አስቴር 8:1-17

  • መርዶክዮስ ሹመት ተሰጠው (1, 2)

  • አስቴር ንጉሡን ተማጸነች (3-6)

  • ንጉሡ ሌላ አዋጅ እንዲወጣ አደረገ (7-14)

  • አይሁዳውያን ድል ተቀዳጁ (15-17)

8  በዚያው ቀን ንጉሥ አሐሽዌሮስ የአይሁዳውያን ጠላት+ የነበረውን የሃማን ቤት ለንግሥት አስቴር ሰጣት፤+ አስቴር ከመርዶክዮስ ጋር ምን ዝምድና እንዳላቸው+ ለንጉሡ ነግራው ስለነበር መርዶክዮስ ንጉሡ ፊት ቀረበ። 2  ከዚያም ንጉሡ ከሃማ ላይ የወሰደውን የማኅተም ቀለበቱን አውልቆ+ ለመርዶክዮስ ሰጠው። አስቴርም መርዶክዮስን በሃማ ቤት ላይ ሾመችው።+ 3  በተጨማሪም አስቴር ንጉሡን እንደገና አናገረችው። እግሩ ላይ ወድቃ እያለቀሰች አጋጋዊው ሃማ ያደረሰውን ጉዳትና በአይሁዳውያን ላይ የጠነሰሰውን ሴራ እንዲያስወግድ ለመነችው።+ 4  ንጉሡም የወርቅ በትረ መንግሥቱን ለአስቴር ዘረጋላት፤+ አስቴርም ተነስታ በንጉሡ ፊት ቆመች። 5  እሷም እንዲህ አለች፦ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነና እኔም በፊቱ ሞገስ ካገኘሁ፣ ነገሩም በንጉሡ ፊት ተገቢ ሆኖ ከተገኘና በእኔ ደስ ከተሰኘ፣ ያ ሴረኛ አጋጋዊው+ የሃመዳታ ልጅ ሃማ+ በመላው የንጉሡ አውራጃዎች የሚገኙትን አይሁዳውያን ለማጥፋት ያዘጋጀውን ሰነድ የሚሽር ትእዛዝ ይጻፍ። 6  በሕዝቤ ላይ መዓት ሲወርድ ዓይኔ እያየ እንዴት አስችሎኝ ዝም እላለሁ? ዘመዶቼ ሲጠፉስ እያየሁ እንዴት አስችሎኝ ዝም እላለሁ?” 7  በመሆኑም ንጉሥ አሐሽዌሮስ ንግሥት አስቴርንና አይሁዳዊውን መርዶክዮስን እንዲህ አላቸው፦ “የሃማን ቤት ለአስቴር ሰጥቻለሁ፤+ አይሁዳውያንን ለማጥቃት በጠነሰሰው ሴራ የተነሳም* በእንጨት ላይ እንዲሰቀል አድርጌአለሁ።+ 8  በንጉሡ ስም የተጻፈንና በንጉሡ የማኅተም ቀለበት የታተመን ድንጋጌ መሻር ስለማይቻል አይሁዳውያንን በተመለከተ ተገቢ መስሎ የታያችሁን ማንኛውንም ነገር በንጉሡ ስም ጻፉ፤ በንጉሡም የማኅተም ቀለበት አትሙት።”+ 9  ስለሆነም ሲዋን* በተባለው በሦስተኛው ወር፣ በ23ኛው ቀን የንጉሡ ጸሐፊዎች ተጠሩ፤ እነሱም መርዶክዮስ ያዘዘውን ሁሉ ለአይሁዳውያኑ፣ ለአስተዳዳሪዎቹ፣+ ለገዢዎቹና ከሕንድ አንስቶ እስከ ኢትዮጵያ ላሉት 127 አውራጃዎች መኳንንት+ ጻፉ፤ ለእያንዳንዱ አውራጃ በራሱ ጽሑፍ፣* ለእያንዳንዱም ሕዝብ በራሱ ቋንቋ ተጻፈለት፤ ለአይሁዳውያኑም በራሳቸው ጽሑፍና በራሳቸው ቋንቋ ተጻፈላቸው። 