ትምህርት 27
ከስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው
የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትህን ለማሳደግ የሚረዳህ ምርምር ማድረግ ትፈልጋለህ? ስለ አንድ ጥቅስ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሰ አንድ ግለሰብ፣ ቦታ ወይም ሌላ ነገር ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ? አሊያም በግል ባሳሰበህ አንድ ጉዳይ ረገድ ሊረዳህ የሚችል ሐሳብ በአምላክ ቃል ውስጥ ይገኝ እንደሆነ ምርምር ለማድረግ አስበሃል? ከሆነ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ለምን ጎራ አትልም?
ጠቃሚ የሆኑ የምርምር መሣሪያዎች ይገኙበታል። የይሖዋ ምሥክሮች በቋንቋህ ያዘጋጇቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በሙሉ አይኖሩህ ይሆናል። በስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ግን በቅርብ የወጡት ብዙዎቹ ጽሑፎች ይገኛሉ። በተጨማሪም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ ጥሩ መዝገበ ቃላትና ሌሎች ጠቃሚ የማመሳከሪያ መጻሕፍት ሊኖሩ ይችላሉ። ከስብሰባ በፊትና በኋላ በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ባሉት መሣሪያዎች መጠቀም ትችላለህ። ቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ኮምፒውተር ካለ ደግሞ ዎችታወር ላይብረሪ የተባለው ፕሮግራም ይኖረዋል። ይህ ፕሮግራም በርካታ ጽሑፎቻችንን የያዘ ሲሆን አንድን ቃል፣ ጥቅስ ወይም ርዕሰ ጉዳይ ፈልጎ በማውጣት በቀላሉ ምርምር ለማድረግ ያስችላል።
በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ለሚካፈሉ ተማሪዎች ጠቃሚ ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ ክፍል እንድታቀርብ ከተመደብክ በስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ተጠቅመህ ክፍልህን መዘጋጀት ትችላለህ። የቤተ መጻሕፍቱን ሁኔታ የመከታተል ኃላፊነት ያለበት የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ የበላይ ተመልካች ነው። በቅርብ የወጡ ጽሑፎች በሙሉ መግባታቸውንና በሚገባ ተስተካክለው መቀመጣቸውን መከታተል የእሱ ኃላፊነት ነው። የምትፈልገውን መረጃ እንዴት እንደምታገኝ የስብሰባው የበላይ ተመልካች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪህ ሊያሳዩህ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ማንኛውንም ጽሑፍ ከስብሰባ አዳራሹ ይዞ መውጣት አይቻልም። መጻሕፍቱን በአግባቡ መያዝ እንዳለብንና ጽሑፎቹ ላይ ምንም ዓይነት ምልክት ማድረግ እንደማይገባንም የታወቀ ነው።
‘ስለ አምላክ እውቀት መቅሰም’ ከፈለግን “እንደተሸሸገ ሀብት” አጥብቀን ልንሻው እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ምሳሌ 2:1-5) እንዲህ ያለውን እውቀት ለማግኘት በምታደርገው ፍለጋ በስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት መሣሪያዎች ሊረዱህ ይችላሉ።
-
በስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ምን ዓይነት የምርምር መሣሪያዎች ይገኛሉ?
-
በቤተ መጻሕፍቱ በሚገባ መጠቀም እንድትችል እነማን ሊረዱህ ይችላሉ?