ምሳሌ 29:1-27
29 ብዙ ጊዜ ተወቅሶ አንገቱን ያደነደነ* ሰው፣+ሊፈወስ በማይችል ሁኔታ በድንገት ይሰበራል።+
2 ጻድቃን ሲበዙ ሕዝብ ሐሴት ያደርጋል፤ክፉ ሰው ሲገዛ ግን ሕዝብ ይቃትታል።+
3 ጥበብን የሚወድ ሰው አባቱን ደስ ያሰኛል፤+ከዝሙት አዳሪዎች ጋር የሚወዳጅ ግን ሀብቱን ያባክናል።+
4 ንጉሥ ፍትሕ በማስፈን አገርን ያረጋጋል፤+ጉቦ የሚፈልግ ሰው ግን ያወድማታል።
5 ባልንጀራውን የሚሸነግል ሰው፣ለእግሩ ወጥመድ ይዘረጋበታል።+
6 መጥፎ ሰው በደሉ ወጥመድ ይሆንበታል፤+ጻድቅ ግን እልል ይላል፤ ሐሴትም ያደርጋል።+
7 ጻድቅ ለድሆች መብት ይቆረቆራል፤+ክፉ ሰው ግን ለእንዲህ ዓይነት ጉዳይ ደንታ የለውም።+
8 ጉራ የሚነዙ ሰዎች ከተማን ያቃጥላሉ፤+ጥበበኞች ግን ቁጣን ያበርዳሉ።+
9 ጥበበኛ ሰው ከሞኝ ጋር ቢሟገት፣ሁከትና ፌዝ ይነግሣል፤ ደስታ ግን አይኖርም።+
10 ደም የተጠሙ ሰዎች ንጹሕ የሆነን* ሰው ሁሉ ይጠላሉ፤+ቅን የሆነውን ሰው ሕይወት* ለማጥፋት ይሻሉ።*
11 ሞኝ ስሜቱን* ሁሉ እንዳሻው ይገልጻል፤+ጥበበኛ ግን ስሜቱን ይቆጣጠራል።+
12 ገዢ የሐሰት ወሬ የሚሰማ ከሆነ፣አገልጋዮቹ ሁሉ ክፉዎች ይሆናሉ።+
13 ድሃንና ጨቋኝን የሚያመሳስላቸው* ነገር አለ፦
ይሖዋ ለሁለቱም የዓይን ብርሃን ይሰጣል።*
14 ንጉሥ ለድሆች በትክክል ሲፈርድ፣+ዙፋኑ ምንጊዜም ጸንቶ ይኖራል።+
15 በትርና* ወቀሳ ጥበብ ያስገኛሉ፤+መረን የተለቀቀ ልጅ ግን እናቱን ያሳፍራል።
16 ክፉዎች ሲበዙ ክፋት ይበዛል፤ጻድቃን ግን የእነሱን ውድቀት ያያሉ።+
17 ልጅህን ገሥጸው፤ ሰላም ይሰጥሃል፤ደግሞም እጅግ ደስ ያሰኝሃል።*+
18 ራእይ* ከሌለ ሕዝብ እንዳሻው ይሆናል፤+ሕግን የሚጠብቁ ግን ደስተኞች ናቸው።+
19 አገልጋይ በቃል ብቻ ለመታረም ፈቃደኛ አይሆንም፤የሚነገረውን ነገር ቢረዳውም እንኳ እሺ ብሎ አይታዘዝምና።+
20 ለመናገር የሚቸኩል ሰው አይተህ ታውቃለህ?+
ከእሱ ይልቅ ሞኝ የተሻለ ተስፋ አለው።+
21 አገልጋይ ከልጅነቱ ጀምሮ ከተሞላቀቀ፣የኋላ ኋላ ምስጋና ቢስ ይሆናል።
22 በቀላሉ የሚቆጣ ሰው ጠብ ያስነሳል፤+ግልፍተኛ የሆነም ብዙ በደል ይፈጽማል።+
23 ሰውን ትዕቢቱ ያዋርደዋል፤+ትሑት መንፈስ ያለው ግን ክብር ይጎናጸፋል።+
24 የሌባ ግብረ አበር ራሱን* ይጠላል።
እንዲመሠክር የቀረበለትን ጥሪ* ቢሰማም ምንም አይናገርም።+
25 ሰውን መፍራት* ወጥመድ ነው፤+በይሖዋ የሚታመን ግን ጥበቃ ያገኛል።+
26 ብዙዎች ከገዢ ጋር ተገናኝተው መነጋገር* ይሻሉ፤ሰው ግን ፍትሕ የሚያገኘው ከይሖዋ ነው።+
27 ጻድቅ ፍትሐዊ ያልሆነን ሰው ይጸየፋል፤+ክፉ ሰው ግን በቀና መንገድ የሚሄደውን ይጸየፋል።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ግትር የሆነ።”
^ ወይም “ነቀፋ የሌለበትን።”
^ ወይም “ነፍስ።”
^ “ቅን የሆነ ሰው ግን ሕይወቱን ለመጠበቅ ይሻል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ቃል በቃል “መንፈሱን።”
^ ቃል በቃል “የሚያገናኛቸው።”
^ ሕይወት እንደሚሰጣቸው ያመለክታል።
^ ወይም “ተግሣጽና፤ ቅጣትና።”
^ ወይም “ነፍስህን እጅግ ደስ ያሰኛታል።”
^ ወይም “ትንቢታዊ ራእይ።”
^ ወይም “የገዛ ነፍሱን።”
^ ወይም “እርግማን የሚያስከትለውን መሐላ።”
^ ወይም “በሰው ፊት መንቀጥቀጥ።”
^ “የገዢን ሞገስ ማግኘት” ማለትም ሊሆን ይችላል። ቃል በቃል “የገዢን ፊት።”