10  እሱም ደብዳቤውን በንጉሥ አሐሽዌሮስ ስም ጽፎ በንጉሡ የማኅተም ቀለበት+ አተመው፤ ደብዳቤውንም ፈረስ በሚጋልቡ መልእክተኞች እጅ ላከው፤ እነዚህ መልእክተኞች ለንጉሡ አገልግሎት የሚያሳድጓቸውን፣ ደብዳቤ ለማድረስ የሚያገለግሉ ፈጣን ፈረሶች የሚጋልቡ ነበሩ። 11  በእነዚህም ደብዳቤዎች ላይ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ አይሁዳውያን በሙሉ ተሰብስበው ሕይወታቸውን* ከጥቃት እንዲከላከሉ እንዲሁም ሴቶችንና ልጆችን ጨምሮ በእነሱ ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩትን የየትኛውም ሕዝብ ወይም አውራጃ ኃይሎች በሙሉ እንዲያጠፉ፣ እንዲገድሉና እንዲደመስሱ ብሎም ንብረታቸውን እንዲዘርፉ ንጉሡ መፍቀዱን የሚገልጽ ሐሳብ ሰፍሮ ነበር።+ 12  ይህም በመላው የንጉሥ አሐሽዌሮስ አውራጃዎች በተመሳሳይ ቀን ይኸውም አዳር* በተባለው በ12ኛው ወር 13ኛ ቀን ላይ እንዲፈጸም ተወሰነ።+ 13  በደብዳቤው ላይ የሰፈረው ጽሑፍ* በሁሉም አውራጃዎች ውስጥ ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ተወስኖ ነበር። በተጨማሪም አይሁዳውያኑ በዚያ ቀን ጠላቶቻቸውን ለመበቀል ዝግጁ እንዲሆኑ ለማድረግ ሲባል ለሕዝቦቹ ሁሉ እንዲታወጅ ተደንግጎ ነበር።+ 14  ለንጉሡ አገልግሎት የተመደቡትን ደብዳቤ ለማድረስ የሚያገለግሉ ፈረሶች የሚጋልቡት መልእክተኞች በንጉሡ ትእዛዝ መሠረት እየተቻኮሉና እየተጣደፉ ወጡ። ሕጉ በሹሻን* ግንብም *+ ታውጆ ነበር። 15  መርዶክዮስም ሰማያዊና ነጭ ልብሰ መንግሥት ለብሶ፣ ትልቅ የወርቅ አክሊል ደፍቶ እንዲሁም ከፍተኛ ጥራት ካለው ክርና ከሐምራዊ ሱፍ የተሠራ መጎናጸፊያ ደርቦ ከንጉሡ ፊት ወጣ።+ የሹሻን* ከተማም እልል አለች። 16  ለአይሁዳውያኑም እፎይታ፣* ደስታ፣ ሐሴትና ክብር ሆነላቸው። 17  የንጉሡ ድንጋጌና ሕግ በተሰማባቸው በሁሉም አውራጃዎችና ከተሞች የሚኖሩ አይሁዳውያን ተደሰቱ፤ ሐሴትም አደረጉ፤ የግብዣና የፈንጠዝያ ቀን ሆነ። ብዙዎቹ የምድሪቱ ነዋሪዎች አይሁዳውያንን ከመፍራታቸው የተነሳ አይሁዳዊ ሆኑ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “በአይሁዳውያን ላይ እጁን በመዘርጋቱም።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “የአጻጻፍ ስልት።”
ወይም “ነፍሳቸውን።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “የደብዳቤው ቅጂ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥትም፤ ምሽግም።”
ወይም “የሱሳ።”
ቃል በቃል “ብርሃን።”