መዝሙር 16:1-11
የዳዊት ሚክታም።*
16 አምላክ ሆይ፣ አንተን መጠጊያ አድርጌአለሁና ጠብቀኝ።+
2 ይሖዋን እንዲህ አልኩት፦ “አንተ ይሖዋ ነህ፤ ለእኔ የጥሩ ነገሮች ምንጭ አንተ ነህ።
3 ደግሞም በምድር ላይ ያሉት ቅዱሳን፣ክብር የተላበሱት አገልጋዮች እጅግ ደስ ያሰኙኛል።”+
4 ሌሎች አማልክትን የሚከተሉ ሐዘናቸውን ያበዛሉ።+
እንደ እነሱ ደምን የመጠጥ መባ አድርጌ አላቀርብም፤በከንፈሬም ስማቸውን አላነሳም።+
5 ይሖዋ ድርሻዬ፣ ዕጣ ፋንታዬና+ ጽዋዬ+ ነው።
ርስቴን ትጠብቅልኛለህ።
6 ለእኔ ርስት አድርገህ ለመስጠት የለካኸው ቦታ ያማረ ነው።
አዎ፣ ባገኘሁት ርስት ረክቻለሁ።+
7 ምክር የሰጠኝን ይሖዋን አወድሳለሁ።+
በሌሊትም እንኳ በውስጤ ያለው ሐሳብ* ያርመኛል።+
8 ይሖዋን ሁልጊዜ በፊቴ አደርገዋለሁ።+
እሱ በቀኜ ስላለ ፈጽሞ አልናወጥም።*+
9 ስለዚህ ልቤ ሐሴት ያደርጋል፤ ሁለንተናዬ* ደስ ይለዋል።
ያለስጋትም እኖራለሁ።*
10 መቃብር* ውስጥ አትተወኝምና።*+
ታማኝ አገልጋይህ ጉድጓድ እንዲያይ* አትፈቅድም።+
11 የሕይወትን መንገድ አሳወቅከኝ።+
በፊትህ* ብዙ ደስታ አለ፤+በቀኝህ ለዘላለም ደስታ* አለ።
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ጥልቅ ስሜቴ።” ቃል በቃል “ኩላሊቴ።”
^ ወይም “ፈጽሞ አልንገዳገድም (አልውተረተርም)።”
^ ቃል በቃል “ክብሬ።”
^ ወይም “ሥጋዬም ያለስጋት ይኖራል።”
^ ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “ነፍሴን አትተዋትምና።”
^ “መበስበስን እንዲያይ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ቃል በቃል “ከፊትህ ጋር።”
^ ወይም “ፍስሐ።”