለሁ እንዲሁም እታደጋችኋለሁ።+  5  ከማን ጋር ታመሳስሉኛላችሁ? ከማንስ ጋር እኩል ታደርጉኛላችሁ?+ወይስ እንመሳሰል ዘንድ ከማን ጋር ታነጻጽሩኛላችሁ?+  6  ከኮሮጇቸው ወርቅ የሚዘረግፉ ሰዎች አሉ፤ብሩን በሚዛን ይመዝናሉ። አንጥረኛ ይቀጥራሉ፤ እሱም አምላክ አድርጎ ይሠራዋል።+ እነሱም በፊቱ ይደፋሉ፤ ደግሞም ያመልኩታል።*+  7  አንስተው ትከሻቸው ላይ ያደርጉታል፤+ተሸክመው ወስደው ቦታው ላይ ያኖሩታል፤ በዚያም ዝም ብሎ ይቆማል። ካለበት ቦታ አይንቀሳቀስም።+ ወደ እሱ ይጮኻሉ፤ እሱ ግን አይመልስም፤ማንንም ከጭንቀት ሊታደግ አይችልም።+  8  ይህን አስታውሱ፤ ደግሞም አይዟችሁ። እናንተ ሕግ ተላላፊዎች ይህን ልብ በሉ።  9  ጥንት የተከናወኑትን የቀድሞዎቹን* ነገሮች፣እኔ አምላክ* መሆኔንና ከእኔ ሌላ አምላክ እንደሌለ አስታውሱ። እኔ አምላክ ነኝ፤ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም።+ 10  ከመጀመሪያ መጨረሻውን፣ገና ያልተከናወኑትንም ነገሮች ከረጅም ጊዜ በፊት አስቀድሜ እናገራለሁ።+ እኔ ‘ውሳኔዬ* ይጸናል፤+ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ሁሉ አደርጋለሁ’+ እላለሁ። 11  ከፀሐይ መውጫ* አዳኝ አሞራን፣+ከሩቅ ምድርም ውሳኔዬን* የሚፈጽመውን ሰው እጠራለሁ።+ ተናግሬአለሁ፤ ደግሞም እፈጽመዋለሁ። ይህን ለማድረግ አስቤአለሁ፤ አደርገዋለሁም።+ 12  እናንተ ልበ ደንዳኖች፣*እናንተ ከጽድቅ የራቃችሁ ሰዎች ስሙኝ። 13  ጽድቄን አምጥቻለሁ፤ሩቅም አይደለም፤ማዳኔም አይዘገይም።+ በጽዮን መዳን አስገኛለሁ፤ ለእስራኤልም ግርማዬን አጎናጽፋለሁ።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

በእንስሶቹ ላይ የተጫኑትን ጣዖታት ያመለክታል።
ወይም “ነፍሳቸውም ተማርኮ ይወሰዳል።”
ቃል በቃል “ይሰግዱለታል።”
ቃል በቃል “የመጀመሪያዎቹን።”
ወይም “መለኮት።”
ወይም “ዓላማዬ፤ ምክሬ።”
ወይም “ከምሥራቅ።”
ወይም “ዓላማዬን፤ ምክሬን።”
ቃል በቃል “ኃይለኞች።”